ከልጅነት እስከ እርጅና ለሀገር የተከፈለ መስዋዕትነት

ከልጅነት እድሜያቸው ጀምሮ ሀገራቸውን ወክለው ሲከራከሩ፤ በየተሳተፉበት መድረክም ሆነ ከመሪዎች ጋር በሚያደርጉት ንግግር ከአላማቸው ዝንፍ ሳይሉ ከሀገርና ከወገን ጎን ቆመው አልፈዋል። የሀገራቸውን ክብር ለማስጠበቅም ይጠቅማል ብለው የሚያስቡትን መንገድ ሁሉ ይጓዛሉ። እውቀታቸውን ተጠቅመው ይፈፅማሉ፣ ይታገላሉ።

ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር ከሌሎች ሀገራት ጋር ያወጣችውን እቅድም ሆነ ሴራ ለማጋለጥ በጊዜው ቅንጣት ታክል ሳይፈሩ ለሀገርና ለወገናቸው ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል፤ ሞግተዋል።

ይህንን ሁሉ ሥራ ሲሰሩም አብዛኛውን የሕይወታቸውን ክፍል ኑሯቸውን ያደረጉት በሰው ሀገር ከጠላቶቻቸው ጋር ፊት ለፊት ተፋጠው ነበር። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ የዲፕሎማሲ ሰው የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሕግ አማካሪ፣ የባህል አምባሳደር ፣ በወዳጆቻቸው ዘንድ ቅን ሰው ናቸው ይባልላቸዋል። እኚህ ሰው ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ይባላሉ።

ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በ1904 ዓ.ም መጋቢት አምስት ከአዲስ አበባ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የኦሮሚያ ክልል ደንቢ ቀበሌ ከአባታቸው አለቃ ሀብተወልድ ሀብቴ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ያደግድጉ ፍልፍሉ ተወለዱ። የአክሊሉ አባት አለቃ ሀብተወልድ ሀብቴ የቤተክህነት ሰው በመሆናቸው እናታቸውም ሆኑ አለቃ ሀብተወልድ ልጆቻችው በዚህ መንገድ እንዲያልፉ ፍላጎታቸው ነበር። አክሊሉም ከወንድሞቹ ጋር ወደ እንጦጦ ራጉኤል አቅንተው መማር ጀመሩ።

የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ታላቅ ወንድማቸው መኮንን ሀብተወልድ በ1911 ዓ.ም 25ተኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ የጉምሩክ ዋና መሥሪያ ቤት ዋና ሹም ተብለው ተመረጡ። በጊዜው አባታቸው አለቃ ሀብተወልድ ሀብቴነህ ካረፉ ስምንት ወራቸው ነበር። መኮንን ሀብተወልድም ሥራቸውን ከተረከቡ ከሁለት ወር በኋላ የእህታቸውን ሁለት ልጆች መክብብና አካለወርቅ እና ትንሹን ወንድማቸውን አክሊሉን ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ በሚል ወደ አዲስ አበባ ለመውሰድ ፈለጉ፤ እናም የገና በዓልን አስታከው ወደ እናታቸው ወይዘሮ ያደግድጎ ፍልፍሉ ጋር ፍቃድ ለመጠየቅ ሄዱ።

አባታቸው አለቃ ሀብተወልድ ሀብቴ የቤተክህነት ሰው ስለሆኑ ልጆቻቸውም ድቁናን እንዲማሩ ይፈልጉ ስለነበር እመት ያደግድጉ ፍልፍሉን ለማሳመን ከባድ ሆነባቸው። መኮንን ሀብተወልድም ከእመት ያደግድጉ ፍልፍሉ ፍቃድ ለማግኘት ሲሉ የርሳቸውን የንሰሃ አባት መምሬ ገብሬ ዮሃንስን አማላጅ እንዲሆኑ ይዘዋቸው ሄዱ። በስንት ልመናና ውትወታም እመት ያደግድጉ ፍልፍሉ አክሊሉን ብቻ እንዲወስዱ ሁለቱ ወንድማማቾች መክበብ እና አካለወርቅ ግን ተስፋ ስላላቸው በዚያው እየተማሩ እንዲቆዩ አሉ።

መኮንን ሀብተወልድም ጥር 11 ቀን 1911 ዓ.ም አክሊሉን ለመውሰድ ወደእንጦጦ ራጉኤል ቤተክርስቲያን ሄዱ። አክሊሉ ግን ከወንድሞቹ ተለይቶ ለመሄድ ፍቃደኛ አልነበረም። መክብብና አካለወልድም አክሊሉ ከኛ ተለይቶ አይሄድም አሉ። መኮንን ሀብተወልድም እናታቸው እመት ያደግድጉ ፍልፍሉ ለአሁኑ የፈቀዱላቸው አክሊሉን ብቻ እንደሆነ እነሱን ደግሞ ሌላ ቀን ተመልሰው እንደሚወስዷቸው ቢነግሯቸውም እነሱ ግን ለመነጣጠል ፍቃደኛ አልነበሩም። መኮንን ሀብተ ወልድም በነገሩ በጣም አዝነው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

ከዛ በኋላ እመት ያደግድጉ ፍልፍሉ ህልም አዩ። ህልማቸውም መኮንን ሀብተወልድ በክብር ልብስ አሸብርቀው በወርቀዘቦ የተለጠፈ ካባ ደርበው ባርኔጣቸውን አድርገው ሶስቱን ወንድሞቻቸውን አስከተለው በቤተ-መንግሥት እየዞሩ መሬት እየለኩ ሲሰጧቸው ይመለከታሉ። እመት ያደግድጉ ህልማቸውን በቀጥታ ከእግዚአብሔር የተነገራቸው መልዕክት አድርገው በመውሰድ የልጆቻቸው እድል በመኮንን እጅ መሆኑን አመኑ።

መኮንን ሀብተወልድ ይህንን ሲሰሙ ደስታቸው ወደር አልነበረውም። ከዚያም መክብብ አካለወርቅና አክሊሉ ጥር 24 ቀን 1911 ዓ.ም ከእንጦጦ ራጉኤል ተነስተው በበቅሎ አዲስ አበባ ገቡ ። በቀጣዩ ዓመት 1912 ዓ.ም መስከረም 20 ቀን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን ጀመሩ። ከወንድማቸው መኮንን ሀብተወልድ ጋር ሲኖሩ ከትምህርታቸው መልስ ‹‹ ምክር መስጫ ›› የሚል ፕሮግራም ነበራቸው። ፕሮግራሙ በቤት ውስጥ ይደረግ የነበረ ሲሆን ይህም በአክሊሉ ልብ ውስጥ የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲሰርፅ አድርገዋል።

አክሊሉ በወንድማቸው ቤት ለስምንት ዓመት ከኖሩ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመማር ወደ ግብፅ አቀኑ። በጊዜው የውጭ የትምህርት እድል አግኝተው ከሄዱ ጥቂት ተማሪዎች መካከል አክሊሉ ሀብተወልድ አንዱ ናቸው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በግብፅ በሚገኘው የፈረንሳይ አሌክሳንድሪያ የሊሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1917-1923 ዓ.ም ተማሩ። ከዛ በኋላም ወደ ፈረንሳይ ተጉዘው በታዋቂው የሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ገብተው የከፍተኛ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።

በዚህ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲቆዩ በተለያየ የትምህርት ፋካልቲዎች ገብተው በህግ ትምህርት ኤል ኤል ቢ እና በንግድ ትምህርት ክፍል አጣምረው በማማር ዲፕሎማ አገኙ ከ1933 – 1935 ዓ.ም ያለውን ጊዜ ደግሞ በኢኮኖሚ አመራር በሕገ መንግሥትና አስተዳደር የሕግ ዶክትሬት ልዩ ዲፕሎማ አግኝተዋል።

አክሊሉ ሀብተወልድ ስለኢትዮጵያ መሟገትና ሀገራቸውን በዓለም ዘንድ በበጎ ስሟ እንዲነሳ ማድረግ የጀመሩት ከተማሪነት ጊዜያቸው ጀምሮ ነበር። በግብጽ በሚማሩበት ወቅት የአሌክሳንድሪያው የኮፕቲክ ፓትሪያርክ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ በመጡበት ወቅት 60 ልጆችን ላስተምር ብለው ጠይቀው ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ። ከዚያም እነዚህ 60 ልጆች ከኢትዮጵያ ተመርጠው ወደ ግብፅ ከሄዱ በኋላ ግን ላኩልኝ ያልኩት ስድስት ልጆች ነው እንጂ 60 አይደለም ብለው ቅሬታ አቀረቡ። በዚህም ምክንያት ለትምህርት የሄዱት ተማሪዎች ለእንግልት ተዳረጉ።

ከተማሪዎቹ መካከልም ሶስት ተማሪዎች ተመርጠው ከካይሮ እነ አክሊሉ ወደሚገኙበት ወደ አሌክሳንድሪያ ሄዱ። በጊዜው ከአክሊሉ ጋር ለትምህርት የተላኩት 20 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። አክሊሉ የተማሪዎቹን ችግር ካደመጡ በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የነበራቸውን ትርፍ ልብስ ከሰጧቸው በኋላ ጉዳዩን ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት አስረድተው ከሚመለከታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቤተክርስቲያን ባለስልጣናት እና ለፓትሪያርኩ የተማሪዎቹን ችግር ካስረዱ በኋላ አስፈላጊው እገዛ እንዲደረግላቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ይህ በደህና ሁኔታ ለስድስት ወር ከቆየ በኋላ ደግመው ተማሪዎች ችግር ላይ መውደቃቸውን ሰሙ። አክሊሉ ይህንን እንዳረጋገጡ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በቴሌግራም ካሳወቋቸው በኋላ እሳቸውም ኢየሩሳሌም ለሚገኘው ቆንሲል ለአቶ ጳውሎስ ትእዛዝ አስተላልፈው ተማሪዎቹ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ አደረጉ። በዚህ ጊዜ አክሊሉ ተማሪ ስለነበሩ ወደ ፖለቲካ ውስጥ አይግቡ የሚል አስተያየት ከሚማሩበት ትምህርት ቤት አስተዳደር ይደርሳቸው ነበር።

አክሊሉ በፈረንሳይ ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት ወቅትም ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር ስታስብ በጊዜው ደግሞ ጀርመን እንዲሁ ፈረንሳይን ለመውረር ፍላጎት የምታሳይበት ወቅት በመሆኑ ፈረንሳይ ከሞሶሎኒ ጋር በይበልጥ መቀራረብ ጀመረች። በሂደትም ፈረንሳይና ጣልያን አንድ ስምምነት ላይ ደረሱ። እሱም ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ፈረንሳይ እንዳትቃወም የሚል ነበር ።

አክሊሉ በዚህ ወቅት እጅግ በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል። በጊዜው በፈረንሳይ ምርጫ ይካሄድ ስለነበር ለምርጫው የሚወዳደሩ ሶስት ፓርቲዎች በጊዜው ፈረንሳይን ይመራ የነበረው የላቫል መንግሥትን በመቃወም ፓርቲዎቹ ንግግር በሚያደርጉበት መድረክ ላይ አክሊሉ ብቻውን እየተገኙ ኢትዮጵያ በሊግ ኦፍ ኔሽን ቀርባ አቤቱታዋን በምታሰማበት ጊዜ አቤቱታዋ እንዳይታይ ማድረጋቸውን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያን አቋሞች ያስረዱ ነበር።

በፓሪስ በሚኖሩበት ወቅት አንደኛው ጣልያን የኢትዮጵያን ስም ለማጉደፍና የወረራ ሀሳቧ ተቀባይነት እንዲያገኝ ኢትዮጵያውያን ኋላቀር የሆኑ ሕዝቦች መኖሪያ እና የባሪያ ንግድ የሚካሄድባት ሀገር ናት በማለት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃኖችና በጋዜጦቻቸው ላይ ያሰራጩ ነበር። አክሊሉ ይህንን የፕሮፓጋንዳ ሃሳብ ለማክሸፍ ከተለያዩ ጋዜጦች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ኢትዮጵያ ጥንታዊትና ነፃነቷን አስጠብቃ የቆየች ሀገር መሆኗን ማስረዳታቸውን ቀጠሉ፤ ከዚህም በሻገር ‹‹ኒውስ ኦፍ ኢትዮጵያ›› የሚል ጋዜጣ መስርተው በየጊዜው የኢትዮጵያን አቋም የሚያስረዱ ጽሑፎችን እና ጣልያን ኢትዮጵያ ላይ ስለምታደርገው ያልተገባ ነገር የሚያስረዳ ጽሑፍ ያትማሉ፤ በየጊዜው እራሳቸውም ይፅፋሉ።

አክሊሉ ሀብተወልድ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚያደርጉትን ተጋድሎ በመመልከት በ19 ዓመታቸው የጄኔቫ የኢትዮጵያ ዴሊጌሽን ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ሆነው ተሾሙ። በጊዜውም የኢትዮጵያ ዴሊጌሽን መሪ ከነበሩት ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ጋር በመሆን በጄኔቭ ስለኢትዮጵያ ይሟገቱ ነበር።

በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት የብላቴን ጌታ ወልደማርያም ነበሩ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም አክሊሉን በፓሪስ የፕሬስ አታሼ አድርገው ሾሟቸው። ብላቴን ጌታ ወልደማርያም በህመም ምክንያት እያደረጉ ለረጅም ጊዜ ከሥራ ይቀሩ ነበር። በዚህም ምክንያት ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ በ22 ዓመታቸው በፈረንሳይ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ።

አክሊሉ ከፈረንሳይ ከተመለሱ በኋላ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። አክሊሉ ሀብተወልድ በኢትዮጵያ ሥራቸውን ሲጀምሩ በምክትል ጽሕፈት ሚኒስቴር የጃንሆይ አማካሪ ሆነው ከመሥራት በሻገር የሚኒስትሮችን ሥልጣንና ተግባር በነጋሪት ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲወጣ አድርገዋል። ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ምክትል ሚኒስቴር በየደረጃው አገልግለው ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው ተሹመዋል።

ጸሐፌ ትእዛዝ በኢትዮጵያ የተለያዩ ትልልቅ ተቋማትን ለማቋቋም በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ባንክ ለማቋቋም በጊዜው ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የምስራቅ አፍሪካን ሽልንግ በመሆኑ የመቆጣጠር ሥራውን የሚሰሩት እንግሊዞች ነበሩ። የኢትዮጵያ ባንክ ሥፍራውም በእንግሊዝ ሆኖ ኢትዮጵያም ወርቋን የምታስቀምጠው እዛ ነበር። አክሊሉ ይህ መሆኑ ምናልባትም ወደፊት ከእንግሊዝ ጋር ብንጋጭ ሀብታችንን ሊከለክሉን ይችላሉ የሚለውን ቀድመው በመገመት ዋና ቢሮው በኢትዮጵያ እንዲሆን የባንኩ የቦርድ አባላትም ኢትዮጵያውያኖች እንዲሆኑ እና በጃንሆይ እንዲሾሙ አድርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲቋቋም አደረጉ።

አክሊሉ ሀብተወልድ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ መመስረትም ዋነኛው ሰው ናቸው። የዩናይትድ ኔሽን ምስረታን አጠናቀው ሲመለሱ አሜሪካን በማህበር ኤርላይንስ እናቋቁም ብለው ይጠይቋቸዋል። እነሱም አይሮፕላንም ሆነ አብራሪ የላችሁም በማለት ይቋሟቸዋል። አክሊሉም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ከጃንሆይ ጋር በመመካከር አንድ አውሮፕላን በብድር በመግዛት እና የማኔጅመንቱን ኢትዮጵያ እየከፈለች ለተወሰነ ጊዜ እንዲያስተዳድሯቸው አደረጉ። ከዚያም ቲ.ደብሊው.ኤ የተሰኘ አውሮፕላን ገዝተው ሥራ እንዲጀምር አደረጉ።

የሊግ ኦፍ ኔሽን ወደ ዩናይትድ ኔሽን ተቀይሮ ሲቋቋም አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ነጻ አልወጡም ነበር። በምስረታው ላይ ከአፍሪካ ተሳታፊ ከነበሩት ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ላይቤሪያ ብቻ ነበሩ። አክሊሉ ሀብተወልድም በዩናይትድ ኔሽን ምስረታ ላይ ተገኝተው ቻርተሩ በሚዘጋጅበት ወቅት በኢትዮጵያ በኩል ብዙ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከዚህም ውስጥ ራሳቸው ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የአክሊሉ ማስታወሻ በሚል በ1967 በፃፉት መጽሐፍ ላይ እንደጠቀሱት አንድ መንግሥት ሌላ ኃይል ሊያጠቃኝ ነው ብለው አቤቱታ በሚያቀርቡበት ጊዜ ሴኩሪቲ ካውንስሉ ሊሰበሰብ ይገባል የሚል ሃሳብ አቀረቡ። ይህንን ሃሳብ አሜሪካኖች የተቃወሙት ቢሆንም አክሊሉ ግን ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር ምልክት በምታሳይበት ወቅት በሊግ ኦፍ ኔሽን ቀርበው አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ አለመሰማታቸውን እና ተቀባይነት ያገኙት ጣልያን ሰላሳ ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ነው በማለት ነገሩን ወደኋላ ተመልሰው አስረዱ። አሜንድመንቱም ተቀባይነት አግኝቶ አሁን ድረስ እያገለገለ ይገኛል።

አክሊሉ ሀብተወልድ ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ በበርቱ ተከራከረዋል በተለይም የኤርትራን ጉዳይ ሁሉም ሀገር ከጥቅሙ አንፃር ይመለከተው ነበርና ለአክሊሉ ቀላል አልነበረም። በተለይም እንግሊዝ አሜሪካ ፈረንሳይና ሶቪዬት ህብረት ጉዳዩን ይበልጥ አወሳስበውት ነበር። ነገር ግን አክሊሉ እጅ ባለመስጠት በተለያዩ መድረኮች ላይ እየተገኙ መሪዎቹን ጭምር ለየብቻ እያነጋገሩ እ.አ.አ በ1950 በተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ ጉባኤ ኤርትራ እንደ አንድ ሆና ኢትዮጵያን በፌዴራል እንድትቀላቀል ተወሰነ።

አክሊሉ ሀብተወልድ ከጣልያን ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ ላይ ለተፈፀመው ግፍ ካሳ ሊከፈል ይገባል ሲሉ ጠየቁ። ነገር ግን ጣልያን በጦርነቱ ወቅት የተሰሩ መሠረተ ልማቶች እንደ ካሳ ይቆጠር ሲሉ ነገሩን ቢያቀሉትም አክሊሉ ግን ያ የራሳቸውን ሃሳብ ለማስፈፀም ያደረጉት እንደሆነ በመሞገት 5ሚሊዮን ዶላር የነበረውን ካሳ 25 ሚሊዮን ዶላር እንዲሆን አድርገዋል። በጊዜው በእንግሊዝ ተይዛ የነበረችውን ጋምቤላን ለማስመለስ በአጼ ምኒልክና በእንግሊዞች መካከል የተፈረመውን እንግሊዝ በሱዳን እስከምትቆይ ድረስ ነው በማለት ሱዳን ነፃ ከመሆኗ ከሶስት ወር በፊት ሁለቱ መንግሥታቶች ተነጋግረው እንዲያስረክቡ ተስማሙ። አክሊሉም ጊዜው ሲደርስ የኢትዮጵያን ፖሊስ ወደ ቦታው ልከው የኢትዮጵያን ባንዲራ እንዲውለበለብ አደረጉ። ይህም ያለምንም ደም መፋሰስ የሰሩት ትልቅ ሥራ ነው። ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ነው ባገለገሉበት ወቅትም ለሀገር ሰላም ሲሉ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁ የመጀመሪያው መሪ ነበሩ።

ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ ወርዶ የደርግ መንግሥት ስልጣኑን ከያዘ በኋላ ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም በጥቅሉ 60 በተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች በተበየነባቸው የሞት ፍርድ ሕይወታቸው አልፏል። የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም የተፈፀመውም በዛው ቀን ነበር ።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2016

Recommended For You