እንደ ሀገር ጤናማና የተረጋጋ የሀገር ውስጥ ብሎም የጠረፍ ንግድ ሥርዓት መፍጠር እንዳልተቻለ ይገለጻል። ሕገወጥ ንግድ እየተባባሰ መጥቷል፤ ሕገወጥ ንግድ በሕገወጦች የሚከወን እንደመሆኑ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ በተሰማሩ ሕገወጦች ሳቢያ ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተረበሸ ይገኛል። ይህም ለኑሮ ውድነቱ አንድ ምክንያት እየሆነ ቀጥሏል።
ሌላው የሕገወጥ ንግድ መልክ ኮንትሮባንድ ንግድ ነው። የኮንትሮባንድ ንግድ ከጤናማ የንግድ ሥርዓት የሚገኘውን ታክስ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ ያለና አንዳንድ ሕገወጥ አካላት ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሀብት እንዲያፈሩ እያስቻለ ይገኛል። ይህ የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አደጋ የጋረጠ ስለመሆኑ ከጉምሩክ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል። የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው አደጋ ሰፊ እንደሆነ ያመላከተው ኮሚሽኑ፤ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ 80 ቢሊዮን ብር የተገመቱ የኮንትሮባንድ ቁሳቁስን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለም አሳውቋል።
ኮሚሽኑ የችግሩን ግዝፈት የሚመጥን አደረጃጀት በመፍጠር እያከናወነ ባለው ተግባር በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን ብሮች የሚገመት የኮንትሮባንድ ቁሳቁስ በቁጥጥር ስር ሲያውል ቆይቷል። ያካሄደው ሪፎርም በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ላይ ጠንካራ ርምጃ እንዲወሰድ እያስቻለው መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህን የሀገር ስጋት በመከላከልና መቆጣጠር በኩል ኃላፊነት የተሰጣቸው አንዳንድ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ባለመሆናቸው ሳቢያ ችግሩን በሚፈለገው ልክ መቆጣጠር እንዳልተቻለ አስታውቋል።
ይህ በሀገሪቱ ላይ ትልቅ አደጋ የጋረጠና ልትሻገረው ያልቻለችው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እያስከተለ ካለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ባለፈ በቀጣይ ሀገሪቱ በቀላሉ ልትወጣው ወደ ማትችለው ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባት እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ። ችግሩን በቶሎ መከላከልና መቆጣጠር ካልተቻለና በዚሁ ከቀጠለ እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ጥፋቶች ሊያስከትልና ሀገራዊ ዕድገትን በዘላቂነት ሊፈታተን ይችላል ሲሉም ነው ያመለከቱት።
የምጣኔ ሀብትና የሕግ ባለሙያው ዶክተር አያሌው አባተ ቢያሻው ፤ ሕገወጥ ንግድ ወይም ኮንትሮባንድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እንዲሁም በማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ እያሳደረ ካለው አሉታዊ ተጽዕኖ ባለፈ እንደ ሀገር ወደፊት የሚያስከትለው ጫና እጅግ ከባድ፣ ውስብስብና ፈታኝ መሆኑን መረዳትና ከወዲሁ መከላከል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ሕገወጥ ንግድ ወይም ኮንትሮባንድ በአገር ኢኮኖሚና የልማት እድገት ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ እጅግ ከባድ ነው። በኢኮኖሚና ልማት እድገት ላይ እያሳደረ ካለው ተጽዕኖ ባሻገር በተለይም በሀገር ደህንነት፣ በሰላምና ጸጥታ፣ በገበያ አለመረጋጋት፣ ማህበራዊ መስተጋብሮችን በማዛነፍ፣ በመልካም አስተዳደርና በአካባቢ መራቆት ላይ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።
ኮንትሮባንድ አሁን ላይ ብዙም ትኩረት ባልተደረገበት የአካባቢ መራቆት ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ እያደረሰ ስለመሆኑ የጠቀሱት ዶክተር አያሌው፤ አካባቢን የሚያራቁቱ በርካታ ሕገወጥ ንግዶች እንደሚካሄዱ ጠቁመው፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛው በፓርኮች ውስጥ በሚገኙ ሀብቶች ላይ የሚደረግ ሕገወጥ ንግድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእዚህም የዝሆንን ጥርስና ኩንቢ ሕገወጥ ንግድን በአብነት ይጠቅሳሉ። ሁለተኛው ሕገወጥ የሆኑና የማይፈቀዱ የዕጾች ዝውውር ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ እነዚህ ብዙም ትኩረት ያላገኙና በአካባቢ መራቆት ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸውና ዘላቂ የሀገር ልማትን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ናቸው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ሌላው ብዙም ትኩረት የማይደረግበት የኮንትሮባንድ ንግድ ሕገወጥ ማዳበሪያ ንግድ ነው። ይህም የሀገሪቱን ልማት ወደኋላ ይጎትታል። በሕገወጥ መንገድ የሚገባው ማዳበሪያ አንደኛ በሕገወጥ መንገድ በመግባቱ ሀገርን ገቢ ያሳጣል። ከዚህ በተጨማሪም ማዳበሪያው ጥራቱ የጠበቀ ባለመሆኑ አፈሩን የሚያመክንና እንዳያበቅል ያደርጋል። በመሆኑም ትክክለኛ ምርት መሰብሰብ አያስችልም፤ ነገ አፈሩን ማከም የማንችልበት ደረጃ ላይ በማድረስ ይጎዳዋል። ስለዚህ የአፈር ብክለት፣ የአየር ብክለትና የውሃ ብክለትን ሊያስከትሉ የሚችሉና ለሰው ልጆች ጤና ጠንቅ የሆኑ ሕገወጥ ንግዶች መሆናቸውን መረዳትና መከላከል ይገባል። በዚህ ላይ ሌሎች ሀገራት በከፍተኛ ሁኔታ ይሰሩበታል።
በማዕድን ዙሪያ የሚፈጸም ሕገወጥ ንግድም እንዲሁ ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻውና በሕገወጥ ንግድ ሀገር ብዙ የምታጣበት እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር አያሌው፤ ሕገወጥ ንግድ ተብሎ ትኩረት የሚደረግባቸው በተለያዩ ሸቀጦችና አልባሳት ላይ የሚስተዋሉትን እንደሆነ ተናግረዋል። ይሁንና ብዙ ድምጽ ያላገኙትና ሀገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዱ ያሉት የአካባቢ መራቆትና ሕገወጥ የመሣሪያ ንግድ መሆናቸውን ነው ያስረዱት። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ።
የአልባሳቱና የሸቀጦች ሕገወጥ ንግድ የዛሬውን ኢኮኖሚ የሚጎዱ ጊዜያዊ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው የአካባቢ መራቆት ሕገወጥ ንግድ መሆኑን ይናገራሉ፤ ይህ ሕገወጥ ንግድ የነገዋን ኢትዮጵያ የሚጎዳ እና የመጪውን ትውልድ የመልማት መብት ከዛሬው የሚያጠፋ ነው ይላሉ። ድርጊቱ ሀገር እንደ ሀገር እንዳትቀጥል የሚያደርግ እንደሆነ አስገንዝበው፣ በመቆጣጠሩ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ሕገወጥ ንግድ በኢኮኖሚ ረገድ የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲባባስ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ አጠቃላይ ሀገሪቷ ማግኘት ከሚገባት ገቢ አንጻር ሕገወጥ ንግዱ ኢኮኖሚውን እጅግ በጣም እየጎዳ መሆኑን አመልክተዋል።
ሕገወጥ ንግድ ወይም ኮንትሮባንድ በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ የሚገኝበት መሆኑን ገልጸው፣ ይህንኑ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ንጹህ ለማድረግ የሚኬድበት መንገድ በራሱ ሌላ ሕገወጥ አሠራርን የሚከተል እንደሆነ ዶክተር አያሌው ይጠቁማሉ። የውጭ ምንዛሪን በማዛባት ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያስከትል እንደሆነም ነው ያመላከቱት። ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱን የመረጃ መረብ ደህንነት ጭምር ተጠቅመው ሊሠሩ የሚችሉ ኮንትሮባንዶች ጥቂት ስላለመሆናቸው የጠቀሱት ዶክተር አያሌው፤ ኮንትሮባንድ ንግድ ከሽብርተኝነትና ከሳይበር ጥቃት ጋር አብሮ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኮንትሮባንድ ለመሥራት ሲባል የሚፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች ይኖራሉ፤ ኮንትሮባንዲስቶች ከትንሽ እስከ ትልቅ ባለሥልጣኑን ማባለግና የመረጃ ደህንነቱን ሃክ ማድረግ እንዲሁም የማሸበር ተግባር በመሥራት ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ የሚፈልጉትን የኮንትሮባድ ሥራ ይሠራሉ።
በመልካም አስተዳርም እንዲሁ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ጠቅሰው፣ ስለዚህ ኮንትሮባንድ ወይም ሕገወጥ ንግድ ሲባል ከሸቀጦችና አልባሳት ባለፈ እንደዚህ ሰፋ ብሎ መታየትና ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።
‹‹ኮንትሮባንድ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድና የከፋ በመሆኑ በደንብ ሊሠራበት ይገባል›› ያሉት ዶክተር አያሌው፤ በዋነኝነት የሀገሪቱን ሕግና አሠራር በሚገባ መፈተሽ ያስፈልጋል ይላሉ። ሕጋዊ አሠራሩ አንዳንድ ጊዜ ሕጋዊ ሆኖ ለሚሠራው ሰው እንቅፋት የሚሆንበት ጊዜ እንዳለም አመልክተው፣ ይህም ወደ ሕገወጥ መንገድ ሊወስደው የሚችል ሰፊ ዕድል መኖሩንና ይህን መከላከል እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ስለዚህ አሠራሩን ቀላልና ግልጽ ማድረግ፣ ተደራሽነትን ማስፋትና ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ ዘመናዊ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል ሲሉ ያስገነዝባሉ።
‹‹ኮንትሮባንድ የሀገር ኢኮኖሚን፣ የማህበረሰብን አጠቃላይ ዕድገት፣ ልማት፣ ደህንነት ያዛባል ብለን ካመንን ይህን ሊቃወም የሚችል ዜጋ መፍጠር ወሳኝና ዋና ሥራ ሊሆን ገባል›› ያሉት ዶክተር አያሌው፤ ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ኃላፊነት ሊሰማው የሚችል ዜጋ መፍጠር ይገባል ይላሉ። ከሥርዓተ ትምህርት /ካሪኩለም/ ጀምሮ መሥራት ተገቢ መሆኑንም ያመለክታሉ። ለዚህም በቀዳሚነት ሊሠሩ የሚገባቸው ብልሹ የአሠራሮችን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመው፣ ይህ ካልሆነ በትክክለኛው መስመር መጓዝ እንደማይቻልም ይገልጻሉ።
‹‹የኮንትሮባንድ ንግድን መንግሥትና የመንግሥት አሠራር ብቻ ሊፈታው አይችልም ›› ያሉት ዶክተር አያሌው፤ የግል ዘርፉን እንቅሰቃሴ በጣም ነጻ ማድረግና መንግሥት ሙሉ አቅሙን ቁጥጥርና ክትትል ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መሥራት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም ይጠቁማሉ። ዶክተር አያሌው ሕግ በአግባቡ ሊከበር እንደሚገባ ጠቁመው፣ ጠረፍ አካባቢ የሚገኙ የአሠራር ሥርዓቶችን ማጠናከርና በክህሎት፣ በዕውቀትና በሥነምግባር ላይ የተመሠረተ መዋቅራዊ አሠራር እንዲደራጅ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ።
ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የትብብር ሥርዓቱን ማዘመንና ማጠናከር አስፈላጊና መሠረታዊ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በተለይም ከአካባቢ መራቆት ጋር ተያይዞ ዛሬ በሚገባቸው ልክ መለየት ያልቻልናቸውንና በደንብ ያልታዩን ሕገወጥ ንግዶች ከኢኮኖሚያዊ ችግር ባለፈ ነገ ከነገ ወዲያ ማህበራዊ ቀውስ ሊያስከትሉ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በሀገር ላይ እንደሚያስከትሉ ይጠቁማሉ። በእዚህ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። እንዲህ አይነቶቹ የኮንትሮባንድ ንግዶች የሚያስከትሉት ቀውስ አሁን ላይታይ እንደሚችልና ቀስ በቀስ ጉዳት እንደሚያደርስ አመልክተዋል። ኮንትሮባንድ ንግድ ምን ያህል ሀገርን ሊጎዳ እንደሚችል በተከታታይ በማሳየትና በማስተማር ማህበረሰቡ ንቃተ ህሊናው እንዲያድግ መሥራት ሌላኛው መፍትሔ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር መስፍን መንዛ የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያሳደረ ባለው አሉታዊ ተጽዕኖ ምክንያት ማህበረሰቡ እየተጋፈጣቸው ያሉ በርካታ ችግሮች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፣ ሀገርም እንደ ሀገር በብዙ እየተፈተነች መሆኑን አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ሕገወጥ ንግድ ለዋጋ ንረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው። አሁን ገበያ ላይ ያለው ሰው ሰራሽ የሆነ ዋጋም በሕገወጥ ንግድ ምክንያት የመጣ ነው። ሕገወጥ ንግድ በሚስፋፋበት ጊዜ ህጋዊ የሆኑ ነጋዴዎች ከጫወታ ውጭ ይሆናሉ። ሕገወጥ ንግድ ወይም ኮንትሮባንድ ንግድ በግልጽ የማይታይና በኔትዎርክ የሚሰራ እንደመሆኑ የተለያዩ የመንግሥት አካላት ጭምር የሚነካኩበትና ረጅም ሰንሰለት ያለው ነው። በዚህም አብዛኛው ሸማች ማህበረሰብ በብዙ መልኩ ተጎጂ ይሆናል።
ሕገወጥ ንግድን ህጋዊ ለማድረግ በሚደረግ ሙከራም ተጨማሪ ሕገወጥ የሆኑ ተግባራት ይፈጸማሉ የሚሉት ዶክተር መስፍን፣ ሕጋዊ መንገድን የማይከተሉ ሕገወጥ ነጋዴዎች በቅናሽ የሚሸጡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተባባሪ እንዳላቸው ያመለክታሉ። ሸማቹ ለምርቱ ካለው ፍላጎት የተነሳ እንዲሁም በሚኖረው መጠነኛ ቅናሽ በሕገወጥ መንገድ የሚሸጡ የተለያዩ ሸቀጦችን በመግዛት የሕገወጦች ተባባሪ የሚሆንበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቅሳሉ። በዚህ ምክንያት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት ሕገወጥ ንግድ እየተስፋፋ እንደመጣና ለሀገር ፈተና የሆነበት ጊዜ ላይ መደረሱን ነው ያመላከቱት።
በሕገወጥ ንግድ ወይም በኮንትሮባንድ ምክንያት ሸማቹ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር እንዳለ ሆኖ መንግሥትም እየተጎዳ እንደሆነ ያነሱት ዶክተር መስፍን፤ ሕገወጥ ነጋዴው ለተገለገለበት መክፈል የሚገባውን ታክስ ባለመክፈሉ መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንደሚያጣ ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ማህበረሰቡ በቂ የሆነ መሠረተ ልማት ማግኘት አይችልም። በመሆኑም ህዝቡ በሁለት መንገድ ተጎጂ ይሆናል ይላሉ።
ዶክተር መስፍን እንዳሉትም፤ ሕገወጥ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ እያደረሰ ይገኛል። በዚህም መንግሥትን ጨምሮ፣ ሸማቹና አምራቹም ጭምር ተጎጂ ናቸው። ነገር ግን የተወሰኑና በሕገወጥ ንግድ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙት ብቻ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ይህንን እንደ ሀገር ፈተና የሆነውን ኮንትሮባንድ መከላከል በዋናነት ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው እንደ ማህበረሰብ እያዳንዱ ዜጋ ተግባሩን ሊጠየፍና ተበባሪ መሆን እንደሌለበትም እሳቸውም ያስገነዝባሉ።
የመንግሥት የቁጥጥር ሥርዓቱን መፈተሽና ጠንካራ ክትትል ማድረግ አለበት የሚሉት ዶክተር መስፍን፤ በተለይም በሕገወጥ ንግድ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አንዳንድ የመንግሥት አካላት ጭምር በመኖራቸው መንግሥት በአሠራር ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የሆነ ክትትልና ቁጥጥሩን ጠበቅ በማድረግ እንዲሁም ጥናት ማካሄድ ይጠበቅባታል ነው ያሉት። ከመንግሥት በተጨማሪም እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን ለመወጣት የሕገወጦች ተባባሪ ከመሆን መቆጠብና ከግል ፍላጎት ባለፈ እንደ ሀገር ሰፋ አድርጎ ማሰብ እንዳለበትም ያስገነዝባሉ።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር በቅርቡ እንዳመለከተው ፤ በኮንትሮባንድና በሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ አካላት የማጭበርበሪያ ዘዴዎች በርካታ ሲሆኑ፤ በተለይም በድንበሮች ስፋት ምክንያት የሚካሄደው ኮንትሮባንድ ሰፊ ነው።
በችግሩ ስፋት ምክንያት ከሪፎርሙ ወዲህ አደጋውን ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ በርካታ ሥራዎች ስለመኖራቸው ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ የሚያመላክት ሲሆን፤ በቀጣይም ከችግሩ ለመውጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የተቀመጠውን የፀረ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ግብረ ኃይል የሚመራበትን ስትራቴጂ በሚገባ ተግባራዊ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክቷል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2016