
ምድር ገሀነብ የሆነችባቸው ሕፃናት፤ ከውጭ ሲያዩት ሠላማዊ በሚመስለው ሆስፒታል ውስጥ እዚህም እዚያም ተኝተዋል። ከብላቴንነታቸው፤ ከማሕፀን ብቅ ከማለታቸው ሕይወት ፍሟን አርገብግባ፤ ውሃዋን አፍልታ ዕምቡጥ ገላቸውን የተቀበለቻቸው ናቸው። በአርባ ምንጭ ከሆስፒታሉ የቃጠሎ ሕክምና ክፍል ይህ ትዕይንት እንግዳ አይደለም።
በማዕከሉ የቃጠሎ ሕክምና ክፍል ካገኘናቸው አንዷ ሕፃን ሮሐማ ኢንድርያስ ትበላለች። የአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ጨቅላ ነች። ዕምቡጥ ገላዋ ነድዶ በነጭ ፋሻ ተጀቡኗል። ከትክሻዋ ገደማ ተነስቶ እስከ ጭኖቿ በፈላ ውሃ ነፍራለች። የእስትንፋስ ማገዣ ተደርጎላታል። የተዥጎረጎረ ገላዋ በተንፈቀፈቀበት የፈላ ውሃ እንደቲማቲም መላላጡን አይደብቅም። ያንጨረጨረውን የፍም እሳት መርገምት ዓይን አውጥቶ ይናገራል።
የሕፃን ሮሐማ እናት ሕይወት ፅዶላ አርባ ምንጭ አካባቢ ነው የሚኖሩት። የቤት ውስጥ ሥራዎችን እየሠሩ ነበር። ውሃ እያፈሉ፤ ጎን ለጎን ሌላም ሥራ እየከወኑ። የፈላ ውሃቸውን ከምድጃ አውርደው ለሌላ ሥራ ደጅ ይወጣሉ። በዚህ አጋጣሚ ነበር ጨቅላ ልጃቸው ሮሐማ ከመደብ ተንሸራትታ የፈላ ውሃ ውስጥ የገባችው። የጨቅላ ልጃቸውን እሪታ ሰምተው ሮጠው የገቡት እናት ያዩትን ማመን አልቻሉም። ልጃቸው በፈላ ውሃ ነፍራለች።
በአርባ ምንጭ አካባቢ ነዋሪዎች ዘንድ ይህ የጨቅላ ሮሐማ ገጠመኝ ብቻ አይደለም። ብላቴና እንዳልከው ጌቱም የዚህ ገፈት ቀማሽ ነው። ሙሉ አካሉን ይዞ መጥቶ ሕይወት በእሳት ያጎደለችው የአንድ ዓመት ሕፃን በሚድህበት ጊዜ ቤት ውስጥ ከሚነድ ምድጃ ተንሸራቶ ገብቶ ነው ቃጠሎ የደረሰበት። ሕፃኑ በተለይ ሁለቱ እግሮቹ እንደማገዶ ጨሰዋል፤ ተቃጥለዋል። በዚህም ሕፃን እንዳልከው በአርባ ምንጭ ሆስፒታል ቃጠሎ ሕክምና ማዕከል ለሰባት ወራት ያህል ተኝቶ እየታከመ ነው።
እናት አቴነሽ ማና በአካባቢው አልነበሩም። ልጃቸውን ለቤት ሠራተኛ አምነው ሰጥተው ነበር። አደራ የተቀበለችው ሠራተኛ እንቅልፍ በጣላት አፍታ ነው ሕፃኑ እሳት ውስጥ የገባው። ጎረቤት ተሯሩጦ ልጁን ወደ ሆስፒታል ባያመጣው ኖሮ ጉዳቱ የከፋ ይሆን እንደነበር ይናገራሉ።
ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገዱት እግሮቹም መንቀሳቀስ፤ መታጠፍና መዘርጋት መጀመራቸውን ያነሳሉ። ምስጋና ለሕክምና ባለሙያዎች እና ስፔሻሊስቶች ይሁንና አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እናት ያስረዳሉ።
ታዳጊ ቤተልሄም ዓለሙ ሌላዋ የ14 ዓመት ገደማ ጉብል ናት። ሙሉ ፊቷ ያልጠገገ የእሳት ለምፅ ይታይበታል። ዓይኖቿ በተዓምር ይትረፉ እንጂ አፍንጫዋና ቅንድቧ በፍም ሟምተዋል። ከንፈርና ፀጉሯ፤ ሽፋሽፍትና ጆሮዎቿ እላዩዋ ላይ ከስለዋል። ለጋነት ብቅ ከማለቷ በነዲድ እሳት ከስማለች።
ታዳጊ ቤተልሄም የሚጥል በሽታ አለባት። ኩሽና ውስጥ የዕለት ሥራዋን እየከወነች ነበር። እሳቷን አቀጣጥላ ጉድ ጉድ በምትል ጊዜ ነው እሳት ላይ የወደቀችው። ለእሳት የተዳረገችው በቤት ማንም ባልነበረበት ወቅት ነውና ለደቂቃዎች በፍም እሳት ተቃጥላለች።
አረመኔው እሳት ያከሰመው የለጋነት ፊቷንና ፈገግታዋን ብቻ አልነበረም። ሲሦ የሚጠጋውን ለጋ አካሏን አዳርሷል። ምሥጋና ለሆስፒታሉ የዘርፉ ስፔሻሊስቶች ይግባና ከሌላ የአካል ክፍሎቿ ላይ እየተወሰደ እንድታገግም እየታገዘች ትገኛለች። ከሁለት ወራት ተኩል ሕክምና በኋላም ጥሩ መሻሻሎች ላይ ደርሳ መንቀሳቀስ ሁሉ ጀምራለች።
ዶክተር ኤፍሬም ጋሻው ጀነራል ሰርጀሪ እና ፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ሰብ ስፔሻሊቲ ሰርጀሪ ባለሙያ ናቸው። በአርባ ምንጭ ሆስፒታል የቃጠሎ ሕክምና ማዕከል እያገለገሉ ነው የሚገኙት።
የቃጠሎ ሕክምና ዘርፍ ትኩረት የተነፈገው ነው። ለዚህም ማሳያ በሆስፒታሎች የቃጠሎ ሕክምና ማዕከል አለማቋቋማቸው እና የባለሙያዎች በብዛት ያለመኖር ይላሉ ባለሙያው። በሀገሪቱ ከ50 የማይበልጡ የዘርፉ ስፔሻላይዝ መኖራቸውንም እንደማሳያ ያነሳሉ።
መንግሥት ትኩረት የነፈገው ዘርፍ ከመሆኑም ሌላ ሕክምናው ረጂም ጊዜን የሚፈልግ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ እንዳይገባበት ያደርገዋል ባይ ናቸው።
የቃጠሎ ሕክምና ዘርፍ ትኩረት ባለመሰጠቱ በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ይደርሳል ይላሉ። የሕክምና ማዕከሉ በአካባቢው የሚገኝ ብቸኛው በመሆኑ የቃጠሎ ሕክምና ተገልጋዮች እንደሚበዙም ይናገራሉ። በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ከሚገኙ በርካታ ሆስፒታሎች ሪፈር ተፅፎላቸው የሚመጡ ታካሚዎች ብዙ መሆናቸውንም ያብራራሉ።
በቃጠሎ በተለይ ሕፃናት እና የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ተጋላጭ እንደሆኑ የሚናገሩት ዶክተር ኤፍሬም፤ ለቃጠሎ ሕክምና ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡትም 70 በመቶ የሚሆኑት ሕፃንነት ዕድሜ ውስጥ ናቸው። የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎችም በዚሁ ልክ ተጋላጮች ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ።
የቃጠሎ ሕክምና በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ቢሆንም እንኳን ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማለትም ሕፃናትንና የሚጥል በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ልዩ ጥንቃቄ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ይመክራሉ። ቃጠሎ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ አደጋው የደረሰባቸውም በፍጥነት ወደ ሕክምና መሄድ ይኖርባቸዋልም ይላሉ።
በአርባምንጭ ሆስፒታል የቃጠሎ ሕክምና ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት ተመስገን አሸብር የዶክተር ኤፍሬምን ሃሳብ ይጋራሉ። ዘርፉ ትኩረት የተሰጠው ባይሆንም በሆስፒታሉ የቃጠሎ ሕክምና ማዕከል ተመስርቶ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ነው የሚያነሱት።
በሁለት ዓመት ገደማ ውስጥም ሆስፒታሉ ማዕከሉን ካቋቋመ 300 የሚጠጉ የቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሕክምና ሰጥቷል ይላሉ። ከሲዳማ እና ኦሮሚያ አጎራባች ክልሎች የመጡትን ጨምሮ የክልሉን ሕዝብ እያገለገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ታካሚዎች አብዛኞቹ ሕፃናት ናቸው። በዚህ ምክንያትም ሃኪሞች በሕክምና ጊዜ እንደሚቸገሩ ገልጸው፤ የሕክምናውን መንገድ አዘምኖ ህመም አልባ የማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ያብራራሉ። የማዕከሉን ታካሚዎችን የመቀበል አቅም ለማስፋትም እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም አጫውተውናል።
በሀገሪቱ ያለው የእሳት አደጋን የመከላከል አቅም ግንባታ እምብዛም በሆነበት በዚህ ዘመን ተጋላጮቹ ሕፃናት እና የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ናቸው እና እንዲህ መሰል የቃጠሎ ሕክምና ተቋማት ሊስፋፉ ቢችሉ ትውልድን ማዳን ይሆናል። በእርግጥም መሰል የሕክምና ማዕከላትን ማስፋፋት ለዕንቡጦች የቃጠሎ መድህን ማዘጋጀት እንደሆነ የሚቆጠር ነው።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም