የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ስፖርት ክለብ ኢትዮጵያን በኦሊምፒክና በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች መወከል የቻሉ ቦክሰኞችን በማፍራት ትልቅ ስም ካላቸው ክለቦች ግንባር ቀደሙ ነው። ክለቡ በቦክስ ስፖርት ስመ ገናና እና ቀደምት ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን እንቅስቃሴው ተቀዛቅዟል። የክለቡ ውጤት ከነበረበት እንዲንሸራተት ምክንያት የሆኑትም የልምምድ ቦታ ማጣትና የገንዘብ ችግሮች ናቸው። ችግሩን በመቅረፍ ክለቡን ውጤታማ ለማድረግና ወደ ቀደመ ዝናው ለመመለስም ግን በዚህ ወቅት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
ክለቡ በኅዳር ወር ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው የኢትዮጵያ ቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብም ዝግጅቱን ከጀመረ ከሁለት ወራት በላይ አስቆጥሯል። ክለቡ የመለማመጃ ቦታ ችግር ያለበት ቢሆንም በጎ ሰዎች ባደረጉት ድጋፍ አብነት አከባቢ በሚገኘው ወወክማ ልምምዱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ሁሉንም የቦክስ ክብደት ሚዛኖችን የያዘ ዝግጅትን በማድረግም የውድድሩን መጀመር ብቻ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝም የክለቡ አባላት ገልጸዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው ሻምፒዮና አጃቢ ሳይሆኑ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ለማንሰራራት ጥረት እያደረገ ያለው ይህ ክለቡ፤ ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት በዓለም መድረክ እንድትወከል የድርሻውን አበርክቷል። ሰለሞን ታደሰ፣ ዮሐንስ ሽፈራው፣ ሲሳይ አበበ፣ ተስፋ ወርቅ፣ ኮማንደር ፀጋሥላሴ አረጋይ እና ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሰ ኮከብ ቡጢኞችን ያበረከተ ታሪካዊ ክለብ ነው። በ1970ቹ እና 80ዎቹ የነበሩት ድንቅና ብቃት ያላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቦክሰኞች ውስጥ አብዛኞቹ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች እንደሆኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያን ባንዲራ በዓለም አደባባይ እንዲውለብለብ ከፍተኛ አሻራቸውን ያስቀመጡ ውድ ስፖርተኞችን ያፈራ ታላቅ ክለብ ነው ቢባልም ማጋነን አይሆንም። ነገር ግን እንደቀድሞ ውጤታማ ቦክሰኞችን የማፍራትና በብዛት ለብሔራዊ ቡድን የማስመረጥ ድርሻው ከቀነሰ ሰነባብቷል፡፡
የማረሚያ ቤት ቦክስ ክለብ ቡድን መሪ ኮማንደር ፀጋሥላሴ አረጋይ (ኮሩ) ስፖርት በተለይ ቦክስ ከገንዘብ፣ ከምግብ፣ ከልምምድና ከመወዳደሪያ ስፍራ አንጻር አቅምን እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ። የልምምድና የመወዳደርያ ቦታና ቁሳቁስ ለማግኘት እንዲሁም የገንዘብ አቅምን ለመፍጠርም እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ቀድሞ ማረሚያ ቤቶች የሚጠቀምበት መዝናኛ ክበብ ለሌላ ጉዳይ መዋሉን ተከትሎ ምትክ ቦታ ቦሌ ኢምፔሪያል አካባቢ እንደተሰጣቸውና እሱን በማሠራት ለልምምድ እንዲውል እንዲሁም በኪራይ ለክለቡ የገቢ ምንጭም ይውላልም ብለዋል። ቀደም ብሎ ቦታው በመወሰዱ ከዛ የሚገኝ ገቢ በመቅረቱ ላለፉት ስድስት ዓመታት ገደማ ክለቡ ችግር ውስጥ በመግባቱ ተቋሙ ለቦክስ ባለው ክብር በመዋጮ ክለቡ እንዲቀጥል ማድረጉን ይጠቅሳሉ። ይህም የሆነው ማረሚያ ቤት ቦክስ ክለብ ታሪካዊ ክለብ በዚህ ጊዜ ፈረሰ ብሎ በትውልድ እንዳይወቀስ ጥረት በሚያደርጉ አካላት እስከ አሁን ቆይቷል። ስፖርቱ ገንዘብ እንደመጠየቁ ማረሚያ ቤት ያፈራቸውና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው እንዲሁም ኦሊምፒክ ድረስ የተወዳደሩ ቦክሰኞችን በማስተባበር የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻም ይደረጋል።
በተጨማሪም በሻምፒዮውናው ተጠናክሮ ለመቅረብ አሠልጣኞች እና ስፖርተኞች በትጋት እየሠሩ እንደሆነም ቡድን መሪው ይጠቁማሉ። ተፎካካሪ ለመሆንም አዳዲስ ቦክሰኞች ቡድኑን እንደተቀላቀሉና የመለማመጃ ቦታ ማመቻቸትን ጨምሮ አስፈላጊ ድጋፍ ተደርጓል። ለዚህም የቡድኑ መነቃቃት እና ልምድ ባላቸው ኢንስትራክተሮች መሠልጠኑ የሥነልቦና እና የአካል ጥንካሬን ለቡድኑ የሚሰጥ በመሆኑ ውጤት እንዲጠብቁ አድርጓል። በቅርብ ጊዜ ለተከታታይ የውድድር ዓመታት በውጤታማነት ለመቀጠል ሁኔታዎችን እያመቻቹ መሆኑንም ያምናሉ። የክለቡን ውጤታማነት ለማስቀጠል ዋነኛ ጉዳይ የሆነውን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍም የገቢ ምንጫቸውን በማስፋት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ተጠናክሮ የሚሠራም ይሆናል። ክለቡ ልምድ ባላቸው፣ በወጣቶችና ታዳጊዎች በመዋቀሩ ከክለቡ አልፎ ለሀገር መብቃት የሚችሉ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤት ስፖርት ክለብ በ1975 ዓም በወቅቱ በማረሚያ ቤት ዋና አስተዳደር በነበሩት በኮሎኔል አበራ አያና አማካኝነት ሊመሠረት ችሏል። ክለቡ ከተመሠረተ አንስቶ የሀገርን ባንዲራ ከፍ ማድረግ የቻሉ በርካታ ስፖርተኞችን ማበርከት ችሏል። አትሌቶች፣ ቦክሰኞች፣ የእጅ ኳስ እና የቮሊቦል ተጫዋቾች የወጡበት አንጋፋና ቀደምት የስፖርት ክለብም ነው። ክለቡ በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና መድረኮችም ኢትዮጵያን ማስጠራት የቻሉ ውጤታማ ስፖርተኞችን ያፈራ ታላቅ የስፖርት ክለብ ነው። ከቦክሱ ባሻገር በአትሌቲክስ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ስለሺ ስህን፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ቁጥሬ ዱለቻ እና አንጋፋውን አሠልጣኝ ኮሚሽነር ሁሴን ሸቦን የመሳሰሉ ፈርጦችንም አበርክቷል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም