የምሁር ዕውቀት የሰዎችን ኑሮና አኗኗር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻሻል የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ። በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ፤ ስለዚህ፣ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” ለመባል ብቁ የሚሆነው ዕውቀቱን ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚጠቀምበት ከሆነ ነው። ምሁርነትም ከዚህ አንፃር ታይቶና ተመዝኖ የሚሰጥ ክብር አንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።
ምሁር ለሚለው ቃል አቻ እንግሊዘኛ ትርጉሙ ኢንተለክቹዋል የሚለው ፍቺ ነው። የአማርኛ ቋንቋ ደግሞ ምሁር የሚለውን ቃል ከፍተኛ የሆነ የማሰብና የመመራመር ችሎታ ያለው ብሎ ይተነትነዋል ወይም ትርጉም ይሰጠዋል። በትምህርት የሚገኘው ዕውቀት በተግባር ለውጥና መሻሻል ካላመጣ ትምህርት መማሩና ማስተማሩ በራሱ ትርጉም የለውም ይላሉ ብዙዎች። የአንድ ሰው በትምህርት የተገኘ ዕውቀት ፋይዳ የሚኖረው በራስና በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ሲያስችል እንደሆነ በመግለፅ።
ምሁርን በተመለከተ በርካታ ሰዎች ጽፈዋል፤ ብዙዎቹ እንደሚናገሩት፤ ሁል ጊዜ ትልቁ የመከራከሪያ ነጥብ ብያኔውን በተመለከተ በግልፅ ማስቀመጥ አለመቻል ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አረዳድ ምሁር ማለት በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አልፎ ዲግሪ የያዘ ሰው ማለት ነው።
ምሁር ምን ማለት እንደሆነ ግን በምሳሌ በቀላሉ እንረዳለን። ሻማ ብንወስድና ሻማ በካርቶን ውስጥ እንዳለ በቤት ውስጥ ቢቀመጥ እንደማንኛውም በቤት ውስጥ እንዳለ ዕቃ ነው። የበራ ሻማ ግን ክስተት ነው። ሻማውን ከብርሃኑ ለይተህ አታየውም። የበራው ሻማ ለራሱ ሲል አይበራም ለሁላችን እንጂ፤ ምሁር ማለት የበራ ሻማ ማለት ነው። የተማረ ማለት ደግሞ ያልበራ ሻማ ማለት ነው፤ የመብራት አቅም አለው ነገር ግን አልበራም።
ስለዚህ ምሁር ማለት በልምድ፣ በትምህርትና በልዩ ልዩ መንገድ ያገኛቸውን ማስተዋሎችና ዕውቀት በሐሳብ መልክ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርብ ሰው ነው። ለዚህ ቃል ብቁ ሆነው የተገኙ ጥቂት የሚባል ቁጥር የሌላቸው በዓለም መድረክ ላይ አዳዲስና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግኝቶችንና ፈጠራዎችን ይዞ ብቅ በማለት የበርካቶችን አንገብጋቢ ችግር የፈቱና ብዙዎችን በስራዎቻቸው ያስገረሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ። ከእነዚህም ልሂቃን መካከል የእርሻ ልሂቅና ተመራማሪ የሆኑት ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ እጃታ አንዱ ናቸው።
ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ስልሳ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት በሆለታ እና ጊንጪ ከተሞች መሃል ላይ በምትገኘው (ኦሎንኮሚ) በምትባል መንደር በ1942 ዓ.ም ተወለዱ። በወቅቱ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት በማምጣት የሚታወቁት ፕሮፌሰር ገቢሳ እስከ 7ኛ ክፍል የተማሩት እዛው ኦሎንኮሚ ሲሆን የዘመናዊ ትምህርት ባካባቢው ባለመኖሩ ቤት ተከራይተው በክፍያ ከሚያስተምር ትምህርት ቤት ነበር የተማሩት:: ቤተሰባቸው በመለያየታቸው ምክንያት ሙሉ በሙሉ ልጃቸውን የማሳደጉ ኃላፊነት የወደቀባቸው እናታቸው ወ/ሮ ሙሉ አያነው ምንም እንኳን ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ ቢሆንም የልጃቸው የትምህርት ጉጉት እና ከእኩዮቹም እንዳይለይባቸው በማሰብ ጠላ እየሸጡ ያስተምሯቸው ነበር::
ፕሮፌሰር ገቢሳ የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ደግሞ ከኦሎንኮሚ 20 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው አዲስ ዓለም ከተማ ዘመድ ጋር በመቀመጥ ቀለባቸውን በየሳምንቱ እየተመላለሱ በመውሰድ አጠናቀቁ:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወቅቱ ከኦክላሆማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር በተከፈተው የጅማ የእርሻ የቴክኒክ ትምህርት ቤት ገብተው በከፍተኛ ማዕረግ በማጠናቀቅ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲን በ1973 ዓ.ም. ተቀላቀሉ::
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእፅዋት ሳይንስ በቀድሞ ስሙ ከዓለማያ ኮሌጅ ባሁኑ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በ1973 ዓ.ም ወስደዋል። እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1976 በእፅዋት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በ1978 በእጽዋት ማዳቀል እና ዘረመል ኢንጂነሪንግ አሜሪካ ከሚገኘው ፑርድ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በመቀጠልም ከፊል በረሃማ በሆኑ የትሮፒካል አካባቢዎች ከዓለም አቀፍ የአዝዕርት ምርምር ተቋማት ጋር ማሽላ ላይ በማተኮር ወደ አፍሪካ በመሄድ ምርምር ማድረጉን ተያያዙት:: ለአምስት ዓመታት ምርምሩን ካከናወነ በኋላ “ሃጂን ዶሮዋን” የተባለ የሱዳንን በረሃ የሚቋቋም እና ውጤቱም በ150% የላቀ ምርት የሚሰጠውን የተዳቀለ ማሽላን አገኙ:: ከዮ.ኤስ.ኤድ ጋር በመተባበርም ይህን ምርጥ ዘር በማምረት ለብዙ ገበሬዎች እንዲዳረስ የዘር ኢንደስትሪ እንቅስቃሴ አስጀመሩ::
ተመራማሪ ገቢሳ በተጓዳኝም Striga ወይም “ሟርተኛው አረም” ተበሎ የሚጠራውን የማሽላ ጠንቀኛ ጠላት ለማጥፋት ወደ ፐርዱ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ ከተመራማሪ ጓደኛው ጋር በመሆን ጥናታቸውን ቀጠሉ:: Striga ወይም “ሟርተኛው አረም” 500,000 ዘሮችን የመበተን እና ዘሩም ከ10 – 20 ዓመት በአፈር ውስጥ የሚቆይ እና የዋናውን ተክል ዘር ሙሉ በሙሉ ወሮ ከጥቅም ውጭ የሚያደርግ አደገኛ አረም ነው:: በምርምራቸውም የዚህን አደገኛ አረም እና የማሽላን ኬሚካላዊ ትስስር በመለያየት ለመታደግ የቻሉ ታላቅ ሰው ናቸው::
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2011 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የዓለም አቀፍ የምግብ እና ግብርና ልማት ቦርድ አባል አድርገዋል ሾመዋቸዋል። ፕሮፌሰር ገቢሳ በተለያየ ጊዜ በማሽላ ላይ ባገኙት አስደናቂ ምርምር የተለያዩ ድቅል የሆኑ የማሽላ ዘሮችን መፍጠር የቻሉ ዕንቁ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
ከ17 በላይ ታላላቅ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፤ የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) 2009 የወርልድ ፉድ ፕራይዝ ተሸላሚም መሆናቸው ይታወሳል። ፕሮፌሰር ገቢሳ በዚህ ዘርፍ የተሸለሙ ሁለተኛው አፍሪካዊ ናቸው። በአፍሪካ ናሽናሊቲ ሳይንስ ሂሮ ሽልማት ከተሸለሙ አፍሪካዊ ሰባት ተመራማሪዎችም አንዱ መሆን ችለዋል።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ ከዚህ ቀደም ጥገኛ አረምን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን ለማዳቀል ለሚሰሩት ምርምር ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ግብረ-ሰናይ ድርጅት አምስት ሚሊዮን ዶላር አሸንፈዋል። በአሜሪካ የፑርዱ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ለሆኑት ገቢሳ እጄታ በቢልና መሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የተሰጠው ድጋፍ ተመራማሪው አረም መቋቋም የሚችል የተዳቀለ ምርጥ ዘር እንዲያለሙ ለማስቻል ነው። በወቅቱ ፕሮፌሰር ገቢሳ ድጋፉ በተለይ ለታዳጊ ሀገሮች ግብርና ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረው ነበር።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ በዘርፉ በሰሩት ስራ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ለሚገኙ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን የዕለት ጎርሳቸውን እንዲያገኙ አስችለዋል። በዚህ ታላቅ ውጤታቸው ከታላላቅ ተቋማት ጋር የሰሩ ሲሆን ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ዮ.ኤስ. ኤድ፣ ሮክፌለር እና ጌትስ ፋውንዴሽን እንዲሁም አባል በመሆንም ከምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ)፣ የሳይንስ ካውንስል፣ የሳሳካዎ ግሎባል የቦርድ አባል እና የአሊያንስ ግሪን ሪቮሉሽን የክብር አባል በመሆን አገልግለዋል::
በርካታ ሽልማቶችን እና ሜዳሊያዎችን ያገኙ ሲሆን በ2009 የወርልድ ፉድ ፕራይዝ ተሸላሚ የዓለም ሎሬት ገቢሳ እንዲሁም ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የብሔራዊ ጀግና የሚል ሽልማት አግኝተዋል:: 2011 ዓ.ም. የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚም ናቸው:: በ2013 ዓ.ም. የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባን ኪሙን በሳይንስ ዘርፍ ሾመዋቸዋል:: ባሳለፍነው ዓመት 2015 ዓ.ም. የቀድሞ ትምህርት ቤታቸው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ አድርጓቸዋል።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ ባሳለፍነው ሳምንት የአሜሪካን ብሔራዊ የሳይንስ ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን 21 አሜሪካውያን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፎች ብሔራዊ የክብር ሜዳሊያ መሸለማቸውን አስታውቀዋል። ብሔራዊ የክብር ሜዳሊያ ከተሸለሙት መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ እንደሚገኙበትም ባይደን በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባወጡት ዝርዝር ላይ አመላክተዋል። በሳይንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሚሰጥ ሽልማት ነው።
በዚህም ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ በሳይንስ ዘርፍ የአሜሪካ ብሔራዊ የክብር ሜዳሊያ ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እጅ ተበርክቶላቸዋል። መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ ለሽልማቱ ያበቃቸው በከፍተኛ የምርምር ስራቸው የእፅዋት ዘረመል ምሕንድስና በመጠቀም በረሃማ የአየር ንብረት እና ነፍሳትን የሚቋቋሙ የአዝርዕት ዘሮችን በማግኘታቸው ነው።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ከዘንድሮው ተሸላሚዎች መካከል አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ እንዲሁም በረሃን የሚቋቋሙ ዕጽዋት በማብቀል የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እንደሆኑ ፕሬዚዳንት ባይደን የክብር ሽልማቱን ለፕሮፌሰሩ ባበረከቱበት ወቅት ተናግረዋል።
በሳይንስና ፖሊሲ ዘርፍ እንዲሁም በምጣኔ ሀብት ማሻሻል ረገድ ፕሮፌሰር ጋቢሳ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለአርሶ አደሮች የተሻለ ሁኔታ መፍጠር የቻለ እንደሆነ እና አገራትን የሚያጠናክርም ነው በማለት ስለ ምርምራቸው በዋይት ሀውስ በተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
የዓለም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሰሩት ሥራ በዓለም መድረክ ከፍ ብለው የሀገራቸውን ስም ያስጠሩ ፀሐፊ፣ አርታኢ፣ መምህር፣ አማካሪ እና ተመራማሪ የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ ከሁለት መቶ በላይ የጥናት ጽሁፎችን ለሕትመት አብቅተዋል። አራት መፅሐፎችን የአርትኦት ስራ ሰርተዋል። ለ28 ዓመታት ያህል በአሜሪካ በሚገኘው ፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ያገለገሉት የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰሩ ዩኒቨርሲቲው አሉኝ ከሚላቸው ተመራማሪዎችም አንዱ ናቸው።
በምግብ ዋስትናው ዘርፍ በተመራማሪነት ባበረከቱት አስተዋጽኦ የዓለም የሎሬትነት ማዕረግን የተጎናጸፉት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ፣” የዓለም ሕዝብ ቁጥር በጨመረ ቁጥር የምግብ ፍላጎት እየጨመረ ይመጣል፤ ይህን ለመቋቋም ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የምርምር ፈጠራ ውጤቶች በመጨመር ይህንን ችግር መቋቋም ግድ የሚል ነው” ይላሉ።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ኢንዲያና በሚገኘው ፕሪዲዩ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ሲሆኑ፤ በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ምግብ ዋስትና ክፍል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እኛም ሀገራቸውን በሥራቸው ከፍ አድርገው ላስጠሩ የሀገር ካስማ ጉምቱ ምሁር ረዥም ዕድሜና ጤና እንመኛለን።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም