የእናት ውለታዋ …

እንደመነሻ …

ወጣቶቹ በፍቅር ዓመታትን ቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ጊዚያት ሀዘን ደስታን አይተዋል፡፡ ክፉ ደጉን ተጋርተዋል ፡፡ ሁለቱም የአንድ ወንዝ ልጆች ናቸው። አፈር ፈጭተው፣ ውሀ ተራጭተው ያደጉበት ቀዬ ባሕልና ወግ አይለያቸውም፡፡ ልብ ለልብ ተናበው የቆዩበት ጊዜ ለመልካም መሆኑን ያውቁታል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ጎጆ ቀልሰው፣ ልጆች ወልደው መኖር ያስባሉ።

ሰሜን ሸዋ ‹‹ደራ›› ዙሪያ፡፡ ከአንዲት አነስተኛ የገጠር ቀበሌ እቴቱ ከበደና ባለቤቷ ትዳር ይዘው ሕይወት ጀምረዋል፡፡ ዓመታት ያዘለቃቸው ትውውቅ ለጎጇቸው ስምረት መልካም ሆኗል፡፡ ሁለቱም ስለነገ ያስባሉ። ስለሚወልዷቸው ልጆች ስለ ዕድገት ትምህርታቸው ዕቅድ ይነድፋሉ፡፡ እንደ አቅማቸው ቤት ማጀታቸውን የሚያግዝ፣ ጎዶሏቸውን የሚሞላ መተዳደሪያ አላጡም፡፡ አንድያ በሬያቸው ከሌላ ተቀናጅቶ አርሶ ያበላቸዋል፡፡

ለዓመታት የዘለቀው ትውውቅ አሁን በልጅ ስጦታ ተባርኳል፡፡ የቤታቸው ድምቀት፣ የሕይወታቸው ተስፋ ያሉት ወንድ ልጅ ሳቅና ለቅሶው ጎልቶ ይሰማል፡፡

እናት እቴቱ ስለ ትንሹ ልጇ አብዝታ ታስባለች፡፡ ነገን አድጎ፣ ተለውጦ ለሀገር ለወገን እንዲጠቅም ምኞቷ ነው፡፡ ይህ ተስፋዋ ሁሌም ከእሷ እንደሆነ ልጇ አራት ዓመት ሞላው፡፡ አሁን ትምህርት ቤት መግቢያው፣ ከእኩዮቹ መዋያው ነው፡፡ እቴቱ ይህን ስታስብ ውስጧ በሀሴት ይሞላል፡፡ ነገውን አሻግራ እያየች በጎ ደጉን ትወጥናለች፡፡

የቀን ጎዶሎ …

አንድ ቀን ትንሹ ልጅ ከእኩዮቹ ሊጫወት ከሰፈሩ ሜዳ ተገኘ፡፡ ልጆቹ እንደወትሮው ከቀያቸው እየሮጡ፣ እየቦረቁ ነበር፡፡ ለእሱም ቢሆን ይህ አይነቱ ፈንጠዝያ አዲስ አይደለም፡፡ ዕድሉን ባገኘ አጋጣሚ እየሮጠ ይጫወታል፡፡ ሲጫወት ደስ ይለዋል፡፡ ደስታው ሳቅ ፈገግታ ያቀብለዋል፡፡

የዛን ቀን ውሎው ግን እንደቀድሞው አልሆነም፡፡ ጥቂት ተጫውቶ እንደቆየ ከመሬት ወደቀ፡፡ መውደቁን ያዩ ሕጻናት በአቅማቸው ደግፈው ሊያነሱት ሞከሩ አልቻሉም፡፡ ጥቂት ቆይቶ አዋቂዎች ደረሱ፡፡

እናት እቴቱ ከስፍራው ስትገኝ ልጇ ተዘርሮ እንደወደቀ ነበር፡፡ አንጀቷ እየተንሰፈሰፈ ከወደቀበት አንስታ አቀፈችው፡፡ ትንሹ ልጅ አያይም አይሰማም። ሀኪም ዘንድ ይዛው ሮጠች፡፡ ምርመራ ተደርጎለት የሚዋጥ መድሀኒት ተሰጠው፡፡

ጥቂት የጭንቅ ቀናት ተቆጠሩ፡፡ አሁንም በሕጻኑ ጤና ለውጥ አልታየም ፡፡ ቤተሰቡ፣ ወዳጅ ዘመድ ተጨነቀ፡፡ ጭንቀቱ መፍትሄ ከተባሉ ጉዳዮች መጠቆም፣ ማመላከት ያዘ፡፡ እናት እቴቱ በሕክምናው ለውጥ ብታጣ ከጸበል ማመላለስ ጀመረች፡፡ እንዳሰበችው ሆኖ ልጇ አልዳነም፡፡

አሁን የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል፡፡ የጥንዶቹ ብቸኛ ፍሬ፣ የኑሯቸው ተስፋ፣ የቤታቸው ብርሀን ላይደምቅ ደብዝዟል፡፡ ትንሹ ልጅ እንደትናንትናው እየሳቀ አያስቃቸውም፡፡ እየሮጠ አያስደስታቸውም፡፡ ጤናውን አጥቶ፣ በሕመም እየተሰቃየ ነው፡፡

ሆድና ጀርባ …

ወራት አልፈው ዓመት መቆጠር ሲጀምር በቤቱ ሰላም ይሉት ጠፋ፡፡ ባልና ሚስት በየምክንያት ሰበቡ መጣላት መጨቃጨቅ ጀመሩ፡፡ የልጃቸው ጤና መጓደል ቋንቋቸውን አለያየው፡፡ የሆድና ጀርባ ኑሯቸው ፍቅራቸውን ከጠብ ጭቅጭቅ ጣለው። በጎጇቸው ክፉ ንግግር ውሎ አደረ፡፡ ቅያሜው መኮራረፉ ጨመረ፡፡

ባልና ሚስትን በየቀኑ የሚያጋጫቸው የትንሹ ልጅ መታመም ሆኗል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባል የሕጻኑን ሕመም በሚስቱ ማላከክ ጀምሯል፡፡ ልጁ የታመመው በእሷና በቤተሰቦቿ ችግር በመጣ ‹‹ የቤት ጣጣ ›› ስለመሆኑ እየተናገረ ነው፡፡ ይህን የሰማችው እቴቱ በንግግሩ ከማዘን አልፋ ተናዳለች፡፡ ለልጃቸው መታመም ሰበቡ የእሱ እንጂ የእሷ ዘመዶች ጣጣ ያለመሆኑን መልሳ እየነገረችው ነው፡፡

አሁን የባልና ሚስት ጎጆ የጠብ አውድማ ሆኗል። በልጃቸው የሚጣሉበት ጉዳይ ከልብ አቀያይሞ አራርቋቸዋል፡፡ ባል በሽተኛ ልጇን ከዓይኑ እንድታርቅ እየነገራት ነው፡፡ እቴቱ የልጇ ሕመም የእርግማንና የሀጢያት ፍሬ ነው መባሉ ከሕመም በላይ ሆኖባታል፡፡

በፉክክር ውሎ የሚያድረው ትዳር አላማረበትም፡፡ ይህን ያወቁ የቅርብ ሰዎች ሁለቱን አቀራርበው ‹‹አንተም ተው፣ አንቺም ተይ›› ሊሉ ሞከሩ፡፡ ሽንቁሩ የሰፋው ጎጆ ቀዳዳው አልጠበበም፡፡ ሽምግልናው አልሰመረም፡፡ በአንድ ቃል ሊለያዩ ወሰኑ፡፡

