ለምጣኔ ሀብት ዕድገት ትልቅ ድርሻ ያለው ኮንስትራክሽን

የብዙ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በሚያድግበት ወቅት በመሠረተ ልማት፣ በቤቶች ልማት፣ ወዘተ. የሚታየው ለውጥ እንዳለ ሆኖ ዘርፉ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት፣ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያበረክተው አስተዋጽኦም በዚያው ልክ ያድጋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ ሀገራት ዋና ዋና የሚባሉ መሠረተ ልማቶች ገና ያልተሟሉባቸው በመሆኑ ካደጉ ሀገራት ይልቅ ሰፊ የኮንስትራክሽን መሠረተ ልማት ሥራዎች በቀጣይ ዓመታት እንደሚሠሩ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ እየተተገበረ ባለው የአስር ዓመቱ መሪ እቅድ በመሠረተ ልማት ዘርፍ ሰፋፊ ሥራዎች ለመሥራት ታቅዶ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ዘርፉ ባለፉት ዓመታት ከኮቪድ 19 ወረርሽን ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ላይ በተጣለ ዓለም አቀፍ ጫናና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከታዩ ግጭቶች እንዲሁም እንደ ሲሚንቶ ካሉ የዘርፉ ግብዓቶችና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ መቀዛቀዝ የታየበት ቢሆንም፣ ዘርፉን ከመቀዛቀዝ ለማውጣት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ዘርፉ በተጠቀሱት ምክንያቶች መቀዛቀዝ ውስጥ የቆየ ቢሆንም፣ የራሱ መሠረታዊ ችግሮች ያሉበት መሆኑም በተለያዩ መድረኮች ይገለጻል፡፡ ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የአቅም ውስንነት እንደሚታይበትም የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት/ ፕሮጀክት አስተዳደር/ በኩል ያለበት ክፍተት መፍታት ሁሌም ይጠቀሳል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ለሚታየው የግንባታ መጓተት አንዱ ምክንያት ተደርጎም በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲጠቀስ ይስተዋላል፡፡

ሰሞኑን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት፣ በሥራ እድል ፈጠራ እና ዘርፉን ለማሳደግ ታሳቢ በተደረጉ ተግባሮችና በባለድርሻ አካላት ሚና ላይ የተካሄደ ጥናት ቀርቧል፡፡ በጥናቱ ላይ ተሳትፎ ያደረጉትና የጥናቱን ውጤት ለታዳሚዎች ያብራሩት ዶክተር ኤርሚያስ እንግዳ እንዳሉት፤ ጥናቱ የተካሄደው በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሴሽን ማህበር ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን የምርት ድርሻ እንዲሁም በቀጣይ ዓመታት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚኖረውን አስተዋጽኦና ለሥራ እድል ፈጠራ ያለውን አቅም ዳሷል፡፡

ዶክተር ኤርምያስ እንዳብራሩት፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ከግብርናው ቀጥሎ ግዙፍ ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስና የሥራ እድል ፈጥሮ የሀገርን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አንጻር የኮንስትራክሽን ዘርፉ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዘርፉ ይህን ኃላፊነቱን እንዲወጣ በጥናቱ የተመላከቱ ክፍተቶችን አርሞ ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል።

ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፦

በጥናቱ ላይ ትኩረት የተደረገው የኮንስትራክሽን ዘርፉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ገቢ ለማሳደግ ምን ያህል አቅም አለው የሚለውን ለማየት ተሞክሯል። በዚህም በጥናቱ መሠረት ለተለያዩ ዘርፎች በጀት ቢመደብ ለአብነት አንድ ሚሊዮን ብር ለግብርናው፣ ለኮንስትራክሽን ወይም ለአገልግሎት ዘርፉ በተመሳሳይ ቢመደብ የትኛው ዘርፍ በኢኮኖሚው ደረጃ የተሻለ እድገት ማምጣት ይችላል የሚለውን መመልከት መቻሉን ዶክተር ኤርምያስ ጠቁመዋል።

በጥናቱ ውጤት እንደተለመደው ግብርናው የኢትዮጵያ ትልቁ የኢኮኖሚ ዘርፍ መሆኑን ነው ያሉት ዶክተር ኤርምያስ፣ የኢንዱስትሪው፣ የአገልግሎት እንዲሁም የኮንስትራክሽን ዘርፎች ሲታዩም የኮንስትራክሸን ዘርፉ ትልቅ የእድገት አቅም እንዳለው የታየበት መሆኑን ተናግረዋል። አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ሲታይ ደግሞ የአገልግሎት ዘርፉ የተሻለ ትልቅ ትሩፋት እንዳለው ጠቅሰው፣ ወደ ኢትዮጵያዊ ሠራተኞች ኪስ ከሚገባው ገንዘብ አንጻር ሲታይ ግን በኮንስትራክሽን ዘርፍ ኢንቨስት የተደረገ ገንዘብ የተሻለ ትሩፋት እንደሚያስገኝ የጥናቱ ውጤት አመላክቷል ብለዋል።

በመሆኑም የኮንስትራክሸን ዘርፉ ከበርካታ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ያለው ጠንካራ ግንኙነት እና በግንባታው ዘርፉ ላይ የሚውለው እያንዳንዱ ገንዘብ የተሻለ ሀገራዊ ምርት እንዲያወጣ አስችሎታል ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም መንግሥት ኮንስትራክሸን ዘርፉ ላይ የሚያውለው ገንዘብ ምን ያህል ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እንዲሁም ኢኮኖሚውን አሁን ካለበት የእድገት አቅም የተሻለ ማስፈንጠር እንደሚችል በመገንዘብ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ሰፊ መሠረተ ልማት መሠራት እንደሚገባው እና ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት የጥናት ውጤቱ መጠቆሙን አስታውቀዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ ፦

በሰው ኃይል ቅጥር ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኮንስትራክሽን ዘርፉ የተዳከመ መሆኑን የሠራተኛ ቅጥሩም በዚያው ልክ የተዳከመ እንደነበር ይገለጻል። የጥናቱ ውጤትም የኮንስትራክሽን ዘርፉን ከዚያ ተግዳሮት ውስጥ በማውጣት ወደ ተሻለ የቅጥር እድገት ማሸጋገርና ዘርፉን በአግባቡ ማሳደግ እንደሚገባ አመላክቷል። በሚቀጥሉት ዓመታት የኮንስትራክሽን ዘርፉን የዕድገት እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ከታሰበ በየዓመቱ ስድስት በመቶ ያህል የሠራተኛ ቅጥር ማደግ ይኖርበታል ያሉት ዶክተር ኤርምያስ፣ ይህም አሁን ካለንበት አንፃር እንደሚሻል ጠቁመዋል። የሰው ኃይሉን ለማሳደግ ተከታታይ የሳይት ላይ ሥልጠናዎችን በመስጠት የተጠናከረ የአቅም ማጎልበት ሥራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን ማሳደግ፦

በጥናቱ ምክረ ሃሳብ ላይ የተቀመጠው አቅጣጫ እንደሚያሳየው የኮንስትራክሸን ዘርፉ ትልቅ ሙስና ያለበት መሆኑን ነው። ስለሆነም በዘርፉ ከተጋረጠው የሙስና አሠራር ውስጥ በመውጣት የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ተወዳድረው የሚያሽንፉበት እና በአግባቡ የሚሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ተቋራጮች ከካፒታልና ግብዓት ጋር በተያያዘ እጥረት እንዳለባቸው የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከመንግሥት ጋር ተሠርቶ አሁን ዓለም ላይ አሉ የሚባሉ የካፒታል ግብዓቶችን የሚያገኙበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበትና በዚህም ተቋራጮቹን ከውጭ ተቋራጭ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በተለይ ከሌሎች ሀገሮች ኩባንያዎች አኳያ ሲታይ የጎላ የጥራት ልዩነት እንደሚታይ ጠቅሰው፣ ለእዚህም ተወዳዳሪነት ላይ በትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል። ከዚህ አንፃር ከሠራተኛ ምርታማነት አቅም፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ ከመከተል አንጻር ሰፊ ሥራዎች መሠራት እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል።

አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት (ጂዲፒ)፦

ባለፉት ስድስት ዓመታት ባለው መነሻ ጥናት መሠረት የግብርናው ዘርፍ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት የሚያበረክተው ድርሻ እየወረደ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ድርሻ ደግሞ በተሻለ ሁኔታ እያደገ የሚሄድበት ሁኔታ መታየቱን ጠቅሰዋል። በጥናቱ የቀረበው አማራጭ ተግባራዊ ከሆነም ለሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት የግብርና ዘርፉ የሚለቀውን የኢኮኖሚ ምርታማነት ድርሻ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከአገልግሎት ዘርፉ ጋር በመሆን በተሻለ አቅም መቀበል የሚችሉበት አቅም እንዳለ ጥናቱ ማሳየቱንም ነው ዶክተር ኤርምያስ ያስታወቁት።

በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት ዘርፍ ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለሀገሪቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል የሰላሳ ዓመት ፍኖተ ካርታ እና የዘርፉን የአሥር ዓመት የሥራ እቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ጥናቱ በዋነኛነት ያተኮረው የሥራ ዘርፉ ለኢኮኖሚው እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በአግባቡ መለየትና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን መስጠት ነው።

ከአሁን በፊት ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው እድገት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ቢታመንም ምን ያህል አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል ለሚለው መልስ ሊሰጥ የሚችል የጥናት ዳታ እና አቅጣጫዎችን ሊያሳይ የሚችል የጥናት ሰነድ አልነበረም ሲሉ ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪው ውስጥ የተሳለጠ አሠራር ለማስፈን እና ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ሰነድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ጥናቱ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ጉዳይ በመንግሥትና በተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚወሰን ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ እድገትና ተወዳዳሪነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ጠቅሰዋል፡፡

ኢንዱስትሪው ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛ ሰፊ የሥራ እድል እንደሚፈጥር አስታውቀው፣ ከዚህም ውስጥ አብዛኛው በክህሎት አልባ እና በመጠኑ ክህሎት ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል። ለከፍተኛ ባለሙያዎች ማለትም ለመሀንዲሶች፣ ለአርኪቴክቶች እና ለፕሮጀክት ሥራ አስኪያጆችም ከፍተኛ የሥራ እድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል።

በመድረኩ የቀረበው ጥናት የኮንስትራክሽን ዘርፉን የአስር ዓመት እቅድ ለማሳካት ምን መሠራት አለበት ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ያመላከተ መሆኑን አስታውቀዋል። የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ እና ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሳተፉበት፤ መጪውን የእድገት አቅጣጫ ታሳቢ ያደረገ ጥናት መሆኑንም ገልጸዋል። በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ ውስንነት እንዳለ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ ውስንነት በአንድ ጊዜ እንደማይቀረፍ ጠቅሰው፣ ክፍተት መለየት የመጀመሪያው ተግባር ነው ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በኮንስትራክሽን ዘርፉ የማኔጀመንት ስፔሻሊቲዎች መካከል የቱ ላይ ችግር እንዳለ በመለየት በክፍተቱ ላይ የክህሎት ሥልጠና እየተሰጠ ነው። በዲዛይን ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላትም በኢንጂነሪንግ ሶፍትዌሮች ላይ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። በማኔጅመንቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢንጂነሪንግ ዘርፉ ላይም ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላትም ሥልጠናዎች እየተሰጡ ናቸው።

አሁን ባለው ሁኔታ አቅርቦቱና ፍላጎቱ እንደማይጣጣም ኢንጂነር ታምራት ጠቅሰው፣ በገጽ ለገጽ ሥልጠና ብቻ ሥልጠናውን ማዳረስ እንደማይቻል ተናግረዋል።ሥልጠናዎችን ሰዎች የትም ቦታ ሆነው “በየትኛም ጊዜ፣ የትም ሆነው /any time anywhere” በሚል መሪ ቃል ቨርችዋል በሆነ መንገድ ማግኘት የሚያስችላቸው ሶፍትዌር ማልማት ሥራ መጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።

ኢንጂነር ታምራት እንዳሉት፤ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት በተለይ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ላይ አሁን ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ለማስቀመጥ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ፈር ቀዳጅ በመሆን ከባለድርሻዎች ጋር በመሆን 300 ለሚሆኑ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሰርተፊኬት ሰጥቷል፡፡ ከዚያ ውስጥም 96 ያህሉ በበይነመረብ የሚሰጥ የሶስት ሰዓት ፈተና አልፈው በዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሰርተፊኬት አግኝተዋል።

በዚህም ተደራሽነቱን ለማስፋት በአነሰ ዋጋ ፣ በአጠረ ወጪ እና በአጭር ጊዜ ባለሙያዎችን በስፋት ለማሠልጠን ሲባልም ኢንስቲትዩቱ ራሱ በአሜሪካ ከሚገኘው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት “አውቶራይዝድ ትራይኒንግ ፓርትነር” ለመሆን ብዙ ደረጃ በመሄድ የተሳካ ሥራ መሥራቱን ጠቅሰዋል። ይሄንንም ሥልጠና ከዚህ በኋላ በራስ አቅም በስፋት በመስጠት ብዙ ባለሙያዎችን ለዓለም አቀፉ ገበያ ጭምር ተወዳዳሪ ለማድረግ እና ሰርቲፋይድ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የኮንስትራክሽን ዘርፉን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ ተወዳዳሪነትን እንዲሁም በአሠራር ሥርዓቱ ላይ የዲዛይን አካታችነትን ከማምጣት አንጻር፣ በኮንስትራክሽን ኮንትራት ላይ ብዙ ጊዜ የሚታዩ የዋጋ ተገማች አለመሆንን፤ ውሉ የተፈረመበት እና የተጠናቀቀበት ጊዜ የተለያየ መሆን እና የመሳሰሉ ችግሮችን መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ላይ በስፋት ሥልጠና እየተሰጠ ነው።

በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉት ክፍተቶች ቢበዙም በተቻለው መጠን ክፍተቶቹን ለመድፈን ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከአካዳሚ አንፃርም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሙያ ማህበራት እና ከሌሎችም ጋር በኢንዱስትሪው ምን ችግር እንዳለና ችግሩን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት በሚሉ ፍላጎቶች ላይ ያተኮሩ ጥናቶች እየተሠሩ ናቸው ብለዋል።

የኮንስትራክሸን ኢንዱስትሪው የጥናት እና የምርምር ሥራዎቹን ለማስፋት የሚያስችለው የልህቀት ማዕከል ለመገንባት የሚያስችለውን ቦታ ሰንዳፋ በረክ በሚባል አካባቢ ተረክቦ የአጥር ሥራው መጀመሩን አስታውቀዋል። የመጀመሪያው ደረጃ የግንባታ እንደሚጀመር ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይህም የሥልጠና አቅም፣ የጥናትና ማሻሻያ አቅምን እንዲሁም የተለያዩ አጥኚዎችን አንድ ላይ በማሰባሰብ ችግር ፈቺ ጥናቶችን የማጥናት፣ እንዲሁም በግብዓት ላይ ለመሥራት እድል እንደሚፈጥር አመላክተዋል። የልህቀት ማዕከሉም የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትን የጥናትና የምርምር ማዕከል የሚያደርገው አንድ ክንፍ እንደሚሆን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ ለረጅም ዓመታት መሬት ባለማግኘት ሳቢያ ወደ ተግባር ደረጃ ሳይገባ መቆየቱን አስታውሰዋል። አሁን ግን ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መሬት በማግኘት እስከ ቀጣይ ሰኔ ወር ድረስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው እንደሚከናወን ጠቁመዋል። በልህቀት ማዕከሉ ግንባታ ወቅት የሚገነቡ ህንፃዎችም የአረንጓዴ ልማትን፣ ስማርት ቴክኖሎጂን ታሳቢ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል። የግንባታ ሥራው አሁን ባለው የህንፃ ሕግ መሠረት እንደሚከናወንም አመላክተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You