ዓባይ እና ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ በረከት ወይስ መርገምት

ስሙን ውሃው ውስጥ ከሚታዩ ቀለማት ያገኘው ቀይ ባህር፤ በጣም ሞቃታማ እና ጨዋማ ነው። በስዊዝ ካናል በኩል ከሜድትራንያን ባህር ጋር የሚገናኝ ሲሆን፤ በአውሮፓ እና በእስያ መካከል የባህር ላይ ትራንስፖርትን ለማካሔድ ዋነኛ መስመር ሆኖ ያገለግላል።

በአፍሪካ እና በእሲያ መሃከል ረዥም ባህረ ሰላጤ የተሰኘው ይኸው ቀይ ባህር፤ አሁን ከኢትዮጵያ ያለው ርቀት 60 ኪሎ ሜትር ግፋ ቢል ከአክሱም ከተማ ጀምሮ ሲለካ ያለው ርቀት ከ135 ኪሎ ሜትር በታች እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ነገር ግን ይህን ያህል ለቀይ ባህር የቀረበችው ኢትዮጵያ የውሃ መተንፈሻ በር አጥታ የባህር ጠረፏን ተነጥቃ እየኖረች ነው።

በሌላ በኩል 6 ሺህ 695 ኪ.ሜ. ርዝማኔ ያለው እና በዓለም ላይ ረጅሙ ወንዝ ተብሎ የሚጠራው ዓባይ ምንም እንኳ መነሻው ከኢትዮጵያ ቢሆንም፤ ሀገሪቱ በወንዙ እንዳትጠቀም የተለያዩ ሤራዎች ሲሰሩባት ኖራለች። ይህ የዓለም ታላቁ ወንዝ 70 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱን ወንዞች የውሃ ድርሻ የያዘ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ በዚህ ታላቅ ወንዝ እንዳትጠቀም ታግዳ ኢኮኖሚዋ እየደቀቀ በርሃብ ዘመናትን አስቆጥራለች።

ለግብጽና ሱዳን ዋና የውሃ ምንጭ የሆነው ይኸው ወንዝ፤ ምንም እንኳ ውሃውን ለመጠቀም ሙከራዎችን ያደረጉ መንግሥታት ላይ የተለያዩ ጫናዎች ቢደረጉም፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም እንዳለባት እያሳመነች በወንዙ ላይ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፤

ቀይ ባህርን በተመለከተ ግን ኢትዮጵያ የባህር ጠረፍ አጥታ ባይተዋር ሆና ያላትን ሀብት ለወደብ ኪራይ ክፍያ ስታውል፤ በተቃራኒው ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ ዐረቢያ እና የመን በዳርቻዎቻቸው ይምነሸነሻሉ፤ እንዳሻቸው በባህሩ ላይ ያለከልካይ ይሳፈራሉ፤ የሚሸጡትን ጭነው ይልካሉ፤ የሚገዙትን አሳፍረው በባህር በራቸው ወደ ሀገራቸው ያስገባሉ። ነገር ግን ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት የቀይ ባህር ጠረፍ የነበራት ሀገር ናት።

የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል በቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደቡት አጼ ካሌብ፤ የዳበረ የባህር ኃይል ነበራቸው። ቀይ ባህርን ተሻግረው የመን እና ደቡብ ዐረቢያን ይቆጣጠሩ እንደነበር አሰብ የማን ናት? በሚለው መጽሐፋቸው የዘረዘሩት ዶክተር ያዕቆብ ኃ/ ማርያም ናቸው።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን በተመለከተ በዝርዝር የፃፉት ዶክተር ያዕቆብ እንደሚተነትኑት፤ በዘመነ መሳፍንት ማዕከላዊ መንግሥት ከመዳከሙ ቀደም ብሎ በአፄ ፋሲል ሞትና በአፄ በካፋ መንገስ መሃከል ለ65 ዓመታት የኢትዮጵያ የባህር ጠረፍ ይዞታ እየተዳከመ ቢሔድም በአጼ በካፋ፣ በአፄ ኢያሱ ሁለተኛ፣ በአፄ ኢዮአስ እስከ 1769 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጠረፍ የተጠናከረ ይዞታ እንደነበራት ታሪክ ይገልፃል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከ1769 ዓ.ም በኋላ የተለያዩ ሴራዎች እየተሠሩባት በቱርኮች፣ በግብጾች፣ በጣሊያኖችና በፈረንሳዮች አማካኝነት የሰሜን ግዛቶቿ እና የባህር ጠረፎቿን የምታጣበት ሁኔታ ተፈጠረ። አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ምኒልክ፣ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና አጼ ኃይለሥላሴ ሁሉም የባህር በር የማስመለስ ጉዳይን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ግዙፍ እና ቀዳሚ ጉዳይ አድርገው ብዙ ጥረት ሲያደርጉ እና ተግተው ሲሠሩ እንደነበር ዶክተር ያዕቆብ በዝርዝር በመጽሐፋቸው ላይ አብራርተዋል።

በአጼ ኃይለሥላሴ የንግሥና ዘመን በዓለም አቀፍ ሕግና የዲፕሎማሲ ምሁር ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ እና ሌሎችም ባደረጉት ጥረት በ1952 ዓ.ም በኤርትራ ሕዝብ ተወካዮች ፍላጎትና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ተቀላቀለች። ለዘመናት ትግል ሲደረግበት የቆየው የባህር በር ጥያቄ ከአንድም ሁለት የምፅዋ እና የአሰብ የባህር በር ባለቤት እንትሆን ማድረግ ተቻለ። በሒደት ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀላቀለች። ነገር ግን የፌዴሬሽኑ መፍረስ ሻቢያ እና ጀበሃን በኋላም ሕወሓትን የመሳሰሉ ነፃ አውጪ ነን የሚሉ ድርጅቶች ተፈጠሩ። በመጨረሻም በድጋሚ ኢትዮጵያ ወደብ የሌላት የባህር ጠረፍ አልባ እስረኛ ሀገር ሆነች።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰርና የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ እንደሚገልፁት፤ ዓባይ እንደሌሎቹ ከኢትዮጵያ የሚመነጩ ወንዞች ሁሉ ድንበር አቋርጦ ወደ ጎረቤት ሀገር የሚሄድ ነው። ከኢትዮጵያም ቢነሳም በሱዳን አልፎ ግብፅ ይወርዳል። ይህ ተፈጥሮዊ መንገዱ ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ተፈጥሯዊ ሒደት የማስተጓጎል ፍላጎት የላትም።

እንደፕሮፌሰር ያዕቆብ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን፤ ይህንን ወንዝ በሠላም እና በመተጋገዝ ሱዳን እና ግብፅም ሊጠቀሙ ይችላሉ። ግብፅ የውሃው ዋናው መዳረሻ መጨረሻ ስለሆነች የዓባይን ውሃ ለብቻዋ መጠቀሟ ግን በምንም መልኩ ተገቢ አይደለም። እስከ አሁን ለብቻ በሚባል ደረጃ ስትጠቀም ኖራለች። ኢትዮጵያ በወንዙ የመጠቀም መብቷን እንዳትተገብር ግብፅ በተለያዩ ወዳጆቿ አማካኝነት ተፅዕኖ ስታደርግ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ አሁን በዓባይ ውሃ መጠቀም ስትጀምር፤ ግብፅ ብቻ ሳትሆን ሱዳንም ‹‹ውሃውን ቀነሳችሁብን፤ እኛ እንጎዳለን፤ ሀገራችን ይደርቃል፤ እንራባለን። ›› የሚሉ እና ሌሎችም ውንጀላዎችን ሲያነሱ ነበሩ። አሁን ግን ያለፈው ቢያልፍም ኢትዮጵያ በወንዟ እየተጠቀመች ነው።

በዓባይ ወንዝ ለምን ተጠቀማችሁበት የሚለው ጣጣ፤ እንደ አንድ ተግዳሮት የሚታይ እንጂ ከፀጋነቱ አንፃር ውሃው በምንም መልኩ ፀጋ እንጂ መርገምት የሚሆንበት ሁኔታ እንደሌለ ያብራራሉ። እንደፕሮፌሰር ያዕቆብ ገለፃ፤ ውሃው ጠቃሚ ነው። ውሃውን ኢትዮጵያ እንዳታለማ የሚፈልጉ ኃይሎች ወይም የጎረቤት ሀገራት የሚፈጥሩት ችግር እና ማልማቷን በቀና አለማየታቸው ችግር ተደርጎ መጠቀስ ይችላል። ነገር ግን ዓባይም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ወንዞች ፀጋ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ይገልፃሉ።

ቀይ ባህርን በተመለከተ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ያዕቆብ፤ ቀይ ባህርን በተመለከተ ግን ውሃው ከአንድ ሀገር ወደ አንድ ሀገር የሚሸጋገር ሳይሆን እዚያው የተኛ ነው። ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ አካል ሆኖ የኖረ ቢሆንም፤ ቀይባህርን የሚነካ የኢትዮጵያ መሬት በኤርትራ በኩል በተካሔደው የነፃ አውጪዎች ጦርነት ምክንያት የሀገሪቱ የቀይ ባህር ዳርቻ አብሮ ሔዷል። ጣሊያን ኤርትራን በሚገዛበት ጊዜ ነጥሎ ለመግዛት ባበጀው ካርታ መሠረት ኤርትራ በመገንጠሏ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቀይ ባህር ተለይቷል። የጠረፍ ይዞታዋም የሌላ የጎረቤት ሀገር ሆኗል።

በጅቡቲም በኩል በፈረንሳዮች አማካኝነት ተይዟል። በርካታ ታሪካዊ ገለፃዎች ሊኖሩት ቢችሉም፤ በታሪክ አጋጣሚ ጎረቤት ሀገሮች ባለወደብ ሆነው ኢትዮጵያ ግን ወደብ አልባ ሀገር ሆናለች። የተኛ ባህር በመሆኑና በኢትዮጵያ ሳይሆን በሌሎች የተያዘ ነው። ይሔ ባህሪው ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የተለየ ነው። በፊት ኢትዮጵያ ወደብ ነበራት ነገር ግን በየመሃሉ በቀኝ ገዢዎች እና በመጨረሻም ነፃ አውጪ ነን የሚሉ የባህር በርን ከኢትዮጵያ የሚገነጥሉ ኃይሎች በመኖራቸው የባህር ዳርቻ ኢትዮጵያ እንዳይኖራት መሆኑ በጣም ያሳዝናል ይላሉ።

አማፂያኑ የያዙትን ቦታ ነፃ ሲያወጡ እና ሲገነጠሉ፤ የተገንጣዮችን ሃሳብ ፍላጎት ከማሟላት አንፃር ለኢትዮጵያ የሚገባውን ድርድር በማድረግ እናንተ ‹‹አዲስ ሀገር እንመሠርታለን ካላችሁ እና በኃይል እዚህ ከደረሳችሁ ለኢትዮጵያ ተገቢ የሆነ የባህር በር ያስፈልጋል፤ መውጫችን አይዘጋብንም የሚል ድርድር አላደረጉም። በፊት በኢትዮጵያ በኩል የነበሩት ኃይሎች ከአማፂያን ጋራ ተባባሪ ስለነበሩ ትልቅ ስህተት ተሠርቷል። የሚሉት ፕሮፌሰር ያዕቆብ፤ ነገር ግን የጎረቤት ሀገሮች ከባህር ዝግ የሆኑ እንደኢትዮጵያ ያሉ ሀገሮች ላይ በድንበራችን አታልፉም ብለው ድንበር መዝጋት አይችሉም። በመተሳሰብ በኪራይ ወይም በሚደረገው ስምምነት በልውውጥ ሰጥቶ በመውሰድ መርህ መጠቀም ያስፈልጋል ይላሉ።

የባህር በርን በተመለከተ ጥንቃቄ እና ትብብር ያስፈልጋል፤ አንድ ሀገር በሌላ ሀገር የባህር በር ለመጠቀም በምን መንገድ መሄድ እንዳለባት በጥብቅ እና በጥንቃቄ በምክክር መሥራት ያስፈልጋል። በሰላማዊ መንፈስ በትብብር እና በሰላማዊ መንገድ የመጠቀም ሁኔታን መምረጥ ጠቃሚ ነው። ይህ ቀላል አይደለም፤ ትልቅ የዲፕሎማሲ ሥራን ይጠይቃል። በሚመች መንገድ ለመጠቀም እና ተፅዕኖ ለመፍጠር ተገቢ የሆነ ዝግጅት እና አነጋገር ሊኖር እንደሚገባ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ያስረዳሉ።

ዓባይን በተመለከተ ውሃው በኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ እስካለ ድረስ ውሃው ወደ ውጪ እንዳይሄድ መከልከል ተገቢ አይደለም። ይህንን ኢትዮጵያ አላደረገችም። ወደፊትም እንዲህ አታደርግም። ድንበር ተሻገሪ ወንዞች ላይ የሚካሔድ ልማት ውሃው የሚደርስባቸው ሀገሮች ላይ በከፋ ሁኔታ ጉዳት እንዳይደርስ በሃሳብም በዲዛይንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ውሃን የመጠቀም መብት የመኖሩን ያህል ሌሎቹ ውሃ እንዳያገኙ የመከልከል ሁኔታ መኖር የለበትም። በዚህ መልኩ መሔድ ከተቻለ ወንዙ ፀጋ እንጂ መርገምት የሚሆንበት ሁኔታ አይኖርም ይላሉ።

እንደፕሮፌሰር ያዕቆብ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ እየተጠነቀቀች እስከ አሁን ድረስ ግድቡ እየተሠራ ነው። በዓባይ ብቻ ሳይሆን በተከዜም፣ በአባኮም፣ በኦሞም፣ በገናሌ እና በዋቢ ሸበሌም በሁሉም ላይ ግድብ አለ። ግድብ ሲሠራ ግን ሌሎቹ እንዳይጎዱ በብልሃት፣ በጥንቃቄ፣ በዕውቀት እና በትልቅ መተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው።

የቀይ ባህር ጉዳይም በተመሳሳይ መልኩ በብልሃት፣ በጥንቃቄ፣ በዕውቀት እና በትልቅ መተሳሰብ ላይ የተመሠረተ አካሔድን መከተል ያስፈልጋል። ‹‹ኢትዮጵያ ለእኔ ይፈቀድልኝ ስትል፤ አልፈቅድም የሚል ካለ በዚህ ነገር አንተም ከእኔ ትጠቀማለህ፤ እኔም ለአንተ እጠቅምሃለሁ›› የሚለው ነገር በደንብ ሥራ ላይ መዋል ይኖርበታል። በደንብ ዝግጅት ያስፈልጋል ብለዋል።

ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን መጠቀም በፊትም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጊዜ ከማሰብ አልፎ መሥራት እና መጠቀም መኖሩን በመጥቀስ፤ ጪስ ዓባይ ላይ፣ ፊንጫ እና መልካ ዋከና እንዲሁም በደርግ ጊዜ በገናሌ ላይ የተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። በየዘመኑ እንደሀገሪቱ አቅም በወንዞች ለመጠቀም የተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። በወንዞቹ ጊዜው በፈቀደው አቅም የተሠራ መሆኑን እና በኢትዮጵያውያን ቁርጠኝነት እና ፍላጎት መሠረት በትጋት ሥራው ውጤታማ ሆኖ እየታየ ነው ብለዋል።

ቀይ ባህርን በተመለከተም፤ በስህተት ኢትዮጵያ የባህር በሯን ብታጣም አሁን ቀስ በቀስ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ለማስመለስ መጣሩ ክፋት እንደሌለው አመልክተዋል። ነገር ግን አሁን የጎረቤት ሀገሮቹ ሉዓላዊ በመሆናቸው ኢትዮጵያ መልሳ በጉልበት ለመውሰድ መሞከር ለስሟም ጥሩ አይሆንም የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በአካባቢው የኢትዮጵያ ወዳጆች ብቻ ሳይሆኑ ጠላቶችም በመኖራቸው ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎቹ አጎራባች ሀገሮች ሰፋ ያለ ችግር እንዳይመጣ እና ሀገሪቱ እንደወራሪ የምትቆጠርበት አጋጣሚ እንዳይፈጠር፤ የባህር በር ባለቤትነትን በተመለከተ ቀስ በቀስ በዕውቀት እና በጥበብ መነጋገር ይጠቅማል ብለዋል። በቂ ዝግጅት ማድረግ፣ በዕውቀት ላይ መመስረት፣ ምክክር ማካሄድ እና በጥንካሬ በመሥራት ባለባህር ጠረፍ ሀገራትን በተለያየ መንገድ በማማለል ቀይ ባህርን ጠረፍ ማድረጉ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም አመልክተዋል።

ፖለቲካል ሳይንስ የተማሩት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሠሩ የነበሩት፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሠሩት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ በበኩላቸው፤ አፍሪካ ውስጥ ግጭት እና ጦርነት ያለባቸው አካባቢዎች በአብዛኛው ሲታዩ ሀብት ያለባቸው ሀገሮች ናቸው። የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ሀብት መርገምት ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ሀብት የሌለበት ሀገር ብዙ ጦርነት የለም።

የተገኘው ፀጋ በሌሎች ሲፈለግ የሀብቱ ባለቤት ላይ ችግር ይፈጠራል። ያንን ሀብት ያለአግባብ ለመጠቀም ሲሉ ሆን ተብሎ በእዛ ሀገር ረብሻ እንዲኖር ይደረጋል። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ዓባይም ሆነ የቀይ ባህር ጉዳይዋ ሲታይ ከሌሎች ሀብታቸው መርገምት ከሆነባቸው የአፍሪካ ሀገሮች ይለያል። ያሉት ኮሚሽነር ሒሩት፤ ‹‹እኛ አቅማችንን ሰብስበን ያለንን ሀብት ለመጠቀም ዝግጁ ሆነናል። ሌሎች ሀብታቸው መርገምት የሆነባቸው ግን ገና ሀብታቸውን መጠቀም ሳይችሉ ድምጥማጣቸውን አጥፍተዋቸዋል። ›› ብለዋል።

ዓባይ ለኢትዮጵያ በፈጣሪ የተሠጠ ፀጋ እንጂ፤ መርገምት አይደለም። የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት ኮሚሽነር ሒሩት፤ የሰው ልጅ በዓለም ሲኖር የሚገባውንም ቢሆን ማንም በትሪ ላይ አያቀርብለትም። ዓባይን ለመጠቀም ሲሞከር ጥቅማቸው የሚጎድልባቸው የመሰላቸው አካላት፤ የማያነሱት ጥያቄ መኖሩ ወንዙ እንደመርገምት እንዲታሰብ የሚያደርግ አለመሆኑን አብራርተዋል።

እንደኮሚሽነር ሒሩት ገለፃ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳይኖራት መደረጉ እና ያንን የፈፀሙ ኃይሎች ለምን ያንን እንዳደረጉ ባይገባቸውም የተፈፀመውን ስህተት ለማረም ዓለም አቀፍ ሕጎች በሚፈቅዱት መልኩ ሠላማዊ መንገዶችን ፈልጎ መቀጠል የተሻለ ነው።

እንደምሁራኑ ገለፃ፤ ዓባይም ሆነ ቀይ ባህር መርገምት አይደሉም። በረከት ሆነው ኢትዮጵያን እንዲያሳድጉ አጠቃቀማቸውን በጥንቃቄ እና በሠላማዊ መንገድ ማንም ላይ ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ መሆን ይኖርበታል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You