የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን(ሉሲዎቹ) ለፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ የማጣሪያ ጨዋታ ዛሬ ናይጄሪያን ይገጥማሉ። ሉሲዎቹ በደርሶ መልስ ጨዋታው ድምር ውጤት ማሸነፍ ከቻሉ ወደ ሶስተኛውና ወሳኙ የማጣሪያ ፍልሚያ የሚያልፉ ይሆናል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በማህበራዊ ድረ ገጹ አማካኝነት ይህን ጨዋታ በቀጥታ እንደሚያስተላልፍም አስታውቋል።
ወራት የቀሩት የ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ በእግር ኳስ ተሳታፊ የሚሆኑ ቡድኖች የሚለዩበት የማጣሪያ ጨዋታ በመከናወን ላይ ይገኛል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በውድድር መድረኩ የሚወክሉትን ቡድኖች ለመለየት ጨዋታዎችን እያካሄደ ይገኛል። ዛሬ ከሚካሄዱ ጨዋታዎች መካከልም አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴድየም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) እና ናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን (ጭልፊቶቹ) መካከል የሚካሄደው ጨዋታ ይጠበቃል። ሉሲዎቹ በመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የቻድ አቻቸውን በሰፊ የግብ ልዩነት በመርታት ወደ ሁለተኛ ዙር ማለፋቸው የሚታወስ ነው። ዛሬ ከቀኑ 9ከ30 ላይም ሉሲዎቹ በሜዳና በደጋፊያቸው ፊት ወሳኝ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።
በኦሊምፒኩ አፍሪካን ወክለው ተሳታፊ የሚሆኑ ሁለት ብሔራዊ ቡድኖችን ለመለየት የሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ አራት ዙሮች አሉት። በእነዚህ ዙሮችም በደርሶ መልስ በሚኖረው ጨዋታ አሸናፊ መሆን የቻሉ ቡድኖች ወደቀጣዮቹ ዙሮች ማለፍ ይችላሉ። ከወራት በፊት አዲስ አበባ ላይ ከቻድ ጋር በመጀመሪያው ጨዋታ 6 ለ ምንም በመርታት አስደናቂ ውጤት ያስመዘገቡት ሉሲዎቹ፤ ከቀናት በኋላም በሁለተኛው ጨዋታ 4 ግቦችን ከመረብ አሳርፈው በድምር ውጤት 10 ለምንም በማሸነፍ በቀላሉ ነበር ይህንን ዙር የተቀላቀሉት። በእጣ አወጣጡ መሠረትም የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ በአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ትልቅ ስም ካላት ከጠንካራዋ ናይጄሪያ ጋር ለቀጣዩ ዙር ተፋላሚ ሆነዋል። ሉሲዎቹ ዛሬ የሚጠብቃቸውን ትልቅ ፈተና በደርሶ መልሱ ውጤት በድል መወጣት ከቻሉ በሶስተኛ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ ከካሜሮን እና ኡጋንዳ አሸናፊ ጋር የሚገናኙ ይሆናል።
ሉሲዎቹ ለዚህ ጨዋታ የሚሆነውን ዝግጅት ለአንድ ሳምንት ያደረጉ ሲሆን ዛሬ በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ አሸናፊ ሆነው ማጠናቀቅ በቀጣይ የሚኖራቸውን እጣ ፈንታ የሚወስን ነው። ለዚህ የማጣሪያ ጨዋታ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ባለፈው ሳምንት ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሃዋሳ ከተማ እና መቻል አብዛኛዎቹን ተጫዋቾች ያስመረጡ ክለቦች ናቸው። የቡድኑ አባላት ከተሰባሰቡበት ጊዜ አንስቶም ልምምዳቸውን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ ሃያ ሁለት በሚገኘው ሻላ ሜዳ እንዲሁም በመስቀል ፍላወር አካባቢ ባለው 35 ሜዳ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ሙሉ ቡድኑ በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ቀላል ጉዳት ገጥሟት የነበረችው አማካይ ኒቦኒይ የን ከቡድኑ ጋር ተቀላቅላ ትናንት እስከተካሄደው የመጨረሻው ልምምድ መሥራት ችላለች።
በዛሬው ጨዋታ ሉሲዎቹን ከሚገጥሙት የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች መካከል አብዛኛዎቹ በሀገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ሲሆኑ፤ ከሀገር ውጪ ባሉ ክለቦች የሚጫወቱት ጥሪ የተደረገላቸው ከቀናት በኋላ አቡጃ ላይ ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ መሆኑን ዘጋርዲያን አስነብቧል። ጭልፊቶቹ ለመጨረሻ ጊዜ በመድረኩ የተጫወቱት እአአ በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሊምፒክ ነበር። በመሆኑም ወደ ታላቁ የስፖርት መድረክ በድጋሚ ለመመለስ ጫና ፈጥረው እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።
አውስትራሊያ በቅርቡ ባስተናገደችው የሴቶች ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ የነበሩት ጭልፊቶቹ 16 ውስጥ መቀላቀል ችለው እንደነበረ አይዘነጋም። ይሁንና ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር በመለያ ምት በመሸነፋቸው ከዚያ በላይ ሊጓዙ አልቻሉም። በአፍሪካ ጠንካራ ከሚባሉ ቡድኖች መካከል የሚጠቀሱት ጭልፊቶቹ በዓለም ዋንጫ ተከታታይ ተሳትፎ ያላቸው ሲሆን፤ እአአ በ2000 እና 2004 በኦሊምፒክ መድረክ ተሳታፊ ነበሩ። በአቴንስ ኦሊምፒክ ተሳትፏቸውም እስከ ሩብ ፍጻሜ መጓዝ ችለው ነበር።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2016