ከቀይ ባህር በጭልፋ

ዛሬ ሦስቱም ጓደኛሞች በኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተዋል። በስፍራው የመገኘታቸው ምስጢር የጓደኛቸው የሮማን የቅርብ ዘመድ የውጭ ሀገር ትምህርቱን አጠናቅቆ የሚመለስበት ዕለት በመሆኑ ሊቀበሉት በማሰባቸው ነው።

እንደአጋጣሚ በአየር መንገዱ ቀድመው የደረሱት ዘነበች ደስታ እና ሮማን ባልቻ ናቸው። የእንግዳ ማረፊያ ወንበር ላይ አረፍ ብለው የሆድ የሆዳቸውን ማውጋት ጀመሩ። መቼም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስመ ጥር እንደመሆኑ ጉዟቸውን በእሱ ያደረጉ ደንበኞች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው፤ ይወጣሉ፤ ይገባሉ። እነሮማንም ከወጋቸው ጎን ለጎን ይህንኑ ሲያስተውሉ ቆዩ። በአየር መንገዱ የሚታየው ወጪ ወራጁ ሲታይ፤ በምድር ላይ ያለ የሰው ዓይነት የቀረ አይመስልም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ዘነበችና ሮማን ወጋቸውን እያወጉና አላፊ አግዳሚውንም እየተመለከቱ በመሆኑ በአየር መንገዱ ቅጥር ግቢ ከአንድ ሰዓት በላይ መቆየታቸውን ልብ አላሉትም ነበር። በዚህ መሃል ጓደኛቸው አበባየሁ ታደሰ ስትቀላቀላቸው፤ ዘነበች ጉንጯን ከጉንጯ ጋር በማነካካት ‹‹እመት አይሞላልሽ! ደርሻለሁ፤ በር አካባቢ ነኝ ስትዪ የነበረው ከቤት ከመውጣሽ በፊት ነበር ለካ!›› በማለት የተናደደችባት ለመምሰል ሞከረች።

አበባየሁ፣ ‹‹እንግዲህ ራይድ ይዤ አልመጣ ነገር የኑሮ ውድነቱ እንደሁ ጣራ ደርሷል ጓደኛዬ…›› እያለች ሮማንንም በተመሳሳይ መልኩ ሠላም ካለች በኋላ እየተቀመጠች። ‹‹ቆይ! ይህ ያማረረሽ የኑሮ ውድነት ድራሹ ይጠፋልሻል ጠብቂ። ወደቡ ብቻ በእጃችን ይግባ!›› ስትል ሮማን ለመቀለድ ሞከረች።

‹‹ወይ ጉድ! ቀይ ባህርን ከመናፈቃችን በፊት እስኪ መጀመሪያ የተወደደው ቀይ ሽንኩርት ይርከስልን። ቀይ ሽንኩርት በቀላሉ ተንጠራርተው የማያወርዱት የቆጥ ላይ ዕቃ ሆኖብን ስለቀይ ባህር ታወሪያለሽ እንዴ!?…›› እያለች አበባየሁ ልትቀጥል ስትል ዘነበች አቋረጠቻት።

‹‹አበብዬ፣ በየፌስቡኩ የምታገኛቸውን ማወናበጃ ወሬዎችን መቀራረምና አጣጥመሽ መዋጥ የጀመርሽው ደግሞ ከመቼ ጀምሮ ነው?›› ብላት ፊቷን አኮሳትራ አየቻት። ‹‹ደግሞ እኮ ቀይ ሽንኩርቱም ቢሆን የአንድ ኪሎ ዋጋ ወደ ሦስት አኃዝ አድርሶ የነበረ ቢሆንም ወደ ሁለት አሀዝ የቀነሰው ወዲያውኑ ነው።

እኔ እንዲያው ግርም የሚለኝ! ጥቂት የማይባል ሰው ልክ ስለባህር በር ማውራትም ሆነ ወደብን መመኘትን እንደ ኃጢአት ሁሉ ለመቁጠር ሲዳዳው ማየቴ ነው። ግን ችግሩ ምንድን ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስኪ እንነጋገር ያሉት ባለፈው ሳምንት ነው አይደል!? እንዴ! እርሳቸው እኮ ‹በወደብ ጉዳይ እንነጋገር፤ እስኪ በባህር በር ጉዳይም እናውራ፤ ስለቀይ ባህርም አውሩ› አሉ እንጂ፤ ‹በቀጣናው ያሉ ሀገሮች ወደብ ካልሰጡን ዘራፍ! አካኪ ዘራፍ! እንላለን› አላሉም! አንዳንዴ ሰው ከድህነት ጋር እንዲህ የቀረበ ወዳጅነትን መስርቷል ማለት ነው? ራስን ለማሻሻል ሕዝብን ማነሳሳት ለጦርነት ተጋብዘሃልና ሆ ብለህ ውጣ ማለት ነው? ዜጋውም ሂድና ተዋጋ አልተባለ፤ ከተፈጥሮ ሀብቱ አካባቢ ያሉ ሀገራትም ቢሆኑ ዛሬውኑ ካልሰጣችሁን ‹እንወጋችኋለን› ያላቸው የለ!…እንዲያው ከቀዩ ባህር በጭልፋ አልን እንጂ…

የምር ግን የባህር በር ያላቸው ሀገራት ምን ነክቷቸው ነው? ገና ለገና ‹ኡ!…ኡ!…› ያሉት? ከሰሞኑ ሲሰነዘሩ የነበሩ መግለጫ መሰል መልዕክቶችን ልብ ብላችኋል ጓደኞቼ…? ‹ይኸኛውን ነገሬን ለድርድር አላቀርብም፤ በዚህኛውም ነገሬ ላይ ከማንም ጋር አልወያይም› ማለታቸው የጤና ነው? ምነውሳ ቀጣናዊ መደጋገፉ ወዴት ሔደ?›› አለች ሁሉ ነገር ምርር ያላት በመምስል።

የልቧን ስትናገር የነበረችውን ዘነበችን ከልቧ ስታዳምጣት የቆየችው ሮማን ‹‹ምን እሱ ብቻ! ኢትዮጵያ እኮ የተናገረችው አንዴ ነው። ነገር ግን ‹ምን ውሃ ውሃ ትላለች…፤ ውሃ ማለት በዛሳ…› እያሉ ከወዲሁ የውሃ ስም ስለተጠራ ብቻ ሠላም እያጡ ያሉ እኮ አሉ። ኧረ እንዲያውም ከወዲሁ ስልችት ያላቸው የቀጣናው ሀገራትም አልታጡም። አንድ መድረክ ላይ ሲወጣ ቀጣናዊ ትብብር፣ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ይባልልኛል ደግሞ …ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የተባለው እኮ የግድ ሁለት ሀገራት አሊያም አንድ ሀገር እርስ በእርሱ ግጭት ሲገባ ብቻ ያለው ማን ነው? የቀጣናው ሀገራት በአካባቢው ለሚገኙ ሀገራት ትብብር ማድረግ ወሳኝ ነው። አፍሪካዊ መፍትሔ ለዚህ ለዚህ ጉዳይም መሥራት አለበት። አፍሪካዊ መፍትሔ የሚባለው ሀገር ከሀገር ጋር ሲጣላ ጠብቆ ማስታረቅን ብቻ ነው ያለው ማን ነው?

ደግሞ እኮ…እኛ ዓባይን የሚያክል ስሙን ለመጥራት እንኳን የገዘፈ ወንዝ በእጃችን ሆኖ ሳለ በጋራ እንጠቀምበት፤ እኛም እናንተም መልማት እንችላለን ብለን በጋራ እየለማን ነው። ሁሉ በደጃችን ሆኖ አካኪ ዘራፍ! አላልንም። የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያ ያላት ዕድል በእጃቸው ሆኖ ቢሆን አስባችሁታል ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ? አስራ ምናምን ዓመት የዓባይን ጉዳይ ወዲያ ሲወስዱትና ወዲህ ሲያመጡት ከርመዋል። ኢትዮጵያ ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ምላሿ አብረን እንለማለን ነበር፤ ይኸው በትዕግስት ዛሬ ላይ በመድረሳችን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለእነርሱም የሚሆን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ቻልን። የተፈጥሮ ሀብቱ እንደሁ ለሁሉ የሚበቃ ነው። ዋና ትብብርና አብሮ ማደግን መቀበል ነው። እንዲያ ከሆነ አንዱ ለሌላው መድህን መሆን ይችላል።

መቼም ኢትዮጵያም እኮ ወደብ፣ የባህር በር ማለቷ ገፊ ምክንያት ስላላት ነው። ያው እንግዲህ መታደልም በሉት ሌላ የሕዝብ ቁጥራችን የትየለሌ ነው። አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ይዘሽ ወደብ አልባ መሆን አይከብድም…? ስለዚህ ሁኔታዎች ሲያስገድዱሽ በዙሪያሽ ያለውን አማራጭ ማየትሽ ጦር መዘዝሽ ወይም ጉልበት ተጠቀምሽ ማለት አይደለም።

ወይ ጊዜና ዘመን? የዛሬውን አያድርገውና እኛም የወደብ ባለቤት ነበርን እኮ! በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት አሉ እማማ ትርፌ፤ 30 ዓመት ሙሉ ትንፍስ ሳንል በእኛው ጥፋት ወደባችን እብስ ሲል ዝም ጭጭ አለን፤ ወደብም እንደ ተራ ዕቃ ‹ሸቀጥ ነው› ተብለን አረፍነው። ይሁና! ግን ደግሞ አሁን አስፈለገን። ችግር ገፍቶ ሲመጣ ያለውን ተጋርቶ መቃመስ ደግሞ የውዴታ ግዴታ አይመስላችሁም ውዶቼ?›› አለቻቸው።

በዚህ በባህር በር እና በወደብ ጉዳይ ላይ እምብዛም ተስፋዋን ያልጣለች የመሰለችው አበባየሁ፣ ‹‹አንቺ ደግሞ ምን ነክቶሽ ነው? የውዴታ ግዴታ ምናምን የምትዪው?›› ስትል ለወጉ ያህል ተናገረች። ‹‹እኔ ቅጥል የሚያደርገኝ በቀይ ባህር ቀጣና ባይተዋር የመደረጋችን ሁኔታ ነው። የቀይ ባህር ፎረም ኢትዮጵያ ያገለለበት ምክንያት በፍጹም ሊያሳምነኝ አልቻለም። በፎረሙ አለመካተታችንን ሳስተውል ደግሞ የሆነ አንዳች እየተዶለተብን ያህል ሰሞኑን ይሰማኝ ጀምሯል።›› አለችና ‹‹ኤዲያ! ለነገሩ ቢቀርስ? ላም አለኝ በሰማይ ዓይነት ነገር ነው…መቼ ሊሆን ነው? አሁኑኑ ቢባል የሚመጣው ነገር ይታያችኋል?…›› ብላ ልትቀጥል ስትል ዘነበች አስጣለቻት።

‹‹አንቺ ልጅ ዛሬ ተወዛግበሻል፤ አንዴ ቀይ ሽንኩርትን ከቀይ ባህር ጋር … አንዴ ደግሞ ተስፋ መቁረጥ ምናምን እየተስተዋለብሽ ነው። ሞኝሽን ፈልጊ እኛ እንኳ ተስፋ አንቆርጥም። በእርግጥ እንዳልሽው ፎረሙ ውስጥ አለመግባታችን የሚያሳጣን ነገር መኖሩ የአደባባይ ምስጢር ነው። አለመካተታችንም ምን ዓይነት የደህንነት ስጋት ሊያመጣብን እንደሚችል አናውቅም። ይህ ግን በባለሙያዎች የሚመለስ ጉዳይ ነው።

እኔ እምላችሁ…እነርሱም እኮ ኢትዮጵያ በፎረሙ ውስጥ ባለመግባቷ የሚያጡት ነገር አለ። ኢትዮጵያ በቀጣናው አለሁ አለሁ የሚለውን ሽብርተኝነትን ከመከላከልና ከማክሰም አንጻር አቻ አይገኝላትም። እንዴ ሠላም በማስከበር ደግሞ እንደ ሀገሬ ማን አለ? በየትኛውም ጥግ ቢኬድ ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያዊነት ደምቆ የሚታይ ነው። ከዚህ አኳያ ሲታይ የቀይ ባህር ፎረም ኢትዮጵያን የሚያህል ኃይል ማጣቱን አስባችሁታል ጓደኞቼ? እነርሱ የቀይ ባህር ፎርም እንዳንገባ ያድርጉን እንጂ፤ እኛ ባለመግባታችን የሚያጡት ነገር መኖሩ እርግጥ ነው። ዝም ብዬ ሳስብ ደግሞ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ያልከፈለችው መስዋዕትነት የለም እኮ!

እኔ ግን… የሚያሳስበኝ ነገር ምን እንደሆነ ልንገራችሁ? ስትል አበባየሁ ተሸቀዳድማ ‹‹ባትነግሪንም እናውቀዋለን ባክሽ፤ የውስጥ ችግራችንን ባህር ውስጥ በመክተት የሚሰጥም ባለመሆኑ አርፈን የውስጡን ችግር እንፍታ፣ ካልሆነ የሚፈጠረው የሚያሳስብ…›› እያለች ልትቀጥል ስትል፣ ልክ እንደ አበባየሁ ሁሉ፤ ዘነበችም አበባየሁን ሳታስጨርሳት፤ ‹‹ወዴት ወዴት! ጨርሶ ያላሰብኩትን? እኔ ለማለት የፈለግኩት በአካባቢው ላይ ያሉ ወደቦች የወታደራዊ የጦር ኃይል ቀጣና እየሆኑ በመምጣታቸው ከእነዚህ ለምድር ለሰማይ ከከበዱ ሀገራት ጋር የምንፋጠጠው እንዴት ነው? ለማለት ነው።

ሰዓቱ እየገፋ በመምጣቱ ሮማን፣ ቀልቧ አንዴ ወደጭውውቱ አንዴ ደግሞ ወደወጪ ወራጁ እያለ የነበረ ቢሆንም፤ ‹‹ባክሽ ከባድ የሚባል ነገር የለም፤ የባህር በር ይኑረን፤ ያውም ያለንን ጥሩ ነገር ሰጥተን አልን እንጂ ከእነርሱ ጋር እንግጠም አላልንም።›› አለችና ‹‹…ድንገት የሆነ ነገር ትዝ አላት፤ በእርሷ አተያይ ትዝ ያላት ራሱ ተጋጣሚው አካል ነው። ድምጿን ከፍ አድርጋ…‹‹እናንተ!!!… ›› ስትል ዘነበችም አበባየሁም ዘመዷ የደረሰ መስሏቸው አሻግረው የሚመጣውን ሁሉ መረመሩ። እርሷ ግን ማለት የፈለገችው ሌላ ሆኖ በጠያቂ ዓይን ደጋግመው ተመለከቷት። ‹‹እንዴ የምታፈጡብኝ…ምን ሆናችሁ ነው? ማለት የፈለግኩት እኮ ዛሬ የሠራዊት ቀን ነው ልላችሁ ነው።›› አለቻቸው።

ሦስቱም ለመከላከያ ሠራዊት ላቅ ያለ አክብሮት እንዳላቸው ከገጻቸው ያስታውቅ ነበር። ‹‹መከላከያችንማ የሀገር ኩራት ነው፤›› ስትል ዘነበች፣ አበባየሁ ቀበል አድርጋ፤ ‹‹በእርሱማ ድርድር የለም!›› አለች። የሚያስገርመው ነገር ሦስቱም በሀገር ጉዳይ ቀልድ አያውቁም። በብዙ ነገር ሊጨቃጨቁና ሊከራከሩ ይችላሉ፤ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ግን መግባባት ላይ ይደርሳሉ። በዚህ መሃል ተጠባቂው የሮማን ዘመድ በመድረሱ ስለውጭውም ስለሀገር ቤቱም እያወጉ ወደ ሮማን ቤት አቀኑ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You