የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የሆነው የሲዳማ ክልል፣ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት በርካታ ምቹ ሁኔታዎችም አሉት፡፡ ክልሉ ያለው ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ሀገርን የሚያኮራ፣ ባለሀብቶችን በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚያነሳሳ እና የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መልካም አጋጣሚና ፀጋ ነው፡፡
የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ የሆኑ ምርቶች መገኛ ነው፡፡ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች በቡና አብቃይነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶች የሚመረቱበት መሆኑም ይታወቃል፡፡ ዓይነተ ብዙ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች፣ የወተት፣ የዶሮ፣ የማር፣ የስጋና ሌሎች ሀብቶች በግብርናው ዘርፍ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ከግብርናው በተጨማሪ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ዕድል ይፈጥራል፡፡ የሲዳማ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በክልሉ ከ17 በላይ የማዕድን ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ በአገልግሎት ዘርፍም ክልሉ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም አለው፡፡ የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሐዋሳ ከተማ ዙሪያ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ክልሉ የሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ፣ የበርካታ አዕዋፋትና እንስሳት እንዲሁም የተፈጥሮ ገፅታዎች እና የብዙ ባህላዊ የሽምግልና ስፍራዎች መገኛ በመሆኑ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንትም ተመራጭ የመሆን አቅም አለው፡፡
ክልሉ በኢንቨስተሮች ተመራጭ እንዲሆን ከሚያስችሉት ነገሮች መካከል የእምቅ ሀብት ባለቤት መሆኑ፣ ሥራ ፈላጊ ወጣት የሰው ኃይል መኖሩ፣ ከአዲስ አበባ ናይሮቢ የሚዘልቀው መንገድ የክልሉን ዋና ከተማ ሐዋሳን አቋርጦ ማለፉ እና ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት መኖር የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ክልሉን ከሀብቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ የኢንቨስትመንት ልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ በክልሉ የኢንዱስትሪ ክላስተር ዞኖችን በማደራጀት የክልሉን ሀብት ለኢንቨስተሮች የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷል፡፡ የክልሉን የኢንቨስ ትመንት አቅምና ምቹ ሁኔታዎችን ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተሠሩ የንቅናቄ ተግባራት አማካኝነትም ብዙ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ማወቅ ተችሏል፡፡ ክልሉ ትኩረት ከሰጣቸው የኢንቨስትመንት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ በምርቶች ላይ እሴት (Value) ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ሲዳማ ክልል በቡና ሀብት ትልቅ አቅም ካላቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ለተከታታይ ዓመታት የጥራት ውድድር (Cup of Excellence) ላይ ቀርቦ አሸናፊ የሆነው የሲዳማ ቡና ነው፡፡
በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት 99 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል፡፡ ባለሀብቶቹ ከሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን፤ በኮንስትራክሽን (31)፣ በአገልግሎት (29)፣ በማምረቻ (22) እና በግብርና (17) ዘርፎች ይሰማራሉ፡፡ ፈቃድ ከወሰዱት ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ በበጀት ዓመቱ በክልሉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ለ17ሺ 800 ዜጎች (1896 ቋሚ እና ጊዜያዊ) የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት አበረታች የኢንቨስትመንት አፈፃፀም ያስመዘገበው ክልሉ፣ በዘንድሮው የበጀት ዓመትም የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በዘርፈ ብዙ የማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ዘርፎች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መታቀዱን በክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ ፈቃድና መረጃ ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ሮባ ይገልጻሉ፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፣ የክልሉን ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት ሀብት በጥናት መለየት፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን የሚጨምሩ ጠንካራና ተከታታይ የፕሮሞሽን ሥራዎችን መሥራት እና ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ የበጀት ዓመቱ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮችን አጠናክሮ ማስቀጠልም የእቅዱ አካል ናቸው፡፡
በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ ለ12 የግብርና፣ ለ34 የኢንዱስትሪ፣ ለ20 የአገልግሎት እና ለ44 የኮንስትራክሽን ዘርፍ ፕሮጀክቶች፣ በአጠቃላይ ለ110 ባለሀብቶች፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዷል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶቹ በአጠቃላይ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንደሚያስመዘግቡም ተጠብቆ ነበር፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ለሚያስመዘግቡ 35 ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ አምስት ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 14 ፕሮጀክቶች (በኢንዱስትሪ ስድስት፣ በአገልግሎት ስድስት፣ በኮንስትራክሽን ሁለት) ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ፈቃድ ከተሰጣቸው ፕሮጀክቶች መካከል በሴራሚክ ምርት ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ የወሰደ አንድ ፕሮጀክት ከፍተኛ ካፒታል (አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር) በማስመዝገቡ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶች ያስመዘግቡታል ተብሎ የታቀደውን የካፒታል መጠን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ማሳካት ችሏል፡፡ በሩብ ዓመቱ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በሚወስዱ ፕሮጀክቶች ለ310 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ 888 ዜጎችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
አቶ ታሪኩ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለግብርና ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ አልተሰጠም ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹አዲስ ፈቃድ ከመስጠት በፊት የቀድሞዎቹን የአፈፃፀም ደረጃ መገምገም አስፈላጊ በመሆኑ በዘርፉ ፈቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶች ኦዲት እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በግብርና ዘርፍ በገቡት ውል መሠረት ሥራ ያልጀመሩና አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ፕሮጀክቶችን የመለየት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ባለሀብቶቹ በገቡት ውል መሠረት መፈፀም አለመቻላቸው በሩብ ዓመቱ በግብርናው ዘርፍ አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዳይሰጥ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለሀብቶች ከሚያነሷቸው ችግሮች መካከል የብድር አቅርቦትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋናዎቹ ናቸው ይላሉ፡፡
የግብርና ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ኦዲት ከማድረግ ባሻገር፣ አብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ አብቃዮች በመሆናቸው በእነዚህ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶችም ልዩ ትኩረት ይሰጣል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለክልሉ ኢንቨስትመንት፣ በተለይም ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች፣ እድገት ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ዕድሎችና ግብዓቶች መካከል አንዱ ከሐዋሳ ከተማ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
የግብርና ውጤቶችን እሴት በመጨመር በብዛትና በጥራት ተወዳዳሪ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ከታመነባቸው እና የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ያሳካሉ ከተባሉ የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ የሆነው ይህ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በ2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከክልሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ውል የፈፀሙ ኩባንያዎች በአቮካዶ፣ በማንጎ፣ በእንጆሪ፣ በቡና፣ በማር፣ በወተት፣ በስጋ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአኩሪ አተርና በሌሎች ምርቶች ማቀነባበር ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ ከሚገኙት ኩባንያዎች፤ የአቮካዶ ዘይት በማቀነባበር ለውጭ ገበያ፣ ወተት እና የተለያዩ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲሁም የማር ምርትን ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡት አምራቾች ናቸው፡፡ ምርቶቹን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ወደ ውጭ ለመላክ በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት ተገኝቷል።
አቶ ታሪኩ እንደሚሉት፣ የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ለምርት የሚያገለግለውን የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱን የሚያገኘው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ነው፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ የፓርኩ መጋቢ በሆኑ ሦስት የገጠር ሽግግር ማዕከላት (በንሳ ዳዬ፣ አለታ ወንዶ እና ሞሮቾ አካባቢዎች የሚገኙ) እና በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል የአቮካዶ፣ የማር፣ የወተት፣ የቡናና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በፓርኩ ውስጥ ለተሰማሩ ለአልሚዎች እያቀረቡ ነው፡፡
የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የማር እንዲሁም የወተት ምርት የሚያቀርቡ ማኅበራት ግብዓቶችን የሚሰበስቡት በገጠር የሽግግር ማዕከላቱ በኩል ነው፡፡ ፓርኩ ግብአቶችን በማቅረብ የገበያ ትስስርና የገቢ ምንጭ ከፈጠረላቸው አርሶ አደሮች በተጨማሪ በየአመቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህ ተግባር የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን የማስቀረትና ገቢ ምርቶችን የመተካት ድርብርብ ዓላማዎች አሉት፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ትልቅ ገበያ ያልነበረው የአቮካዶ ምርት በአሁኑ ወቅት ደረጃ ወጥቶለት አርሶ አደሩ ምርት በስፋት እያቀረበ፣ ገቢ እያገኘና አዳዲስ ዝርያዎችን እያለማ ነው፡፡ ፓርኩ አርሶ አደሩ ጥሬ ዕቃን በብዛትና በጥራት እንዲያቀርብ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህም የግብርና ምርታማነት እንዲጨምርና የአርሶ አደሩ ሕይወት እንዲሻሻል እያደረገ ነው፡፡
«በፓርኩ ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶች ግብዓቶችን ከየአካባቢው ሲሰበስቡ ለአርሶ አድሮች ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች ግብዓቶች በጥራት እንዲቀርቡና ምርታማነት እንዲጨምር እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም ፓርኩ የግብዓቶችን ጥራት በማሻሻል ምርታማነት እንዲጨምር ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል። ሲሉ ጠቅሰው፣ ፓርኩ ለግብርና ኢንቨስትመንት እድገት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል›› ብለዋል፡፡
‹‹በፓርኩ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች ለፓርኩ ግብዓት የማቅረብ አቅም ያላቸው በመሆኑ በፓርኩ ውስጥ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስርም ሆነ የሥራ ዕድል በመፍጠር የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው፡፡ ባለሀብቶች ወደ ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው እንዲያለሙ የሚከናወኑት የፕሮሞሽን፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የክትትል ተግባራት በልዩ ትኩረት ይከናወናሉ ሲሉ በመጠቀስ፣ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ መጠናከር ያለውን ሚና ያስረዳሉ፡፡
በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፍ ስለሚከናወኑ ተግባራት በሐዋሳ ሐይቅ ዙሪያ ትልልቅ ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን በመገንባት ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም ነው ያመለከቱት፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን በማከናወን የሐዋሳ ሐይቅን፣ የአላሙራ እና የታቦር ተራሮችን እንዲሁም ጉዱማሌ አደባባይን ለቱሪስቶች ምቹ የማድረግ ሥራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ የመስህብ ስፍራዎችን ለማልማት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች የመሬት ዝግጅትና ሌሎች ግብዓቶች በፍጥነት እንዲሟሉላቸው እንደሚደረግም አመልክተው፣ ባለሀብቶች በቱሪዝም ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ በ2016 የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ወጣቶች በሐዋሳ ሐይቅ አካባቢ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ በተለይም በሐዋሳ ዙሪያ የመዝናኛ ማዕከላትን መገንባት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም ተናግረው፣ ብዙ ባለሀብቶች በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩና ጥያቄ እያቀረቡ እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡
በክልሉ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክ ቶች የክልሉን ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት በዘንድሮው የበጀት ዓመትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ታሪኩ ይናገራሉ። ‹‹ከዚህ ቀደም ትምህርት ቤቶችን (አለታ ወንዶ) እና የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን (ሐዋሳ ዙሪያ) ገንብተው ያስረከቡና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ባለሀብቶች አሉ። በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ደግሞ፣ አርሶ አደሮች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲላመዱ ያስቻሉ ቁሳቁስንና አሠራሮችን አበርክተዋል፡፡ በ2015 የበጀት ዓመት 480 የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቴክኖሎጂ ሽግግር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። በዶሮ እርባታ እና በንብ ማነብ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ለዚህ አበርክቶ የሚጠቀሱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ ማስቀጠል የበጀት ዓመቱ የዘርፉ እቅድ አካል ነው›› ይላሉ፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም