የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ትልቅ አጋር የሆነው ዋልያ ቢራ ባለፉት በርካታ ዓመታት ቡድኑን በተለያየ መንገድ ሲደግፍ ቆይቷል። አሁን ግን ዋልያ ቢራ ከዋልያዎቹ ጋር የነበረውን የ56 ሚሊየን ብር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ማቋረጡ ታውቋል።
ዋልያ ቢራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ዋና አጋር በመሆን መጋቢት 12/2011 ላይ ለአራት ዓመታት የሚቆይ ውል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ማደሱ የሚታወስ ሲሆን፣ ‹‹በውል ስምምነቱ መሠረት ተጠቃሚ አልሆንኩም›› በሚል ውሉን ሊያቋርጥ መሆኑ መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል። ድርጅቱ ውሉን ከማቋረጡ በፊት ለፌዴሬሽኑ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በማስገባትም የሶስት ወር ጊዜ ሰጥቶ ነበር።
ቀደም ሲል ድርጅቱ የገባው ውል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳውና በደጋፊው ፊት በሚያደርገው አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ምርቱ እንዲያስተዋውቅለት ሲሆን፣ ክፍያውም ለአራት ዓመት በየሩብ ዓመቱ የሚከፈል 56 ሚሊዮን ብር ነው። ይሁንና ዋሊያ ቢራ የአጋርነት ስምምነቱን ባደረገ ማግሥት፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ስታዲየሞች የዓለም አቀፉንም ሆነ የካፍን ዝቅተኛ መሥፈርት አያሟሉም በሚል ዕገዳ እንዲተላለፍባቸው አድርጓል። በዚህም ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው የሚያደርጋቸው ሁሉም ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ እንደሚሆን ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም።
የሃይኒከን ምርት የሆነው ዋልያ ቢራ አክሲዮን ማህበር ብሔራዊ ቡድኑ በተደጋጋሚ በስደት ከሀገር ወጥቶ በመጫወቱ ምክንያት የምርቱ ተጠቃሚዎች (ታርጌት ከስተመሮቼ) ሀገር ውስጥ የሚገኙ ናቸው፣ ብሔራዊ ቡድኑ ደግሞ በሀገር ውስጥ ከተጫወተ ዓመታት ተቆጠሩ በሚል ስምምነቱን ማፍረሱን ትናንት በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው የፌደሬሽኑ 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገልጿል። ይህም በተደጋጋሚ ፌደሬሽኑ በስታዲየም እጦት ዋጋ እየከፈለ እንደሚገኝ ትልቅ ማሳያ እንደሚሆን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተናግረዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የ2015 ዓመታዊ ሪፖርቶች ሲቀርቡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዓመቱ ለብሔራዊ ቡድን ከ106 ሚሊየን ብር በላይ ማውጣቱን አስታውቋል። ፌዴሬሽኑ በስሩ በሁለቱም ጾታዎች ከዋናው ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ እና ሉሲዎቹ) ባለፈ በተለያዩ የእድሜ እርከኖች የሚገኙ ቡድኖችን ይመራል፣ ያስተዳድራል። እነዚህ ቡድኖች በተለያዩ ውድድሮች ለሚኖራቸው ተሳትፎም ወጪውን ይሸፍናል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ፌዴሬሽኑ በጠቅላላ ጉባኤው ባቀረበው ዓመታዊ የፋይናንስ ሪፖርት ለቡድኖቹ የወጣውን ወጪ ተመላክቷል። በዚህም ደረጃውን የጠበቀ ስቴድየም ባለመኖሩ በሃገር ወስጥ አቻ ቡድኖችን እንዳይገጥም ለታገደው የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከ66 ሚሊየን ብር ብር በላይ ወጪ ተደርጓል። ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በተለያዩ የዕድሜ እርከን ላሉ የወጣት ቡድኖች ከ40 ሚሊየን ብር በላይ መውጣቱ ተጠቁሟል።
በቀረበው የፌዴሬሽኑ ዓመታዊ የፋይናንስ ሪፖርት መሰረት ፌዴሬሽኑ አስቀድሞ ገቢ ከሚያገኝባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ከስታዲየም የሚሰበሰብ ቢሆንም በዓመቱ ግን ምንም ዓይነት ገቢ እንዳልተገኘ ተጠቁሟል። ይኸውም ፌዴሬሽኑ ከስፖርት ማዘውተሪያ ጋር በተያያዘ በተለይ በወንዶች ብሔራዊ ቡድን ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉን የሚያመለክት መሆኑ ተገልጧል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፊፋ እና ካፍ መስፈርት ያሟላ ስታዲየም በሃገሪቷ ባለመኖሩ ለእግር ኳስ ልማት መዋል ያለበት ወጪ ለውጭ ሀገራት ጉዞና ተያያዥ ወጪ እየዋለ በመሆኑ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎችን በሃገሩ ማከናወን ባለመቻሉ ከዋና አጋሩ ዋልያ ቢራ ጋር የነበረው ውል መቋረጡ አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ ወጪውን ለመቀነስ እንዲሁም ስፖንሰሮችንም ለመመለስ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ በሃገር ውስጥ ሊኖር እንደሚገባም ተመላክቷል።
ከብሔራዊ ቡድን ባለፈ ፌዴሬሽኑ በታዳጊዎችና ሴቶች የእግር ኳስ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል። በጉባኤው በቀረበው ዓመታዊው ሪፖርት የክለቦች ፍቃድ (የላይሰንስ) ጉዳይ፣ የታዳጊዎች ውድድር፣ ከተለያዩ ሀገራት ፌዴሬሽኖች ጋር የተደረጉ ስምምነቶች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለብሔራዊ ቡድኑ የሚያደርገው የቅናሽ እያነ መምጣቱና የመስተንግዶ ጉዳይ፣ የሴት ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ወደ ውጪ ሄዶ የ ‹‹A›› ላይሰንስ እንዲሰለጥን መደረጉ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችም ቀርበዋል። የጉባኤው አባላት በቀረበው ሪፖርት ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላም በሰጡት ድምፅ ጸድቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም