የወርቅ ልማቱ ፈተናዎችና ተስፋዎች -በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ካላቸው እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ወርቅ ከሚመረትባቸው ክልሎች መካከል የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይጠቀሳል። ክልሉ ወርቅ በተለይ በባህላዊ መንገድ በስፋት ይመረትበታል። በወርቅ ልማት በአብዛኛው የተሰማሩት አነስተኛ አምራቾች ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በወርቅ ልማት ሥራ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች በልማቱ መሳተፍ ጀምረዋል።

ክልሉ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ በብዛት በማስገባት ይታወቅ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በሚፈለገው መጠን እየተመረተ አይደለም። ለዚህም ህገወጥ የወርቅ ማምረትና ግብይት ተግባር አንዱ ምክንያት በመሆን ይጠቀሳል። በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ አለመግባታቸውና ወርቅን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በቴክኖሎጂ ታግዞ ማምረት አለመቻልም ሌሎች በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀመድ እንደሚገልጹት፤ ወርቅ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ማዕድን ነው። በክልሉ ወርቅ በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ የሚመረት ሲሆን፣ አብዛኛው በባህላዊ መንገድ መመረቱ የወርቅ ምርትን መጠን እንዳይጨምር አድርጎት ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የወርቅ ማዕድን ለሕገወጥ ተግባር የተጋለጠ ሲሆን፣ ክልሉ በመሆን ይህን በወርቅ ማምረትና ግብይት ስራ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የኮንትሮባንድ ተግባር ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

የቢሮ ኃላፊው በ2016 በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት 525 ኪሎግራም ወርቅ ለማምረት ታቅዶ፤ 104 ኪሎ ግራም ወርቅ መመረቱን ይናገራሉ። አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእዚህም ዋናው ምክንያት ኩባንያዎች በሚፈለገው ደረጃ ወደ ሥራ አለመግባታቸው መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል። ኩባንያዎች በዚህ ክረምት ወቅት እምብዛም የስራ እንቅስቃሴ እንዳላደረጉ ይገልጻሉ። ሌላው አብዛኛው ወርቅ በባህላዊ መንገድ በአነስተኛ አምራቾች የሚመረት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የሚመረተውን የወርቅ መጠን አነሰተኛ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ነው የተናገሩት። በቀጣይም ሁሉም አምራቾች ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሆነም አመላክተዋል።

የባለፈው ዓመት የወርቅ ምርት ግኝት አፈጻጸምም እንዲሁ ዝቅተኛ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል። በባለፈው ዓመት 3ሺ ኪሎግራም ለማምረት ታቅዶ፤ 478 ኪሎ ግራም ወርቅ ብቻ ማምረቱን ገልጸዋል። አፈጻጸሙም ከ20 በመቶ በታችና በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት ። ይህም የወርቅ ጉዳይ ምን ያህል ፈታኝ ሁኔታ እንደገጠመው ማሳያ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፤ በተለይ ከዶላር መጥፋት ጋር ተያይዞ ሕገወጦች በወርቅ ላይ በመረባረብ ዋጋው ከፍና ዝቅ እንዲልና ምርቱም ከገበያ ውጪ እንዲሆን ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ዓምና የገጠመው ችግር ዘንድሮ እንዳይደገም የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል የሚሉት ኃላፊው፤ አምራቾች ይነስም ይበዛም ለባንክ እንዲያስገቡ የሚያደርግ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህም በዘንድሮው አፈጻጸም ላይ ችግር ይገጠመናል የሚል ስጋት እንዳይኖር የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። አምራቾች ያመረቱትን ወርቅ ወደ ባንክ የማያስገቡ ከሆነ ፈቃዳቸውን እስከመሰረዝ ድረስ የሚደርስ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ነው ሃላፊው የገለጹት። አምራቾቹ እርምጃ ተወሰዶባቸው ፈቃዳቸው ከተሰረዘ በብዙ መልኩ ኪሳራ ውስጥ እንደሚገቡ ሃላፊው ጠቅሰው፣ ያመረቱትን ወርቅ ወደ ባንክ የማስገባት ግዴታቸውን እንደሚወጡ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ወርቅ ለማምረት በአነስተኛ አምራችነት ተደራጅተው ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ የገቡት 373 አምራቾች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ በሥራ ሆነው ምርቱን ለባንክ እያቀረቡ ያሉት 100 ያህሉ ብቻ ናቸው። የተቀሩት ወደ ሥራ የገቡ ቢሆንም፣ አምርተው ለባንክ ለማቅረብ የበቁ አይደሉም፤ የሚቀራቸው ሥራ አለ ይላሉ።

