የአርመን ህዝብ ትምህርት ቤት እና ያልተፈታው ውዝግብ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ስር በሚገኘው የአርመን ትምርት ቤት መዘጋት ጋር ተያይዞ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የፍረዱኝ አምድ የምርመራ ዘገባ መሠራቱ ይታወቃል። በዘገባውም የትምህርት ቤቱ ባለቤት እኔ ነኝ የሚል አካል ማግኘት እንዳልቻልን እና ትምህርት ቤቱም ተዘግቶ ለመጠጥ ቤት አገልግሎት መዋሉን ጠቁመን ነበር።

ትምህርት ቤቱን በተመለከተ ቀደም ሲልም ሌሎች ዘገባዎች የተሰሩ ቢሆንም፤ የዚህኛው ዘገባ ለንባብ መብቃት ግን ባለቤቱ እኔ ነኝ የሚል አካል እንዲገኝ አድርጓል። ዘገባውን የተመለከቱ የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች ነን ያሉት የማህበሩ አባላትም ትምህርት ቤቱ ‘ባለቤት የለውም’ መባሉ ትክክል አይደለም፤ “ባለቤቶቹ እኛ ነን” ሲሉ ወደ ዝግጅት ክፍላችን ቀርበዋል።

የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች እኛ ነን ያሉት አካላት ትምህርት ቤቱ ለመጠጥ ቤት አገልግሎት እየዋለ ነው መባሉንም ያስተባበሉ ሲሆን፤ ሃሳባቸውን በቃል ከመግለጽም ይልቅ በጽሑፍ ማቅረብን መርጠዋል። እኛም ለዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ እትማችን ያለፈውን ዘገባ ቀጣይ ክፍል ይዘን የቀረብን ሲሆን፤ በዚህም የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች በጽሁፍ የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ፣ እንዲሁም ከሰነዶች የተገኙ መረጃዎችን በጥልቀት በመመርመር እና ከባለድርሻ አካላት የተገኙ ማስረጃዎችን ዋቢ በማድረግ እንደሚከተለው ተሰናድቷል። ምልካም ንባብ።

ከአርመን ማህበር በጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ

ቀደም ባለው ዘገባችን ለወጣው መረጃ የአርመን ኮሚዩኒቲ ማህበር በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ እንዳመለከተው፤ የአርመን ኮሚዩኒቲ ማህበር ትምህርት ቤት ማቲን ኬቮርኮፎ ከተባሉ አርመናዊ ከተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በ1925 ዓ.ም የህንጻ ግንባታው የተጀመረ ሲሆን፤ ግንባታው ተጠናቅቆ የመማር ማስተማር ሥራ የጀመረው በ1927 ዓ.ም ነው።

ፋሽት ጣሊያን ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር ጥረት ባደረገባቸው አምስት ዓመታት ወቅትም በትምህርት ቤቱ የነበሩ ተማሪዎች ሳይበተኑ የትምህርት ቤቱ ስም ቪቶሪዮ ኢማኑኤል ተብሎ ስያሜ ተሰጥቶት የትምህርት ግልጋሎት ሲሰጥ ነበር። ፋሽት ኢጣሊያን ከኢትዮጵያ በወጣ ጊዜም ይህ ትምህርት ቤት ለአርመን ኮሚዩኒቲ እንዲመለስ ተደርጓል።

በዚህ ትምህርት ቤት የአርመን ዝርያ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ወንድም እና እህት ኢትዮጵያውያን ልጆች እና የልጅ ልጆች ጋር ሲማሩ ያደጉበት እና በተለይም ኢትዮጵያዊ እና አርመኖች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ሲወራሱበት የነበረ ተቋም ነው።

በእንደዚህ አይነት ትውልድን በመቅረጽ ለ48 ዓመታት አገልግሎት የሰጠው ትምህርት ቤት በ1975 ዓ.ም በደርግ መንግሥት ተወረሰ። በዚህም ሳቢያ ተቋሙ አሳካዋለሁ ብሎ የጀመረው ተቋማዊ ዓላማ ፈተና ገጠመው። ይህ የደርግ ርምጃ ነው እያደረ እየዋለ ታሪካዊውን ትምህርት ቤት እንዲዘጋ ያደረገው።

ትምህርት ቤቱ በባለቤትነት የተቋቋመውና ይተዳደር የነበረው በኢትዮጵያ የአርመን ማህበር ነው። አድራሻውም አርመን ቤተክርስቲያን እና በርካታ የአርመን ዜጎች የተለያዩ ግንባታዎችን እና የልማት ሥራዎችን አከናውነው ይገኙበት በነበረው /Armenian quarter/ በኋላ ላይ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ቀበሌ 01 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የነበረ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቱ የተመዘገበበት የቤት ቁጥርም 726 ነው።

በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ከነበሩት የኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶች መካከል አርመን ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት አንዱ መሆኑን የሚገልጸው የጽሑፍ ምላሹ፤ ከ1927 ዓ.ም ጀምሮ የተደራጀ እና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን አመላክቷል። በዚህም በሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ብቁ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ግንባር ቀደም ተቋም መሆኑንና በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ እውቅና እንዳለው ይጠቁማል።

በደርግ ዘመነመንግሥት የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት በመ/ቁ1 /1/1/14/75፣ ግንቦት 2 ቀን 1975 ዓ.ም በተላለፈ ትዕዛዝ፤ ትምህርት ቤቱን “ለትምህርት ሚኒስቴር እንድታስረክቡ” በሚል ትምህርት ቤቱን መወረሳቸውን እና በዚህም ምክንያት የትምህርት ሥራውን ምቹ ባልሆነ የኮሚዩኒቲው ክለብ አጎራባች በሆነ ቤት ውስጥ ትምህርት እየሰጡ ለመቆየት መገደዳቸውንም ነው ጽሑፉ የሚያስረዳው።

ነገር ግን በየጊዜው የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት እና ቁጥጥር መመሪያ እየተጠናከረ በመምጣቱ ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት ጊቢ መንግሥት ለትምህርት ሥራው ያወጣውን መስፈርት ሙሉ በሙሉ ማሟላት የማይችልበት ደረጃ መድረሱን በጽሑፉ የጠቆሙት አባላቱ፤ ይሁንና ቦታው መሀል ከተማ መገኘቱና በዝቅተኛ ዋጋ አገልግሎት መስጠቱን ይፈልጉ በነበሩ ቅን ወላጆች በመታገዝ በተለያየ ጊዜ ዕውቅና ፈቃድ እድሳት እየተደረገለት መቆየቱን ያነሳሉ።

ትምህርት ቤቱ በ1925 ዓ.ም ያስገነባውን ህንጻ ከተነጠቀ በኋላ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ፣ እንዲሁም ከቁጥጥር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚሰጠውን ግብረ መልስ በማገናዘብ የመዋዕለ ሕጻናትቱን ማስተማሪያ ቦታ ቀደም ብሎ የመማር ማስተማር አገልግሎት ይሰጥበት ከነበረው ጊቢው በማስወጣት የቤተ ክርስቲያኑ ንብረት በሆነ ቤት ለማዘዋወር መገደዳቸውንና የወላጅ ኮሚቴ ባሉበት 700 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ለመስጠት ጥረት ቢያደርጉም፣ የቁጥጥር ቢሮውን መስፈርት ማሟላት አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ሳይፈልጉ ተገደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ሥልጠና እና ጥራት የሙያ ብቃት ማረጋጫ ባለሥልጣን አራዳ እና ቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ ትምህርት ቤቱ መዘጋቱን ይገልጻሉ።

ለዚህ ሁሉ ችግር መነሻ የሆነው የደርግ መንግሥት በየትኛውም የኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶች ላይ ያልወሰደውን ርምጃ በአርመን ትምህርት ቤት ላይ መፈጸሙ ነው ሲሉ በጽሑፍ ሃሳባቸውን የገለጹት የማህበሩ አባላት፤ ይህም ትምህርት ቤቱ ስሙን የማይመጥንና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዳይችል ማድረጉን ያስረዳሉ።

ማህበሩ የተወረሰውን ህንጻ ለትምህርት ሥራ አገልግሎት አስቦ የገነባው ነበር። ህንፃው ይመለስለት ዘንድ ጥቅምት 9 ቀን 1988 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ‹‹ፕራቬታይዘሽን ኤጀንሲ›› አቤት ብሎ ነበር። ይህን አቤቱታ ተከትሎም የኢትዮጵያ ‹‹ፕራቬታይዘሽን ኤጀንሲ›› ሕንጻው ከሕግ ውጭ የተወረሰ መሆኑን በማረጋገጡ ታህሳስ 12 ቀን 1992 በቁጥር 20/ነ2/360/7524/92 በተጻፈ ደብዳቤ ሕንጻው ለአርመን ኮሚኒቲ እንዲመለስ የሚል ውሳኔ አስተላለፈ። ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ውሳኔውን በመቃወም ለፕራቬታይዜሽን ቦርድ ባቀረበው አቤቱታ መነሻነት የትምህርት ቤቱ ሕንጻ ሳይመለስ ቀርቷል።

የደርግ መንግሥት ለ10ኛው የአብዮት በዓል ዝግጅት በግዮን ሆቴል ለማክበር በሚሰናዳበት ወቅት በሆቴሉ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ይገኝ የነበረውን የብሄራዊ ቤተ-መንግሥት የሚባለውን ትምህርት ቤት እንዲፈርስ አደረገ። ለፈረሰው ትምህርት ቤት ተተኪ ቦታ በመስጠት የራሱን ግንባታ መገንባት ሲገባው፣ የአርመን ኮሙኒቲ ትምህርት ቤትን ህንጻ አንድ ቀን በማይሞላ የማስጠንቀቂ ደብዳቤ እንዲወረስ በማድረግ ከግዮን ሆቴል ለተነሳው ብሄራዊ ቤተ መንግሥት ትምህርት ቤት በምትክነት እንዲሰጥ ተወሰነ። በዚህም በአርመን ኮሚዩኒቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች እንዲበተኑ ተደረገ።

ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ የቤተመንግሥት ትምህርት ቤት ተብሎ የሚጠራው ትምህርት ቤት የራሱን ህንጻ የገነባ እና ያላግባብ ከተወረሰው ትምህርት ቤታችን የለቀቀን ቢሆንም፤ አሁን ላይ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ አግባብ የተወረሰው የትምህርት ቤት ህንጻ ለግለሰብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ባንጻሩም የትምህርት ጥራትና ቁጥጥር ቢሮ ትምህርት የምትሰጡበት ቦታ መስፈርቱን አያሟላም ተብሎ የኮሚዩኒቲውን ትምህርት ቤት መዘጋቱ እጅግ የሚያም ከመሆኑም ባሻገር ሀገሪቱ የተሻለ የሰው ኃይል ለማፍራት የምታደርገውን ጥረትም የሚያሰናክል ነው።

የዚህ የትምህርት ቤት ሕንጻ ቀድሞውኑ ለትምህርት አገልግሎት የተገነባ በመሆኑ ከበቂ ጊቢና ይዞታ ጋር ከ18 በላይ ክፍሎች ነበሩት። ስለሆነም አሁን ላይ ይህ ያለአግባብ የተነጠቅነው ህንጻ ቢመለስልን እና ብንሰራበት በተሻለ ጥራት እና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ያካባቢውን ወላጆች ቅሬታም መመለስ ያስችላል።

ለዚህም የተወረሰባቸውን የትምህርት ቤት ህንጻ ለማስመስ ከላይ እስከታች ለሚገኙ የተለያዩ አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት በደብዳቤ የተጠየቀ ሲሆን፤ በቀድሞው ጊዜ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዜናዊ ፣ ቀጥለውም ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም የአዲስ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ለክቡር አቶ ታከለ ኡማ አቤቱታ በማቅረባቸውን ነው በጽሑፍ ምላሻቸው ያመላከቱት።

በተለይ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ቀደም ብሎ ተወርሶ የነበረ የሁሉም አብያተ ቤተክርስቲያናት ንብረት ተመልሷል። ይሁን እንጂ የአርመን ኮሚኒቲ ንብረት የሆኑት የትምህርት ቤት፣ ቤተ-ክርስቲያን እና ባለአራት ወለል ፎቅ ሕንጻ እንዲመለስላቸው ቢጠይቁም እስካሁን መልስ አላገኙም። በተለይ የትምህርት ቤቱ ሕንጻ አለመመለስ ጥራት ያለው የትምህርት ሥራ በማቅረብ በእውቀት የታነጸ እና ክሕሎት ያለው ሀገር የሚረከብ ትውልድ የመፍጠር ዓላማቸውን እውን ለማድረግ የሚያስችላቸውን እድል ያኮላሸ ሆኗል።

ምንም እንኳን ለትምህርት ግልጋሎት የሠሩት ህንጻ ቢወረስም በእውቀት የታነጸ እና ክሕሎት ያለው ሀገር የሚረከብ ትውልድ ለመፍጠር የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ የመዋዕለ ህፃናቱን ክፍል ከፍተኛ ወጭ በማውጣት ግንባታ አድርገው እንደነበር ያስረዳሉ።

ነገር ግን መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እንተደዘገበው ማህበሩ የትምህርቱን መስፈርት ለማሟላት ባለመፈለጉ ትምህርት ቤቱ መዘጋቱን ያትታል ያሉት አባላቱ፤ ይህም ማህበሩ ከሠራው አድካሚ ሥራ አንጻር ዘገባው ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ።

በተለይ ትውልድን ገንቢ የነበረው ተቋም ወደ ትውልድ አጥፊነት (መጠጥ ቤት) እንደተቀየረ ተደርጎ የቀረበው ሪፖርት ትክክል አለመሆኑን፤ የጋዜጣውን አዘጋጆች ጭምር ቤቱን እንዲጎበኙት በማድረግ እውነታውን እንዲያውቁት ማድረጋቸውን ህዝብ ይወቅልን ሲሉ አስረድተዋል።

ህሊና ያለው ሰው እንደሚያስበው ሁሉም ልጆች በዕውቀት የበለጸጉ፤ በአካል ጥንካሬና ሥነ-ምግባር ተኮትኩተው ሊያድጉ የሚችሉት ምቹ የመማሪያ ከባቢ ሲኖራቸው። ለትምህርት ጥራት ምቹ ሁኔታ ሲኖር እንጂ ለወላጅ ቅርብ የሆነ ቦታ ስለሆነ ብቻ ልጆች በእውቀትና በክህሎት ተወዳዳሪ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ አይታሰብም።

በዚህ ሁኔታ መማር ደግሞ እውቀት ሊያስገኝ አይችልም። ስለሆነም ማህበሩ ህንጻችን ያስገነባቸው የተሻለ ትምህርት ለትውልድ ለመስጠት አስቦ በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ትምህርት ቤቱን ይመልስልን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ትምህርት ቤቱ ከተመለሰ የተሟላ እና ደረጃውን የጠበቀ ትምህር መስጠት እንደሚችሉ አመልክተዋል።

የአራዳና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የዕውቅና ፈቃድ እድሳት ጽህፈት ቤት

የአራዳና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የዕውቅና ፈቃድ እድሳት ጽህፈት ቤት ቡድን መሪ የሆኑት ጺዮን ጌታቸው እንደሚሉት፤ የአርመን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጽህፈት ቤቱ ተቋሙን መምራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም በ2012 ዓ.ም ጀምሮ የእውቅና ፈቃድ እድሳት ትምህርት ቤቱ ጥያቄ አቅርቦ በባለሙያዎች ምዘና ተደርጐለታል። ምዘና በተደረገበት ወቅት ከምድረ ጊቢው ስፋት ጀምሮ የመዘዋወሪያ ቦታና መሰል የዕድሳት ቅደመ ምልክታ ውጤት ተሰርቶለታል።

በወቅቱ ሁሉንም አሟልቶ የሚጠየቁ መስፈርቶችን አሟልቶ በመስፈርቱ መሠረት ተመዝኖ አጠቃላይ 75 እና ከዚያ በላይ ውጤት ማምጣት የነበረበት ቢሆንም፤ 58 ነጥብ ስምንት ሶስት ነው። ይህም የጊቢው አጠቃላይ ስፋት እንኳን ተይዞ መስፈርቱን አላሟላም። የቁጥጥር ባለሥልጣ መሥሪያ ቤቱ ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት አንድ ትምህርት ቤት ማሟላት የነበረበትን መስፈርት ሳያሟላ ሲቀር ከአንድ ወር በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ምዘና ይደረግለታል።

በዚህ መሠረት የጊቢው አጠቃላይ ስፋት በድጋሚ በተለካ ጊዜ 1 ሺህ 200 ካሬ ሜትር በመሆኑ መስፈርቱን አሟልቶ ተገኝቷል። በሁለተኛው ዙር በተደረገ ምዘናም 72 ነጥብ 05 ውጤት አምጥቶ ነበር። ይህም 75 ነጥብ ማሟላት ስላልቻለ እውቅና ፈቃዱን ማደስ አልቻለም።

ስለዚህ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሁለት ጊዜ ዕድል ተሰጥቶት ማሟላት ካልቻለ ወደ ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ሥልጠና፣ ጥራትና ቁጥጥር ባለሥልጣን የወደቁ ተቋማት በሚል ስም ዝርዝሩ ከውጤቱ ጋር በማድረግ ይላካል። ባለሥልጣኑም በመልካም አስተዳደር ተመልክቶ መቀጠልና አለመቀጠሉን ከህዝቡ ችግር አኳያና ነባራዊ ሁኔታ ጋር አይቶ እንዲቀጥል የሚያደርጓቸው ተቋማት አሉ። አልፎ አልፎ ያለውን ሁኔታ በማየት ከ50 በላይ ያመጡ ትምህርት ቤቶችም እንዲቀጥሉ ይደረጋል።

ምዘና ባደረገበት ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቶ ስለነበር አርመን ትምህርት ቤት በ2013 በማስተማር ሥራው እንዲቀጥል ተደርጓል። ሆኖም ግን የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች እንዲቀጥል ስለማይፈልጉ የሚሰጣቸውን የማስተካከያ ቼክ ሊስት ተቀብለው ከማስተካከል ይልቅ ይባስኑ እንዲቀንስ ተደረገ።

በ2014 ዓ.ም የማመልከቻ ደብዳቤ ሲያስገቡ ከበፊት የነበረውን የቦታ ስፋት አልጠቀሱም። ትምህርት ቤቱ ነባር ተቋም ሲሆን የእውቅና ፍቃድ እድሳት ሲደረግ የሚከናወነው በቼክ ሊስት ሜዳው፣ ምድረ ጊቢው እንዳለ የሚወሰድ ነው። ነገር ግን መቀጠል ስላልፈለጉ ሜዳው የክበቡ ነው የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ጀመሩ።

መጀመሪያውኑ መስፈርት አላሟሉም የተባሉት የክለቡ የሚሉትን ይዞታ አጠቃሎ ነው። የዕውቅና ፈቃድ እድሳት ላይ ነባር ተቋም ሲሆን የትምህርት ቤት ቼክ ሊስት ሙሉ በሙሉ ያጠቃልላል። ጥሩ አፈጻጸም ካለው ያለውን ነጥብ በመስጠት ከሌላው ደግሞ ክፍተቱን እንዲያስተካከል ዜሮ ነጥብ በማስቀመጥ የምዘና ውጤት ይሰጣል። አዲስ ተቋም ሲሆን ከጅምሩ የምድረ ጊቢ ስፋት ካላሟላ ሌሎች ቼክ ሊስቶች አይታዩም።

ለምሳሌ፣ አንድ የትምህርት ተቋም ትምህርት ቤት ለመባል እውቅና ለማግኘት አንድ ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ቦታ ሊኖረው ይገባል። ይህን ካላሟላ እውቅና ፈቃድ አይሰጠውም። አርመን እንደ ትምህርት ቤት የምድረ ጊቢውን ስፋት 1200 ካሬ ሜትር አስመዝግቧል። ፍቃድ የተሰጠውም ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል ለማስተማር ስለሆነ ሲያስተምር የነበረው ከአንድ እስከ አራት ባለው ነው። ሲመዘን የነበረውም በዚህ መስፈርት ነው።

2014 ዓ.ም ቼክ ሊስት እንደገና እንዲሰራ ተደርጐ የምድረ ጊቢው ስፋት ማግኘት ከሚገባው አራት ነጥብ ማሟላት ሳይችል ቀርቶ ሁለት ነጥብ ብቻ አገኘ። ይህም የሆነው ከዚህ ወዲያ የማህበሩ ነው። ከዚህ መልስ የትምህርት ቤት የሚል ሃሳብ እያነሱ ስለመጡ ነው። ከመመገቢያ ክፍሉም ጋር ተያይዞ ሲገመገም ትምህርት ቤቱ በምዘናው ዜሮ ነጥብ ነው ያገኘው። “ይህም ተቋሙ እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ በትምህርት ዘርፍ መቀጠል አለመፈለጉን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

የቀጣናው ወላጆች ትምህርት ቤቱ እንዳይዘጋ ስልሚፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት ድጋፍ እስከ ማድረግ ደርሰው ነበር። ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቱ የነበረው ተነሳሽነት ዝቅተኛ ስለነበር ሊዘጋ መቻሉን ይገልጻሉ።

የባለሥልጣን ጽህፈት ቤቱ የሚያስጠብቀው የመሬት ጉዳይ ሳይሆን የትምህርት ቤት ስታንዳርድ ነው የሚሉት ኃላፊዋ፤ ተቋሙ አጠቃላይ እንቅስቃሴው በትምህር ዘርፉ መቀጠል እንደማይፈልግ በማሳየቱ ቢሯቸው ትምህርት ቤቱን በተገቢው መንገድ መዝኖ ከደረጃ በታች ሆኖ በማግኘቱ መዘጋቱን ይናገራሉ።

መሬት ልማት አስተዳደር የይዞታ ቴክኒክ አጣሪና የካርታ ዝግጅት

ዝግጅት ክፍላችን፣ የአርመን ትምህርት ቤት ይዞታን በተመለከተ ለትምህርት ቤት ተብሎ የተሰጠን ቦታ ለሌላ ዓላማ መጠቀም የሚቻልበት አግባብ መኖርና አለመኖሩን በአራዳ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር የይዞታ ቴክኒክ አጣሪና የካርታ ዝግጅት ባለሙያ ለሆኑት አቶ አብነት አበባው ጥያቄ አቅርቧል።

አቶ አብነት፣ የባለይዞታ መብት ሲፈጠር ቤቱ በማን እንደተያዘ ለማወቅ ሲታይ የሲአይኤ መረጃ እንደሚታይ ገልጸው ፤ መብት ሲፈጠር ደግሞ የ1988 የአየር ካርታና የ1991 ዓ.ም ሲአይኤስ መረጃን መሠረት ባደረገ መልኩ መሆኑን ያስረዳሉ።

መብት ሲፈጠር የልኬት ባለሙያው መሬት ላይ ወርዶ ሲለካና ሲያጣራ ትምህርት ቤት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንና አለመሆኑን ለክቶ ያጣራል። ከአጣራና ካገናዘበ በኋላ የ1988 የአየር ካርታን በማየት እና መሬቱ የማን እንደሆነ ተጣርቶ በመመሪያው መሠረት መብት ይፈጠራል። በዚህ መሠረት አሁን ላይ ውዝግብ የተነሳባቸው የቤት ቁጥር 726 እና 714 የሚባሉ ቤቶች መብት የተፈጠረላቸው የጂአይኤስ እና የሲአይ ኤስ መረጃውን በመመልክት መሆኑን ያስረዳሉ። በመረጃው መሠረት አርመን ክበብ እና ትምህርት ቤት በአንድ ተቋም የሚተዳደሩ የተለያየ ይዞታዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎች አንድ ተቋምና አንድ አካል ከሆኑ በአንድ ላይ መብት ሊፈጠርላቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።

ለድርጅት ተብሎ ለሌላ አገልግሎት ሲጠቀም በተገኘ ባለይዞታ ላይ ምን አስገዳጅ ነገር አለ? ተብለው የተጠየቁት ባለሙያው አንድ ድርጅት ለአንድ የሆነ አገልግሎት ብሎ መሬት ከወሰደ በኋላ ለሌላ ተግባር ማዋል ቢፈልግ ሂደቱን ተከትሎ የፈለገውን የማድረግ መብት አለው። ይህ ግን የራሱ የሆነ አሠራር አለው። ይሁን እንጂ ታሪካዊ ይዘት ያላቸውን ቦታዎች ከተፈቀደላቸው አግልግሎት ውጪ ሲጠቀሙ ቢገኙ ጉዳዩን መጠየቅ ያለበት ቅርስ ጥበቃ እንጂ መሬት አስተዳደር አለመሆኑን ይናገራሉ።

ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች

ሰነድ አንድ ፡- የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት በቁጥር መ/ቁ1/1/1/14/75 በቀን 2/9/1975 ዓ.ም ለአርመን ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት የጻፈው ደብዳቤ እንደወረደ “በከፍተኛ 13 ቀበሌ 02 ውስጥ የሚገኘው የአርመን ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ለመንግሥት ሥራ ስለተፈለገ በአስቸኳይ ዛሬውኑ ከሰዓት በኋላ ትምህርት ቤቱን ለትምህርት ሚኒስቴር እንድታስረክቡ እያስታወቅሁ፤ በምትኩም ለትምህርት ቤታችሁ የሚሆን ቤት እንዲሰጣችሁ ለሚመለከተው ክፍል ትዕዛዝ የተላለፈ መሆኑን እናሳውቃለን።”

ሰነድ ሁለት ፡- የአርመን ኮሙዩኒቲ ትምህርት በቀን 3/10/2012 ዓ.ም በቁጥር AC-00032/2020 ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር አቤቱታ አቅርበዋል። በአቤቱታውም የአርመን ቤተክርስቲያን አገልጋዮች የተቋቋመው ባለአራት ፎቅ ቤት እና በ1975 የተወረሰው ትምህርት ቤቱ እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል።

ሰነድ ሶስት፡- የጥራት እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ትምህርት ቤቱን ከዘጋበት አንዱ ምክንያት በቼክ ሊስት በተቀመጠ ግምገማ ነው ። በዚህ ግምገማ ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ ዋነኛ ምክንያቱ ግን ትምህርት ቤቱ ለትምህርት ያዘጋጃቸው የክፍል ስታንዳርድ መሆኑን ትምህርት ቤቱ ከተገመገመባቸው የቼክ ሊስት ሰነዶች ያሳያሉ።

የምርመራ ቡድኑ ግኝት

ግኝት አንድ፡- ከወረዳ እና በክፍለ ከተማ ትምህርት ቢሮዎች እንዲሁም በከተማዋ የትምህርት ጥራት ቁጥጥር ባለሥጣን አዲሱ ትምህርት ቤት በ 1844 ካሬ ሜትር ጊቢ ላይ እንደሚገኝ ተደርጎ መታሰቡ ስህተት ነው። ይህ የተጠቀሰው ቦታ ለአርመን ህዝብ ማህበር ትምህርት ቤት የሚል የካርታ ስም ይሰጠው እንጂ በውስጡ ሁለት የቤት ቁጥሮችን የያዘ ነው።

በዚሁ ካርታ በቤት ቁጥር 720 የተመዘገበው የትምህርት ቤቱ ይዞታ ሲሆን በቤት ቁጥር 714 የተመዘገበው ደግሞ የአርመን ኮሙኒቲ መዝናኛ ክብብ ነው። ስለሆነም ከዚህ ቀደም ትምህርት ቤቱ ለመጠጥ ቤት መዋሉን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰው ጥቆማ በቤት ቁጥር 714 የተመዘገበውን ቤት የአርመን ኮሙኒቲ መዝናኛ ከበብ መሆኑን ካለመረዳት የመነጨ መሆኑን ተመልክተናል።

ግኝት ሁለት፡- የምርመራ ቡድኑ የተለያዩ አካላትን ጠይቆ ባረጋገጠው የምርመራ ሥራ መሠረት 18 ክፍል ያለው እና ተወርሶ የነበረው ትምህርት ቤት አሁን ላይ ለመንግሥት የትምህርት አገልግሎት የማይሰጥ ከመሆኑም ባሻገር፤ በወር በ30 ሺብር ለአንድ ድርጅት ተከራይቶ እደሚገኝ ደርሶበታል።

ሙሉቀን ታደገ እና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2016

Recommended For You