በማዕድን፣ በውሃ፣ በመሬት ሀብቶች ባለጸጋነቱ የሚታወቀው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ በግብርና፣ በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፎች ለሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት እምቅ አቅም ያለው አካባቢ ነው። የክልሉ ሕዝብ ዋና የኢኮኖሚ መሠረት ግብርና ሲሆን ከ92 በመቶ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል የተሠማራው በዚሁ ዘርፍ ላይ ነው። የክልሉ ጠረፋማ ወረዳዎች ከግብርናው በተጓዳኝ በባህላዊ መንገድ የወርቅ ቁፋሮ ሥራ ያከናውናሉ።
ግብርና ዘርፍ በዓመታዊ ሰብሎች፣ በቅባት እህሎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡናና በቅመማ ቅመም፣ በእንስሳት እርባታና ዓሳ ልማት እንዲሁም በንብ ማነብ ዘርፎች ከፍተኛ አቅም አለው። በማምረቻው ዘርፍ ደግሞ በግብርና ማቀነባበር እንዲሁም በወረቀትና የወረቀት ውጤቶች ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ክልሉ ምቹ ነው።
ክልሉ በወርቅ ሀብታቸው ከሚታወቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ ሲሆን፣ ከወርቅ በተጨማሪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚን በብርቱ የሚደግፉ እና ለሀገር ውስጥ ምርት የሚውሉ የሌሎች ማዕድናት መገኛም ነው። የግራናይት፣ ቶርማላይን፣ ግራፋይት፣ የድንጋይ ከሰል፣ መዳብ፣ ብረት፣ እምነበረድ፣ ጥቁር ድንጋይ፣ ኖራ፣ ጅብሰም፣ ጠጠርና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ክምችት አለው። ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግዙፉ የዓባይ ግድብ መገኛ መሆኑ፣ ክልሉ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆን ተጨማሪ አቅም ይፈጥርለታል።
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለማልማት የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም ክልሉ ካለው ሰፊ ሀብት አንፃር ጥረቶቹ ያስገኙት ውጤት በቂ ባለመሆኑ፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ለክልሉ ምጣኔ ሀብት እድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማድረግ ታቅዷል። የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም እድል የሚፈጥር በመሆኑ ለዘርፉ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። በግብርናና በሌሎችም ኢንቨስትመንቶች የተሰማሩ ባለሃብቶች በገቡት ውል መሠረት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ብርቱ ክትትል እንዲደረግና የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ያላለሙ ባለሀብቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሬት እንዲነጠቁ አቅጣጫ ተቀምጧል። መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን የማድረግ ሀገራዊ ጥረትን ለማገዝ በአሶሳ ከተማ ለኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የሚውል 300 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል።
በክልሉ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የክልሉን ሕዝብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ። የክልሉ ኅብረተሰብ ከኢንቨስትመንት ሥራዎች በሥራ እድል ፈጠራ፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ ዕድል ተጠቃሚ እየሆነ ነው። የሥራ ዕድል ፈጠራው ለኅብረተሰቡ የገቢ ምንጭ በመሆን ኑሮውን እንዲያሻሽል አስችሎታል። የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ደግሞ የአካባቢው ኅብረተሰብ የምርትና የግብይት ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲያከናውንና የተሻሉ ውጤቶችን እንዲያገኝ እያገዘው ነው። ከሥራ እድል ፈጠራና ከቴክኖሎጂ ሽግግር ባሻገር በኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች በማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ላይ በመሳተፍ ኅብረተሰቡ የመንገድ፣ የጤና፣ የትምህርትና የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው ሹሞ እንደሚገልፁት፣ ቢሮው የሀብት አማራጮችን በማጥናትና በማስተዋወቅ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ እንዲገቡ እና ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን በኢንቨስትመንት ላይ እንዲያውሉ በማድረግ የክልሉን የገቢ አቅም ለማሳደግ፣ ለኅብረተሰቡ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማስፋፋትና ለማስተላለፍ እንዲሁም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
በክልሉ በ2015 የበጀት ዓመት በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በግብርና ማቀነባበር (Agro-Processing) እና በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ልማት ዘርፎች የተሰማሩ 82 አነስተኛ እና 12 መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች አሉ። ከእነዚህ በተጨማሪም አራት ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በግብርና ማቀነባበር፣ በጥጥ መዳመጥ እና በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ልማት ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ከ252 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው።
እንደ አቶ ጋሻው ማብራሪያ፣ በክልሉ በ2016 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 134 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል። ፈቃድ ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል 107 በግብርና፣ 15 በአገልግሎት (ትምህርት፣ ጤና፣ ነዳጅ ማደያ፣ የገበያ ማዕከላት…)፣ ሰባት በማምረቻ እና አምስት በኮንስትራክሽን ዘርፎች የሚሰማሩ ሲሆን፤ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ ለ15 ሺ 518 ዜጎች (2568 ቋሚ እና 12 ሺ 950 ጊዜያዊ ) የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሥራ እድል ፈጠራ ረገድ፣ 42 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም 165 ቋሚ የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ 49 ነባር አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከር ደግሞ ለ64 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
በሩብ ዓመቱ ካጋጠሙ የዘርፉ ችግሮች መካከል ለከተማና ለገጠር ኢንቨስትመንት የሚውሉ መሬቶች በወቅቱ ተዘጋጀተው አለመገኘት፣ ለባለሃብቶች አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በተሟላ መልኩ በወቅቱ አለማድረግ እና ለኢንዱስትሪ ዞኖች አገልግሎት የሚውል መሬት ተለይቶና ተከልሎ አለመቀመጥ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ አቶ ጋሻው ይገልፃሉ። ችግሮቹን ለመፍታትም ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ እየተሰራ ነው።
አቶ ጋሻው በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደሩ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ይገልፃሉ። ከእነዚህም መካከል የዘርፉ መዋቅር በሰው ኃይል አለመሟላቱ፣ የኢንዱስትሪ ክላስተር ቦታ በህጋዊ ካርታና ይዞታ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለመሰጠትና መጓተት፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ማነስና በሚፈለገው ልክ አለመሰጠት፣ ለዘርፉ ልማት የሚመጥን በቂ በጀት አለመመደብ፣ የክትትልና ድጋፍ ማነስ እንዲሁም ስለዘርፉ አጠቃላይ ሁኔታ ከፌዴራል መንግሥት ባለድርሻ አካላት ለክልሉ አስፈፃሚ አካላት የግንዛቤ ስልጠናዎች አለመሰጠት ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም ‹‹የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረቻ ቦታ ችግር ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት ለኢንዱስትሪዎቹ በቂ መሬት በማቅረብ ረገድ የሚፈለገውን ውጤት አላስገኙም። ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የግብዓትና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት (ኢግልድ) ጋር ውይይቶችን ብናደርግም እስካሁን ድረስ ግብዓት አልቀረበም። የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ሥራ በፌዴራል መንግሥት በኩል እንደሚሰራ ይታወቃል። ሆኖም ግን ከቦታ ርክብከብ ውጭ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አልተደረገም። የክትትልና ድጋፍ ሥራው አነስተኛ በመሆኑ የዘርፉ እድገትና አፈፃፀም ክልሉ በዘርፉ ካለው አቅም አንፃር ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው›› ይላሉ።
ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚታወቅባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል አንዱ የእርሻ ኢንቨስትመንት ነው። ለእርሻ ተግባር ምቹ የሆነው ሰፊው የክልሉ መሬት፣ ለዘርፉ ልማት አስቻይ ሁኔታዎችን የሚፈጥር የሀገር ሀብት ነው። በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ለምርት አቅርቦት፣ ለሥራ እድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ሚና አላቸው። ለሀገር የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ያላቸው አበርክቶም ቀላል አይደለም። የእርሻ ኢንቨስትመንት ለግብርናው ዘርፍ እድገትና ለመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑና ክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ አቅም ስላለው ለእርሻ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት ይሰጣል።
የክልሉ የመሬት እና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ ስለክልሉ የእርሻ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ቀደም ሲል ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፣ ለእርሻ ምቹ የሆነ ሰፊ መሬት ያለው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በግብርና፣ በተለይም በእርሻ፣ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እምቅ አቅም ካላቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእርሻ ምቹ የሆነውን የክልሉን መሬት መጠን በጥናት የመለየቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም፣ ክልሉ ለእርሻ ኢንቨስትመንት የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ መሬት እንዳለው ገልጸው ነበር።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ 633 ባለሃብቶች ከክልሉ መንግሥት ጋር የኢንቨስትመንት ውል ፈፅመው በ448ሺ 289 ሄክታር መሬት ላይ የእርሻ ኢንቨስትመንት ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ አቅም ያለው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ለጥራጥሬና ለቅባት እህሎች እንዲሁም ለጥጥ ምርት ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተተገበረ በሚገኘው የስንዴ ልማት መርሃ ግብር የራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከትና ሀገራዊ ንቅናቄው ስኬታማ እንዲሆንም የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዚህም በቆላ ስንዴ ልማት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ይደረጋል፤ የመስኖ ልማት መከናወን በሚችልባቸው አካባቢዎች እንዲሰማሩና ልዩ ትኩረት እንዲያገኙም እየተደረገ ነው።
በሌላ በኩል የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፍ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በርካታ ፈተናዎችን ማስተናገዱ ይታወቃል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል የፀጥታ መደፍረስ፣ መሬት ወስዶ ወደ ሥራ አለመግባት እና መሬቶችን ከኢንቨስትመንት ይልቅ ለሌሎች ተግባራት ማዋል ይጠቀሳሉ። እነዚህ ችግሮች ክልሉም ሆነ ባለሃብቶች ባቀዱት ልክ ወደ ሥራ እንዳይገቡ እና ሥራቸውን እንዲያቋርጡ ጫና በማሳደር ዘርፉ በምርት አቅርቦት፣ በሥራ እድል ፈጠራም ሆነ በቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያስገኛቸው ጥቅሞች እንዲቀንሱ አድርገዋል። በአሁኑ ወቅት የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ የተሻለ በመሆኑ ባለሃብቶች ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችል እድል እንደፈጠረና አሁን የፀጥታ ችግር በክልሉ ለኢንቨስትመንት መሰናክል የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዳልሆነም አቶ ቢኒያም መግለፃቸው ይታወሳል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም