ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ስሟን ያስጠሩ፣ ሰንደቅ አላማዋን በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ጀግኖች ልጆች አሏት። ከእነዚህ ውስጥ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የታላላቆች ታላቅ ሆነው ተገኝተዋል። ይህም በመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት መቶ ታላላቅ የአገር መሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ደራሲያንና ሰዓሊያን ተመርጠው የአገራቸውን ሰንደቅ አላማ፣ ስማቸውና የህይወት ታሪካቸው ተፅፎ ወደ ጨረቃ ሲላክ የአርቲስቱ የህይወት ታሪክ ተፅፎ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጋር ጨረቃ ላይ የተቀበረው ግልባጭ የሁላችንም ክብር ሆኖ ይገኛል። አርቲስቱ የአራት አካዳሚዎች አባል በመሆናቸው ሥራዎቻቸው በርካታ በሆኑ ታላላቅ ሙዚየሞች በቋሚነት ለህዝብ በመታየታቸው በየደረጃው ሜትር አርቲስት፣ የሥነ ጥበብ ሊቅ፣ የዓለም ሎሬት፣ እጅግ የተከበሩ የሚባሉ ማዕረጎችን አሰጥቷቸዋል።
ስለ አርቲስቱ በተለያዩ ቋንቋዎች መጽሐፍት ተጽፈዋል። ሎሬቱ በተሸለሙባቸው መድረኮች ላይ ስለሰው ዘር መገኛነታችን፣ ስለስነ ህፃዎቻችን፣ ስለነፃነታችን፣ ስለባህልና ወጋችን ሰብከዋል። አንደበታቸው በቃላት፣ ጣቶቻቸው በቀለምና ብሩሻቸው ሲያወሩ ‹‹ኪነ ጥበብ የሰው ልጅን መንፈስ ለማዳበር፣ አገራችንን ለማሳደግ፣ ለማሳወቅ እና ለህይወታዊ ኑሮ ተስፋ ለመፍጠር የላቀ ሚና ይጫወታል። ዛሬ የምንሠራው ሥራ የዛሬን ህይወት እያንፀባረቀ ለነገው ትውልድ ፈር መቅደድ አለበት›› ይላሉ። ኪን ማንኛውንም የሰው ኑሮ የሚነካ እንደሆነ አስረግጠው ያስረዳሉ።
በዓለም የታወቁና የተከበሩት ኢትዮጵያዊው ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ በሰሜን ሸዋ በምትገኘው የሸዋ ነገሥታት ከተማ አንኮበር ጥቅምት 12 ቀን 1925 ዓመተ ምህረት ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ተወለዱ። ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በግፍ ሲወራት፣ የልጅነት ትዝታቸውም ይሄው የግፍ ወረራ እና ጦርነት የሚያስከትለው የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ሲሆን ከነፃነትም በኋላ አቢዩ ሥራ በወረራ የተበላሸችውን ሀገራቸውን እንደገና መገንባት ላይ አልመው ነበር። ለዚህም የሀገር ግንባታ አስፈላጊውን እውቀት መሸመት የፈለጉት በማዕድን ምሕንድስና ዘርፍ ነበር። ወላጆቻቸውና ዘመድ አዝማዶች ግን የኪነ ጥበብ ስጦታቸውን በቤታቸውና በከተማው ዙሪያ በሚስሏቸው ስዕሎች ተገንዝበውት ነበር።
የመጀመሪያና መካከለኛ ትምህርታቸውን የት እና መቼ እንዳጠናቀቁ የተጻፈ መረጃ ባናገኝም፤ ገና በአስራ አምስት ዓመታቸው ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው የምሕንድስና ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ እንግሊዝ አገር ተላኩ። በወቅቱ ለትምህርት ወደ ውጭ የሚሄዱ ተማሪዎች ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሲሰናበቱ፣ ጃንሆይ የሰጧቸውን ምክር አፈውርቅ ተክሌ ሁሌም ያስታውሳሉ። ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹ ተግታችሁ አጥኑ፣ ተማሩ ብለው ከመከሩን በኋላ ጠንክራችሁ መሥራት እና ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የምትገነቡበትን ዕውቀት ይዛችሁ ተመለሱ። ስትመለሱ አዕምሯችሁ ዝግጁ የሆነ እውቀታችሁም ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚችል ጥበብን ሸምቶ እንዲመለስ ነው እንጂ አውሮፓ ውስጥ እንዴት ያሉ ረዣዥም ፎቅ ቤቶች እንዳሉ ወይም መንገዶቻቸው የቱን ያህል ስፋት እንዳላቸው እንድትነግሩን አይደለም ›› ይሏቸው እንደነበር ደጋግመው ገልፀዋል።
የዓለም ሊቀ ሊቃውንት፣ የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ በእንግሊዝ አገር የአዳሪ ተማሪ ቤትን ኑሮ ሲያስታውሱ የባዕድ ባህላት፣ የአየር ለውጥ እና የተለመደው የተማሪ ቤት ዝንጠላ እንዳስቸገራቸው ያወሳሉ። ቢሆንም ትምህርታቸውን በትጋት ሲከታተሉ ቆዩ። በተለይም በሂሣብ፣ በፖካርሲን (chemistry) እና በታሪክ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት በማምጣት ሰለጠኑ። ነገር ግን አስተማሪዎቻቸው የተፈጥሮ ስጦታቸው ኪነ ጥበብ እንደሆነ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜም አልወሰደባቸውም። በእነሱም አበረታችነት በእዚህ ስጦታቸው ላይ የበለጠ ለማተኮር ወስነው በሎንዶን የኪነ ጥበብ ማዕከላዊ ትምህርት ቤት (Central school of Arts & Crafts) ትምህርታቸውን ተከታተሉ።
ከዚህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ለከፍተኛ ጥናት በስመ ጥሩው የሎንዶን ዩኒቨርሲቲ የስሌድ ኪነ ጥበብ ማዕከል (Faculty of Fie Arts at Slade) የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተማሪ (ከተከተሏቸው አፍሪካውያን አንዱ የሱዳን ተወላጁ ኢብራሂም ኤል ሳላሂ ናቸው) በመሆን ገቡ። በዚህም በስዕል፣ በቅርፅ እና በስየቃ (architecture) ጥናቶች ላይ አተኩረው ተመረቁ።
ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ በየጠቅላይ ግዛቶቹ እየተዘዋወሩ፣ በየቦታው እስከ ሦስት ወራት በመቀመጥ የኢትዮጵያን ታሪክ እና የብሔረሰቦቿን ባህልና ወግ ሲያጠኑ ቆዩ። “ምኞቴ በዓለም የታወቀ ኢትዮጵያዊ የኪነ ጥበብ ምሑር መሆን ስለነበር፣ የአገሬን ወግና ባህል ጠንቅቄ ማወቅና ማጥናት እንዳለብኝ አውቄያለሁ። ሥራዬ የዓለም ንብረት ይሆናል ነገር ግን በአፍሪካዊነት ቅመም የጣፈጠ ሥራ ነው የሚሆነው።” ይሉ ነበር። ከሁሉም በላይ ግን የዓለም ሊቀ ሊቃውንት፣ የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ፤ የላቀው ድካማቸውና የምናየውም ውጤት፣ የኪነ ጥበብ ሥራቸው የአገራቸውን ታሪክ የሚያንፀባርቅ ሕብረተ ሰብአዊ መሣሪያ እንዲሆን ነው። በውጭ የተማሩ ቢሆኑም፣ እሳቸው ‘ዋጋ ቢስ’ የሚሉትን፣ እንደሌሎች (ምዕራባውያንም ሆኑ ሌሎች) የሚጠቀሙበትን ‘ኩረጃ’ ላለመከተል በትጋት ተፋልመዋል።
ወደ ውጭ ሊሄዱ ሲነሱ የሰሙትን የንጉሠ ነገሥቱን ቃላት ”….ኢትዮጵያን ለመገንባት አዕምሯችሁ ዝግጁ ይሁን፣ ለዚህም የሚጠቅም ጥበብን ሸምቱ…” ያሏቸው ቃላት በውስጠ ጆሯቸው እያስተጋቡ፤ ከውጭ ሲመለሱ የተመደበላቸውን ሚኒስቴራዊ ሥራ ትተው የኪነ ጥበብ ሥራቸው ላይ በማተኮር ስዕሎቻቸውን በአገር ውስጥም በውጭ አገርም እያሳዩ ለማገልገል ቆረጡ።
በሃያ ሁለት ዓመታቸውም ሥራቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያውን የኪነ ጥበብ ትርዒት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቀረቡ። ወዲያውም ከዚህ ትርዒት ባገኙት ገቢ ተመልሰው ወደ አውሮፓ በመሄድ ለሁለት ዓመት በኢጣልያ፣ በፈረንሳይ፣ በእስፓኝ፣ በፖርቱጋል፣ በብሪታኒያ እና በግሪክ የጠለቀ የኪነ ጥበብ ጥናት አከናወኑ። በተለይም በእነዚህ አገሮች ውስጥ በስደት የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ኃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት በጥልቅ አጠኑ። እንዲሁም የመስታወት ስዕል (stained glass art) እና የ’ሞዜይክ’ አሠራርን ጥበብ ተምረው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
በዚህ በሁለተኛ መልሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን በኃይማኖታዊ የግድግዳና ጣሪያ ስዕሎች፣ የ’ሞዜይክ’ ሥራዎች፣ መስኮቶቹንም በመስ ታወት ስዕሎች እንዲያሳምሩ ቀጥረዋቸው አሁን የምናያቸውን እንደ አዲስ አበባ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘው የመጀመሪያው “የዳግማዊ ምፅዓት ፍርድ” ስዕል፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ንግሠት የሚያሳየው “ኪዳነ ምሕረት”፣ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የዘውድ ሥርዓት የሚያሳዩ ሥራዎችን ሠርተዋል። አከታትለውም አሁን በሐረር ከተማ የሚገኘውን የልዑል ራስ መኮንንን ሐውልት ሠሩ። የስዕል እና ሌላ የኪን ሥራዎቻቸው ወዲያው በ’ቴምብሮች’፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የኪነ ጥበብ ትርዒት ላይ እየታወቁና እየገነኑ መጡ።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ አገራችን ካፈራቻቸው ታላላቅ የስነ ጥበብ ሰዎች መካከል በዘመናዊ የስዕል ጥበብ ቀዳሚ ናቸው። የሀገራችን ታላቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ የኢሊባቡርን የተፈጥሮ ውበት ወንዙን፣ ኮረብታውንና ደኑን ሲገልፅ በአፈወርቅ ተክሌ ጣቶች የተሠሩ ስዕሎች ይመስላሉ ነበር ያለው። አዘውትረው ‹‹ኢትዮጵያ ምን ሠራህ ብላ ትጠይቀኛለች›› ይላሉ። በዓለም ከታወቁት የጥበብ ሥራዎቻቸው መካከል ‹‹የሰሜን ተራሮች››፣ አዲስ አበባ በአፍሪካ አዳራሽ መግቢያ የሚታየው በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ላይ የተሳለው ትልቅ የመስታወት ስዕል (አንደኛው የአፍሪካን የቀድሞ ዕሮሮ፤ ሁለተኛው የአህጉሯን የወቅቱን ትግል እና ሦስተኛው ደግሞ የዚችን ትልቅ አህጉር
የወደፊት ተስፋ የሚያሳዩ ናቸው። በአዲግራት የ’ዳግመኛ ምጽዓት ፍርድ ስዕል፣ በሎንዶን ‘ታወር ኦፍ ለንደን’ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ቤት ከብር እና ከእንጨት የተሠራ የመንበር መስቀል፣ በሩሲያ፣ አሜሪካ እና በሴኔጋል ትርዒቶች የታዬው ‘የመስቀል አበባ’፣ “እናት ኢትዮጵያ’፣ የአቡነ ተክለ ኃይማኖት ምስል፣ ‘ደመራ’ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ‹‹በኢትዮጵያ ላይ ክፉ አትይ፣ ክፉ አትስማ፣ ክፉ አትናገር›› የሚለው የአርቲስቱ መሪ ሀሳብ ነው።
በዓለማችን ላይ ምርጦች አሉ፤ ደግሞም የምርጦች ምርጥ አለ። የአሜሪካን ባይኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ‹‹እርስዎ የምርጦች ምርጥ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰው ወይም ‹ግሬት ማይንድ› የሚለውን ክብር ተጎናፅፈዋል›› ሲል በጥበብ ሥራዎቻቸው ላበረከቱት ድንቅ ሥራ የበዛ አድናቆቱን ገልፆላቸዋል። ዋሽንግተን በተካሄደው ወርልድ ፎረም ላይም ከአንድ ሺህ እጩዎች መካከል ተመርጠው የ21ኛው ክፍለ ዘመን የታላቅ አዕምሮ ባለቤት ተብለው ተሸልመዋል።
የዓለም ሊቀ ሊቃውንቱ፣ በማይነጥፉ ቀለሞቻቸው የአገራቸውን ስም እና ታሪክ አትመዋል። ለረጅም ዓመታት ከቶም ባረ ገበ የፈጠራ ክህሎታቸው መላውን ዓለም ያስደመመው የስዕል ሥራዎቻቸውን እረፍት በማያውቁ ጣቶቻቸው ቀልመው አቅርበዋል። በኢትዮጵያ የስነ ስዕል ታሪክ ጊዜ የማይሽራቸው ታላቅ ሰዓሊ ናቸው። ዘመናትን ተሻግረው ለሌሎች ትውልዶች አርአያ መሆን ችለዋል። ታላቁ የጥበብ ሰው መላው የህይወት ዘመ ናቸውን አገራችንና አህጉራችንን መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ እጅግ ድንቅ የሆኑ የስነ ጥበብ ሥራዎችን አመንጪ የነበሩ ታላቅ የፈጠራ ሰው ነበሩ። ከሥራዎቻቸው መካከል አስር በመቶዎቹ ኃይማኖታዊ ናቸው።
የዓለም ሊቀ ሊቃውንት የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ፣ አዲስ አበባ ጦር ኃይሎች አካባቢ ራሳቸው በነደፉትና ባሠሩት ባለ ሃያ ሁለት መኝታ ቤቱ ‘‘ቪላ አልፋ’ ብለው በሰየሙት መኖሪያ ቤት ይኖሩና ይሠሩ ነበር። አልፋ ፕሮፌሠሩ መምህራቸው በልጅነታቸው ያወጡላቸው ቅፅል ስም ነው። የአልፋ ቪላ ሰገነት የትውልድ አካባቢያቸውን ያስታውሳቸዋል።
ይህን ቪላ የሠሩት ለፈጠራ ሥራዎቻቸው በቂ ቦታ ለማግኘት እንጂ በአንድ ቤተ መንግሥት በመሰለ ታላቅ ቪላ ውስጥ መኖር ፈልገው አይደለም። በውጭ አገር ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱበት ጊዜ ከገጠማቸው ችግሮች አንዱ የስዕል ማሳያ ቦታ ወይም ቤት (ጋለሪ) በመሆኑ ለዚህም ሲባል ቪላውን ገነቡ። ቅጥር ግቢውም ገጣሚያን ግጥሞቻቸውን አልፎ አልፎ ለወዳጆቻቸው እንዲያነቡላቸው የሚያገለግል የሜዳ መድረክ እና አንዳንድ የሚያውቋቸውን ቦታዎች እንዲያስታውሳቸው አስበው ድንጋያማ የአትክልት ቦታ እንዲኖረው ተደርጓል።
ይህ ቪላ በአጠቃላይ የሎሬቱ ስዕሎች መኖሪያ ነው። የሰዓሊው አባት ምስልና በመኝታ ቤታቸው እናታቸው ሲፈትሉ የሚያሳይ ስዕል አለ። መኝታ ቤታቸው ጠበብ ብላ ምቹ ናት። ከትምህርት ቤት ጀምሮ የተዋወቋቸው የእንግሊዝ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች የጋበዟቸውንና የረዷቸውን ታላላቅ የጥበብ ቤተሰቦች ቤታቸው ጋብዘው ሊያሰተናግዱበት የሚያርፉበት የመኝታ ቤት አንድ ክፍል ይዟል።
በቤቱ ውስጥ ካሉ ታሪካዊ ስዕሎች ውስጥ አንዱ በደርግ ዘመነ መንግሥት ቪላውን ለመንግሥት አስረክበው ሊወጡ አንድ ሳምንት ሲቀራቸው የሳሉት ስዕል ነው። ፍልሚያን የሚያሳየው ስዕላቸውም ለዕንግዶቻቸውና ለራሳቸው የሚስተምረው ትምህርት እንዳለ ይገልፃሉ። ይኸውም በወጣትነት ዘመንህ ሽማግሌ ነው ብለህ አበውን አትናቅ የሚል ነው። ይህ ጅንኑ የተሰኘው ስዕል የቫቲካኑን ሽልማት ያስገኘ ነው። ይህንንም በዓለም ላይ በሁለት መቶ ዓመታት ብቻ ስልሳ ሰዎች ተሸልመውታል። የዚህ ሽልማት ተሸላሚ ‹‹ፕሪንስ ኦፍ ዘ ሆሊሲቲ›› ተብሎ ይጠራል። ይህ ሥራ ለአገራችን አርቲስቶች ትልቅ ነገር ነው። ሁሉም አርቲስቶች በስነ ጥበብ ሙያ እስከዚህ ደረጃ መድረስ ይቻላል ብለው እንዲያምኑ ዕድል ይሰጣቸዋል። በዚህም ምክንያት ከማይሸጡና ለአገራቸው ካቆዩዋቸው ስዕሎቻቸው መካካል አንዱ ሆኗል።
‘‘ቪላ አልፋ’ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን የአርቲስቱ የፈጠራ ውጤቶች ሁሉ መመንጫ ድንቁ ስቲዲዮ አንዱ ነው ። በዚህ ክፍል ሞዴሎች የሚሠሩበት እንደመሆኑ መጠን ግርማ ሞገስ የተላበሱ ወንበሮች ከፍ ባለ መድረክ ላይ ተደላድለው ተቀምጠዋል። በክፍሉ ውስጥ የተጀመሩና ወደ ማለቅ የቀረበ ደረጃ የደረሱ ስዕሎች፣ በብዙ አውደ ርዕዮች ላይ ያልታዩ ለብዙ ዓመታት የለፉባቸውና ብዙ ተስፋ የጣሉባቸው፣ በመስታወት አሊያም በቅርፃቅርፅ ወይም በሐውልት መልክ ሊሠሩ የሚችሉ የሎሬቱ የፈጠራ ሥራዎች ይገኛሉ።
ለየሥራዎቻቸው በሰጧቸው ስያሜ በቪላው ልዩ ልዩ ክፍሎች ተሰድረዋል። ‹‹እኔ ለአገሬ›› በሚለው ርዕስ ላይ የሰሜንን፣ የምሥራቅን፣ የምዕራብን፣ የደቡብን ጀግኖችን የሚወክሉ ብዙ ስዕሎችን ሠርተዋል። ‹‹የሰሜን ተራራ›› በጣም ከታወቁት መካከል ከፍተኛ ዋጋ የተሰጠውና በቪላው ውስጥ ከሚገኙት አንደኛው ነው። ‹‹የመስቀል አበባ›› የተሰኘው ሌላኛው ታዋቂ ሥራቸውም በቤቱ ውስጥ ይገኛል ።
የመስቀል አበባ አፈጣጠር ለየት ያለ መሆኑን የሚያምኑት ሎሪቱ በአበባዋ ስም የሰየሟትን ሥራ የጀመሩት የመስቀል አበባን ለመዘከር ብለው እንደሆነ በአንድ ወቅት ተናግረዋል። በዓመት አንዴ ብቅ የምትል ብርቅዪ ቱባ አገር በቀል አበባን መጀመሪያ በመታጠቢያ ቤት በብርጭቆ ውስጥ አድርገው መሳል ፈልገው ነበር። በዚህ ሐሳብ ብዙ ከተጨነቁ በኋላ አንድ ነገር በሐሳባቸው ብልጭ አለ።
መስቀል አበባ አጊጣ በጣም ውብ የሆነ መልክ ይዛ በውስጧ ግን ምንም አይነት ስሜት እንደማይታይባት አሰቡ። በዚህም መሰረት የመስቀል አበባ ብለው የሰየሟትን ስዕል ሳሉ። ስዕሏ አንዲት ባህላዊ ልብስ የለበሰች ሴት ወደ ገዳም የምትገባ ትመስላለች። አንድ እግሯ ብቻ ነው የሚታየው፤ ሌላው ግን የለም። እንደ ዘበት የያዘችው አበባ ከእጇ ሊወድቅ ምንም አልቀረው። ሌላኛው እጇ ካባውን ገንጥሎ የሚወጣ ይመስላል። እናት ኢትዮጵያ ብለው የሰየሙት ስዕል መሰረቱ እነኛ የተፈጥሮ የሰሜን ተራሮች ናቸው። አንዲት እናት ባቀፈችው ልጅ ዘልቃ ሩቅ ታያለች። አጣፍታ በለበሰችው ሸማ ጥለት ዙሪያ ያለው የሸማው እንቅስቃሴ የሚያሳየው ተራራውን፣ ወንዙን፣ ያልተነካውን የኢትዮጵያን መሬት የውስጥ ሀብት ነው።
ከተለያዩ አገራት ያገኟቸው ሽልማቶችም በቪላው አንዱ ክፍል ይገኛሉ። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት የመጀመሪያው ሽልማታቸው፣ ከፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት የተሰጣቸው ልብስ፣ ዋናው ‹‹የዳቬንቺ ዳይመንድ›› የተባለው በሊዮናርዶ ዳቬንቺ የተሰየመው ሽልማት፣ ፒናክል፣ የዲያመንድ ቀለበት፣ ካሉት ሽልማቶች ከሁሉም ከፍተኛው የቫቲካኑ አልባሳት፣ ዘ ኦርደር ኦፍ ሰን ሲልቨየስተር የተባለው በወርቅ የተለበጠ ታላቅ ሽልማት እና ሌሎችም ይገኛሉ። ብዙዎቹ ጎብኚዎች ቀጠሮ ይዘው ከውጭ አገር የሚመጡት የሎሬቱን ስዕሎች ለማየት ነው። በመሆኑም እንግዳና ጋዜጠኞችን የሚቀበሉበት፣ የሚያስተናግዱበት ክፍል አንድ የቤቱን ክፍል ይዟል። የቪላው ሌላኛው ክፍል ቤተ መጽሐፍት ሲሆን ስለ ስዕል ምንነት፣ ታሪክ ፍልስፍና የሚተርኩ መጻሕፍት በወጉ ተደርድረው ይታያሉ።
የቪላ አልፋ እና ድንቅ የፈጠራ ሥራዎቹ ባለቤት አፈወርቅ ህልፈት ሲሰማ አስደንጋጭ ነበር። በደረሰባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ማክሰኞ ሚያዝያ 2ቀን 2004 ዓመተ ምህረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩን። ሎሬቱ በዓለም እውቅናና አክብሮት እንዲቸራቸው ያደረጉ ሥራዎቻቸውንና የስዕሎቻቸው መኖሪያ ቤት ቪላ አልፋን ያወረሱት ለዘመድ አዝማዳቸው ሳይሆን ለሚወዷት አገራቸው ነበር። በቪላ አልፋ የነበሩ ስዕሎቻቸውን ለመጠበቅ ሲባልም በወቅቱ ታሽጓል።
የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ጥበበኛ የእጅ ውጤት የሆኑ ስዕሎቻቸው ዛሬም እንደታሸጉ ናቸው። ብዙዎች ሊያዋቸው የሚፈልጓቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የስዕል ሥራዎቻቸው አሁንም ከህዝባዊ እይታ ተሰውረዋል። እውቁ ኢትዮጵያዊ የስነ ጥበብ ባለሙያ ህይወታቸው ከማለፉ በፊት መኖሪያ ቤታቸው ሙዚየም እንዲሆን የተናዘዙ ቢሆንም ይህ እውን ሳይሆን ሰባት ዓመታት ተቆጥሯል።
ከህዝብ እይታ መሰወራቸውን በተመለከት የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበር ምክንያቱን ለማጣራት ያደረገው ጥረት ከቁጭት ያለፈ እንዳልነበረ የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ አክሊሉ ሰለሞን ነግረውናል። አቶ አክሊሉ አልፋ ቪላ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመዘጋቱ የሚያስፈራቸውም የሚያሰጋቸውም ነገር አለ። ስዕሎች በሆነ ቤት ውስጥ ዝም ብሎ አንድ ቦታ ተዘግቶባቸው ብርሃን ሳያገኙ ማስቀመጥ ተገቢ ካለመሆኑ ባሻገር ስዕሎቹ እንዳይበላሹ ሰግተዋል። ሰባት ዓመት በጣም ብዙ ጊዜ በመሆኑ ስዕሎቹ በዚያው ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው ከሆነ አደጋ ደረሶባቸዋል የሚል ፍርሃትም አላቸው። ሎሬቱ በአራት መቶ ሃምሳ ገፅ የተመዘገቡ የፈጠራ ሥራዎችን እና ቤቱ ውስጥ የነበሩ ቁሳቁሶች ማንኪያ፣ ሹካ ሳይቀር ለአገር አበርክተዋል። እነዚህ ለአገር የተበረከቱ ስጦታዎች እስካሁን ድረስ እንክብካቤ ሳይደረግላቸው በአንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው የሚገኙ ከሆነ መበላሸታቸው እንደማይቀር አቶ አክሊሉ ያስገነዝባሉ።
እንደ ሰዓሊያን ማህበር ሊቀመንበሩ ገለፃ በአገራችን ለስዕልም ሆነ ለጥበብ ብዙ ትኩረት አይሰጥም ነበር። ነገር ግን አሁን አሁን ለውጦች እየታዩ ነው። መንግሥት በዓለም የሚታወቁትን ምርጥ የሎሬቱን የጥበብ ሥራዎች ከያዘው ሰባት ዓመት ሊሞላው ነው፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ቀደምቱና ግንባር ቀደም የተለየ ዘመናዊ የአሳሳል ዘይቤ የተከተሉ ሰዓሊ ናቸው። ከኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ ያሳረፉት አሻራ በዓለም እንዲታወቁ አድርጓቸዋል። ሥራዎቻቸው ለራሳቸው ትልቅ እውቅና ክብር አሰጥቷቸዋል።
ዓለም ያደንቃቸዋል፤ ያከብራቸዋልም። በጣሊያን አገር በሚገኝ አንድ ትልቅ እና ታዋቂ ሙዚየም ውስጥ የሎሬቱ ምስል ተቀርፆ (ራሳቸው የቀረፁት) ይገኛል። በዚህ የታላላቅ ሰዎች ምስል ተቀርፆ በሚታይበት የምስል አውደ ርዕይ ላይ የእሳቸውም ምስል ይገኛል። የመጀመሪያው የጥቁር ሰዓሊ ሥራ በዛ ሙዚየም ውስጥ ተካቶ ይገኛል። ይህ ለሳቸውም ለኛም በአገር ደረጃ ትልቅ ኩራት ነው። በጣም ትልቅ እውቅና የነበራቸውና አገር ወዳድ ሰዓሊ ማክበር፣ ማስታወስ፣ ሥራዎቻቸውን በአግባቡ ይዞ ለትውልድ ማስተላለፍ ከኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ ተግባር ነው። ሌሎች እያከበሯቸው፣ እያስታወሷቸው እኛ የራሳችንን ሰው መዘንጋትሥራዎቻቸውን ደብቆ ማስቀመጥ ጥፋት ነው። ሎሬቱ ሰዓሊያን እንደተምሣሌት የሚታዩ ሰዓሊ ናቸው። እሳቸው ቤታቸውንና ሥራዎቻቸውን በእንክብካቤ ነበር የሚይዙት። አሁን ላይ የሎሬቱ ቤትንም ሆነ ሥራዎቻቸው በምን ሁኔታ ተይዘው እንደሚገኙ ሰዓሊ አክሊሉ የሚያውቁት ነገር የለም።
እንደ አክሊሉ አስተያየት አሁን ላይ አልፋ ቪላ በሌሎች ቤቶች ተውጦ አካባቢው ወደ መንደርነት በመቀየሩ ከዚህ ቀደም የነበረው ግርማ ሞገሡ ስለተገፈፈ ለሙዚየምነት ብዙ አያዋጣም። አቶ አክሊሉ ቪላ አልፋን ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር አመቺ ነው ብለው አያስቡም። የአርቲስቱን ሥራዎች በእርግጥ ካገኘናቸው በከተማችን አንድ ታላቅ ለስነ ጥበብ ብቻ የሚውል ሙዚየም ገንብቶ ለሎሬቱ ሥራዎች አንድ ክፍል ሰጥቶ ማሰታወስ ክብር መስጠት ያስፈልጋል። ቤቱ እንደዚሁ ተቀምጦ ሌሎች ቁሳቁሶቻቸውን ይዞ ቢቀመጥና ስዕሎቻቸው ከዛ ወጥተው በሚሠራው የስነ ጥበብ ሙዚየም ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ያምናሉ። አገራችን ካላት ቅርሶች አንፃር በርካታ ሙዚየሞች ቢያስፈልጋትም በተለይ ራሱን የቻለ የስነ ጥበብ ሙዚየም የላትም። ከዚህ ቀደም እንደ ስዕል፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ በአጠቃላይ ስነ ጥበብ እንደቅርስ ስለማይታይና ሙዚየም ስላልነበረ ለዚህ ዘርፍ ራሱን የቻለ ሙዚየም ያስፈልገዋል ባይ ናቸው።
ነገር ግን ቪላ አልፋ ለሙዚየምነት እድሳት ላይ ነው። በቀጣይ የሎሬቱ የጥበብ ውጤቶች ለእይታ በሚያመችና ጎብኚ በእጅ በማይነካቸው መንገድ ለመደርደር እየተሠራ መሆኑን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይገልፃል። የቤቱ እድሳትም ሆነ የጥበብ ውጤቶቹ በአግባቡ ተደርድረው ለህዝብ እይታ ክፍት የሚሆኑበት የጊዜ ገደቡ በትክክል መቼ እንደሆነ አይታወቅም። የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊው እንዳሉት በያዝነው በጀት ማብቂያ ቪላ አልፋ የእደሳ ሥራው ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል። ከዘገየ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር ላይ ተጠናቆ የሎሬቱ ሥራዎች ለህዝብ እይታ ይፋ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል ብለዋል።
ቪላ አልፋ ባለፉት ሰባት ዓመታት ዝግ ሆኖ መቆየቱ መንግሥት የራሱን ጀግና እና አርአያ የሆነ ትልቅ ሰው ችላ ማለቱንም ያሳያል የሚሉ በርካቶች ናቸው። በእርግጥም በዓለም ላይ የታወቀ፣ የዓለም ሎሬት፣ በተጨባጭ በእውቀት በስሎ ለኢትዮጵያዊያንና ለአፍሪካዊያን ተጠቃሽ ሰው፣ ለአፍሪካ ሕብረት ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ ጥበበኛን ኢትዮጵያዊ ማስታወስ የመንግሥት ተግባር ነበር። መንግሥት ይህንን ባለምጡቅ አዕምሮ ኢትዮጵያዊ የት ወደቀ? ሥራዎቹስ የት ደረሱ? ብሎ መከታተል ለህዝብም በግልፅ ማሳወቅ ነበረበት። አፈውርቅ የህብረተሰቡ ጀግና ነው።
ህብረተሰቡ ስማችንን በዓለም ላይ ያስጠራ ምርጡ ሰው የት ወደቀ? ጀግናችን ሰባት ዓመታት ሙሉ ምን ዋጠው? ሥራዎቹ በምን ሁኔታ ይገኛሉ? ታላቁ ሰው ለአገሩ ያበረከተው ውድ ሥራዎቹ ለአገር ጥቅም ውለዋል?፣ ቪላ አልፋስ ለምን ተዘጋ? ብሎ መጠየቅ ነበረበት። አፈወርቅ ልጅ የለውም፣ አፈወርቅ ዘመድ የለውም። አፈወርቅ ሠርቶ፣ ለፍቶ፣ ደክሞ ያካበታቸውን በገንዘብም ይሁን በአድናቆት እጅግ ውድ የሆኑ የጥበብ ሥራዎቹን ለአገሩ ለኢትዮጵያ ነው ያወረሰው።
ኢትዮጵያ ወራሼ ነች ብሎ ሀብቱን ያስረከበ ሰው ነው። ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር እንግዛህ የተባለውን የጥበብ ሥራ ኢትዮጵያ መሬት ላይ የተፈራ ሀብት፣ እውቀት፣ ጥበብ ከኢትዮጵያ ውጭ መውጣት የለበትም በሚል አቋሙ ሳይሸጥ ለአገሩ አስረክቧል። ይህንን ሁሉ ነገር ለአገሩ የለፋ ባለሙያ ሥራዎች የት ደረሱ ብሎ መጠየቅ ያለበት መንግሥትና ህብረተሰቡ ነው። በተለይ የቅርስ ጥበቃና ጥናት ባለሥልጣን ኃላፊነት የጎላ ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የዓለም ውዶቹን የጥበብ ቅርሶች ከታሰሩበት ፈትቶ አገር ገቢ እንድታገኝ፣ ወጣት ተመክሮ እንዲቀስም፣ የሎሬቱ አገራዊ ምኞት እንዲሳካ የቪላ አልፋ በር ክፍት ማድረግ ዛሬ ነገ የሚለው ተግባር መሆን የለበትም። እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የዓለም ውዶቹ የጥበብ ሥራዎች ከሰባት ዓመታት እስር በኋላም ተፈትተው ለማየት ሁላችንንም አጓጉቶናል።
ቪላ አልፋ የተባለ ስያሜ የተሰጠው የስነ ጥበብ አዋቂው የአፈወርቅ ተክሌ መኖሪያ ቤት ከአምስት መቶ በላይ ስዕላትን፣ ከተለያዩ አገራት የተቀበሏቸው ሽልማቶችንና የእሳቸው ሙሉ ንብረት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ለከተማዋም ልዩ መስህብ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ዓመታትን የዘገየው ለምንድን ነው ስንል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን ጠይቀናል። በባለሥልጣኑ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፋንታ በየነ በመጀመሪያ የሕግ ክርክር ስለነበረበት ሲቀጥል የንብረት ቆጠራ ከዛም ለእድሳት የሚያስፈልግ በጀት ለማስመደብ በኋላም እድሳት እየተደረገ ስለሆነ ዘግይቷል ብለውናል።
ኃላፊው እንዳሉት ሎሬቱ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ንብረት ይገባኛል የሚሉ አካላት አንድ ሁለት ዓመታት ያህል በፍርድ ቤት ሲከራከሩ ቆይተው ለመንግሥት ተወስኖለታል። ከውሣኔው በኋላ አልፋ ቪላንና በውስጡ የነበሩትን ቅርሶች ተረክቦ የነበረው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነበር። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም የሎሬቱን ቅርስ ሙዚየም እንዲሆን በመወሰኑ እና ሙዚየሞች ደግሞ የሚተዳደሩት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሥር በመሆኑ በ2006 ዓመተ ምህረት በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ሥር ሆኖ እንዲተዳደር መደረጉን አቶ ፋንታ ያስረዳሉ።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከተረከበ በኋላ ከተለያዩ አካላት በተውጣጡ ኮሚቴዎች አማካኝነት ቪላ አልፋ ውስጥ የነበሩ ንብረቶችን ለመቁጠር አንድ ዓመት መፍጀቱንም ጠቅሰዋል። ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላም ለህዝብ እይታ ክፍት ማድረግ አልተቻለም ያሉት ኃላፊው ቤቱም ሆነ በውስጡ የነበሩት አንዳንድ ቅርሶች የተጎዱ ስለነበሩ በጀት ለማስመደብ የወሰደው ጊዜ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ማደስ መገባቱን ተናግረዋል።
የሎሬት አፈውርቅ ተክሌ አብሮ አደግና የቅርብ ጓደኛ ገጣሚና የቲያትር ፀሐፊ አያልነህ ሙላቱ ግን የሎሬቱ ሥራዎች ባለፉት ሰባት ዓመታት ከህዝብ እይታ ርቀው የቆዩት አቶ ፈንታ በገለፁት ምክንያት አይደለም ይላል። እንደ አያልነህ እምነት ይህንን ሁሉ ዓመታት የሎሬት አፈወርቅ የጥበብ ሥራዎችን ህዝብ እንዳያያቸው ዘግቶ ማስቀመጥ አንደኛ ለአገሪቱ ቅርስ የሚያስብ አካል ወይም ሰው መጥፋት ነው።
ሁለተኛ የዚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሥራዎች ጠንቅቆ አለማወቅና ሥራዎቹ በዓለም ላይ ያላቸውን ታላቅነት ወይም ክብር ካለማወቅ የመጣ ነው። ሦስተኛ ምናልባት አርቲስቱ በዓለም ላይ የተጎናፀፈውን ክብር የማይወዱ አካላት ሥራዎቹ ይህንን ሁሉ ዓመታት ከህዝብ ተሰውረው እንዲቆዩ አድርገው ሊሆን ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ተራ ምቀኝነት ከመሆኑ ባለፈ ሙያውን የማያውቁና ከእውቀት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው አካላት ተግባር ነው ይላል።
የሎሬቱ የረጅም ዓመት ጓደኛ ገጣሚ አያልነህ በአውደ ርዕዩም ሆነ በሌላው ቀን አብሮት የኖረ በመሆኑ እያንዳንዱ ስዕል የት እንዳለ፣ ምን እንደሆነ፣ በምን መልኩ እንደተደረደረ ጠንቅቆ ያውቃል። በኋላም ሎሬቱ ህይወቱ ሲያልፍ ፍርድ ቤት የንብረት አጣሪ ኮሚቴ ውስጥ መድቦት እያንዳንዷን የሎሬቱን ንብረት መዝግቦ ለመንግሥት አስረክቧል። በሎሬቱ ሥራዎች ውስጥ ሁሉም ቦታ ሆኖ አይቷል፤ ያውቃልም። ቪላ አልፋ ሲታሸግ በቦታው ነበር። በወቅቱ ቤቱ የታሸገው በውስጡ የነበሩ ቅርሶችን በአግባቡ ተቆጥረው ርክክብ ለማድረግ በሚል ነበር። እነ አያልነህ ቆጥረውና ሰንደው ርክክቡን ቢፈፅሙም የቪላ አልፋን በር የሚከፍተው አልተገኘም።
እንደ አያልነህ ገለፃ ቪላ አልፋ ለመንግሥት ሲሰጥ የታደሰ ቤት በመሆኑ መታደስ ካለማስፈለጉ ባለፈ በውስጡ የነበሩት ስዕሎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀና አቀማመጣቸው ባመረ መልኩ የተደረደሩ ነበሩ። ሰዓሊው ይታይልኝ ብሎ ባስቀመጠው፣ ዓለም በሙሉ እንዲመለከታቸው በሚያመች መልኩ የተሰደሩ፣ ንግሥት ኤልሳቤት እና ልጆቿ ሳይቀሩ መጥተው ያዩት የስዕል ተርታ መነካት እንዳልነበረበት ሲያስረዳ ገጣሚ አያልነህ የነበረውን የስዕል ተርታ መንካት ማለት ታሪክን ማፍረስ ማለት ነው ይላል።
ሰዓሊው ራሱ እንዳሰቀመጠው ተብሎ ለህዝብ እይታ መቅረብ እንደነበረበት የአያልነህ እምነት ነው ። የዓለም ሎሬቱ፣ የስዕል አባቱ፣ የሙያው ንጉሡ የደረደረውን የስዕል አቀማመጥ የትኛው እውቀት ያለው ሰው ነው የሎሬቱን ሥራዎች በሌላ የአቀማመጥ ስልት የሚደረድርለት? ይህንንስ የሚያደርገው ሎሬቱ ስዕሎቹን ሲሠራ አብሮት የነበረ ወይስ ስለ ስዕሎቹ ጠንቅቆ የሚያውቅ ባለሙያ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄ አዘል አስተያየቶችን ሰንዝሯል። ወራሽ ነን የሚሉ ሰዎች በወቅቱ ቢመጡም ፍርድ ቤት ሎሬት አፈወርቅ ንብረቱን ለኢትዮጵያ ማውረሱን ሲያረጋግጥ ብዙ ጊዜ አልወሰደም።
ወሰደ እንኳን ቢባል መንግሥት ጉዳዩን ባጭር ጊዜ መጨረስ እየቻለ ነበር። ይገባናል የሚሉ አካላት መጥተው ፍርድ ቤቱ ለአገሪቱ ባይወስን እንኳን አገር የምትፈልገው ቅርስ መሆኑን በማስረዳት ካሳ ከፍሎ የአገር ሀብት ማድረግ ይችላል። አራት ዓመትም ወሰደ ሁለት ዓመት መንግሥት ጉዳዩ በፍጥነት እንዲያልቅ ማስገደድ ይችል ነበር። ደግሞም ይህንን ሁሉ ዓመት ፍርድ የማይገኝበት አገር አገር አይደለም። አያልነህ አንዱ ምክንያት ብሎ የሚያስበው ሎሬቱ ለኢህአዴግ የተንበረከከ ስላልነበረ ሥራዎቹ ከህዝብ እይታ እንዲርቁ ተደርጓል።
አያልነህ እንደሚለው የኮሚቴውን ሥራ ሠርተው ሲጨርሱ የቪላ አልፋ በር ተዘጋ። ሥራዎቹ ከዚያን ጊዜ በኋላ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አያውቅም። ይህንን ሁሉ ዓመት ስዕሎቹ ተዘግቶባቸው ከቆዩ ቀለማቸው እንዳለ አይቀመጥም። ቀለማቸው በነበራቸው ደረጃ ልክ አሁን ላይ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም።
ቤቱ ለበርካታ ዓመታት ሲዘጋ የአየር መታጨቅ ስለሚኖር የስዕሎቹ ቀለም ቢጠፋ፣ ቢረግፍ ኃላፊነቱን ማን ነው የሚወስደው የሚለውም በደንብ መታየት እንዳለበት ያሳስባል። ሎሬቱ በህይወት በነበረበት ጊዜ ስዕሎቹን በየሳምንቱ እያወጡ ቅባት እየተቀቡ፣ እየተወለወሉ፣ እየተናፈሱ ተመልሰው ወደ ቦታቸው ይቀመ ጣሉ። ይህን ተግባር ሳያቆራርጥ የሚከውን ሰው በቋሚነት መድቦላቸው እንክብካቤ ያደርግላቸው ነበር።
አሁንስ የታላቁ ሰዓሊ የጥበብ ሥራዎች በምን ሁኔታ ይገኙ ይሆን የሚለውን ጥያቄ ለአቶ ፈንታ አቅርበንላቸው ሲመልሱ ‹‹በቪላ አልፋ ውስጥ የነበሩ ቅርሶች በቆጠራው መሰረት
እያንዳንዳቸው ታሽገው ደረጃውን የጠበቀ ጊዜያዊ ማቆያ ቤት በዛው በግቢው ውስጥ ተሠርቶላቸው እንዲቆዩ ተደርጓል›› ብለዋል። የስዕሎቹን ጤንነት እንዲጠበቅና የመጀመሪያ ገፅታቸው በተለያየ ምክንያት እንዳይቀየር ብሎም እንዳይበላሽ በየጊዜው የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የመደባቸው ወደ ሰባ የሚደርሱ ባለሙያዎች መኖራቸውን ኃላፊው ነግረውናል። ነገር ግን ይህ ተግባር መከወን አለመከወኑን፣ ተመደቡ የተባሉት ባለሙያዎች ስዕሎቹን በምን መልኩ እየተንከባከቡ እንደሆነና የእነሱንም ሀሳብ ለማካተት ቀጠሮ ሳንይዝ በተደጋጋሚ በድንገት ተገኝተን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካልንም።
ቪላ አልፋ ውስጥ መግባት አይቻልም፤ በር ላይም የተሟላ መረጃ የሚሰጥ አካል አላገኘንም። ቤቱ እየተጠገነ መሆኑን ብቻ አረጋግጠናል። ቪላ አልፋን ሰዓሊው እንደ መኖሪያም ይጠቀሙበት ስለነበር ሙዚየም እንዲሆን ሲፈለግ ሎሬቱ ደርድረውት የነበረው የስዕል አቀማመጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስጎብኘት አመቺ ሆኖ ባለመገኘቱ እንዲሁም ቤቱም በአንዳንድ ሥፍራዎች ውሃ ያስገባ ስለነበር መጠገንና በዘርፉ ባለሙያዎች የቅርሶቹን አደራደር እንደገና ማደራጀት ማስፈለጉን አቶ ፈንታ ነግረውናል።
በዚህ ሀሳብ ገጣሚና የቲያትር ፀሐፊ አያልነህ አይስማማም። እንደእሱ ገለፃ ምንም ሌላ ምክንያት መደርደር ሳያስፈልግ አልፋ ቪላ በነበረበት ሁኔታ ክፍት አድርጎ አርቲስቱ ሥራዎቹን ለፈረንጆች እያሳየ ያገኝ የነበረውን ገንዘብ ይቺ ድሀ አገር እንድታገኝ ማድረግ ይገባ ነበር።
ሎሬቱ አገሩን ከመጠን ባለፈ ስለሚወድ ሥራዎቹንና ንብረቱን ለአገሩ አውርሷል። በእሱ ሥራዎች አገሩ ገቢ እንድታገኝ በማሰብ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ዶላር እንግዛህ ያሉትን ስዕሎች ሳይሸጥ አሰቀምጦ ለአገሩ ያበረከተው። አፈወርቅ ለአፍሪካዊያን አብነት የሆነ አፍሪካዊያን የሚያደንቁትና የሚወዱት አርቲስት ነው። ለአህጉሪቱ ማህበርም የራሱን ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የአፍሪካ ሕብረት ስብስባ መደረጉን ተከትሎ የሎሬቱ ሥራዎች ትልቅ የገቢ ማስገኛ ይሆኑ ነበር። ይህንን የሚያመቻች አካል በመጥፋቱ መሪዎቹ እየመጡ የሚወዱትንና የሚያደንቁትን አርአያቸውን የጥበብ ሥራ ሳይመለከቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት ይመለሳሉ። አፈወርቅ አውደ ርዕይ እያዘጋጀ በዓለም ላይ ከተሰባሰቡ ቱሪስቶች ከፍተኛ ብር ያገኝ ነበር። ይህን አሁንም በመድገም ለአገር ገቢ ማግኝት እየተቻለ ቤቱን ዘግቶ መቀመጥ ሌላ ችግር መኖሩን እንደሚያመላክት አያልነህ ያስባል።
የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ፈንታ ግን ቪላ አልፋ እስካሁን ተዘግቶ የቆየበት ምክንያት ከበስተጀርባ ሌላ ምክንያት ኖሮትአይደለም ይላሉ። እንደ እሳቸው አባባል የመንግሥት ሥራ እንደ ግለሰብ በአንድ አካል ብቻ ወዲያው ታስቦ ወዲያው ተከውኖ የሚጨረስ ሳይሆን ሁሉም ነገር ሂደት ባለው መልኩ በተለያዩ አካላት የሚሠራ ነው።
የቤቱን ጉዳይ በሆነ ጊዜ ፍርድ ቤት ይዞት ቆየ ከዛም ቆጠራው ሌላ ጊዜ ወሰደ ለጥገናውም በጀት ለማስመደብና ጨረታ ለማውጣትም ጊዜ አስፈልጓል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተደማምረው ቤቱ እስካሁን ዝግ እንዲሆን አድርጎታል። የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባን ተገን ተደርጎ የሎሬቱ ሥራዎች ለዕይታ ማብቃት ቢቻል ገቢ ማግኘት እንደሚቻል የሚያምኑት አቶ ፈንታ የሕብረቱ ስብሰባ በየዓመቱ የሚቀጥል ስለሆነ ወደፊትም ገቢ ማግኘት ስለሚቻል ዋናው ትኩረት የተደረገው የቅርሱን አደራደር፣ አቀማመጥ ላይ ነው ብለዋል። አብዛኛው የሙዚየም አላማ ማስተማር ነው።
ሙዚየሙ እንደ ሎሬቱ ያሉ ሌሎች አርቲስቶችም እንዲወጡ ሥራዎቻቸውን በተለይ ለአዲሱ ትውልድ ለማስተዋወቅ መሥራት ያስፈልጋል። አዲስ አበባ የኮንፍረንስ ከተማ እንደመሆኗ መጠን በሕበረቱ ስብሰባ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችን ተገን ተደርጎ ገቢ ለማግኘትም ሆነ ለማስተማር የቪላ አልፋ እድሳት ሲያልቅ እንደሚጠቀሙበት ኃላፊው ተስፋ አድርገዋል። የቤቱ እድሳት በፍጥነት ተጠናቆ ክፍት ባለመሆኑ ገቢ ከማግኘት፣ አገራችንን ከማስተዋወቅ፣ ወጣቱን ከማስተማርም አንፃር በተወሰነ መልኩ የታጣ ነገር እንዳለም ጠቅሰዋል።
አያልነህ እንደሚለው የጥበብ ባለሙያዎችም አርአያቸውና ሥራዎቹን አስታውሰው መጠየቅ ነበረባቸው። ቤተ መንግሥት የሚመስለውን ቪላ አልፋን የሠራው ለጥበብ ሰዎች ተምሣሌት ለመሆን ነው። አርቲስትም እንደዚህ መኖር እንደሚችል ለማሳየት አስቦ ሠራው እንጂ እሱ በትንሽ ጎጆ ውስጥ መኖር ይችል ነበር።
አያልነህ ሎሬቱን ‹‹ከመንግሥት አንዲት ሳንቲም ሳይወስድ የኖረ ጥበበኛ ነው። ዛሬ ማንኛውም አርቲስት ከመንግሥት ትከሻ ላይ እየወጣ ቤት ሲሠራ እሱ ግን ዓፄ ኃይለሥላሴ እንኳን ቤት ልስጥህ፣ መሬት ልስጥህ፣ ሹመት ልስጥህ ሲሉት አሻፈረኝ ነው ያላቸው። እኔ ቤት የምሠራው፣ ኑሮዪንም የምመሰርተው፣ ህይወቴንም የምመራው በራሴ ጥበብ ነው ብሎ አቋም ወስዶ በተግባር አውሏል።›› ሲል ገልፆታል።
አልፋ ቪላን ሲሠራ እንዲት ሳንቲም ከመንግሥት ሳይወስድ ገንብቷል። ሎሬቱ በአንድ ወቅት ለምንድን ነው የገነባኸው ተብሎ ሲጠየቅ አርቲስትም እንዲህ መኖር ይችላል የሚለው ለማሳየት ነው ብሏል። አርቲስትም በራሱ ልዑል ነው፣ ልዑል ለመሆን ከቤተ መንግሥት ዘር መወለድ የለበትም የሚል አቋም አለው። የሎሬቱ ሥራዎች ባለፉት ሰባት ዓመታት
ከህዝብ እይታ መሰወራቸውን በተመለከት የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበር ምክንያቱን ለማጣራት ያደረገው ጥረት ከቁጭት ያለፈ እንዳልነበረ የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ አክሊሉ ሰለሞን ነግረውናል። አቶ አክሊሉ አልፋ ቪላ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመዘጋቱ የሚያስፈራቸውም የሚያሰጋቸውም ነገር አለ። ስዕሎች በሆነ ቤት ውስጥ ዝም ብሎ አንድ ቦታ ተዘግቶባቸው ብርሃን ሳያገኙ ማስቀመጥ ተገቢ ካለመሆኑ ባሻገር ስዕሎቹ እንዳይበላሹ ሰግተዋል።
ሰባት ዓመት በጣም ብዙ ጊዜ በመሆኑ ስዕሎቹ በዚያው ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው ከሆነ አደጋ ደረሶባቸዋል የሚል ፍርሃትም አላቸው። ሎሬቱ በአራት መቶ ሃምሳ ገፅ የተመዘገቡ የፈጠራ ሥራዎችን እና ቤቱ ውስጥ የነበሩ ቁሳቁሶች ማንኪያ፣ ሹካ ሳይቀር ለአገር አበርክተዋል። እነዚህ ለአገር የተበረከቱ ስጦታዎች እስካሁን ድረስ እንክብካቤ ሳይደረግላቸው በአንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው የሚገኙ ከሆነ መበላሸታቸው እንደማይቀር አቶ አክሊሉ ያስገነዝባሉ።
እንደ ሰዓሊያን ማህበር ሊቀመንበሩ ገለፃ በአገራችን ለስዕልም ሆነ ለጥበብ ብዙ ትኩረት አይሰጥም ነበር። ነገር ግን አሁን አሁን ለውጦች እየታዩ ነው። መንግሥት በዓለም የሚታወቁትን ምርጥ የሎሬቱን የጥበብ ሥራዎች ከያዘው ሰባት ዓመት ሊሞላው ነው፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ቀደምቱና ግንባር ቀደም የተለየ ዘመናዊ የአሳሳል ዘይቤ የተከተሉ ሰዓሊ ናቸው። ከኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ ያሳረፉት አሻራ በዓለም እንዲታወቁ አድርጓቸዋል። ሥራዎቻቸው ለራሳቸው ትልቅ እውቅና ክብር አሰጥቷቸዋል። ዓለም ያደንቃቸዋል፤ ያከብራቸዋልም።
በጣሊያን አገር በሚገኝ አንድ ትልቅ እና ታዋቂ ሙዚየም ውስጥ የሎሬቱ ምስል ተቀርፆ (ራሳቸው የቀረፁት) ይገኛል። በዚህ የታላላቅ ሰዎች ምስል ተቀርፆ በሚታይበት የምስል አውደ ርዕይ ላይ የእሳቸውም ምስል ይገኛል። የመጀመሪያው የጥቁር ሰዓሊ ሥራ በዛ ሙዚየም ውስጥ ተካቶ ይገኛል። ይህ ለሳቸውም ለኛም በአገር ደረጃ ትልቅ ኩራት ነው። በጣም ትልቅ እውቅና የነበራቸውና አገር ወዳድ ሰዓሊ ማክበር፣ ማስታወስ፣ ሥራዎቻቸውን በአግባቡ ይዞ ለትውልድ ማስተላለፍ ከኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ ተግባር ነው።
ሌሎች እያከበሯቸው፣ እያስታወሷቸው እኛ የራሳችንን ሰው መዘንጋትሥራዎቻቸውን ደብቆ ማስቀመጥ ጥፋት ነው። ሎሬቱ ሰዓሊያን እንደተምሣሌት የሚታዩ ሰዓሊ ናቸው። እሳቸው ቤታቸውንና ሥራዎቻቸውን በእንክብካቤ ነበር የሚይዙት። አሁን ላይ የሎሬቱ ቤትንም ሆነ ሥራዎቻቸው በምን ሁኔታ ተይዘው እንደሚገኙ ሰዓሊ አክሊሉ የሚያውቁት ነገር የለም።
እንደ አክሊሉ አስተያየት አሁን ላይ አልፋ ቪላ በሌሎች ቤቶች ተውጦ አካባቢው ወደ መንደርነት በመቀየሩ ከዚህ ቀደም የነበረው ግርማ ሞገሡ ስለተገፈፈ ለሙዚየምነት ብዙ አያዋጣም። አቶ አክሊሉ ቪላ አልፋን ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር አመቺ ነው ብለው አያስቡም። የአርቲስቱን ሥራዎች በእርግጥ ካገኘናቸው በከተማችን አንድ ታላቅ ለስነ ጥበብ ብቻ የሚውል ሙዚየም ገንብቶ ለሎሬቱ ሥራዎች አንድ ክፍል ሰጥቶ ማሰታወስ ክብር መስጠት ያስፈልጋል።
ቤቱ እንደዚሁ ተቀምጦ ሌሎች ቁሳቁሶቻቸውን ይዞ ቢቀመጥና ስዕሎቻቸው ከዛ ወጥተው በሚሠራው የስነ ጥበብ ሙዚየም ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ያምናሉ። አገራችን ካላት ቅርሶች አንፃር በርካታ ሙዚየሞች ቢያስፈልጋትም በተለይ ራሱን የቻለ የስነ ጥበብ ሙዚየም የላትም። ከዚህ ቀደም እንደ ስዕል፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ በአጠቃላይ ስነ ጥበብ እንደቅርስ ስለማይታይና ሙዚየም ስላልነበረ ለዚህ ዘርፍ ራሱን የቻለ ሙዚየም ያስፈልገዋል ባይ ናቸው።
ነገር ግን ቪላ አልፋ ለሙዚየምነት እድሳት ላይ ነው። በቀጣይ የሎሬቱ የጥበብ ውጤቶች ለእይታ በሚያመችና ጎብኚ በእጅ በማይነካቸው መንገድ ለመደርደር እየተሠራ መሆኑን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይገልፃል። የቤቱ እድሳትም ሆነ የጥበብ ውጤቶቹ በአግባቡ ተደርድረው ለህዝብ እይታ ክፍት የሚሆኑበት የጊዜ ገደቡ በትክክል መቼ እንደሆነ አይታወቅም። የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊው እንዳሉት በያዝነው በጀት ማብቂያ ቪላ አልፋ የእደሳ ሥራው ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል። ከዘገየ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር ላይ ተጠናቆ የሎሬቱ ሥራዎች ለህዝብ እይታ ይፋ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል ብለዋል።
ቪላ አልፋ ባለፉት ሰባት ዓመታት ዝግ ሆኖ መቆየቱ መንግሥት የራሱን ጀግና እና አርአያ የሆነ ትልቅ ሰው ችላ ማለቱንም ያሳያል የሚሉ በርካቶች ናቸው። በእርግጥም በዓለም ላይ የታወቀ፣ የዓለም ሎሬት፣ በተጨባጭ በእውቀት በስሎ ለኢትዮጵያዊያንና ለአፍሪካዊያን ተጠቃሽ ሰው፣ ለአፍሪካ ሕብረት ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ ጥበበኛን ኢትዮጵያዊ ማስታወስ የመንግሥት ተግባር ነበር። መንግሥት ይህንን ባለምጡቅ አዕምሮ ኢትዮጵያዊ የት ወደቀ? ሥራዎቹስ የት ደረሱ? ብሎ መከታተል ለህዝብም በግልፅ ማሳወቅ ነበረበት። አፈውርቅ የህብረተሰቡ ጀግና ነው። ህ
ብረተሰቡ ስማችንን በዓለም ላይ ያስጠራ ምርጡ ሰው የት ወደቀ? ጀግናችን ሰባት ዓመታት ሙሉ ምን ዋጠው? ሥራዎቹ በምን ሁኔታ ይገኛሉ? ታላቁ ሰው ለአገሩ ያበረከተው ውድ ሥራዎቹ ለአገር ጥቅም ውለዋል?፣ ቪላ አልፋስ ለምን ተዘጋ? ብሎ መጠየቅ ነበረበት። አፈወርቅ ልጅ የለውም፣ አፈወርቅ ዘመድ የለውም። አፈወርቅ ሠርቶ፣ ለፍቶ፣ ደክሞ ያካበታቸውን በገንዘብም ይሁን በአድናቆት እጅግ ውድ የሆኑ የጥበብ ሥራዎቹን ለአገሩ ለኢትዮጵያ ነው ያወረሰው።
ኢትዮጵያ ወራሼ ነች ብሎ ሀብቱን ያስረከበ ሰው ነው። ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር እንግዛህ የተባለውን የጥበብ ሥራ ኢትዮጵያ መሬት ላይ የተፈራ ሀብት፣ እውቀት፣ ጥበብ ከኢትዮጵያ ውጭ መውጣት የለበትም በሚል አቋሙ ሳይሸጥ ለአገሩ አስረክቧል። ይህንን ሁሉ ነገር ለአገሩ የለፋ ባለሙያ ሥራዎች የት ደረሱ ብሎ መጠየቅ ያለበት መንግሥትና ህብረተሰቡ ነው።
በተለይ የቅርስ ጥበቃና ጥናት ባለሥልጣን ኃላፊነት የጎላ ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የዓለም ውዶቹን የጥበብ ቅርሶች ከታሰሩበት ፈትቶ አገር ገቢ እንድታገኝ፣ ወጣት ተመክሮ እንዲቀስም፣ የሎሬቱ አገራዊ ምኞት እንዲሳካ የቪላ አልፋ በር ክፍት ማድረግ ዛሬ ነገ የሚለው ተግባር መሆን የለበትም። እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የዓለም ውዶቹ የጥበብ ሥራዎች ከሰባት ዓመታት እስር በኋላም ተፈትተው ለማየት ሁላችንንም አጓጉቶናል።
ዘመን መፅሄት መጋቢት 2011 ዓ.ም
በሣሙኤል ይትባረክ