የጁዶ ስፖርትን በአጭር ጊዜ ውጤታማ የማድረግ ጅምር

የዘመናዊ ስፖርት መሠረቶች ባህላዊ ጨዋታዎችና እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ከሚዘወተሩ የባህል ስፖርቶች መካከል አንዱ ትግል ሲሆን ከኦሊምፒክ ውድድሮች መካከል አንዱ ከሆነው የጁዶ ስፖርት ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተዘውታሪ የሆነውን ባህላዊ ስፖርት ከዘመናዊው ጋር በማቀናጀት ውጤታማ መሆን ቢቻልም ብዙ አልተሠራበትም፡፡ በቅርቡ በብሔራዊ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ በፌዴሬሽን ደረጃ የተመሠረተው የጁዶ ስፖርት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከምትሳተፍባቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ ለመሆን አቅዶ እንቅስቃሴውን ጀምሯል፡፡

በኢትዮጵያ ካሉ የስፖርት ማኅበራት 32ኛው ሆኖ የተመዘገበው ጁዶ ለዓመታት የዘለቀ እንቅስቃሴ ቢኖረውም ተዘውታሪነቱ ግን የተገደበ ነበር፡፡ ላለፉት ዓመታት የጎላ እንቅስቃሴ የነበረውም በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ኦሮሚያ ክልሎች ሲሆን፤ ሀገር አቀፍ ደረጃ እንደ ፌዴሬሽን ዕውቅና ማግኘቱን ተከትሎም የተሻለ እድገት ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተደርጎበታል፡፡ ፌዴሬሽኑ አዲስ እንደመሆኑ በቅደም ተከተል በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ቢጠበቅበትም፤ በጥቂት ክለቦች እና ግለሰቦች የተገደበውን ስፖርት በተደራጀና ወጥ በሆነ አካሄድ ተዘውታሪነቱን ለማስፋት እንደሚሠራ ጠቁሟል፡፡ ከተወዳዳሪነትና ውጤታማነት ጋር በተያያዘም ስፖርቱ ባህላዊ መሠረት ያለው በመሆኑ በአጭር ጊዜ የተሻለ ደረጃ ላይ የመድረስ ዕድል እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡

የጁዶ ስፖርት ከትግል ስፖርት ጋር ያለው ተቀራራቢነት ፌዴሬሽኑ እምቅ አቅም ያላቸውን ስፖርተኞች በስፋት ለማገኘት ያስችለዋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ የባህል ስፖርተኞች የተሻሉ ታጋዮች በመሆናቸው ከዘመናዊው የጁዶ ስፖርት ጋር በማቀናጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ተፎካካሪና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ጥረት የማድረግም እቅድም በፌዴሬሽኑ በኩል ተወጥኗል፡፡ በትልቁ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያ የምትወከልበት ስፖርት እንዲሆን ለማስቻልም ጥረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ማስተር ወንድሙ ደሳለኝ እንደሚናገሩት፣ ጁዶ ከኦሊምፒክ ስፖርቶች አንደኛው እንደመሆኑ በብሔራዊ ደረጃ በፌዴሬሽንነት ተመዝግቦ እንቅስቃሴ አለማድረጉ የዘገየና ስፖርቱ እንዳያድግ ያደረገ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ስፖርቱ በሚገባው ልክ ማደግ ባለመቻሉ ኢትዮጵያ በበርካታ ኦሊምፒኮች በጁዶ ሳትሳተፍ መቅረቷም የሚያስቆጭ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ይገልጻሉ፡፡ አሁን በብሔራዊ ደረጃ እውቅና ማግኘቱም ለስፖርቱ በርካታ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ሲሆን፤ የመጀመሪያውና ዋነኛው ስፖርቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲስፋፋና እንደልብ ለመንቀሳቀስም የሚያግዝ ነው፡፡ በኦሊምፒክ ኢትዮጵያን መወከል የሚችሉ ስፖርተኞችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማፍራት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራትም መንገድ ይከፍታል፡፡ ስፖርቱ በስፋት ሲዘወተርና ሲስፋፋ በአህጉር አቀፍና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሀገራቸውን የሚወክሉ ስፖርተኞችን እንዲወጡ የሚረዳም ይሆናል፡፡

ከተጠቀሱት ነጥቦች ባሻገር ጁዶ በፌዴሬሽን ደረጃ መቋቋሙ የሚያስገኘው ጥቅም በጣም ብዙ መሆኑን የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ፤ የጁዶ ስፖርት እንደሌሎች የፍልሚያ ስፖርቶች በቀላሉ የሚሠራ አለመሆኑን ያብራራሉ፡፡ ሌሎች የፍልሚያ ስፖርቶች እንደልብ በአደራሾች ውስጥ በቀላሉ የሚከወኑ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ጁዶ የመወርወርና የመጣል ዓይነት ባህሪን በመላበሱ ለስፖርቱ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ያስፈልጉታል። እነዚህን ቁሳቁሶች ለማሟላትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ለማግኘት ሀገር አቀፍ ዕውቅናው የሚያግዘው ይሆናል፡፡ ለስፖርቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በሀገር ውስጥ የማይገኙ በመሆኑ ለማሟላት

 ሰፊ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ የራሱ የሆነ ልብስና ምንጣፍ የሚያስፈልገው ሲሆን ውድና በቀላሉ የማይገኙም ናቸው፡፡ ስለዚህም ከኤምባሲዎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ጥቅም ላይ የዋሉትን በእርዳታ መልኩ ለማሰባሰብና ግዢዎችን አድርጎ ለማቅረብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ፌዴሬሽን መሠረቱ ከአስፈላጊም በላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም ሕጋዊ አሠራርን በመከተል ለስፖርቱ የሚያስፈልገውን መሣሪያ በእርዳታና በግዢ ማምጣት ያስችለዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በቅደም ተከተል መሠራት የሚገባቸውን ሥራዎችን ካከናወነ በኋላም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመተባበር ስፖርተኞችን በአንድ በማሰባሰብ ወደ ሥልጠና እንደሚገባም አስታውቋል፡፡ ወደ ውድድር ከመግባቱ በፊት አንድ ማዕከል ውስጥ በመሰበሰብ ብቁ የሆኑ ሰልጣኞች፣ አሰልጣኞችና ዳኞች ማሰልጠን የመጀመሪያ ሥራው ይሆናል፡፡ ይህንንም ለመከወን እቅዱን መሠረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውም ታውቋል፡፡

ስፖርቱ አዲስ በመሆኑና እንደ ሌሎቹ በስፋት ባለመታወቁ ከመንግሥት ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ ከሚመለከታቸው አካላት እንዲደረግለት ጥሪ አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም ስፖርቱ የኦሊምፒክ ስፖርት እንደመሆኑም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ድጋፉን እንዲያደርግና ስፖርቱን በጋራ በመደገፍ በአጭር ጊዜ ውጤታማ ማድረግ ይገባል፡፡ ስፖርቱን ለማሳደግ እቅዶችን በመንደፍና ባለሀብቶችን በማሳተፍ የፋይናንስ ምንጩን ለማስፋት የሚሠራም ይሆናል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You