የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን የካፍና የፊፋን መስፈርት ያሟላ ስቴዲየም በማጣቱ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎቹን በሌሎች ሀገራት ለማከናወን ከተገደደ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለተለያዩ ወጪዎች የተዳረገ ሲሆን የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አጋር ዋልያ ቢራም በዚሁ የተነሳ በአራት ዓመት የሚከፍለውን የ56 ሚሊዮን ብር ማቋረጡ ታውቋል። ፌዴሬሽኑ 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከትናንት በስቲያ በአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረገበት ወቅት ይህን ችግር በዝርዝር አቅርቧል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፤ የፊፋ እና ካፍ መስፈርት ያሟላ ስታዲየም በኢትዮጵያ ባለመኖሩ ለእግር ኳስ ልማት መዋል ያለበት ወጪ ለውጭ ሀገራት ጉዞና ተያያዥ ወጪ እየዋለ በመሆኑም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መፍትሔ እንዲያበጅ ጠይቀዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ችግሩን ተመልክቶ ብሔራዊ ቡድኑ በሀገሩ ሜዳ ጨዋታውን እንዲያደርግ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁሟል። በጉባኤው ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚህ ወቅት፤ እግር ኳስ በኢትዮጵያ ካለው ሕዝባዊ መሠረት ባሻገር በዓለም አቀፍ መድረክ ለገጽታ ግንባታና በስፖርት ዲፕሎማሲ ከሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በእግር ኳስ ልማትና ከሌሎች ሀገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ትብብር ለመፍጠር የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ካላት ታሪክ አንጻር ሀገሪቷን የሚመጥን ውጤት በዓለምና በአህጉር አቀፍ መድረክ ለማስመዝገብ ፌዴሬሽኑ በትኩረት መሥራት አለበት ነው ያሉት አምባሳደር መስፍን፣ መንግሥት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስፈርትን ያሟላ ስታዲየም በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በሜዳው እንዲጫወት በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ፌዴሬሽኑ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በጋራ ለመሥራት የያዘውን በጎ ጅምር አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በሀገራችን ማስተናገድ ያልተቻለበት ብዙ ችግርች ቢኖርም መንግሥት እነዚህን ችግሮች ፈቶ የስፖርት ቤተሰቡን ጥያቄ በአጭር ጊዜ ለመመለስ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ አቅም፣ ልምድና እውቀት አናሳ እንደሆነና እግር ኳስን ለመሠረተችና ለመራች ሀገረ የማይመጥን እንደሆነም አንስተዋል። በዚህ ምክንያት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እየሰፉና ዓለም በደረሰበት ደረጃ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል። እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ ሁሉንም የስፖርት ማኅበራትን የመሩት በስፖርት ማዘውተሪያ ላይ ምን ሠራን የሚለውን መለስ ብለው ማየት እንደሚኖርባቸውም አስረድቷል። የሜዳና የሲቪል ሥራዎች አንድ ላይ ኮንትራት መሰጠቱ ደረጃውን የጠበቀ የማውተሪያ ስፍራ እንዳይኖር በማድረጉ ችግሩን ለመፍታት እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ የነበሩ ስህተቶችን ለማረም በጋራ እየሠሩ እንደሆነም ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳትምን ከፌዴሬሽኑ ጋር ክትትል በማድረግና የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት የቀደመ ስሙን ይዞ እንዲጠናቀቅ ጥሩ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም አመላክተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ከሁሉም ሀገር አቀፍ ማኅበራት አንጻር መንግሥት በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኖም በሙሉ አቅሙ እግር ኳሱን እየደገፈ እንደሆነና በእግር ኳሱ የሚፈሰው ሀብት ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባም አሳስበዋል። በእግር ኳሱ የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ ጥንቃቄ ሊደረግበትና አሠራር ሊበጅለት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። በቂና ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት ማዘውተሪያ ተገንብቶ ቀርቧል ማለት ባይቻልም የክልል ቢሮ ኃላፊዎች የፌዴሬሽኑንና የመንግሥትን ጭንቀትን በመረዳት በክልል የተጀመሩ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ካለው ውስን ሀብት ተቀንሶ የሚጠናቀቁበትንና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ጥረት መደረግ እንደሚኖረበትም ጠቁመዋል። በተጨማሪም በፌዴራል መንግሥት ደረጃ እየተሠሩና እየታደሱ ያሉ ስታዲየሞችም በፍጥነት ተጠናቀው ችግሩ እልባት ማግኘት እንዳለበት አክለዋል። ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የጀመረውን ለስፖርት ማዘውተሪያና ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል በመቀጠል የስፖርት ቤተሰቡ የሚመኘውን ለውጥ ለማምጣት ከፌዴሬሽኑ ጋር በመሆን እንደሚሠራም ቃል ገብተዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም