በተማሪዎች ውጤት የተንፀባረቀው የመምህራን ምዘና

ምዘና ባደጉት ሀገራት ረጅም እድሜ ያለውና የተለመደ አሠራር ነው። ከዚህ አኳያ ምዘና ለሙያ ብቃት፣ ለአሠራር ጥራትና ለአገልግሎት ቀልጣፋነት ያለው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የተመረቁ የጤና ባለሙያ አመልካቾች የሙያ ፈቃድ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ የሚጠበቅባቸው መሆኑ የምዘና አንዱ ማሳያና በሌሎች ሴክተሮች ውስጥም እንዳለ አመላካች ነው። ወደ ትምህርቱ ሴክተር ሲመጣ ደግሞ ምዘና ለረጅም ጊዜ ስሙ ሲነሳ የነበረ ነው። በሂደት ደግሞ ወደ ሥራ ተገብቶበት ለመምህራን የመመዘኛ ጥያቄዎች ተሰጥተው የምዘና ተግባሩ ተከናውኗል።

በመሠረቱ “ምዘና ለምን?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል። ከተነሳው ርዕሰ ጉዳይ አኳያና ከተለያዩ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ምዘና ሙያዊ ጥንካሬ እና ድክመቶችን በመለየት የመምህራንን ብቃት ለማሻሻል፤ መምህራን የተማሪዎቻቸውን አቅም ያጎለብቱ ዘንድ ለማስቻል፤ ተጠያቂነትን ለማስፈን፤ በትምህርት ሥርዓቱ የሚፈለገውን የትምህርት ጥራት ለማምጣት፤ በየደረጃው ያሉ መምህራንና የትምህርት ተቋማት አመራሮች ወሳኝ ሚና ያላቸው እንደ መሆኑ መጠን ያንን አቅም ለማዳበር፤ እንዲሁም፣ የትምህርት ሥርዓቱ በተወዳዳሪ መምህራን እንዲሞላ እና የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የሚያገለግል ሁነኛ የመማር-ማስተማር መሣሪያ ነው።

የመምህርነት ሙያ ቀደም ሲል በሠለጠኑበት እውቀት ብቻ በመጠቀም የሚሠራበት ሳይሆን በየጊዜው የራስን አቅም መገንባትን የሚጠይቅ በመሆኑ ምዘናና የሙያ ፍቃድ የመኖሩ ጉዳይ ያንን አቅም ለመፍጠር ያግዛል። የመምህራን ምዘና በሥራ ያሉትን መምህራን የማብቃት ሥራ መሥራትና አዲስ ወደ ሙያው የሚገቡትንም በሙያ ምዘናው ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የማስተማር ብቃታቸውን በቀጣይነት ለማረጋገጥ ያስችላል። በአጠቃላይ የመምህራንና ትምህርት ተቋማት ሙያ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ሥርዓት፣ ማለትም ሙያው የሚጠይቀውን ሥነምግባር፣ እውቀት፣ ክህሎትና የተግባራት ክንውን ባካተተ ሁኔታ ተገቢውን ሙያዊ ብቃት ስታንዳርዶችን (professional Competence Standards) የሚያሳይ ሥርዓት መሆኑን ለአዲስ ዘመን ማብራሪያ የሰጡት ባለሙያ ይናገራሉ፡፡

ሌሎች በርካታ የመስኩ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደሚደመጠው፣ የመምህራንና የትምህርት ተቋማት አመራር ሙያዊ እንቅስቃሴ ዋና ግብ የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻልና ያወቀ ትውልድ መፍጠር ነው። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር እምነት ከሆነ ደግሞ ለመምህራንና ለትምህርት የሥራ ኃላፊዎች የሙያ ፍቃድ መስጠትና ማደስ መምህሩንና የትምህርት አመራሩን በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ተግተው እንዲሠሩ ያስችላል።

ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች የሙያ ፍቃድ አሰጣጥና እድሳት ዳይሬክቶሬት የሙያ ፍቃድ ባለሙያ አቶ ሺፈራው ከፍያለው እንደሚገልፁት በሐምሌ 2014 ዓ∙ም ወር በተደረገ አዲስ አደረጃጀት ምክንያት ይህ ዘርፍ ወደ “የትምህርት ጥራትና ሥልጠና ባለሥልጣን” ይሄዳል በሚል ተዘሏል። ከሥራው አስፈላጊነትና በስህተት መዘለሉ አኳያ እንደገና እንዴት መቀጠል እንዳለበት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

ከሌሎች፣ ልምድ ከተወሰደባቸው ሀገራት (ኢንዶኔዥያ፣ አውስትራሊያ፣ ፊሊፒንስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ በቅርብ ጀምረው ውጤታማ የሆኑትን ዓረብ ኤምሬትስ ወዘተ) መረዳት የተቻለውም ይህንኑ ሲሆን፤ የሙያ ፍቃድ መስጠትና ማደስ ለትውልዱ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን የላቀ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።

እንደ አቶ ሺፈራው ማብራሪያ፣ ከእነዚህ ሀገራት ልምድ በመነሳትና ጉዳዩን ከሀገራችን አኳያ በመቃኘት ትምህርት ሚኒስቴር በ2014 ዓ∙ም ምዘናውን የሰጠ ሲሆን፣ ከተገኘው ውጤት መረዳት እንደ ተቻለውም ከአጠቃላይ፣ ምዘናውን ከወሰዱት መምህራን መካከል 24 ነጥብ 2 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው መመዘኛውን በማለፍ የሙያ ፍቃድ ያገኙት።

በአሁኑ ግዜም መምህራኑ ምዘናውን እየተቀበሉ ሲሆን እንደውም ከክልሎች እየደወሉ ‘ለምን አትፈትኑንም?′ የሚል ጥያቄን እያነሱ ይገኛሉ። በተለይ አንዳንድ ክልሎች አንዳንድ ሥራዎች ሲኖሩ እድሉን በቅድሚያ የሚሰጡት የሙያ ፍቃድ ሰርተፊኬት ላላቸው መምህራን በመሆኑ ብዙዎች ያንን እድል ለማግኘት ምዘናውን ለመውሰድ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ምዘናው እየተለመደና እየተፈለገ መጥቷል።

ከሌሎች ሀገራት፣ በተለይም ልምድ ከተወሰደባቸው ሀገራት አንዳንዶቹ ምዘናውን ላለፉ መምህራን 100 ከመቶ የደመወዝ ጭማሪ (ለምሳሌ 5ሺህ ብር ከሆነ ደመወዙ 10ሺህ) ስለሚያደርጉ ምዘናው በጣም ተፈላጊ ነው። ይህም አንድ መምህር በሚቀጥለው ዓመት ምዘናውን ካላለፈ የተጨመረለት ደመወዝ ይቀነስበታል ማለት ነው። በመሆኑም፣ ጭማሪውን ደመወዝ ላለማጣት መምህሩ በከፍተኛ ደረጃ ተዘጋጅቶ ምዘናውን የመውሰድ ፍላጎት አለው። ይህ ዝግጅት ደግሞ ለመምህሩ ብቻም ሳይሆን አጠቃላይ የመማር-ማስተማር ሥራው ላይ የሚኖረው መልካም ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም። በኢትዮጵያም ማበረታቻና ይህን የሚያሳይ አሠራር ቢዘረጋ ጥሩ ነው።

እንደ አቶ ሺፈራው አስተያየት በኢትዮጵያ ምዘናው እንጂ ተግባራዊ የተደረገው ምዘናውን ባለፉና ባላለፉት መምህራን መካከል ምንም አይነት መለያ የለም። ሁለቱም ማስተማሩን ይቀጥላሉ። ያላለፉት “ምን ይቀርብኛል” በሚልም ዝግጅት ሲያደርጉ አይታዩም። በመሆኑም ይህ ሊታሰብበት ይገባል።

እንደሀገር ሲታይ የመምህራን እጥረት አለ። ከዚህ አንፃር መመዘኛውን ወስደው ያለፉም የወደቁም ሥራቸውን ይቀጥላሉ። ይህ እንዲሆን የተደረገው የመምህራን እጥረት በፈጠረው ችግር እንጂ ተገቢ ሆኖ አይደለም። ያላለፈ መምህር ለተጨማሪ አቅም ግንባታ ወደ ሥልጠና መሄድ ያለበት። ከዛ አቅሙን ገንብቶ ሲመጣ የማስተማር ሥራውን መቀጠል ይችላል። ነገር ግን በዚህ መሠረት አይደለም እየተሄደ ያለው። ምክንያቱ ደግሞ የመምህራን እጥረት ጉዳይ ነው። ወደ ፊት ግን ወደዛ ነው መኬድ ያለበት።

በአዲስ አበባ ከተማ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን አማካኝነት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የመምህራን የሙያ ብቃት ምዘና፤ እንዲሁም፣ የመምህራን፣ የሱፐርቫይዘሮች እና ርዕሰ መምህራን የሥራ ምዘና ውጤቱ (JEG) እየተሰጠ ይገኛል። ተፈታኞችም ሁለት አይነት ፈተናዎችን፣ ማለትም የጽሑፍ ፈተና (80 ከመቶ) እና የማህደረ ተግባር ፈተና (20 ከመቶ) እንዲሁም የጽሑፍ ፈተናውን 62 ነጥብ 5 እና ከዛ በላይ ያመጡ ተመዛኞች የማህደረ ተግባር ፈተናውን እንደሚወስዱ ባለሥልጣኑ በወቅቱ መግለፁ ይታወቃል።

በዚሁ መሠረትም፣ በ2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሙያ ብቃት ምዘና ከወሰዱ 1ሺህ 835 መምራን መካከል 1ሺህ 600ዎቹ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘት ችለዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን የብቃት ምዘናውን እንዲወስዱ ባይገደዱም የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የሌላቸው መምህራን ማስተማር እንደማይችሉ መመሪያው ደንግጓል።

ከላይ አቶ ሺፈራው ከሰጡት አስተያየት መረዳት እንደሚቻለው በትምህርት ሚኒስቴር በ2014 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው ውጤት ከተመዘኑት የትምህርት ቤት መምህራንና የትምህርት አመራሮች መካከል ያለፉት 24 ነጥብ 2 ከመቶ ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ምዘናውን ማለፍ አልቻሉም።

ይሁንና በዚህ ምዘና ውጤት ተገኝቷል። መምህራኖቻችን እና የትምህርት አመራሮቻችን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። በሚደረገው የክትትል (ሱፐርቪዥን) ሥራ የብቃት መመዘኛ የወሰዱ መምህራንና የትምህርት አስተዳደር ባለሙያዎች ያሉባቸው ትምህርት ቤቶች የተሻለ አፈፃፀም አሳይተዋል። ምዘናው ይህ አሠራር ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑ የታየበትና ለትምህርት ጥራት እውን መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጥቷል።

በመምህራን ምዘና ላይ የታየው ውጤት በተማሪዎች ላይም ተንፀባርቋል። በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ብዙ ተማሪዎች እንደወደቁ ሁሉ በመምህራን ምዘናም በርካታ መምህራን ወድቀዋል። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከነዚህ ውስጥ የመምህራኖች በበቂ ሁኔታ ለምዘናው አለመዘጋጀት አንዱ ነው። የምዘናው ጥራት የተዋጣለት አለመሆንም እንደሁለተኛ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል።

ምዘናውን ያለፉ መምህራንን የሚያበረታታ ሽልማትም ሆነ ሌላ እንዲያገኙ የሚያደርግ አሠራር ገና አልተዘረጋም። ምናልባት ‹‹ባልፍም ብወድቅም ምን ይቀርብኛል›› የሚል ነገር በመምህራኖች በኩል ሊኖር ይችላል። ከዚህ አኳያ ያለፉትን ሊያበረታታ የሚችል አሠራር ቢዘረጋ ጥሩ ይሆናል።

24 ነጥብ 2 ከመቶ ብቻ መምህራን ማለፋቸውና የአብዛኛው መውደቅ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው በተማሪዎች ውጤት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። የመምህሩ ብቃት ማነስ ጎልቶ መታየቱ፣ መውጣቱ አይቀርም። ውጤቱም ሲታይ ከላይ ተመጋጋቢ ሆኗል። ይህ ደግሞ የሚያሳየው አስቀድሞ በመምህራን ላይ መሥራት ተማሪ ላይ መሥራት መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም የመምህራን ብቃት መጠበቅ፣ መኖርና መረጋገጥ አለበት። መምህራን ከመንግሥት የሚጠብቁት ነገር እንደ ሀገሪቱ አቅምና ሁኔታ ሊሟላላቸው ይገባል።

አቶ ሽፈራው እንደሚናገሩት ተመራቂ መምህራንን መመዘንን በተመለከተ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከአውስትራሊያ የተለየ አካሄድ ትከተላለች። አውስትራሊያ ‹‹በተቋሞቼ አቅም አምናለሁ፤ ተቋሞቼ በሚገባ መምህራንን አሠልጥነው እንደሚያወጡ አውቃለሁ›› ትላለች። ስለዚህ የአውስትራሊያ መምህራን ተመርቀው ሲወጡ። ወይም ወደ መምህርነት ሙያ ሲቀላቀሉ አይመዘኑም። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን መምህራን ተመርቀው ሲወጡ ይመዘናሉ።

ይህ ሊሆን የቻለው በአፕላይድ ተመርቀው፤ ለተጨማሪ አንድ ዓመት የማስተማር ሥነ-ዘዴን (ፔዳጎጂ) ተምረው የጨረሱት ተፈትነው ምዘናውን ማለፍ ባለመቻላቸው ነው። ይህ ውጤት ለመምህራን ኮሌጆችና ለሚመለከታቸው ሁሉ ተሰጥቷል። ውጤቱም ብዙ ነገር አስተምሯል።

ሦስት አራተኛው መምህር ምዘናውን ማለፍ አለመቻሉ የትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ብቃቱ ያልረጋገጠ መምህር ከተበራከተ ለዚህ ትልቁን ሚና የተጫወተው የማይጨበጠው እና በግብታዊነት የሚቀያየረው የመም ህራን ሥልጠና ሥርዓት መሆኑ የአንዳንዶች እምነት ነው።

ኤፍሬም ተክለያዕቆብ የተባሉ ሰው በ2018 /እ.አ.አ./እንዳሰፈሩት፣ የ2007 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ዓመታዊ አብስትራክት (ጭማቂ) እንደሚያሳየው በሀገሪቱ ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ትምህርት ድረስ 497 ሺህ 735 መምህራን የነበሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 429 ሺህ 288፣ ወይንም 86 ነጥብ 24 ከመቶው እድሜያቸው ከ 40 ዓመት በታች ነው:: እነዚህ መምህራን ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሥራ ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ ውጤት ናቸው:: በመሆኑም፣ የምዘናው ውጤት ወደ ወደኋላ በመመለስ የመምህራን ቅበላን፣ ሥልጠናን እንዲሁም ተከታታይ ማብቃትን እና ማበረታቻ ሥርዓትን ለመፈተሽ መነሻ ሐሳብ ሆኖ ማገልገል ይኖርበታል።

ያነጋገርናቸው የጉዳዩ ባለቤት እንደሚሉት ምዘናው ባጠቃላይ የትምህርት ማዕቀፉ አካል እንጂ ብቻውን ተነጥሎ ሊታይ የሚገባው አይደለም። በመሆኑም በእሱ ብቻ አጠቃላይ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይገባም። ሌሎች በርካታ መመዘኛዎችም አሉ። የእነሱ ሁሉ ድምር ነው የመምህሩ የመጨረሻ ሙያዊ ማንነት መገለጫ። የምዘና ውጤቱ ወደ ኋላ በመመለስ አሠራሮች ሁሉ እንዲፈተሸ እድል መፍጠር አለበት።

መምህራንን የመመዘኑ ተግባር አስፈላጊነቱ የሚታመንበትና አይቀሬ ከሆነ በተጠናከረ ተቋማዊ አሠራር መደገፍ እንዳለበት የማንም እምነት ስለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም። ይህ እውነት ከሆነ፣ የመመዘንና ለተመዛኙ ግብረ-መልስን በተገቢው የመስጠት ተቋማዊ ብቃት ሊኖር ይገባል። የመምህራን ምዘና ውጤታማነት በመዛኙም ሆነ በተመዣኙ በኩል ተገቢ የሆነ ብቃትና ክህሎት ላይ የተመሠረተ መሆኑም ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል::

በሌላ አነጋገር ‹‹የምዘናው ውጤት የተመዛኙን ክፍተት ብቻ ሳይሆን የመዛኙም ችግር ነፀብራቅ ነው›› ከሚለው የባለሙያዎች አስተያየት ጋርም አለመስማማት አይቻልም። በመሆኑም፣ እንደ አንድ የሚኒስቴሩ የምዘናና የሙያ ፍቃድ አሰጣጥ ዘርፍ ተዋቅሮ ሥራውን ሲሠራ የነበረው እንደ ገና በተጠናከረ መልኩ ተመልሶ ሥራውን በባለቤትነት ሊይዘውና ሊያከናውነው ይገባል። የትምህርት ጥራትን የማስጠበቁ ተግባርም መጠናከር ይኖርበታል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You