አንድ ሀገር ራሷን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምታስተ ዋውቅባቸው መንገዶች የኪነ-ጥበብ ውጤቶች ይጠቀሳሉ። እንደ ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ባለቤት ለሆነች ሀገር ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራበት ለሀገራችን ኢኮኖሚ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ነው።
ትውልድና እድገቱ በጎንደር ከተማ ከባህር ዳር 120 ኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ ደግሞ 700 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝ እብናት የምትሰኝ ትንሽዬ ከተማ ውስጥ ነው። የልጅነት ጊዜውን ከተወለደባት እብናት ውጭ ታላቅ እህቱ መምህርት በመሆኗ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተዘዋውሮ አሳልፏል። በባህር ዳር ከተማም ከወንድሙ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ሲኖር እብናትንም ቢሆን አልተዋትም። ሀብታሙ መኮንን።
አባቱን በሞት ያጣው የ10 ዓመት ልጅ እያለ ነበር። በልጅነት እድሜው ይህን ማስተናገዱ ከባድ የሥነ-ልቦና ጠባሳ አሳድሮበታል። በልጅነት የአባትን ፍቅር በቅጡ አለማግኘት እንደ ቀላል የሚተው ነገር እንዳልሆነም ይናገራል። አባታቸው የቤተሰቡ የገቢ ምንጭ ነበሩና የአባቱ ህልፈት እሱን ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡን ኢኮኖሚም ጭምር ጎድቶታል። ‹‹ አባቴን በልጅነቴ በማጣቴ በሕይወቴ ውስጥ እንደ አርዓያ የምወስደው ሌላ ምሳሌ የሚሆነኝን ሰው ለመፈለግ ጊዜ ወስዶብኛል›› ሲል የአባትነትን ዋጋ ከመመኪያነት ባሻገር ለልጆቹ የሕይወት መንገድን የሚያሳይ መሆኑንም ጭምር ያስታውሳል። በዚህ ውስጥ ግን በጠንካራና ጀግና እናት እጅ እንዳደገ ይናገራል።
ሀብታሙና ኪነ-ጥበብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁት የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት አማተር የቲያትር ክበባት ቡድን ትያትሮችን ለማሳየት በትምህርት ቤታቸው ሲመጡ ነው። በትምህርት ቤት ውስጥ በተለያዩ ድራማዎች ላይ ይሳተፋል። ነገር ግን የቲያትርም ሆነ የፊልም ሙያ በሳይንስ ደረጃ ተቀርጾ በዩኒቨርሲቲ እንደሚሰጥ መረጃው አልነበረውም ።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ የብዙ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች መነሻ ነው የሚባልለትን የሚኒ ሚዲያን ክበብ ተቀላቅሎ የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ዜናዎችን ማቅረብ ጀመረ።
በትምህርት ቤት ጓደኛው አማካኝነትም የቲያትር ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሰጥ መረጃውን አገኘ። ይህ መረጃ ለሀብታሙ ዓይኑን የገለጠለት ነበር። ከዚም የ12ተኛ ክፍል ትምህርቱን ሲጨርስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መማርን ምርጫው አደረገ። ቤተሰቦቹም ምርጫውን አልተጋፉትም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚህ የትምህርት ክፍል ስለፊልም እንደ መጀመሪያ የሆነውን እውቀት ማግኘት ሲችል በርካታ የሀገራችን የፊልም ባለሙያዎችን ያወቃቸው በዩኒቨርሲቲ ቆይታው እንደነበር ያስታውሳል።
ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ በቅድሚያ ካወቃቸው የፊልም ባለሙያዎች አንዱ ሲሆኑ ፕሮፌሰሩ መነሻቸው ከጎንደር በመሆኑ አንድ ከአዲስ አበባ ውጭ ካለች ትንሽዬ ከተማ የመጣ ሰው በዚህ ልክ ሙያው ላይ አበርክቶ ማድረግ ይችላል የሚለውን ሥነ-ልቦና በእኔ ውስጥ ማሳደር ችሏል ሲል ይናገራል። እንደ ዳዊት ጣሰው ፣ አበበ ቀጸላ ያሉ የቀደሙ ፊልም ሠሪዎች ሀብታሙ እንደ ምሳሌ የሚወስዳቸው ባለሙያዎች ሲሆኑ ፕሮፌሰር ተሾመ ኃይለገብርኤል በፊልም ትምህርት ውስጥ እንዲቀጥል መነሻው አድርጓቸዋል።
ሀብታሙ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በነበረበት ወቅት አብዛኛው ትኩረቱ የነበረው ትምህርቱ ላይ ነበር። ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን መምህራኑ በሚሰጧቸው ፕሮጀክቶች ላይ በንቃት ተሳትፎ ያደርጋል። ሆኖም ሀብታሙ በይበልጥ መማርና ማወቅ የሚፈልገው ስለፊልም ነው። እሱ የሚማርበት የትምህርት ክፍል ደግሞ አትኩሮቱ ቲያትር ላይ በመሆኑ ስለፊልም ለማወቅ ያግዘው ዘንድ የተለያዩ ጥናቶችን ያደርጋል፣ ስለ ፊልም ሙያ ራሱን ያስተምራል።
ሀብታሙ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከጓደኞቹ ጋር ጥሩ መግባባት እና ትብብር ስለነበረው እውቀቱን ለማሳደግ እነዚህን መንገዶች መጠቀሙ አሁን ለደረሰበት ደረጃ በእጅጉ እንደጠቀመው ይናገራል። ወደሙያው ለመግባት ካለው ፍቅር የተነሳ የሚያገኛቸው መረጃዎችና የትምህርት እድሎች በቂ ናቸው ብሎ አያምንም። ባገኘው እውቀት ላይ ሙከራዎችን ያደርጋል በበይነመረብ ላይ የሚገኙ ትምህርቶችን እየወሰደ ራሱን ለማሳደግ ይጥራል። በ2010 ዓ.ም ትምህርቱን በቲያትርና ሥነ ጥበባት የትምህርት ዘርፍ ሲያጠናቅቅ የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ነበር። ይህ ለሀብታሙ የተለየ ትርጉም አለው።
ሀብታሙ ለመጀመሪያ ጊዜ በፊልም ኢንደስትሪ ውስጥ ‹‹ተፈጣሪ›› ፊልም የፕሮዳክሽን ማናጀር ሆኖ ነበር ራሱን የፈተሸው። በሌላ ጊዜም ከአሜሪካ የመጣ የፕሮዳክሽን ኩባንያ በአዲስ አበባ ዘጋቢ ፊልም ሲሰራ ሀብታሙ ረዳት ዳይሬክተር ሆኖ የመሥራት እድልን አገኘ። በፊልሙ ላይ በነበረው ተሞክሮም የሚያስበውን ያክል ተጽዕኖ ለመፍጠርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ባለሙያ ለመሆን ይበልጥ ራሱን ማብቃት እንዳለበት ተረዳ።
በከፍተኛ ማዕረግ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ሲወጣ በመጀመሪያ ራሱን የጠየቀው በሚፈልገው መንገድ ታሪክን በፊልም ቀርጾ ለማጋራት ብቁ ነኝ ወይ የሚል ነበር። ምንም እንኳን ዘመኑን ሙሉ በፊልም ኢንደስትሪ ውስጥ መቆየት መሥራትና ተጽእኖ ማምጣት ቢፈልግም በቂ ባልሆነ እውቀትና ክህሎት ግን ወደ ኢንደስትሪው መግባት አልመረጠም ስለዚህም ለራሱ ያቀረበው አማራጭ ራሱን በተሻለ እውቀት ማብቃት ነበር።
ሀብታሙ ከተመረቀ በኋላ የታላቅ እህቱን አርዓያ የተከተለ ይመስላል፤ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በረዳት መምህርነት ሥራውን ጀመረ። መምህርነት የምናውቀውን ለሌሎች ማካፈል በመሆኑ ሀብታሙ ይህ ደስታ የሚሰጠው ቦታ ሆኖ አግኝቶታል። በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በረዳት መምህርነት ለሁለት ዓመት ከስምንት ወር ሲያስተምር ተማሪዎችን የማስተማር ብቻ ሳይሆን ራሱንም በብዙ ያስተማረበት ጊዜ እንደነበር ይገልፃል።
ሀብታሙ መምህርነት ሙያን የተቀላቀለው ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ ብዙም ሳይቆይ በመሆኑ ወጣት መምህር መሆን በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል። ‹‹ ለተማሪዎቼ ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለሚሰራው ማህበረሰብም መምህር አልመስልም ነበር፤ ወጣት መሆኔ በእኔና በተማሪዎቼ መካከል ያለውን ቅርርብ ጥሩ እንዲሆንና ተማሪዎቼ ከትምህርት ውጭ ያላቸውን ሃሳብ እንዲያማክሩኝ እድል ሰጥቶኛል ›› ሲል ይናገራል።
ባለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን እውቀት ሁልጊዜ የሚታደስ በመሆኑ ለተማሪዎች የሚገባቸውን እውቀት ለመስጠት መምህሩ ራሱን በየጊዜው ማሳደግ የተለያዩ ጥናቶችን ማድረግና በተጨማሪም የማህበረሰብ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል ይላል።
መምህር በነበረበት ወቅት ስለነበሩት ገጠመኞች እንዲሁ አጋርቶናል። ‹‹የመጀመሪያ ቀን ለማስተማር ወደ ተመደብኩበት ክፍል ስገባ ተማሪዎች መምህር እየጠበቁ በክፍሉ በር ላይ ቆመው ነበር። እኔም አብሬአቸው የምማር ስለመሰላቸው አላስተዋሉኝም እናም ሥራዬን ለመጀመር መምህራችሁ እኔ ነኝ ብዬ መናገር ነበረብኝ።›› በማለት ያስታውሳል።
ሀብታሙ የተለያዩ እድሎችን በመሞከርና ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለአቻዎቹ የሚያስተላልፈው መልዕክትም ‹‹ወጣት ስንሆን ትልቁ አቅማችን ከሌሎች በተለየ ራሳችንን ማሳደግና ማስተማር የምንችልበት ጊዜና አቅም አለን። ጊዜ ደግሞ በዓለም ላይ በጣም ውዱ ስጦታ ሲሆን ወጣቶች በሚወዱት ነገር ላይ ራሳቸውን በማስተማር በሙያቸው ምሳሌ የሚደረጉ መሆን ይችላሉ። አጭር መንገድ የለም ፤ ጠንክሮ መማርና መሥራት ያስፈልጋል ያኔ ሕይወት ቀላል ትሆናለች ብዬ አስባለሁ›› ሲል ሃሳቡን ያጋራል።
ሀብታሙን ለየት የሚያደርገው ነገር በእውቀት ላይ ያለው እምነት ነው። በቂ ነው የሚባል እውቀት የለም በማለት ሁሌም ራሱን ብቁ ለማድረግ ይጥራል። ከሁለት ዓመት በላይ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ካስተማረ በኋላ በፊልም ሙያ ሁለተኛ ዲግሪውን ለመማር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መጣ። ሀብታሙ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የንድፈ ሃሳብ እንጂ ቴክኒካል የሆነውን እውቀት በሚፈልገው መጠን እንዳላገኘ ይናገራል። ሌሎች አማራጮችን በሚሞክርበት ወቅትም ሁለት ትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ መሳተፍ ቻለ። አንደኛው (multi choice talent factory) የተሰኘ ከአፍሪካ 60 ተማሪዎችን መርጦ በምስራቅ አፍሪካ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ምዕራብ አፍሪካ ላይ ነፃ የትምህርት እድል የሚሰጥ ተቋም ሲሆን የትምህርት እድሉን ለማግኘት የሚጠበቅበትን መስፈርት ካሟላ በኋላ ፈተናውን አለፈ።
የጀመረውን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ለጊዜው አዘግይቶ ጉዞውን ወደ ኬንያ አደረገ። ኩባንያው የሚሰጠው የትምህርት እድል ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ተግባር ተኮር ስልጠና ነው። በአሁን ሰዓት ስልጠናውን በኬንያ እየወሰደ ይገኛል። በኬንያ ያለው የፊልም ኢንደስትሪና ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት የፊልም ግንኙነት የተሻለ በመሆኑ ሌሎች እድሎችን ለማግኘት እንደረዳውም ጭምር ይናገራል። በዚህም እድል አማካኝነት በድርሰትና በዳይሬክተርነት የተሳተፈበትን የመጀመሪያ ፊልሙን መሥራት ጀምሯል።
