ትኩረት የሚሻው የብሬል መጽሐፍት ተደራሽነት

ሞገስ ጌትነት ይባላል፡፡ በከፊል የእይታ ችግር አለበት፡፡ ከዓመታት በፊት ለዐይነ ሥውራን የሚሆን ሁለት የብሬል ቤተ መጽሐፍትን በየካቲት 12 እና በጥቁር አንባሳ ትምህርት ቤት አቋቁሟል። በዚህም ከዘጠነኛ ክፍል እስከ 12 ክፍል ያሉ አይነ ሥውራን ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተል፡፡ የሦስት ልጆች አባት የሆነው ሞገስ፤ በአሁን ወቅት የግል ሥራውን በመሥራት እንዲሁም ባለው ጊዜ የልጆች መጽሐፍ በመጻፍ የድርሰቱን ዓለም በሰፊው ለመቀላቀል መንገድ ላይ ይገኛል፡፡

በቅርቡም ‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች› የተሰኘ የልጆች መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡ ልጆች በስነ-ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ ለማድረግ፣ የአካባቢያቸውን እንዲሁም የአገራቸውን ታሪክ፣ ባሕል እና ቅርስ እንዲያውቁ ለማድረግ በምስል የታገዘ እና ልጆችን በሚመጥን መልኩ በአራት ምዕራፎች ከፋፍሎ አዘጋጅቷል፡፡ መጽሐፉ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ስለመሆኗ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ያስተዋወቁ የታላላቅ ሠዎች ታሪክን አካቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በዝርዝር ቀርበውበታል።

‹‹የመጽሐፉ ዓላማ ልጆች አካባቢያቸውን እንዲያውቁ ብሎም እንዲወዱ እና ከመደበኛ ትምህርታቸው ባሻገር ሌሎች መጽሐፍትን እንዲያነቡ ብሎም የንባብ ክህሎታቸው እንዲዳብር ለማድረግ ያለመ ነው፡፡›› የሚለው ሞገስ፤ ስለብሬል ጠቀሜታ ቀድሞ ግንዛቤ ያለው በመሆኑ በተለይም ዐይነ ሥውራን ታዳጊዎች እንዲያነቡ ለማድረግ፣ በሥነ ጽሁፍ አማካኝነት ትምህርታዊ መረጃዎችን እንዲያገኙ ለማስቻል ‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች› መጽሐፍን በብሬል ጭምር ለንባብ እንዲበቃ አድርጓል፡፡

የብሬል መጽሐፍት ውስንነቶች መኖራቸውን የተረዳው ሞገስ ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን መጽሐፉን በብሬል ጭምር ያዘጋጀው እንጂ ሥራው ፈታኝ መሆኑን ይናገራል፡፡ ወደ ብሬል ለመቀየር እንዲሁም የመጽሐፉ የሕትመት ዋጋ የሚፈትን መሆኑን በመጥቀስ፤ አጋዥ ካገኘ ግን ወደ ተለያዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በማምራት ለታዳጊ ዐይነ ሥውራን ተማሪዎች መጽሐፉን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እቅድ አለው፡፡

ሞገስ እንደሚገልጸው፤ ዐይነ ሥውራን ማንበብ ይፈልጉ እንጂ አብዛኞቹ የሕትመት ውጤቶች በብሬል የተዘጋጁ ባለመሆናቸው ይህንን እድል አያገኙም፡፡ ከንባብ ይልቅ በማዳመጥ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የወረቀት ዋጋ መናር እና ተያያዥ ችግሮች አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር እንቅፋት መሆኑን በመገንዘብ፤ ችግሩን ያገናዘበ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የብሬል ወረቀት ውድ መሆን፣ በይዘትም ሰፋ እና ገዘፍ ማለት እንደ አንድ ተግዳሮት የገለጸው አቶ ሞገስ፤ ቤተ መጽሐፍት ሲከፈቱ አካቶ ወይም ለአይነ ስውራን ተስማሚ የሆኑ ቤተ መጽሐፍትን መሥራት ቢቻል ችግሩን እንደሚያቀል ይመክራል። የተለያዩ ጸሐፊዎችም ድጋፍ ሊያደርጉላቸው የሚችሉ አካላትን በማፈላለግ እና ምሳሌ ሊሆን የሚችሉ ሥራዎችን በመሥራት የድርሻቸውን ቢወጡ፤ ዐይነ ሥውራን ያሻቸውን የስነ ጽሑፍ ውጤቶች እንዲያነቡ ያግዛቸዋል፡፡

‹‹የሞገስ አንዱ ፍሬ ነኝ›› በማለት ራሳቸውን የሚገልጹት አቶ ሆነልኝ መልኬ፤ የሞገስ ቀድሞ ተማሪና አሁን ደግሞ ጓደኛ ናቸው፡፡ በ1997 ዓ.ም አቶ ሞገስ ‹‹ዐይነ ሥውራን በትምህርት መታገዝ አለባቸው፡፡›› ብለው ‹ኦሲስ የዐይነ ሥውራን ድጋፍ ማሕበር›ን በማቋቋም በትምህርት ላይ ብዙ ሥራዎችን መሥራታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ እና በየካቲት 12 ትምህርት ቤቶች የዐይነ ሥውራን ቤተ መጽሐፍትን ማቋቋም በመቻላቸው፤ እርሳቸውም አንዱ ተጠቃሚ እንደነበሩም ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በርካታ ዐይነ ሥውራን የሕይወት ክሕሎት ስልጠና እንዲያገኙ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

እንደ አቶ ሆነልኝ ገለጻ፤ የዐይነ ሥውራን ሕይወት በኢትዮጵያ አስከፊ የሚባል አይነት ነው፡፡ ችግሩ በትምህርት እና በሌሎች ላይም በስፋት የሚታይ ነው፡፡ ችግሩ በስፋት በሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ የሚታይ ሲሆን፤ የድርሰት ውጤቶች ጉድለቶችን መሙላት አለባቸው፡፡ ነገር ግን በእኛ ሀገር ብዙ ጊዜ ደራሲያን ወይም የኪነ ጥበብ ሠዎች የሚዘነጉት የኅብረተሰብ ክፍል አለ። የተተወ (የተረሳ) ነገር ካለ በራሱ ሙሉ አይደለም ወይም ጎዶሎ ነው የሚሉት አቶ ሆነልኝ፤ መጽሐፉን በብሬል ማሳተም መቻል በራሱ ምልክት ነው በማለት ይገልጹታል፡፡

የሰባት ዓመት ታዳጊ እያሉ በዘመኑ በብሬል የታተሙ መጽሐፍትን አግኝተው ማንበብ አዳጋች እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሆነልኝ፤ እንደ እነ ሞገስ ያሉ እና ዐይነ ሥውር ሕጻናት እና ታዳጊዎች እንዲያነቡ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች መበረታታት እና መመስገን እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡

ሞገስ በበኩሉ፤ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር ማድረግ አለበት ይላል፡፡ ‹‹በእርግጥ በሥራ ቦታ ላይም ይሁን በትምህርት ቤት አካባቢ አጥጋቢ ባይሆንም የመንግሥት አስተዋጽኦ አለ ማለት ይቻላል›› የሚለው ሞገስ፣ መጽሐፍትን ወደ ብሬል በማስቀየር እንዲሁም የብሬል መርጃ መሳሪያዎችን ድጋፍ የማድረግ ጥረቶች እንዳሉ ያስረዳል፡፡ ዐይነ ሥውራን ሠራተኞች በመንግስት ሥራ ላይ እንዲሠማሩ ረዳቶችን በመቅጠር እንዲሠሩ እየተደረገ ያለው ጥረት መበረታታ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ለዐይነ ሥውራንም ሆነ አካል ጉዳተኞች የሚሠሩ ሥራዎች እንደ ዜጋ መብት መቆጠር አለበት፡፡›› ስለዚህም የነገዋን ኢትዮጵያ ከማቆየት አንጻር ልጆች ላይ መሥራት እንዳለበት ያስረዳል፡፡

ሞገስ በያዝነው ዓመት የ‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች› ተከታዩን ክፍል ለማሳተም ቀን ቆርጦለታል። ‹‹ቀጣዩንም መጽሐፍ በብሬል የማሳተሙ ነገር ሳይታለም የተፈታ ነው›› ይላል፡፡

በተያያዘም፤ ‹‹ወላጆች ልጆቻቸውን፣ ምግብ በማብላት፣ በማልበስ፣ ትምህርት ቤት በማስገባት ኃላፊነታቸውን የተወጡ አድርገው ያስባሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ ለልጆቻቸው ጊዜ በመስጠት በመቀራረብ እና የነገ ሕይወታቸው ላይ መሥራት ይገባል፡፡›› ያለው ሞገስ፤ ‹ቤተ አእምሮ› የተሰኘ ማሕበራዊ ትስስር ገጽ በመክፈት ወላጆች ለልጆቻቸው ማስነበብ ስላለባቸው መጽሐፍት እና ሌሎች መረጃዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You