በኩባንያ ደረጃ ወርቅ ለማምረት ፈቃድ የወሰዱት ሁለት ኩባንያዎች መሆናቸውን አቶ ካሚል ጠቅሰው፣ አንዱ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ ተገኝቶ ከሥራ ውጭ እንዲሆን ከተደረገ ከስድስት ወራት በላይ አስቆጥሯል ብለዋል።

ኩባንያው ሕጋዊ በሆነ መልኩ ማንኛውንም ባለሙያ /የውጭ ሀገር ዜጋም ቢሆን/ ቀጥሮ ማስራት ሕጉ እንደሚፈቅድለት ጠቅሰው፤ ይህ ኩባንያ ግን በሕገ ወጥ መንገድ የውጭ ሀገር ዜጎች ቀጥሮ ሲያሰራ በመገኘቱና እነዚህ የውጭ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወርቅ ሲያዘዋዋሩ በመያዛቸው ምክንያት እርምጃው እንደተወሰደበት ተናግረዋል። በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በክልሉ ወርቅ በሕገወጥ ፣መንገድ ሲዘዋወሩ በተገኙ ከሰላሳ በላይ በሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ እርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቀዋል።

የውጭ ሀገር ዜጎች ቀጥረው እንዲያሰሩ ከማዕድን ሚኒስቴር የሚፈቀድላቸው ልዩ አነስተኛ አምራቾች መኖራቸውን የሚጠቅሱት ኃላፊው፤ በሕገወጥ መንገድ ወደ ክልሉ የሚገቡት የውጭ ሀገር ዜጎች በሚፈቅድላቸው አካላት ሽፋን ሾልከው መግባታቸውን በተደረገው ማጣራት ማረጋገጣቸው አመላክተዋል።

ባለፈው ዓመት እንደ ችግር ከታዩት አንዱ የወርቅ ምርት መጠን አነስተኛ መሆን አንዱ እንደሆነ የጠቅሱት ኃላፊው፤ ዘንድሮ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው የወርቅ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ላይ መሆኑን አመላክተዋል። ‹‹እስካሁን ወርቅ እየተመረተ ያለው ድሮ ቅድመ አያቶቻችንና አያቶቻችን በሚያመርቱበት ባህላዊ መንገድ ነው።›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ወቅቱ የደረሰበትን የተሻለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የበለጠ ወርቅ ማምረት እንደሚቻል አስታውቀዋል።

‹‹እስካሁን በባህላዊ ዘዴ የሰው ኃይል በመጠቀም አምራቾቹ በራሳቸው ጥረት የሚመርቱትን ወርቅ ነው ለብሄራዊ ባንክ እንዲገባ ለማድረግ የምንቆጣጠረው›› ያሉት ኃላፊው፤ በዚህ መንገድ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አኳያ እድሉ ውስን መሆኑንም ገልጸዋል። ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ የማድረግ እና ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች የመውሰድ ውስንነቶች እንዳሉ አመላክተዋል።

ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር አንጻር ቴክኖሎጂ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ባለመሆኑ አሁን ላይ በሚፈለገው ልክ ምርት እየተገኘ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ። ‹‹ በህገወጥ ወርቅ ማምረትና ግብይት ላይ ተሰማርተው በቁጥጥር ሥር የዋሉ የውጭ ሀገር ዜጎች ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በአንድ ጊዜ ብቻ ያመረቱት የወርቅ ምርት መጠን እኛ ከምናመርተው ጋር ሲነጻጸር በጣም ሰፊ ልዩነት ያለውና አይተነው የማናወቀው አይነት ምርት ነው››ሲሉ የቴክኖሎጂን አስፈላጊትነት አመልክተዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ወርቅ በሰው ኃይል ብቻ ተፈልጎ የሚገኝ አይደለም ፤ በቴክኖሎጂ መታገዝን የግድ ይለዋል። ወርቁ የት ቦታ እንደሚገኝ የሚጠቁም ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል። ወርቅንና ሌሎች ነገሮች የሚለይ ኬሚካልም ያስፈልጋል።

አሁን ጥቅም ላይ የዋለው ወርቅን ከሌሎች ነገር ለመለየት የሚያስችለው ኬሚካል እንኳን በጥናት በተረጋገጠው መሠረት 30 በመቶ ያህሉን ብቻ የሚያጣራ ነው። 70 በመቶ የሚሆነው ወርቅ አፈር ውስጥ የሚቀር መሆኑን ኃላፊው መረጃዎች ዋቢ አርገው አመልክተዋል። ይህም ወርቅ የወጣበትን ተረፈ ምርት መልሶ የማጠብ አሰልቺ ሥራ እንዲሰራ እያደረገ ነው። ይህንን የሚያሻሸሉት ደግሞ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው።

በባለፈው ዓመት በጥቁር ገበያ ላይ የወርቅ ዋጋ ከፍተኛ የሆነበት አንዱ ምክንያት ወርቅ የመግዛት አካሄድ የሚከተሉ ሕገወጦች መበራከታቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ አስመጪና ላኪዎች እንደሚገኙበት አስታውቀዋል። ቀደም ሲል ብሔራዊ ባንክ 35 በመቶ ጭማሪ አድርጎ ወርቅ ይገዛ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰው፤ አሁን ላይ እስከ 60 በመቶ ጭማሪ አድርጎ እየገዛ መሆኑን አስታወቀዋል። ሆኖም ግን በጥቁር ገበያ የወርቅ ዋጋ ከዚህ በሚበልጥ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል። ዋጋው ከአንድ ሺብር በላይ ልዩነት እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህም ሕገወጥነቱ እንዲስፋፋ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ክልሉም የመቆጣጠር ሥራዎቹ አጠናክሮ በመቀጠል በሕገወጥ ግብይት ላይ የተሰማሩ አካላትንም በማደን በቁጥጥር ሥራ እየዋለ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በመንግሥት በኩል በአሠራር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች እንደሚፈቱ ጠቁመው፤ የቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ በማስቀጠል በሕገወጥ ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው አረጋግጠዋል።

ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተጠናከረ ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል። ይህን ተከትሎም አሁን ላይ መሻሻሎች እየታዩ ናቸው፤ እስከ ማምረቻ ቦታዎች ድረስ በመሄድ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመስራት ሰዎች ወርቅ እንዳያሻሹ ለባንክ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ሰዎች በሕገወጥ መልኩ ወርቅ ይዘው ቢገኙ ወይም ወርቅን ከባንክ ውጪ በሌላ በማንኛውም ሕገወጥ መንገድ ሲገዛም ሆነ ሲሸጥ የተገኘ የሚወሰድበትን እርምጃ ማስገንዘብ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፤ ይህን ሁሉ ተከትሎም ለውጦች መሻሻሎች ታይተዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ በወርቅ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮች በአብዛኛው በአሠራር የሚፈቱ ናቸው ። አሁን ላይ ለወርቅ ምርቱ ትልቁ ተግዳሮት የሆነው የአመራራት ስራው በቴክኖሎጂ በመታገዝ በኩል ያለበት እጥረት ነው ። በቴክኖሎጂ አለመታገዝ በወርቅ ማምረት ስራ ላይ ከፍተኛ የምርት ብክነት እንዲኖር አድርጓል። ያለው የወርቅ ክምችትና የሚመረተው መጠን እኩል አይደለም። ከሦስት ጊዜ በላይ የተመረተው አካባቢ ላይ እንደገና መፈለግ ሥራ ይሰራል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ በቴክኖሎጂ እጦት ምርቱ ለብክነት መዳረጉን ነው ። ከተገኘው ወርቅ 30 በመቶ ብቻ የሚሰበሰብ ፤ሲሆን 70 በመቶ በአፈር ውስጥ የሚቀር ስለመሆኑ ምርቱ ለብክነት ለመዳረጉ ማሳያ ነው።

ሌላኛው ተግዳሮት ለወርቅ ማምረት ሂደት ጥቅም ላይ የሚውለው ኬሚካል እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ይህ ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉ በተለይ ለቀጣዩ ትውልድ ትቶት የሚያልፈው ጠባሳ ቀላል የሚባል አይደለም፤ አካባቢን ከመበከል ባለፈም ስለኬሚካል ያለው እውቀት እምብዛም ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ቀላል አለመሆኑን ይናገራሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ወርቅን ከሌላ ባእድ ነገር ለመለየት ከኬሚካል ውጪ ሌላ ምንም አይነት አማራጭ ስለሌለ ኬሚካል መጠቀም የግድ ነው። በክልሉ ሁለት አይነት ወርቅ የሚመረት ሲሆን፣ አንደኛው ጠጠር ተፈጭቶ የሚመረት ወርቅ ነው። በተለይ ጠጠር ተፈጭቶ የሚመረተውን ወርቅ ከሌሎች ባእድ ነገሮች ለመለየት ኬሚካል የግድ አይቻልም። ይህ ሲሆን ግን የሚያደርሱት ጉዳት ዝቅተኛ የሆነ ኬሚካሎችን መጠቀም ይመከራል።

አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ግን ሌላ አማራጭ ባለመገኘቱና የጎንዮሽ ጉዳት እንደሚስከትል እየታወቀ መሆኑን ተናግረዋል። አምራቾቹ ኬሚካሉን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። የእጅ ጓንት፣ ማስክና የመሳሰሉትን በማድረግ በጥንቃቄ እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተጠቀሙባቸውን ቁሳቁስ ጉድጓድ ተዘጋጅቶ እንዲቀበሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው የወርቅ አይነት ‹‹ደብል›› ወርቅ የሚባለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ማእድን ማጠቢያ ማሽን ውስጥ ብቻ አስገብቶ በማጠብ ብቻ ወርቁ እንደሚመረት ጠቁመዋል። የዚህ ወርቅ አመራረት ከኬሚካል ጋር እንደማይገናኝ ገልጸዋል። ይህ አይነቱ ወርቅ በብዛት እንደማይገኝ አመልክተው፣ በክልሉ በአብዛኛው የሚመረተው ጠጠር ተፈጭቶ የሚመረተው ወርቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ኃላፊው በማእድን ልማት በሀገር ደረጃ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለ አንድ ኩባንያ በክልሉ ወርቅን ለማምረት መሰማራቱንም ጠቁመዋል። ‹‹ኩምሩክ ማይኒንግ›› የተሰኘው ኩባንያ በክልሉ ወርቅ ለማምረት በ2014 ፈቃድ መውሰዱን ጠቅሰው፣ ኩባንያው በተያዘው ዓመት ሥራ እንደሚጀመርም አስታውቀዋል። ኩባንያው የክልሉን የወርቅ ምርት በመጨመር ረገድ ተስፋ እንደተጣለበትም ገልጸዋል።

በቅርቡ የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በ2016 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፍ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መታቀዱን መግለጻቸው ይታወሳል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ‹‹አላይድ ጎልድ ማይንኒን›› የተሰኘ የአውስትራሊያ የወርቅ አምራች ኩባንያ አካል የሆነው ‹‹ኩምሩክ ማይኒንግ›› ኩባንያ ወርቅ ለማምረት እያከናወነ ያለውን ተግባር በማሳያነት ጠቅሰዋል። ኩባንያው የወርቅ ማዕድን ፍለጋውን መጨረሱን ጠቅሰው፣ ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ “በኢትዮጵያ ትልቁ የወርቅ ኩባንያ” ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን ማምረቻ እየገነባ እንደሆነም መግለጻቸው ይታወሳል።

ወርቅነሽ ደምሰው

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2016

Recommended For You