አስራ አንድ ዓመታት የዘለቀው ትዳር ዕርቀ- ሰላም አላሸነፈውም፡፡ መፋታት፣ መለያየት ዕጣ ፈንታው ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ ሁሉም አልዘገየም፡፡ ያለው ንብረት ተቆጠረ፡፡ ብቸኛው በሬ ተሸጠ፡፡ ትዳር ተፈታ፣ ጎጆ ፈረሰ፡፡ እቴቱ ከባሏ በፍቺ ከተለየች በኋላ ደራ ላይ መቆየት አላሻትም፡፡ ልጇን ይዛ ካገሯ ለመውጣት ወሰነች፡፡

ባል የልጁ ጉዳይ ጉዳዩ አልሆነም፡፡ እቴቱ ምቾቱን አልተጋፋችም፡፡ እሱ ግን ሕመምተኛ ልጇን አዝላ፣

ጎጆዋን አፍርሳ ከቀዬው ስትወጣ በዝምታ አስተዋላት። እናት ለልጇ ጤና ፍለጋ አገር ጥላ ኮበለለች፡፡

ብዙ ያየችበት፣ መከራ የከፈለችበት ልጅ ለእሷ ትርጉሙ ይለያል፡፡ ሁሌም እንግልቷን፣ ያሳያታል፣ ችግሯን ይነግራታል፡፡ ይህ ሁሉ ምክንያት ውስጧ ቢኖር ለትንሹ ልጅ ‹‹ታምሩ›› ስትል ስም አውጥታለች፡፡

የታምሩ እናት…

አንድ ማለዳ እቴቱ ጓዟን ሸክፋ ታምሩን በጀርባዋ አዝላ ከአውቶቡስ ተሳፈረች፡፡ አሁን ተወልዳ ያደገችበትን ቀዬ፣ ትዳር ይዛ ወግ ማዕረግ ያየችበትን አገር ትታው እየሄደች ነው፡፡ በልጇ ጤና ማጣት ባሏ ጠልቷታል፣ ጎጆዋ ፈርሷል፡፡ እሷ ግን የአንድ ልጇ ሕመም ዛሬም ችግሯ ነው፡፡ ፈጽሞ አትተወውም አትጥለውም፡፡ ዛሬም እሱን ይዛ ከቤቷ ወጥታለች፣ ከአገሯ ርቃለች፡፡

እቴቱ የገባችበት መኪና አዲስ አበባ እንደሚያደርሳት ታውቃለች፡፡ አገሩን ግን ከዚህ ቀድሞ አታውቀውም። ስፍራው ስትደርስ ‹‹የኔ ›› የምትለው ወዳጅ ዘመድ አይቀበላትም፡፡ መኪናው ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ እቴቱ ታምሩን ታቅፋ ታስባለች፣ ትተክዛለች፡፡

አዲስ አበባ …

መዳረሻውን መሀል አዲስ አበባ ያደረገው አውቶቡስ ካሰበው ሲደርስ መንገደኞችን አውርዶ የጫነውን ዕቃ ማረገፍ ጀመረ፡፡ እቴቱ ከወንበሯ ተነስታ ከመኪናው ወረደች፡፡ ግርግሩ፣ ጫጫታው ፈጥኖ ተቀበላት። ሁኔታው ግር እያላት ጥቂት ቆየች፡፡ ስፍራው እሷ እንዳደገችበት አገር አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር ተለየባት፡፡

ልጇን እንዳዘለች የምትፈልገውን ጠየቀች፡፡ የጠየቀቻቸው በቅርብ የሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን አመላከቷት፡፡ አላመነታችም፡፡ ከእግሯ ነጠቅ እያለች ወደ አጸዱ ተጠጋች፡፡ ከስፍራው ስትደርስ እየመሸ ነበር። ልመና ላይ የነበረች ሴት አግኝታ ችግሯን አዋየቻት፡፡ ሴትዬዋ ከእሷ ቤት እንድታድር ፈቀደችላት፡፡

ሌቱ በሀሳብ በጭንቅ ነጋ፡፡ ወፍ ሲንጫጫ ጉዞ ወደ ቤተክርስቲያን ሆነ፡፡ እቴቱ ያሳደረቻትን ሴት ተከትላ ከጎኗ ተቀመጠች፡፡ ለነፍስ ያሉ ምጽዋዕት ሲሰጡ እጇን አልሰበሰበችም፡፡ የሚጣልላትን በፈጣሪ ሥም አመስግና ተቀበለች፡፡ ቀኑ አለቀ፣ ፀሀይዋ ጠለቀች። መሸት ሲል ማደሪያዋ አሳሰባት፡፡ መልሳ ትናንትና ያሳደረቻትን ሴት ጠየቃቻት፡፡ ሴትዬዋ አራት ልጆች አላት፡፡ መተዳዳረያዋ ልመና ነው፡፡ ወጪዋን እየተጋራች አብራት እንድትኖር ይሁንታ ሰጠቻት፡፡

መልካም ዓይኖች …

እቴቱ በቤተክርስቲያን ጥግ እየዋለች መለመንን ለመደች፡፡ ትንሹን ልጅ የሚያዩ ሁሉ አያልፏትም። ሕመሙን ሰረዱ፣ መታመሙን ሲያውቁ የእጃቸውን ይሰጧታል፡፡ አንድ ቀን ግን በተለየ ትኩረት ያስተዋላቻት አንዲት ሴት ወደ እሷ ቀረበች፡፡

ይህች ሴት እንደሌሎች ቤተክርስቲያን ለመሳለም የመጣች ናት፡፡ ታምሩን አስተውላ እያየች ለምን እንደማይናገር፣ እንደማይጫወት ጠየቀቻት፡፡ እቴቱ ሁሉንም አልደበቀችም፡፡ የልጇን ታሪክ ጨምሮ በእሷ ላይ የሆነባትን አንድ በአንድ ነገረቻት፡፡

ሴትዬዋ ሁሉን ከሰማች በኋላ ከልብ አዘነች፡፡ ይህ ስሜት ግን በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ሕመምተኛውን ልጅ በመኪናዋ ይዛ ጴጥሮስ ሆስፒታል ሕክምና እንዲከታተል አገዘችው፡፡ እቴቱ ከታምሩ ጋር ለወራት በሆስፒታሉ ቆየች፡፡ የል ቀናዋ ሴት ድጋፍ አልራቃትም። ለልጁ መድሀኒት እየገዛች፣ የዕለት ወጪውን ሁሉ ሸፈነች። ‹‹አይዞሽ›› ባይ ያገኘችው እቴቱ ውስጧ በተስፋ ሞላ፡፡ ስለነገ ብዙ ማሰብ ማቀድ ያዘች፡፡

የጊዜው ሕክምና እንዳበቃ እናት ዝም አላለችም።፡ መልካም በምታስብላት ሴት የስንቅ ድጋፍ በ ‹‹ሽንቁሩ ሚካኤል›› ለሁለት ዓመታት ፀበል ስታስጠምቀው ቆየች።ሴትዬዋ ቦታው አድርሳት ብቻ አልተመለሰችም፡፡ የጎደላትን እየሞላች፣ የታዘዘውን መድሀኒት እየገዛች ከጎኗ ቆመች፡፡

እቴቱ ከጸበል ቆይታዋ በኋላ ‹‹በቃኝ›› አላለችም። ሕክምናውን ከዕምነቷ አዛምዳ ለልጇ ጤንነት ሌት ተቀን ባተለች፡፡ ከጸበል ከወጣች በኋላ ማረፊያ ቤትና የዕለት ጉርስ አልነበራትም፡፡ ከቤተክርስቲያን ደጃፍ ሰዎች የሚመጸውቷትን እየተቀበለች የእሷንና የልጇን ሕይወት አቆየች፡፡

እቴቱ ስለ ልጇ በጎ ክፉ ስትሰማ ቆይታለች። በርካቶች ከልብ አዝነው አግዘዋታል፡፡ አንዳንዶች ፊት ነስተው አስቀይመዋታል፡፡ በወቅቱ እሷም ተከፍታ አዝናለች፣ አልቅሳለች፡፡ ከሁሉም ግን አብራት ስትለምን የነበረች አንዲት ሴት የተናገረቻትን ክፉ ቃል አሁንም አትዘነጋም፡፡

ይህቺ ሴት የእሷ ልጆች በጤና አድገው ነገ እንደሚለቋት እየነገረች አቁስላታለች፡፡ በሕመምተኛ ልጇ የዕድሜ ልክ ሸክም እንደሚከተላት እየነገረችም ከእሷ መብለጧን ነግራታለች፡፡ በዚህ ንግግሯ እቴቱ ለቀናት አዝና አልቅሳለች፡፡ ዛሬም ድረስ ይህን ቃል አልረሳችውም፡፡

እቴቱ የዛኔ በልጇ ጤና ላይ ያሰበችውን ያህል ለውጥ አላየችም፡፡ እንዲያም ቢሆን ተስፋ መቁረጥ አላሸነፋትም፡፡ ‹‹አራብሳ›› አካባቢ ወደሚገኝ አንድ ጸበል ቦታ ልጇን ይዛ ተቀመጠች፡፡ ሌሎች ስፍራዎችን አዳርሳ እንደወጣች ለጎኗ ማረፊያ የቤት ኪራይ ፈላለገች፡፡

ትዳሯን ፈታ ከአገር ቤት ከወጣች ወዲህ እቴቱ ቤት ይሉትን ወግ አታውቅም፡፡ ከቤተክርስቲያን ደጃፍና ከጸበል እንክርት ያላለፈ ማንነቷ በድካምና መከራ የታሸ ነው፡፡ አሁን እግሯ ‹‹ጣፎ›› ከሚባል ሰፈር አድርሷታል፡፡ አንዲት ደሳሳ ቤት አግኝታም እንደሌሎች በጣራ ስር አድራለች፡፡ ለክፍያው የሚሆን በቂ ገንዘብ ባይኖራትም የአቅሟን እየታገለች ነው፡፡

ውሎ አድሮ የታምሩ አንደበት ለውጥ ማሳየት ያዘ። እናቱ የምትለውን እየሰማ ለመናገር ይሞክረ ጀመር፡፡ ንግግሩ ለሌሎች ባይሰማም ከእቴቱ ጋር ይግባባሉ። የሚሻውን ትጠይቀዋለች ፡፡ የሚፈልገውን ‹‹አምጪ›› ይላታል፡፡ ይህ አይነቱ ለውጥ ለእናት እቴቱ ታላቅ ተስፋ ነው፡፡

ባገኝም በልቼ ባጣም….

ትንሹ ታምሩ ሕመሙ ድንገት በተነሳ ጊዜ ብስጩ ነው፤ ያገኘውን ይወረውራል፣ ይጮሀል፣ ይታገላል፡፡ ይህ ልማዱ ለሌሎች አይመችም፡፡ እናቱ አብዝታ ትጨነቃለች። ሙሉ ትኩረቷ ልጇ ነውና አንዳንዴ ከእጇ ታጣለች፡፡ ይህኔ ልበ መልካሞች ለልጁ ዳቦ ይገዙለታል፡፡ ለእሷም ከተራረፈው አምጥተው ያጎርሷታል፡፡

ቤት ተከራይታ በምትኖርበት ስፍራ ለዕለት ገቢዋ እንዲሆን ስፌት እየሰፋች ትሸጣለች፡፡ የእጇን ጥበብ ከሚያዩት መሀል ጥቂቶቹ ይገዟታል፡፡ አንዳንዴ ገበያ ሲጠፋ ደግሞ እቴቱ የልጇን ችግር እያስረዳች እንዲገዟት ትማጸናለች፡፡ አንዲያም ሆኖ ሳይሳካ ቀርቶ ጦም ውላ የምታድርበት ጊዜ አይጠፋም፡፡ ጥቂት ባገኘች ቀን እናት ‹‹ለእኔ›› አትልም፡፡ የእጇን ለልጇ አጉርሳ ባዶ ሆዷን ታድራለች፡፡

እቴቱ ካገሯ ከወጣች ወዲህ መለስ ብላ አታውቅም። የአዲስ አበባ ኑሮዋ አምስት የድካም ዓመታት አስቆጥሯል። በነዚህ ዓመታት ስለባለቤቷ ብዙ ሰምታለች፡፡ አዲስ ሚስት አግብቶ ሌሎች ልጆች ወልዷል፡፡ ለአንድም ቀን ግን ልጄ የት ደረሰ ብሎ አያውቅም፡፡

ይህን እውነት ስታስብ ውስጧ ያዝናል፡፡ ስለ ልጇ የከፈለችው መከራ ባይቆጫትም የቀድሞ ባሏን በደል ፈጽሞ አትረሳም፡፡ እንዲያም ሆኖ የፈጣሪ ምስጋና ከአፏ ውሎ ያድራል፡፡ ደጋግማ ‹‹ተመስገን›› ትላለች፡፡

የቀን ሙሉ…

አንድ ቀን እቴቱ መልካም ዓይኖች ጎበኙዋት። ተከራይታ በምትኖርበት አካባቢ ችግሯን ያስተዋሉ የመንደሩ ኮሚቴዎች መኖሪያ እንድታገኝ መክረው የቤት ባለቤት አደረጓት፡፡ እቴቱ ‹‹የድሀ ድሀ በሚለው›› መዋቅር ተካታ ቤቷን ተረከበች፡፡ ደስታዋ ወደር አጣ፡፡ ታሪኳን ለቀየረ ፈጣሪዋ አሁንም ደጋግማ ምስጋና አቀረበች፡፡

አሁን እናት እቴቱና ትንሹ ልጇ ዘግተው የሚከፍቱት፣ የሚገቡበት ቤት አላቸው፡፡ ታምሩ ዘጠኝ ዓመቱን ደፍኗል፡፡ በአካባቢው ከሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውሎ ይገባል፡፡ ትምህርት ቤቱ እሱን መሰል ተማሪዎችን አካቶ የሚያስተምር ነው፡፡ የታምሩ ባህርይ ከሌሎች ለየት ይላል፡፡ ካልያዙት ያለማቋረጥ ይጓዛል፡፡ ሲይዙት ይበሳጫል፣ ይናደዳል፡፡

ይህ ልምዱ ያስቸገራቸው መምህራን ለእናቱ ዘወትር ወቀሳ ያቀርባሉ፡፡ እቴቱ ልጇ እንደ ሌሎች ቢማር፣ ቢድንላት ብዙ ታስባለች፡፡ ራሷን የመቻል አቅም ከእሷ ነውና ማንንም ማስቸገር አትሻም፡፡ ዛሬን የሚረዳት ብታገኝ ጉልት ብትነግድ ትወዳለች፡፡ የእጅ ስራዎቿ ገበያ አግኝተው ገቢ ቢያመጡላት ደስ ይላታል፡፡

ደስታዋ ሙሉ እንዲሆን ግን ልበ ቀናዎችን ትፈልጋለች፡፡ ለልጇ የከፈለችው በጎነት ዋጋ ያገኝ ዘንድ መልካም እጆች እንዲተባበሯት ለሚሰሟት ሁሉ መልዕክት ታደርሳለች፡፡ ጠንካራዋ፣ ብርቱዋ እናት እቴቱ ከበደ፡፡

 መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You