ሀብታሙ በኢትዮጵያ ያሉ የፊልም ትምህርትቤቶች እንደ ኢትዮጵያ ላለች ባለ ብዙ ባህልና ታሪክ ላላት ሀገር ብቁ ናቸው ለማለት የሚያስደፍሩ አይደሉም ። በመንግስት ደረጃ ካሉ የትምህርት ተቋማት ይልቅ የግል ማሰልጠኛ ተቋማት የተሻለ እንደሚንቀሳቀሱ ይናገራል ።
ሀብታሙ ስለ ፊልም ቴክኒካል እውቀት ብቻ ሳይሆን የፊልም ኢንደስትሪ ውስጥ ስላለው ቢዝነስ ማወቅ ጠቃሚ እንደሆነ ያውቃል። ፊልም የአንድ ሀገር ታሪክ ባህልና ትውፊት የሚንጸባረቅበት በመሆኑ ይህ ታሪክ በዓለም ደረጃ ተዋውቆ መሸጥና የሀገር ኢኮኖሚ ላይ የራሱን ዐሻራ ማሳረፍ ይገባዋል የሚል እሳቤ አለው። የአፍሪካ ሕብረት የ2063 አጀንዳ የፈጠራና የባህል ቅርስ ኢኮኖሚን ማሳደግ እና ለሀገር ጂዲፒ አበርክቶ እንዲኖረው ማድረግ በእቅዱ መጠቀሱን አስታውሶ ሌሎች ሀገራት ኢንደስትሪው ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ቁመና ላይ እንዲደርስ እንዳደረጉትም ይናገራል። ኢትዮጵያም ከነዚህ ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ በዓለም ደረጃ እንደምንታወቅባቸው ቡናና አበባ ዘርፉ ኢኮኖሚውን መደገፍ እንዲችል ማድረግ ይገባል።
ሀብታሙ ሁለተኛው የተሳተፈበት ስለ ፊልም ኢንደስትሪ ቢዝነስ የተሻለ እውቀት እንዲኖረው የሚያስችል በደርባን የሚካሄደው ትልቁ ዓመታዊ የአፍሪካ የፊልም ገበያና ፊልም ፌስቲቫል (Durban film mart) ነበር። (Durban film mart) የአፍሪካን የሲኒማ ልማትና ፕሮዳክሽን ማሳደግ አላማው ያደረገ ሲሆን በንግዱ ዓለም ፊልምን እንዴት ውጤታማ በሆነ መልኩ ማስኬድ ይቻላል ስለሚለውና አጠቃላይ ስለ ፊልም ቢዝነስ ተሳታፊዎች ልምድ እንዲቀስሙ ያደርጋል። በዚህ ዓመት በኤግዚቢሽኑ ላይ ለመሳተፍ ከ200 በላይ ሰዎች ተወዳድረው 30 ተሳታፊዎች ተመርጠዋል። ሀብታሙም በዚህ ዓመት በፌስቲቫሉ ላይ የሚሳተፍ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነው።
ሰባት የሚደርሱ አጫጭር ፊልሞችን፣ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን በዳይሬክተርነትና በተዋናይነት እስካሁን የተሳተፈባቸው ሥራዎች ናቸው። ሀብታሙ በቅርቡ አንድ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ተሳትፏል። ውድድሩ ( International Emmy Award ) የተሰኘ በየዓመቱ አንድ ርዕስን በመምረጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ወጣት ፊልም ሠሪዎችን የሚያሳትፍ የአጫጭር ፊልም ውድድር ነው። በዚህ ዓመት ‹‹ለሰላም እንቁም›› በሚል ርዕስ ለተወዳዳሪዎች ክፍት በሆነው ውድድር ላይ ሀብታሙ ‹‹ጦርነት አቁመን ለሰላም እንነሳ›› የሚል ሃሳብን ይዞ በውድድሩ ተሳትፏል። በሀብታሙ ፊልም ትኩረት ያገኙት ሕጻናት ሲሆኑ አንዲት መምህር በማስተማሪያ ክፍል የስም ጥሪ ለማድረግ ስትገባ በክፍሉ አንድም ተማሪ አልነበረም። እናም ፊልሙ በጦርነት ውስጥ የመጀመሪያ ተጎጂዎች ሕጻናት ናቸው በሚል ይዘት የጦርነትን አስከፊነት የሚሳይ ነው።
ውድድሩ በዳኞች የውስጥ ግምገማ ሁለት ዙሮችን ካለፈ በኋላ በሕዝብ ድምጽ እንዲሰጥበት ይፋ ተደረገ። ሀብታሙም በጽሑፍ በዳሬክቲንግና ኤዲቲንግ የተሳተፈበትን ፊልም ያሸንፍ ዘንድ የተለያዩ የማህበራዊ ድህረ-ገጾችንና የማህበረሰብ አንቂዎችን በመጠቀም ድምጽ ስጡኝ አለ። በሕዝብ ምርጫ 25 ፊልሞች ውስጥም ሲመረጡ ቀጥሎ በነበረው የዳኝነት ሂደት አሸናፊ መሆኑን ከኢትዮጵያና ከምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው መሆኑንም ከኩባንያው መልዕክት ደረሰው ።
ውድድሩ ካስቀመጣቸው መስፈርቶች አንዱ ፊልሙ የአንድ ደቂቃ ርዝማኔ ይኑረው የሚል ነበር። ነገር ግን አንድን ሃሳብ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ማስተላለፍ ቀላል አልነበረም። በመሆኑም ሀብታሙ የእርሱ ፊልም ተመራጭ የሆነው ሃሳቡ ለሰዎች ስሜት ቅርብ በመሆኑ የሰዎችን ቀልብ በመያዙ ሊያሸንፍ እንደቻለም ይናገራል። በውድድሩ ከአምስት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በበጀትም በቴክኒካል ብቃትም የተሻሉ የሚባሉ ፊልሞች ለውድድር ሲቀርቡ ኩባንያው በሌሎች ሁለት ዘርፎች ሌሎች ውድድሮችንም ያዘጋጃል።
ሀብታሙና ፊልም ቁርኝታቸው ከልጅነት ነው። አሁን የ27 ዓመት ወጣት ሲሆን መድረስ የሚፈልግበት ትልቁ ህልሙ በፊልም ትምህርት ቤት ውስጥ በፕሮፌሰርነት ማዕረግ ደረጃ ድረስ መማር ይፈልጋል። ወደፊት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ስለ ፊልም ሲነሳ ከሚዘከሩ ባለሙያዎች ውስጥ ሀብታሙ መኮንን የሚል ስም እንዲታወስ ነው። በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ፊልሞችን መሥራት የሠራቸውን ፊልሞች በዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ላይ ይዞ በመቅረብ ማሳየትና አሸናፊ እንዲሆኑ ማድረግ ይፈልጋል። በሀገራችን ከተከናወኑ ታሪኮች ውስጥ የካራማራን የድል ታሪክ በፊልም መልክ መሥራት ይፈልጋል። በሀገራችን እምብዛም ያልተለመደውን የታላላቅ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ በፊልም ማስቀመጥና መጽሐፎችን ወደፊልም መቀየር በእቅዶቹ ውስጥ ተቀምጠዋል። በዚህ ውስጥ ግን ወደ መምህርነት ሙያው መመለስንም አልረሳም።
ሀብታሙ የኢትዮጵያን የፊልም ኢንደስትሪ የላቀ ደረጃ ላይ ማድረስ ህልሙ ነው። እንቅስቃሴው ተማሪ በነበረበት ወቅት የተጀመረ ሲሆን ኢትዮጵያ የራሷ የሥነ-ጥበብ ምክር ቤት (Ethiopian Art Council) እንዲኖራት ማድረግ ነው። ምክር ቤቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ የፊልም ድርጅቶች ጋር ትብብሮችና ግንኙነቶች እንዲኖራትና ኢትዮጵያውያን የፊልም እውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። የፊልም ምደባ ሰሌዳ (Film Classification Board) ራሱን ችሎ ማቋቋም በእቅዱ ውስጥ ይገኝበታል። ቡድኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩ ማንኛውንም ፊልሞች የሀገራችንን ባህል ወግና ሥነ-ምግባርና የተከተሉ እንዲሆኑ የሚመዝንና ከሌሎች ሀገራት ተሰርተው የሚመጡ ፊልሞችን የባህል ተጻራሪ እንዳይሆኑ ይቆጣጠራል። ፊልሞች ተሰርተው ለእይታ ከመቅረባቸው በፊትም በየትኛው የእድሜ ክልል ሊታዩ እንደሚገባ ይቆጣጠራል።
ሀብታሙ በሕይወቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ በእቅዶቹና በስኬቶቹ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላት እናቱን እህትና ወንድሞቹን ያመሰግናል። ባሸነፈበት የፊልም ሥራ ውስጥ በቅንነትና በጓደኝነት በሙያቸው ያገዙትን ተዋናይ ምህረት ወረደ፣ ሲኖማቶግራፈር ሄኖክ ተሾመና ያገዙትን የኡጋንዳ፣ የኬንያና የታንዛንያ ዜግነት ያላቸውን ጓደኞቹን እንዲሁም አሸናፊ እንዲሆን የመረጡትን ኢትዮጵያውያንን አመስግኗል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም