የአዲስ አበባን የማዘውተርያ ስፍራዎች ችግር በጥናት ለመፍታት እየተሠራ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ምዕራፍ ያከናወናቸውን ተግባራት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል:: ቢሮው የወጣቶች ስዕብና መገንቢያና የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ላይ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ጥናት አድርጎ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጿል::

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በርካታ የስዕብና መገንቢያ ማዕከላት የሚገኙ ሲሆን የተወሰኑት የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን ያካተቱ ናቸው:: ማዕከላቱ በሚፈለገው መጠንና ጥራት ካለመሠራታቸውም በላይ ለታለመላቸው ዓላማ ከመዋል አኳያም ጥያቄዎች ይነሳሉ:: የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችም ጥያቄ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች ዋንኛው ሲሆን የመጠናቸው ማነስ ብቻ ሳይሆን ከአገልግሎትና ጥራት አንጻር የሚፈለገውን ያህል አይደሉም::

የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ የከተማው ቁልፍ ሥራ መሆኑን ለዚህም ቢሮው ጥናት በማድረግ መታረምና መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች እያስተካከለ መሆኑን አስታውቋል:: በዚህ ዓመትም እንደ ቁልፍ ጉዳይ ተደርጎ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሠራል:: የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ ቢኖሩም ከአጠቃቀም ጋር ጉድለቶች እንዳሉ በመድረኩ ተነስቷል:: ለዚህም የመፍትሄ ጥናት አድርጎ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ ነው:: በአሁኑ ወቅት በጥናት የተረጋገጡ 1 ሺ 169 የሚጠጉ ነባርና አዳዲስ የማዘውተርያ ስፍራዎች አሉ:: እነዚህ ስፍራዎች በተለምዶ አገልግሎት ቢሰጡም ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ግን የላቸውም::

ቢሮው ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘው ገቢ 12 የህጻናት መጫወቻና የወጣቶች ስፖርት መዘውተርያ ስፍራ እንዲገነባ በማድረግ ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን ጠቁሟል:: ቢሮው ባለፈው ዓመት 27 የማዘውተርያ ስፍራዎችን ገንብቶ ማስተላለፍም ችሏል:: በዘንድሮ ዓመትም አዳዲስ የማዘውተርያ ስፍራዎችን መገንባት፣ ነባሮችንም በማደስና በመጠገን ወደ ሥራ ማስገባትና ያሉባቸውን ችግሮች መፍታትም ቁልፉ ሥራ ይሆናል:: በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ቢሮው 7 አዳዲስ የማዘውተርያ ስፍራዎችን መገንባቱንና አምስቱን ማደሱን በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል::

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፤ ስፖርቱ ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን በመደበኛነት ማስፋፋት ማልማትና አዳዲስ መገንባትና ነባሮችን ማደስ ቢሮው እንደ ቁልፍ እቅድ መያዙን ያብራራሉ:: ባለፉት አራት ዓመታት 510 የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግም ተሞክሯል::

ትልልቅ ስታዲየሞችን ኢንተርናሽናል ደረጃ እንዲይዙ ለማድረግ እየተሠራም ነው:: ከመንግሥት በጀት በተጨማሪም ባለሀብቱን በማስተባበር የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን በማልማትና በመገንባት ወጣቱ አላስፈላጊ ስፍራ እንዳይገኝና ተተኪ ስፖርተኞች እንዲፈጠሩ ለማድረግም እቅድ ተይዟል:: የሁሉም ስፖርቶች ማጠንጠኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ነው ምክንያቱም ታዳጊዎች፣ ወጣቶችና ክለቦች ልምምድ የሚሰሩበት ውድድር የሚያደርጉበት የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ አስፈላጊ ይሆናል:: እነዚህም የሁለት በአንድ፣ የሶስት በአንድ እና የጥርጊያ ሜዳዎች በየአካባቢው እንዲለሙ በፍጥነት በመገንባት ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በስፋት መሠራታቸውንም ጠቅሰዋል::

ከስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ጋር ተያይዞ የተከናወኑ ስራዎች የመኖራቸውን ያህል ጉደለቶችም እንዳሉ ያነሱት አቶ በላይ፤ ለምተው ለአገልግሎት የሚተላለፉ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ከአጠቃቀም ጋር በተያያዘ ለታለመላቸው ዓላማ ከማዋልና ለአገልግሎት ክፍት ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ይገልጻሉ:: እነዚህን ክፍተቶች ለመመለስ ጥናቶች እንደተጠናቀቁና በየደረጃው ባለው ተቋም አሠራርና ሕግ ከጸደቁ በኋላ ወጥነት ባለው መንገድ ወደ ሥራ እንደሚገባም ተመላክቷል::

ቦታዎቹ እንዴት ይተዳደሩና በማን መተዳደር እንደለባቸው በጥናት ከተለየ በኋላ ሥራቸውን በአግባቡ መሥራትና ለታለመላቸው ዓለማ እንዲውሉ ይደረጋልም ብለዋል:: የሀገርን ባንዲራ በዓለም አደባባይ ለማውለብለብ የተተኪ ስፖርተኞች ሚና ወሳኝ በመሆኑ ይህ በሁሉም የከተማው ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች የታዳጊ ፕሮጀክቶችና ወጣቶች ውድድር ደረጃና ጥራታቸውን የጠበቁ የሚሆኑት ወጣቶችን ሲያሳትፉ በመሆኑ ከአገልግልግሎት አሰጣጥ ጋር መታረምና መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች በዓመቱ በትኩረት ይሠራሉ::

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2016

Recommended For You