ትኩረት የሚሻው የዓይን መነጽር አጠቃቀም

በአንድም ሆነ በሌላ መልክ በርካቶች መነፅርን ለዕይታ ችግር ይሆን ለመዘነጥ አሊያም አደገኛ ብርሃንን ለመከላከል ይጠቀሙበታል። ታዲያ ተገልጋዮቹ የሚጠቀሙትን መነፅር በሐኪም ትዕዛዝ የሚገለገሉበት አልያም መነፅሩ የጥራት ደረጃውን በሚገባ የጠበቀ ይሆን? የሚለው ጉዳይ እምብዛም ትኩረት አይሰጠውም።

ይች ችግር ደግሞ በዓይናቸው ላይ ሊያመጣው የሚችለውን መዘዝ ሲታሰብ ጉዳዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። የዐይን ሕክምና ባለሙያዎች ሰዎች የዓይን መነፅር ሲጠቀሙ ባለሙያዎችን ማማከር እንደሚገባቸውና የሚጠቀሙበት መነፅር ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።

በአለርት ሆስፒታል የዓይን ስፔሽያሊስትና የዓይን ሕክምና ክፍል ኃላፊ ሰለሞን ቡሳ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ መነፅር ሁለት ዓይነት ተግባር አለው። የመጀመሪያው የፀሐይ ብርሃንንና አቧራን ለመከላከል አገልግሎት ላይ የሚውል ነው። ሁለተኛው ተጠቃሚው ተመርምሮ በሐኪም ታዞለት የሚጠቀመውና የዕይታ መዛባትን ለማስተካከል የሚሰጥ ነው።

መነፅሮች የተለያየ የብርሃንና የጨረር መጠን ያላቸው በመሆኑ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መጠቀም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፤ መነፅሩን በማይጠቀሙበት ወቅት ዓይናቸው የፀሐይ ብርሃንን መቋቋም ስለማይችል በአግባቡ ማየት ይሳናቸዋል ይላሉ።

እንደዚሁ ጤነኛ ዓይን እያላቸው ከእነሱ የዓይን ዕይታ አቅም ጋር የማይሄድ መነፅር እየተጠቀሙ የጽሑፍ ወይም የንባብ ሥራ በሚያከናውኑበት ሰዎች የዓይናቸው ዕይታ እየደከመ እንደሚሄድ ሐኪሙ ያስረዳሉ።

መነፅር የሚደረገው በሕክምና ምርመራ እንጂ እንዲሁ ከገበያ ተገኘ ተብሎ ለጌጥም ሆነ ለሌላ አገልግሎት ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ዶክተር ሰለሞን ይገልጻሉ።

የዓይን ስፔሽያሊስቱ እንደሚናገሩት፤ መነፅር በየመደብሩ እንደማንኛውም ሸቀጥ በመሸጥ ላይ ይገኛል። ገዥዎች በየመደብሩ እየሄዱ አንስቶ በመለካት አማረብኝ ወይስ አላማረብኝም እያሉ ገዝተው ይጠቀሙታል። ሻጮቹም ቢሆኑ በዘርፉ ያልሰለጠኑ በመሆናቸው የፀሐይ ነው፣ የማንበቢያ ነው፣ አምሮብሃል ወዘተ…. እያሉ በዘፈቀደ መሸጣቸውን ቀጥለዋል።

 መነፅሮቹ ሲታዘዙ ግን በሕክምና ምርመራ ወቅት የአንደኛው ዓይንና የሌላኛው ዓይን የዕይታ መጠን የሚለያይበት ሁኔታ ስላለ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ነው ይላሉ።

ወቅቱ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ሕፃናት ሳይቀሩ በስልክ፣ በቴሌቪዥን፣ በኮምፒዩርና ሌሎች የቴክኖሎጂ ተዋጽዕኖዎች ውስጥ ሆነው ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ ያሉት ሐኪሙ፤ ከስልክም ሆነ ኮምፒዩተር የሚወጣው ጨረር ወደ ዓይን በሚገባበት ወቅት የመመልከቻ ማዕከል የሆነውን የዓይን ርግብ እክል በመፍጠር የዕይታ መጠንን ይቀንሳል ሲሉ አስረድተዋል።

በዚህም በዕድሜ ርዝመት የሚመጣው የዕይታ ማነስ አሁን ላይ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 30 ባሉ ወጣቶች ላይም እየተከሰተ እንደሆነ ዶክተር ሰለሞን ያብራራሉ።

ሰዎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሚጠቀሙበት ወቅት ለዓይናቸው እረፍት እየሰጡ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንደ ዶክተር ሰለሞን ማብራሪያ፤ ለፀሐይ ብርሃን፣ ለአቧራና ለመዘነጥም ቢሆን መነፅር መጠቀም የሚፈልግ ሰው ባለሙያን አነጋግሮ መጠቀም አለበት።

በኢትዮጵያ በተደረገ ጥናት አንድ ነጥብ ስድስት በመቶ የሚሆኑት የዕይታ ችግር ያለባቸው ሲሆኑ፤ ሰባት ነጥብ ስምንት በመቶ ዜጎች ደግሞ አነጣጥሮ የማየት እክል አለባቸው። ከዚህ መነሻነት ተመርምሮ እራስን ማወቅና መነፅር መጠቀም ተገቢ ነው ይላሉ።

በራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል የዓይን ሐኪም የሆኑት አቤነዘር ሀብታሙ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ደረጃውን ያልጠበቀ የዓይን መነጽርን መጠቀም እንዲሁም ያለ ሕክምና ባለሙያ ትዕዛዝ መነፅሩን መጠቀም የዓይን መንሸዋረር፣ ደብዛዛ ዕይታና ራስን የማዞር፣ ከፍተኛ የራስ ምታት ስሜት ያስከትላል።

በተጨማሪም ዓይንን ማሳከክና ማቃጠል፣ የዓይን ቆብ መዛልና በረጅም ጊዜ በዓይን ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ያብራራሉ።

«በኢትዮጵያ አብዛኛው ማኅበረሰብ መነፅርን የቅንጦት አድርጎ ነው የሚያስበው፤ ነገር ግን መነፅር ከሐኪም ትእዛዝ ውጪ መነፅር ማድረግ በሕክምና ሊድን የሚችል የዓይን ህመምን ወደ ከፋ ደረጃ ሊያሸጋግር ስለሚችል ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ሐኪም አቤነዘር ያሳስባሉ።

በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡን በስፋት እያጠቁ ከሚገኙ የጤና ችግሮች መካከል የዓይን ሕመም አንዱ ሲሆን ሰዎች ያለባቸውን የዓይን ዕይታ ችግር ለዓይን ሕክምና ባለሙያዎች በዝርዝር ማስረዳት እንዳለባቸውና ለዕይታቸው የሚሆን መነጽር እንዲያዙላቸው ቢያደርጉ መልካም ነው ይላሉ።

ኅብረተሰቡ ዓይኑን ከአቧራ፣ ከፀሐይና መሰል ድርጊቶች ለመጠበቅ በሚል የሕክምና ባለሙያዎችን ሳያማክርና ሳይመረመር የሚያደርጋቸው መነፅሮች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል። አብዛኛው የዓይን ህመም በመታከምና በሐኪም ትእዛዝ በሚደረግ መነፅር መስተካከል እንደሚገባ ምክራቸውን ለግሰዋል።

«መነፅር መድኃኒት ነው፤ እንደማንኛውም ሸቀጥ በየቦታው መሸጥ የለበትም» ያሉት ሐኪሙ፤ የዓይን መነጽሮችን በባለሙያ ትዕዛዝ መጠቀም የዓይንን መድከም በመቀነስና ከዓይነ ስውርነት ይታደጋል፤ ኅብረተሰቡ የዓይኑን ደህንነት በየጊዜው በመከታተል ጤናውን መጠበቅ ይኖርበታል ሲሉ ይናገራሉ።

በተለይ ሞባይልና ኮምፒዩተር እንዲሁም ሌሎች ብርሃን አመንጪ መገልገያዎች ላይ ለረጅም ሰዓት ከመጠቀም መቆጠብ የዓይንን ጤንነት ለመጠበቅ መፍትሄ መሆኑን ይመክራሉ።

ለፀሐይ ብርሃንና ለአቧራ መከላከያ ሊውሉ የሚችሉ መነጽሮችንም በጤና ባለሙያ ምክርና እገዛ ብቻ መጠቀም እንደሚገባ ሐኪም አቤነዘር አስረድተዋል።

በዘርፉ ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ተጨማሪ ሙያተኞችን በማሰልጠን ወደ ገበያ ማስገባት እንዳለበትና ያለሙያቸው በየመደብሩና በየመንገዱ መነፅር የሚሸጡ ዜጎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት የዓይን ሐኪሞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You