አፍሪካ በሁለት ቡድኖች ለምትወከልበት ኦሊምፒክ እግር ኳስ የአህጉሪቱ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታዎች ከቀናት በኋላ ይደረጋሉ። የመጀመሪያውን ዙር የማጣሪያ ጨዋታ በሜዳው ከናይጄሪያ ጋር በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ የሚያስችለው እድል አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ቢሆንም የፊታችን ማክሰኞ አቡጃ በሚካሄደው የመልስ ጨዋታ ይፋለማል።
በ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ውድድራቸውን እያደረጉ የሚገኙት ሉሲዎቹ ከትናንት በስቲያ በአበበ ቢቂላ ስቴድየም ናይጄሪያን ገጥመው 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወቃል። በሜዳቸው በአህጉሪቱ ጠንካራ የሆነውን የናይጄሪያ ቡድንን የገጠሙት ሉሲዎቹ በጨዋታው ነጥብ መጋራታቸው በቀጣይ የሚኖራቸውን የማጣሪያ ጉዞ ከባድ አድርጎታል።
በጨዋታው ሉሲዎቹ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በሚጫወቱ ከዋክብት የተሞላውን የናይጄሪያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ጭልፊቶቹን) ብርቄ አማረ 5ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠረችው ግብ መምራት ቢችሉም፣ ከእረፍት መልስ 51ኛ ደቂቃ ላይ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ኮከብና የጭልፊቶቹ አምበል የሆነችው ራሺዳት አጂባዴ በሉሲዎቹ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና መረብ ላይ ያሳረፈቻት ድንቅ ግብ አቻ አድርጋለች።
ሁለቱ ቡድኖች በቀሪዎቹ 40 ደቂቃዎች ኳስና መረብ ሳያገናኙም ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በኦሊምፒክ መድረክ የሶስት ጊዜ የተሳትፎ ታሪክ ያላት እንዲሁም በቅርቡ ዓለም ዋንጫ ላይ ተካፋይ የነበረችው ናይጄሪያ ለሉሲዎቹ ፈተና ይሆናሉ በሚል ይጠበቁ ነበር። ነገር ግን እንደተጠበቀው በናይጄሪያዊያኑ በኩል የተለየ ብልጫ ማሳየት አለመቻላቸው ታይቷል። በተለይ የቀድሞዋ የሊቨርፑል፣ አርሰናል እና አሁን የባርሴሎና ተጫዋች የሆነችው አሲሳት ኦሾላ በጨዋታው የጭልፊቶቹ ልዩነት ፈጣሪ ትሆናለች ተብሎ ቢጠበቅም፣ ብቸኛዋ የአፍሪካ የባሎን ድ ኦር ሽልማት እጩ በጨዋታው ምንም መፍጠር አለመቻሏ ታይቷል።
በሜዳና በደጋፊያቸው ፊት የነበራቸውን እድል ያልተጠቀሙት ሉሲዎቹ በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ኳስና መረብ ማገናኘት ባለመቻላቸው ሙሉ ነጥብ ማሳካት ተስኗቸዋል። ከቀናት በኋላ በሚኖራቸው የመልስ ጨዋታም ላይ የተለየ ስልት ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
ጨዋታውን ተከትሎም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል፤ ሁለቱም ቡድኖች በጫና ውስጥ ሆነው የተጫወቱ ቢሆንም ጭልፊቶቹ ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው ነጥብ ሊጋሩ መቻላቸውን ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል። ከእረፍት በኋላ ቡድኑ የነበሩበትን ክፍተቶች አርሞ ወደ ጨዋታ ቢመለስም በተጫዋቾች በኩል ችኮላ ባይኖርባቸው የተሻለ ነገር ማድረግ ይቻል እንደነበር አሰልጣኙ ገልፀዋል። ለመልሱ ጨዋታም ከመጀመሪያው ጨዋታ በመነሳት የተለየ ዕቅድ እንደሚያዘጋጁም አሰልጣኙ ጠቁመዋል።
የጭልፊቶቹ ዋና አሰልጣኝ ጀስቲን ማዱጉ በበኩላቸው ነጥብ ይዘው ለመውጣት አቅደው ቢጫወቱም፤ በሉሲዎቹ በኩል በገጠማቸው ጠንካራ ፍልሚያ እንዲሁም ጥራት የሌላቸውና ደካማ ኳሶች ምክንያት ነጥብ መጋራታቸውን ገልጸዋል። በቀጣዩ ጨዋታም ይህንኑ አርመው እንደሚገኙና ውጤት እንደሚያስመዘግቡም አመላክተዋል።
የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ማክሰኞ ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም አቡጃ ላይ የሚካሄድ ሲሆን ሉሲዎቹ ከሜዳቸው ውጪ ከባድ ፍልሚያ የሚጠብቃቸው ይሆናል። ሉሲዎቹ በደርሶ መልስ ድምር ውጤት ማሸነፍ ከቻሉ በቀጣዩና ሶስተኛው ዙር ማጣሪያ ከካሜሩንና ዩጋንዳ አሸናፊ ጋር ይገናኛሉ።
ሁለት የአፍሪካ ቡድኖች በሚሳተፉበት ኦሊምፒክ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማለፍ በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመሩት ሉሲዎቹ ከቀናት በኋላ ወደ ናይጄሪያ ያመራሉ። 11 ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት ትልቅ ስም ያላቸው ጭልፊቶቹ በዓለም ዋንጫ ተከታታይ ተሳትፎ ያላቸው ሲሆን፤ እአአ በ2000 እና 2004 በኦሊምፒክ መድረክ ተሳታፊ እንደነበሩ ይታወቃል። በ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ ተሳትፏቸውም እስከ ሩብ ፍጻሜ ሲጓዙ ከቤጂንግ ኦሊምፒክ በኋላ ግን በመድረኩ አልተካፈሉም። በመሆኑም ጭልፊቶቹ በፓሪሱ ኦሊምፒክ ተሳታፊ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2016