አስደናቂ እና አስገራሚ የሆኑ ቅርሶችና የቱሪስት መስህቦች በበዙባት ሕዝባዊት ቻይና 56 ብሔር፣ ብሔረሰቦች ሰም እና ወርቅ ሆነው፣ ኅብር ፈጥረው እና ተዋድደው በሰላም ይኖሩ ባታል። ከእነዚህ ውስጥ ሀን ተብሎ የሚታወቀው እና የቋንቋው መሠረት የሆነው የቻይና ሕዝብ 91.5 % ቢሊዮን ሲሆን፤ ቀሪው 1.14 % ቢሊዮን የአናሳ ብሔረሰቦች ስብስብ ነው። በአጠቃላይ የቻይና ሕዝብ ቁጥር 1.4 ቢሊዮን ሲሆን፤ ይኸውም ቁጥር ከፍ ሊል የቻለው እያንዳንዷ የቻይና ሴት (ከአናሳ ብሔረሰቦች በስተቀር) ቀደም ሲል በወጣው የወሊድ ቁጥጥር ሕግ እና ገደብ መሠረት አንድ ብቻ እንድትወልድ ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ በአሁኑ ጊዜ ሁለት ሁለት እንድትወልድ በመፈቀዱ ነው።
ይህም የሕዝብ ቁጥር ከአፍሪካ የሕዝብ ቁጥር ጋር የሚስተካከል ነው። በቁጥር አነስተኛ የሆኑት ብሔረሰቦች 4 (አራት) የራስ አገዝ ክፍለ አገሮች ሲኖሯቸው፤ የከተማ፤ የንዑስ ከተማ እና የቀበሌ አስተዳደርም አሏቸው። ሁሉንም የቻይና ዜጎች ከከተማ እስከ ገጠር፤ ከጠረፍ እስከ ጠረፍ የሚያግባባቸው፤ ማስታወቂያዎች እና ታፔላዎች የሚፃፉት ማንዳሪን ተብሎ በሚታወቀው የሀገሪቱ ቋንቋ ቻይንኛ ነው። እነዚህ አናሳ ብሔረሰቦች በሕዝባዊት ቻይና ምክር ቤት የ13.6% የውክልና ድምፅ አላቸው። በቻይና 34 ክፍለ ሀገሮች ሲኖሩ፤ በሁሉም ቦታዎች አስገራሚ እና ማራኪ ታሪካዊ ቦታዎች እና የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ።
ከአስደናቂ እና አስገራሚ ታሪካዊ ቦታዎች እና የቱሪስት መስህቦች ውስጥ በዚህ ጽሑፍ በሕዝባዊት ቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ (በቀድሞ አጠራሯ ፔኪንግ) እና በድህነት ቅነሳ ሞዴል በሆነችው እና ከቤጂንግ ወደ ደቡባዊ ቻይና 1‚800 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው እና በድህነት ቅነሳ ሞዴል በሆነቺው በጉይጆ ክፍለ ሀገር ስለሚገኙት ታሪካዊ ቦታዎች እና የቱሪስት መስህቦች በጥቂቱ ለማስቃኘት እሞክራለሁ።
በቤጂንግ ከተማ ታሪካዊ እና የቱሪስት መስህቦች ከሆኑት ውስጥ የመንጎልያን እና የጃፓንን፤ የሌሎችን ወረራ ለመከላከል የተገነባው እና ከ20 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሆነው ታላቁ የቻይና ግንብ፤ የቤጂንግ ከተማ ፕላን ኤግዚቢሽን አዳራሽ፤ የሒኑሀ (ዥኑዋ) ዜና አገልግሎት ድርጅት፤ የከተማዋ ሙዚየም፤ ዓለም አቀፍ የቻይና ዲጂታል ሚዲያ የህትመት ቡድን፤ የቻይና ሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ሙዚየም፤ ታላላቅ የንግድ ማዕከላት፤ ኢምፔሪያል አካዴሚ፤ የፈላስፋው የኮንፊሺየስ ማዕከል፤ በከተማው እምብርት ላይ የሚገኘው፤ ሁልጊዜ በቱሪስት ፍሰት የሚጨናነቀው እና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሣይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የመንግሥተ ሰማይ ቤተ መቅደስ (ቤተ ጣዖት) ተጠቃሾች ናቸው። በተለይ በቻይና ሙዚየም ውስጥ ወደ ኅዋ ያመጠቁት የሮኬት ምስል፤ የዓለም ታላላቅ የፖለቲካ መሪዎች፤ የሣይንቲስቶች፤ የአገር አሳሾች እና ተጓዦች ፎቶ ግራፎች፤ የሰዓሊዎች ምስሎች፤ የነሞናሊዛ ስዕሎች፤ ኢንዱስትሪያሊስቶች—ፎቶ ግራፎች በሥርዓት ተሰድረው ይገኛሉ።
በቻይና ታሪክ ታላቁ ግንብ ከክርስቶስ ልደት በፊት (ከ771-576) ተጠናክሮ በቻይና የመጀመሪያው ንጉሥ በሆነው በኩይን ሺ ሁዋንግ የተሠራው ለጦር ምሽግ እና ለሀገር መከላከያ እንዲሆን እና ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ221-206 የተመሠረተውን አዲሱን የኩይንን ሥርዎ መንግሥት ከወረራ ለመጠበቅ ታስቦ እና ከክርስቶስ ልደት ከ475-221 ድረስ በአካባቢው የነበሩ የጦረኛ መንግሥታትን እና የእስያ ዘላን ወራሪዎችን፤ የመንጎልያ ፈረሰኞችን፤ የጃፓን ጦረኞችን ጫና ለመቆጣጠር ታቅዶ ነው።
በመንኮራኩር ላይ ሆኖ መሬት ላይ ከሚታዩ ነገሮች ውስጥ ዋነኛው የቻይና ግንብ መሆኑ፤ በታሪክ የተመዘገበውን አስደናቂ ቦታ የዓለም ቱሪስት በየዕለቱ የሚጎበኘው ሲሆን፤ የቻይና መንግሥት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ጎብኚዎች ከፍተኛ የሆነ ገቢ እንደሚያስገባ ይታወቃል።
በጥንታውያን የቻይና አማንያን አስተሳሰብ መንግሥተ ሰማይ ክብ፤ መሬት ደግሞ አራት ማዕዘን እንዳላቸው ተደርገው ይታሰቡ ነበር። በየቀኑ ከፍተኛ በሆነ የቱሪስት ፍሰት ከሚጨናነቁ የቤጂንግ ከተማ ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ የመንግሥተ ሰማይ ቤተ መቅደስ ( Temple of Heaven) የሚባለው አንደኛው ሲሆን፤ የጥንቱን እሳቤ መሠረት ባደረገ መልኩ የተገነባ ነው። የመንግሥተ ሰማይ ቤተ መቅደስ ሕንፃ የሚንግና ኩዊንግ ሥርዎ መንግሥት ነገሥታት እንዲኖሩበት ታስቦ የተሠራው እ.ኤ.አ በ1420 ነው። ቤተ መቅደሱ ሦስት ክብ ጉልላቶች ሲኖሩት፤ ከላይ ያለው የመንግሥተ ሰማያት፤ ሁለተኛው የመሬት፤ ሦስተኛው ደግሞ የሰው ልጅ ምሳሌ እንዲሆን ታስቦ እንደታነፀ ይነገራል። (ታንጿል) ። ነገሥታቱ በመንፈስ ወደ መንግሥተ ሰማይ ሄደው በያመቱ አስተማማኝ ዝናብ በመላ ቻይና እንዲዘንብ፤ በቂ ምርት እንዲገኝ፤ አስተማማኝ ዝናብ በመላ ቻይና እንዲዘንብ፤ በሀገር ላይ ፍቅር እና ሰላም እንዲኖር ፀሎት ያደርጉበት ነበር።
አብዛኞቹ የሕንፃው አዳራሾች እንደገና ተጨምረው የተገነቡት በኩዊንግ ሥርዎ መንግሥት (ዘመን አቆጣጠር) ከ1644-1911 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። መሠረቱ የተጣለው ደግሞ በሚንግ ሥርዎ መንግሥት ከ1368- 1644 ባለው ወቅት በተለይም በንጉሥ ጂያጂንግ ዘመን ነው። የግቢው ንጣፍ እና የመግቢያ በር ምሰሶዎች የተሠሩት በተፈጥሮ ከሚያንፀባርቅ እብነ በረድ ነው። በ273 እስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ የተገነባው ቤተ መቅደስ የቻይናን ጥንታዊ የንድፍ አሠራር ያመለክታል። ፀሎተኞች ስለ አዝመራ እና ስለ ሰብል (ልዩነቱ ምንድን ነው) በረከት የሚፀልዩበት፤ የመሥዋዕት ማቅረቢያ ክፍል፤ ነገሥታት ለፈጣሪ የሚፀልዩበት እና የሚማልሉበት አዳራሾች በየዘርፉ ቆሞው ይታያሉ። ከቤተ መቅደሱ ጋር ተያይዞ የተገነባው ድልድይ፤ ረጃጅም መተላለፊያ ኮሪዶሮች፤ ባለኮከብ መልክ ድንጋይ፤ ዘጠኝ አስፈሪ የደራጎን ምስሎች፤ የሙዚቃ ማሳያ ቦታዎች፤—–ይገኛሉ።
ቤተ መቅደሱ በቻይና ታሪክ በአሠራሩ እና በውበቱ እጅግ ከፍ ያለ እና በአስደናቂነቱ በምሣሌነት የሚጠቀስ ነው። የቻይና የመንግሥተ ሰማይ ቤተ መቅደስ እ.ኤ.አ በ1998 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሣይንስ እና የባህል ድርጅት በቅርስነት ተመዝግቧል። በቻይናም በተለያየ ወቅት ብሔራዊ የቻይና ሕዝብ የስልጣኔ መገለጫ በመባል የክብር ቦታውን ይዟል። ቤተ መቅደሱ ውስጥ የቡድሂዝም እምነት ተከታይ የሆኑ እና ቢጫ ልብስ የለበሱ ካህናት መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጣሉ። (ውርውር ሲሉ ይታያሉ)።
ከበርካታ ቱሪስቶች ጋርም ፎቶግራፍ ይነሣሉ። የእንስሳት መስዋዕት ወደሚሰዋበት እና የበግና የሌላ እንስሳ ምስል ወደሚታይበት ክፍል መግባት ፈጽሞ የተከለከለ ሲሆን፤ ለመስዋዕት የሚቀርቡ የእንስሳቱን ምስል ያነሣሁት በርቀት ላይ ሆኘ ነው። እንስሳቱ የሚታዩበት ቦታ ቤተ መስዋዕት እና ቤተ አምልኮ ተብሎ ይጠራል። ይህም የቻይና ጥንታውያን ነገሥታት የሚፀልዩበት እና ከፈጣሪ ጋር በመንፈስ የሚገናኙበት የተቀደሰ ቦታ ተደርጎ ይታያል (ይታመናል)። በቻይና ውስጥ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ቱሪስት ከሚጎበኛቸው ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ የተከለከለው ከተማ (ዘፎርቢድን ሲቲ) አንደኛው ነው። ሙሉ በሙሉ ከእንጨት የተገነባው ቤተ መንግሥት በጥንቱ ዘመን የቻይና ነገሥታት ይኖሩበት የነበረ ሥፍራ ነው።
በቻይና የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ እንደ ሞዴል በምትታየው እና 34ተኛዋ ክፍለ ሀገር በሆነቺው በጉይጆ ግዛትም በርካታ ታሪካዊ ቦታዎች እና የቱሪስት መዳረሻዎች ይገኛሉ። ለአብነት ያህል በቢጀ ወረዳ በዳፋንግ ቀበሌ በሊዩሎንግ እና በሼሂያንግ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ጥንታውያን የቤተ መንግሥት ሕንፃዎች፤ በሞታይ ከተማ የቆሙት የኮንፊሺየስ፤ የማኦዜዱንግ እና የቹኤን ላይ፤ የቀድሞው ነገሥታት፤ የፈላስፎች፤ የሀገር መሪዎች፤ የሥነ ጥበብ ሰዎች ሐውልቶች ተጠቃሾች ናቸው። በሚያምር እና በሚስብ መልኩ የቆሙትን የሐውልቶች ብዛት ስመለከት «እናንተ፡ ሐውልታት እኔ አገር ብትሆኑ ኖሮ በአካፋ እና በዶማ ፍርስርሳችሁ ይወጣ ነበር ብዬ ተሣለቅሁባቸው። ለምን ቢባል በሀገራችን የቆመ ሐውልት በመልካምነቱ እና በመጥፎነቱ የታሪክ ማስታወሻ ሆኖ መቀመጥ እና መከበር ሲገባው፤ በጊዜያዊ ጫጫታ እና እብሪት ለማፍረስ ስለምንቸኩል ነው። ለዚህም በአፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር (E.C.A) ጽ/ቤት አካባቢ ቁሞ ኋላ ያፈረስነው የሌኒን ሐውልት፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሱዳን ተነስተው እና በኦሜድላ በኩል በእግር ተጉዘው ጎጃም ፍኖተ ሠላም ከተማ በድል አድራጊነት መግባታቸውን እና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መትከላቸውን የሚያመለክተው ሐውልት፤ ፒያሳ ሲኒማ ኢምፓየር በሕንዶች ለማስታወሻነት ቁሞ የነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት፤ ጂግጂጋ የጀግናው አፈወርቅ ወልደ ሰማዕትን የጀግንነት ሐውልት—ፍርስርሱ እንዲወጣ ከማድረጋችን አልፎ አዲስ አበባ ያለውን የምኒልክን ሐውልት እና ሐረር ከተማ ላይ የቆመውን የራስ መኮንን ሐውልትን ለማፍረስ በየጊዜው ስንዝት እንታያለንና ነው።
ከዚህ በታች የምንመለከተው፤ የሰውን ልጅ ትኩረት የሚስበው፤ መንፈስን የሚያድሰው እና የሺያንግን ጥንታዊ ከተማ ሕንፃዎች የሚወክለው ቤት የሚያመለክተው የጥንቱን የቻይና ቤት አሠራር ነው። ይህ ሕንፃ በቤተ መንግሥትነት በ11ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባ እና የነገሥታት መኖሪያ የነበረ ነው። ነገር ግን ዛሬ የቱሪስት መናኸሪያ የሆነው የሺያንግ ጥንታዊ ከተማ ከሁለት ጊዜያት በላይ በጦርነት ፈርሶ የነበረ ሲሆን፤ የከተማውን ሕንፃዎች እና የቤተ መንግሥት ሕንፃዎችን የሚወክለው ይህ ቤት የቀድሞ ቅርፁን እና ውበቱን በጠበቀ መልኩ እንዲታደስ ተደርጎ እና በሙዚየምነት ተጠብቆ በውስጡ ያካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋን እና ልዩ ልዩ ታሪክ የሚነበብባቸው የስዕል መገለጫዎችን አካትቶ እንዲይዝ ተደርጓል።
በዚያው ሺያንግ የጥንት ቤተ መንግሥት ውስጥ በሚገኝ አደባባይ ላይ ሌሎች የቱሪስት መስህብ የሆኑ የልዩ ልዩ የዱር እና የቤት እንስሳት ምስሎች ክብ ቅርፅ ይዘው ይታያሉ። እነዚህም በቁጥር አስር ሲሆኑ፤ አደባባዩ የቻይናን ዘመን አቆጣጠር ተከትሎ ቻይናውያን በአዲስ ዓመታቸው በእንስሳቱ ምስል ዙሪያ እየዞሩ እና እየዘፈኑ በዓላቸውን የሚያከብሩበት እና ፈንጠዝያ የሚያደርጉበት ቦታ ነው። ዘመናቸውም የዝንጀሮ፤ የጦጣ፤ የነብር፤ የደራጎን፤ የበሬ፤ የጥንቸል—- ወዘተ. እየተባለ እየተሰየመ በያመቱ ተሰይሞ ይከበራል።
በጉይጆ ክፍለ ሀገር ዳንሻይ ከተማ በኩያንዶንግናን ውስጥ የምትገኘው የዋንዳ የገጠር መንደር የዓለም ቱሪስቶች መዲና ተደርጋ ትታያለች። በዚያች የገጠር ከተማ ቀለመ ደማቅ የሆኑ የሚያዎን እና የዶንግን፤ የሚጃንግን ብሔረሰቦች የሚወክሉ ልጃገረዶች እና ወጣት ወንዶች (ጎረምሶች) እንደ ቃጭል ድምጽ በሚያሰማ ባህላዊ አለባበስ አሸብርቀው፤ የብር ዘውድ ደፍተው በዋንዳ ከተማ የውዝዋዜ መድረክ ላይ ሌትም ቀንም ያለምንም ረፍት በሚየዎ የሙዚቃ መሣሪያ እየታጀቡ እና እየተጫወቱ የሚያቀርቡት ድራማ፤ የሚያሳዩት ዘመናዊ ዳንስ እና ባህላዊ ጭፈራ ቱሪስቶችን በእጅጉ ይማርካል። ከዚህም በላይ በራሳቸው ግብዣ ከሁሉም ቱሪስት ጋር ለመደነስ እና ፎቶ ግራፍ ለመነሣት የሚያሳዩት በጎነት እንግዳ አክባሪ እና ሰው አፍቃሪ መሆናቸውን ያመለክታል።
በአንሹን ከተማ ውስጥ የሚገኘው፤ በውበቱ እጅግ የሚያምረው እና የመላው ዓለም ቱሪስቶች መናኸሪያ የሆነው፤ 77.8 ቁመት እና 101 ሜትር ስፋት ያለው እና በምድራችን በድንቅነቱ እና በትልቅነቱ የሚታወቀው የሁዋንግሁዋሾው ፏፏቴም በየቀኑ ቱሪስቶች አይተው የሚደመ ሙበት ስፍራ ነው። ወደ ፏፏቴው ሌሎች 12 ፏፋቴዎች ከተለያየ አቅጣጫ መጥተው ፏፋቴውን ይቀላቀሉታል። መብረቃዊ ድምጽ ያለውን እና እንደ ነጎድጓድ ልብ የሚያሸብረውን ይህንን የፏፏቴ ትዕይንት ከ300 ዓመታት በፊት አፋፉ ላይ ቁሞ የተመለከተው፤ ተጓዥ እና ዝነኛው የጂኦግራፊ ምሁር የነበረው ቻይናዊው ሁ ሂያኬ ይህ እንደ አንበሳ የሚያገሳው እና ጭሱ የአካባቢውን ሰማይ የሚሸፍነው የፏፏቴ ምንጭ የሚነሣው ከግሪክ አለታማ ድንጋይ ሥር ነው ብሎ ነበር።
በመሆኑም ነጎድጓዳማውን ፏፏቴ በደንብ ለማየት የሚቻለው ወደ ገደሉ ሥር በመውረድ ነው። እስከ ገደሉ ሥር እርከን እርከን ያለው የጣውላ መንገድ የተዘረጋለት ሲሆን፤ ከገደሉ ሥር ሲደረስ ቦታው በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ቱሪስቶች ስለሚጨናነቅ ከቡድን ውስጥ ማን የት እንዳለ ለመለየት ያስቸግራል። ያ ሁሉ ወፈ ሰማያት ቱሪስት ወደላይ የሚመለሰው ደግሞ በረጅሙ በተዘረጋ አሳንሰር ሲሆን፤ ከአስጎብኚው የተለየ እና ቻይንኛ የማያውቅ እንግዳ ችግር ውስጥ ይወድቃል። በበኩሌም ፎቶ ግራፍ ለማንሣት ስል ከመንጋዎቼ (ከጓደኞቼ) ለብዙ ደቂቃዎች ተለይቼ እና ያሉበትም ቦታ ጠፍቶኝ ስለነበር ብዙ መጉላላት ደርሶብኛል።
በፏፏቴው ሥር እና ከገደሉ በላይ በአለው መንደር ደግሞ በእጅጉ ለዓይን የሚማርክ እና የቻይናን የእደ ጥበብ ውጤቶችን የሚያመላክት ብርቅ እና ድንቅ ነገር ስለሚታይ ቦታውን እየጎበኙ ዕቃ መግዛት፤ መዝናናት፤ መደነስ እና መጨፈር ያስደስታል። በዚያው በአንሹን ከተማ የሚገኘው እና የጨረቃ ቅርፅ ያለው የደራጎን ቤተ መንግሥትም የቱሪስቶችን ትኩረት በመሳብ ይታወቃል። ባሊ አዛሊያ ተብሎ የሚጠራው እና 125.8 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻ ቦታ ይገኛል። ይህ ቦታ በዓለም ትልቁና የተፈጥሮ ደን መናፈሻ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን፤ በአበባ ያሸበረቀ ነው። በተፈጥሮ ዛፍ ላይ በሚያብቡት አበቦች የተዋበው የባሊ አዛሊያ ደን የአዛሊያ ሥርዎ መንግሥት ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ «የገነት እስትንፋስ» በሚል ተጠብቆ የዓለምን ሕዝብ በማዝናናት ላይ ይገኛል። በተለይም በያመቱ ሚያዝያ ወር ላይ ሕዝባዊ ፌስቲቫል የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚያ የደስታ እና የፈንጠዝያ በዓል ላይ የዓለም አቀፍ ቱሪስቶች እና የሀገር ውስጥ እንግዶች እየተገኙ የዕረፍት ጊዜያቸውን ያሳልፉበታል። ወደ ጉይጆ ዋና ከተማ ወደ ጁዋንግ መዳረሻ ቦታ ላይም ቱሪስቶችን የሚያስደንቅ እና ለእይታ የሚያምር በሒሒው ወረዳ ጥንታዊው የጂሾው ከተማ እና የጥንት ነገሥታት ቤተ መንግሥት ይገኛል። ቤተ መንግሥቱ በቅርስነት ተይዟል ። ከተማውን ልዩ የሚያደርገውም ከገደል ሥር እየፈለቀ በየመንደሩ በቦይ የሚፈሰው ንፁህ ውሃ ነው።
እነዚህን ታሪካዊ ቦታዎችን እና የቱሪስት መስህቦችን የተመለከተ አጭር ዘገባ ለማየት እና ጽሑፍም ለመጻፍ የተነሣሣሁት ከኢትዮጵያውያን እና ከአፍሪካውያን ጓደኞቼ ጋር በመሆን ቦታዎቹን በመጎብኘቴ ነው። ስለአየኋቸው እና ለዚህም ምስጋና ይግባቸው እና ክቡር ዶክተር አቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀደም ሲል ለኪነ ጥበብ ሰዎች ጥሪ አድርገው እና በቤተ መንግሥት ሰብስበው ስለኪነ ጥበብ ጠቀሜታ በአወያዩበት ወቅት ለ50 ሰዎች የቻይና ጉብኝት ዕድል ሲሰጡ፤ እኔም ከኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ተመርጨ የዕድሉ ተጠቃሚ ሆኛለሁ። ለዚህም ለክቡር ዶክተር አቢይ አህመድ ላቅ ያለ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ!!
ምንጭ
Information Office of the People’s.Government of Guizhou Guizhou Bureau of Statistics (2018) An Overview of Guizhou,Guizhou Publishing Group.
Handbook( 2018) Renowned Commentators or Columnists of Major Media from African Countries Visit Guizhou
Overviewof Evergrandes Partner Assistance Program In Bijie City ,Guizhou Province ,China 2018
ዘመን መጸሄት መጋቢት 2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Khả năng của bạn trong việc liên kết các ý tưởng rất tuyệt vời, tạo ra một narrative chặt chẽ.