ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎ መነቃቃቶች እየታዩ ናቸው። በመዳረሻ ልማት ግንባታ፣ በገበያና ማስተዋወቅ እንዲሁም አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎች ተጨማሪ የዘርፉን አቅም እንዲገነቡ ከማድረግ አንስቶ ልዩ ልዩ ለውጦች እየተደረጉ ናቸው። በተለይ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ የተጠናቀቁና የጎብኝዎች ምርጫን ያሰፉ መዳረሻዎችን እዚህ ላይ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። በተለያዩ ክልሎች በመጨረሻው የግንባታ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ ትላልቅ የቱሪዝም ፕሮጀክቶችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳዩና የቱሪዝም ኢንቨስትመንትን ያነቃቁ እንደሆኑ ይታመናል።
የቱሪዝም ዘርፍ በኢኮኖሚ ላይ በጎ ተፅዕኖ እንዲኖረውና ለእድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በቀጣይም በመንግስት በርካታ ተግባራት እንዲከናወኑ ይጠበቃል። ከእነዚህ ውስጥ ጠንካራ ፖሊሲ፣ ሕግና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ማውጣትና ተግባር ላይ ማዋል የሚሉት ይገኙባቸዋል። ክትትልና ድጋፍ ከማድረግ እንዲሁም ሕጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ መደላድል ከመፍጠር በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም ላይ የሚኖረው የበለጠ ተሳትፎ እንዲጎለብት መንገድ መጥረግም የመንግስት ኃላፊነት ነው።
ቱሪዝም የመዳረሻ ልማት (መሰረተ ልማት)፣ የገበያና ማስተዋወቅ ተግባር በጥልቀት ሊሰራባቸው ከሚገቡ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ሀብት በማስተዋወቅ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ማስፋፋትና የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ የአስፈፃሚው ድርሻ ነው። በዘርፉ መዋለንዋይ በማፍሰስ የሚሳተፉ ባለሀብቶች እና የግል ተቋማትን መጋበዝ እና ትኩረታቸውን መሳብ ይገባል።
ከዚህ አንፃር ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በመንግስት በኩል ተግባራዊ የተደረጉ ስራዎች አሉ። በግሉ አቅም የማይሸፈኑ የመዳረሻ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን በመስራት ኢንቨስተሮችን የመስዕብ ስፍራ ባሉባቸው ቦታዎች ሆቴሎች፣ ሎጆችና ልዩ ልዩ የአገልግሎት ተቋማትን እንዲገነቡና የሆስፒታሊቲ ንኡስ ዘርፍ እንዲጎለብት ጥረት መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ የተሰኙት ፕሮጀክቶች ናቸው።
የቱሪዝም ዘርፉ የሚፈለገውን ትኩረት እንዲያገኝና የግል ባለሀብቶችም በኢንቨስትመንት ተሳታፊ እንዲሆኑ የፌደራል መንግስትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚያከናውናቸው ተግባሮች ባሻገር የክልል መንግስታት በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ ያሉ የመስህብ ሀብቶችን በማስተዋወቅና በማልማት የድርሻቸውን ይወጣሉ። ኢንቨስተሮችም በቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ላይ በልዩ ልዩ አገልግሎት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ጥሪ ያደርጋሉ።
የግል ባለሀብቶች በቱሪዝም ኢንቨስትመንት በስፋት ከሚሳተፉባቸው ክልሎች ውስጥም የሲዳማ፣ የቀድሞው የደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ የአማራና የኦሮሚያና ክልሎች ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ክልሎች በርካታ የቱሪዝም መስህቦች ከመኖራቸውም ባሻገር የአገር ውስጥና የውጪ ቱሪስት ፍሰቱም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመብራት፣ የመንገድ እና የመሳሰሉትን መሰረተ ልማት ፍላጎቶች በማሟላት ኢንቨስተሮች በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ላይ እንዲሰማሩ ማበረታቻዎች እየተደረጉ ነው። ባለሀብቶችም በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ዘርፉን የሚያነቃቁ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎት እያሳዩ ነው።
በያዝነው ዓመት በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ ከባለሀብቶች ጋር በቅርበት ለመስራት እቅድ ነድፈው ከሚንቀሳቀሱ ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ክልል አንዱ ነው። ክልሉ መስከረም ወር ላይ የዓለም የቱሪዝምን ቀን በማስመልከት ባዘጋጀው “የቱሪዝም ሳምንት አውደ ርዕይ” ላይ ይህንን እቅዱን ይፋ አድርጓል። በተለይ ኢንቨስተሮች ሊያለሟቸው የሚችሉና አዳዲስ የሆኑ ስምንት መዳረሻዎችን ለይቶ የማስተዋወቅ ስራ መጀመሩን አስታውቋል። ይህንን በተመለከተ በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የሀብት ማሰባሰብና የቱሪዝም ፈንድ ዳይሬክተር የሆነው አቶ ሂክሰን ደበሌ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም በቱሪዝም ዘርፍ ያለው ተነሳሽነትና መነቃቃት ደካማ ነበር። ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ መንግስት ዘርፉን ዋንኛው የኢኮኖሚ ምሰሶ በማድረግ የወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች መሻሻሎች እንዲታዩ ምክንያት ሆነዋል።
ከተቋቋመ ሶስት ዓመታትን እያስቆጠረ የሚገኘው የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽንም ይህንን ለውጥ ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን አቶ ሂክሰን በመግለፅ በተለይ የክልሉን የመስህብ ስፍራዎች በማስተዋወቅ፣ የኢንቨስትመንት ስፍራዎችን በመለየት እና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ገቢ በማሳደግ ረገድ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነ ይናገራል።
በኢትዮጵያ በታሪክ፣ በተፈጥሮ፣ በቅርስ በባህል እጅግ በርካታ የሚaሆኑ የቱሪዝም መስህቦች እንዳሉ የሚናገረው አቶ ሂክሰን ከዚህ ውስጥ በርካታ የዘርፉ ሀብት በኦሮሚያ ክልል እንደሚገኝ ይገልፃል። በክልሉ ባሉ አካባቢዎች የተለያየ መልከዓ ምድር፣ ባህል፣ ቅርስ እንዲሁም ልዩ ልዩ የቱሪዝም መስህቦች መኖሩን ጠቅሶ፣ እምቅ ሀብት ቢኖርም ያንን አልምቶ፣ አስተዋውቆና ወደ ኢኮኖሚ ቀይሮ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ በሚፈለገው ልክ እንዳልተሰራ ይናገራል።
“የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በክልሉ ወደ 20 የሚደርሱ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ውጤት እያመጣ ነው” የሚለው ዳይሬክተሩ፣ ኮሚሽኑ ይህንን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይገልፃል። በአዳዲስ የመዳረሻ ስፍራዎች ላይ የግል ባለሀብቶች ገብተው እንዲያለሙ በትብብር ከክልሉ መንግስት ጋር እንዲሰሩ ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ መሆኑን ጠቁሟል።
የኦሮሚያ ክልል የቆዳ ስፋት ትልቅ መሆኑንና እምቅ የቱሪዝም ሀብት መኖሩን የሚያነሳው ዳይሬክተሩ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም መዳረሻዎች ለማልማትና ባለሃብቱን በኢንቨስትመንት እንዲሳተፍ ለማድረግ እንደሚቸግር ይገልፃል። በተለይ በውስን የሰው ኃይል፣ ከጊዜና የመሰረተ ልማትን በሚፈለገው ልክ ለማዳረስ ከሚጠይቀው ሰፊ ሀብት አንፃር በሁሉም አካባቢ መድረስ እንደሚቸግር ይገልፃል። ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ በ2016 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል የግል ባለሀብቱ በኢንቨስትመንት ቢሳተፍባቸው ውጤታማ እንደሚሆኑ የታመነባቸው ስምንት ቦታዎችን መለየት እንደተቻለ ይገልፃል። እነዚህን የመስህብ ስፍራዎች ለባለሀብቶች በማስተዋወቅና መዋለንዋይ እንዲያፈሱ ለማሳመን እቅድ በመንደፍ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል።
“የመጀመሪያው ባለሀብቱ እንዲሳተፍበት የሚፈለገው እና የማሕበረሰብ አቀፍ ሎጅ እንዲገነባ የታቀደበት የፍል ውሀና ውብ መልከዓ ምድር ያለው ‘ሻሎ’ የተባለ ስፍራ ነው” የሚለው ዳይሬክተሩ፣ ስፍራውም ወደ ሀዋሳ መስመር ሲኬድ ጥቁር ውሀ እንደሚገኝ ጠቁሟል። ስፍራው በኦሮሚያ ክልል ስር ያለ አዲስ መዳረሻ መሆኑን ይገልፃል። ይህ ስፍራ ኢንቨስተሩ እንዲሳተፍባቸውና እንዲለሙ ከሚፈለጉት ስምንት መዳረሻዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይገልፃል። በስፍራው ባለሀብቱ ቢሳተፍም ማሕበረሰቡንና ወጣቱን ያሳተፈ አካታች የቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንዲሆን ታስቦ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስታውቋል።
በሆቴልና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ በሁለተኛነት የተለየው መዳረሻ የአዳማ ከተማ መሆኑን የሚገልፀው አቶ ሂክሰን ደበሌ፤ በከተማዋ በ “ማይስ ቱሪዝም” (የስብሰባ፣ ኮንፍረንስ እና ኤግዚቢሽን) ዘርፍ በርከት ያሉ ባለሀብቶች መዋለንዋያቸውን እንዲያወጡ እየተሰራ መሆኑን ይገልፃል። ከተማዋ ታላላቅ ስብሰባዎችን፣ አውደ ርዕይ እና ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በምታከናውንበት ወቅት ያንን መሸከም የሚያስችል የሆቴል፣ የሎጅና መሰል የሆስፒታሊቲ ስፍራዎች በባለሀብቶች እንዲገነቡ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን መስራት መጀመሩን ይገልፃል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በ2016 ዓ.ም የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ባለሀብቶች እንዲገቡበትና እንዲሳተፉ በማሰብ ከለያቸው ስፈራዎች መካከል ሌላው በሰላሌ (ደብረ ሊባኖስ) አካባቢ የሚገኝና “ጫገል” ተብሎ የሚጠራ ስፍራ አንዱ ነው። በዚያ አካባቢ ያለው የፖርቹጊዝ ድልድል፣ የጭላዳ ባቡን ዝርያ፣ የጀማ ፏፏቴን፣ መልከዓ ምድሩን ጨምሮ ልዩ ልዩ መስህቦችን የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሆነ ይጠቁማል። በዚህ አካባቢ ባለሃብቱ ገንብቶ የአገልግሎት ዘርፉን እንዲያዘምን እና የልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፍ እንደሚፈለግ ይገልፃል።
ዳይሬክተሩ እንዳለው፤ ኮሚሽኑ ከላይ ከተነሱት የተለዩ መስህብ ስፍራዎች በተጨማሪ በአብያታ ሻላ፣ በባሌ፣ በቦረና እና ኢሊባቡር ኢንቨስተሮች ቱሪዝምን መሰረት አድርገው እንዲሳተፉ ፕሮጀክቶች ቀርፆ እየሰራ ይገኛል። በተለይ በኢሊባቡር አካባቢ የቡና ምርት በስፋት ስለሚታወቅና ልማቱም የተስፋፋ በመሆኑ ከእርሱ ጋር የተያያዘ የቱሪዝም መስህብ በኢንቨስተሮች እንዲጀመር ፍላጎት አለ። በተለምዶ አካባቢው ከጅማ ጀምሮ በኢሊባቡር ወለጋ ድረስ የቡና መስመር “coffee root” መሆኑ ስለሚታመን ይህንን መሰረት ያደረገ የተፈጥሮ ሎጆች እንዲገነቡ መስራት ውስጥ ተገብቷል። ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶችም የቡና ሀብት በሚገኝባቸው እነዚህ አካባቢዎች ለጎብኚዎች ምቹ ሎጆችንና መዝናኛ ስፍራዎች እንዲገነቡ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠረላቸው ነው።
እምቅ የቱሪዝም ሀብትን ወደ ኢኮኖሚ አቅም ለመቀየር ቅድሚያ መሰራት የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ መሰረተ ልማት መገንባት፣ ማስተዋወቅ እና የግል ባለሀብትን ማሳተፍ ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ መስፈርቶች መሟላታቸው ብቻ በቂ አይደለም። የቱሪዝም ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን በቀዳሚነት “ሰላም” እና የተረጋጋ ከባቢ ከምንም በላይ ሊኖር ይገባል። በተለይ የግል ባለሀብቶች በነፃነትና ሀብታቸውና ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ “ሰላም ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ቱሪዝም በተለይ ደግሞ ኢንቨስትመንት ያለ ሰላም ሊሳካ እንደማይችል የዘርፉ ባለሙያዎችም ይናገራሉ።
ከላይ ካነሳነው አመክንዮ አኳያ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በፕሮጀክቱ ለይቶ ኢንቨስተሮች እንዲሳተፉበት በጋበዘባቸው መዳረሻዎች በተሳካ መልኩ ውጤታማ ልማት እንዲከናወንባቸው ከሰላም አንፃር ምን ምቹ ሁኔታ እንዳለ የዝግጅት ክፍላችን ለዳይሬክተሩ ጥያቄ አንስቶ ነበር። እርሳቸውም በክልሉ 90 በመቶ በላይ የተረጋጋና ለቱሪዝም ልማት ምቹ የሆነ ሰላም መኖሩን ይገልፃሉ። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ “ምንም እንከን የለም” የሚል ድምዳሜ አለመኖሩን ይናገራሉ።
በአጠቃላይ በዓለም ላይ ካለው አለመረጋጋት እና በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚፈጠሩ ግጭቶች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ነገሮች ቢኖሩም ችግሮቹ በመንግስት ልዩ ትኩረት እልባት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚሽኑም የማሕበረሰቡን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ከቱሪዝም ልማቱም ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን በማስቻል ከሰላም አንፃር ራሱ ዘብ የሚሆንበት እድል እየተፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል። ከዚህ መነሻ በ2016 በባለሀብቶች ተሳትፎ እንዲለሙ የተመረጡ መዳረሻዎች ስኬታማ አፈፃፀም እንዲኖራቸው የተግባር ስራዎች መጀመራቸውን ነግረውናል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2016