ምርትንከብክነትየሚታደገውየበቆሎመፈልፈያማሽን

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የህብረተሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ አዳዲስ፣ ችግር ፈቺና እሴት የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ረገድ በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ:: በየዓመቱ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የፈጠራ ውጤቶች በሰልጣኞችና በአሰልጣኞች አማካይነት ተፈጥረው እየተጎበኙ፣ አልፎም ተርፎ የፈጠራ ውጤቶቹን ለሚያስፋፉ አካላት እየተላለፉ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል::

የፈጠራ ውጤቶችን ከሰሩት መካከልም የድሬዳዋ ሻሎም ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ አሰልጣኝና የወርክሾፕ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ሽፈራው ይገኙበታል፤ እሳቸው የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን ነው ያሰሩት:: አቶ ሙሉቀን እንደሚሉት፤ የህብረተሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ በርካታ የፈጠራ ሥራዎች ተሰርተዋል:: ከእነዚህ ውስጥ በእሳቸው የተሰራው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀው በ3ኛው የክህሎት ውድድር ላይ የቀረበው በሰው ኃይል የሚሰራ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን አንዱ ነው::

ይህ የፈጠራ ሥራ ምንም ዓይነት ኃይል (የኤሌክትሪክ ኃይል ወይም ነዳጅ) አይጠቀምም:: ይህም ከውጭ ሀገራት ከሚገባው የበቆሎ መፈልፈያ ለየት ያደርገዋል:: ከውጭ በውድ ዋጋ የሚገባው የበቆሎ መፈልፈያ በኤሌክትሪክ ኃይል ወይም በነዳጅ አልያም ከሁለቱ በአንዱ አማራጭ የሚሰራ ነው:: አዲሱ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን ግን በሰው ኃይል ብቻ የሚሰራ ስለሆነ ለኤሌክትሪክ ኃይል ወይም ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ የሚያስቀር ነው::

ይህንን የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን ለመስራት ያነሳሳቸው ዋነኛ ምክንያት በቆሎ በሀገራችን በስፋት መመረቱ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሙሉቀን፤ በተለይ በምስራቁ የሀገራችን አካባቢ ከሁሉም የአዝዕርት ዓይነት በላይ በስፋት የሚመረት እና አመራረቱም ባህላዊ መንገድ የሚከናወን በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ:: የበቆሎ ምርት በስፋት ይመረት እንጂ በሚመረተው ልክ ምርቱን መሰብሰብ እንዳልተቻለም ይጠቁማሉ:: አርሶ አደሩ ምርቱን ለመሰብሰብ የሚጠቀመው በሰው ኃይል ወይም በእንስሳት በባህላዊ መንገድ ስለሆነ ምርቱ በአግባብ ለመሰብሰብ እንደሚቸገር ጠቅሰው፤ በዚህ ሂደትም ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው የበቆሎ ምርት ለብክነት እንደሚዳረግ ይናገራሉ:: ይህ ደግሞ በአካባቢያቸው የሚመለከቱት በምርት አሰባሰብ ሂደት የሚፈጠረውን የምርት ብክነት እና የአርሶ አደሩ ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ችግር ፈቺ ፈጠራ ለመስራት መነሳሳታቸውን ይገልጻሉ::

አዲሱ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን የበቆሎ ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት የሚባክነውን ምርት ለማስቀረት የሚያስችል ነው:: ከዚህ በተጨማሪም በባህላዊ መንገድ ለማምረት የሚያስፈልገው ብዛት ያለው የሰው ኃይል እና የሚወስደውን ጊዜ በመቆጠብ በተሻለ መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርትን የሚያመርት ጉልበትን የሚቆጥብ ማንም ሰው በቀላሉ ሊሰራ የሚችለውን የፈጠራ ሥራ መሆኑን አስረድተዋል::

ይህ ማሽን የተሰራው በአካባቢው ላይ በቀላሉ ከሚገኙ ብረት ነክ ቁሳቁስ እንደሆነ ይናገራሉ:: ማሽኑ በሰው ኃይል በማሽከርከር የሚሰራ ሲሆን፤ በሰዓት የሚያመርተው መጠን እንደሚያሽከረክረው ሰው ፍጥነት ይለያያል:: በፍጥነት የሚያሽከርክረው ሰው በሰዓት ውስጥ ብዙ ያመርታል፤ ፍጥነቱን ቀነስ አድርጎ በመጠኑ የሚያሽከረክር ከሆነ ደግሞ የሚያመርተው በዚያው ልክ ይሆናል:: የማምረት ሂደቱ እንደየሰዎቹ የማሽከርከር አቅም የሚወሰን ቢሆንም፤ አንድ መካከለኛ አሽከርካሪ ነው ተብሎ የሚገመት ሰው እንኳን ከአንድ ደቂቃ እስከ አምስት ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ እስከ 20 ኪሎ ግራም በቆሎ በመፈልፈል ማምረት እንደሚችል ይገልጻሉ:: በተመሳሳይ ፈጣን የሆነ አሽከርካሪ ከሆነ ደግሞ በደቂቃ እስከ 20 ኪሎ ግራም ማምረት የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፤ አመራረቱ እንደየሰው አጠቃቀም የሚለያየ መሆኑን አብራርተዋል::

አቶ ሙሉቀን እንደሚሉት፤ በቆሎውን ወደ ማሽኑ ለማስገባት የሰው ኃይል ሳያስፈልግ ማሽኑ በተቀመጠለት የስበት ኃይል አማካኝነት ወደ መፈልፈያው እንዲገባ ይደረጋል:: በቆሎ ወደ ውስጥ ከገባ በኋላ ሲሽከረከር በማሸት ፍሬውን ከቆረቆንዳው ላይ ያላቅቃል፤ ከዚያም በኋላ ፍሬው በአንድ በኩል፣ ቆረቆንዳው ደግሞ በሌላኛው በኩል ይወጣል:: በዚህ አመራረት ሂደት ምንም አይነት የምርት ብክነት የለም:: ቆረቆንዳውም ቢሆን ለከብቶች መኖ ሊውል የሚችል ነው:: በተለይ ለወተት ተዋጽኦ ምርት እንስሳት ዋንኛ የመኖ ግብዓት ስለሚሆን አካባቢን አይበክልም፤ ምንም የሚጣል ነገር የለም:: በፍጥነት ብዙ ምርትን በመስጠት ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ይቆጥባል::

ከውጭ የሚገባውን መተካት የሚችል በመሆኑ የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት ረገድ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው የሚሉት አቶ ሙሉቀን፤ ማሽኑ በብዛትና በጥራት ተመርቶ አርሶ አደሩ ጋር ተደራሽ እንደሆነ ይናገራሉ::

ይህ የፈጠራ ሥራ ለሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ከሆነ በኋላ የውስጥ ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ወደውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪን ሊያስገኝ የሚችል እንደሆነ አመላክተዋል:: ‹‹ይህ ማሽን ሲታይ ቀላል እንደሆነ ይታሰባል እንጂ በተለይ በአብዛኛው በግብርና ሥራ የሚተዳደር ሕዝብ ባላት የእኛ ሀገር አስፈላጊነቱ በእጅጉ የላቀ ነው›› የሚሉት አቶ ሙሉቀን፤ አርሶ አደሩ ከባህላዊ የአመራራት ዘዴ ወጥቶ ይህ ማሽን ቢኖረው ወይም ደግሞ ሁለት ሦስት ሆነው በሕብረት ገዝተው ቢያመርት በብዙ መልኩ ውጤታማ መሆን ይችላሉ ይላሉ:: ይህ ሲባል ደግሞ ለአርሶ አደሩ ድካም የሚያስቀር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ከሀገር አንጻር ያለው ጠቀሜታ ጉልህ እንደሆነ ይናገራሉ::

የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኑ በድሬዳዋና አካባቢዋ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ተደርጎ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል የሚሉት አሰልጣኙ፤ ማሽኑን የገዙ አርሶ አደሮችን ለራሳቸው ከመጠቀም ባለፈ ለሌሎች እያከራዩ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ይላሉ:: ማሽኑ ተነቃቃይና ተገጣጠሚ ስለሆነ ካለበት ቦታ ላይ አንቀሳቅሶ የትም ቦታ ላይ ወሰዶ መጠቀም እንደሚቻል ይናገራል:: አርሶ አደሩ ለሌላው ለማዋስም ሆነ ለማከራየት በሚፈልግበት ወቅት ነቃቀሎ በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ለማዘዋዋር እንደሚችል ይገልጻሉ::

አሰልጣኙ እንደሚሉት፤ ማሽኑ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ስለማሽኑ አጠቃላይ ሁኔታ አስመልክቶ ከተጠቃሚ አርሶ አደሮች መረጃዎች መሰብሰብ ችሏል:: ቀደም ሲል በነበረው ተሞክሮ አንድ ፈጠራ ተሰርቶ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ስለ ፈጠራ ሥራው መረጃ ይሰበሰባል:: ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ከአርሶ አደሩ ግብዓቶችን በመሰብሰብ እንዲሻሻል ይደረጋል:: ከዚያ መሻሻል ያለበት ነገር ካለ እንዲሻሻል ይደረጋል:: በዚህም መሠረት ቀደም ሲል ይህንን መሰል በተወሰነ መልኩ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን ተሰርቶ ነበር:: ነገር ግን ተጠቃሚው አርሶ አደሩ በሰጠው አስተያያት ሙሉ ለሙሉ በማንዋል በሰው እጅ የሚሰራ እንዲሆን ተደርጓል:: በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራው ከማንዋሉ አንጻር ሲታይ በጥሩ ሁኔታ ይፈለፍላል፤ ጥሩ ምርት ያመርታል፤ ፍጥነትም አለው:: ነገር ግን በሚጦዝበት ጊዜ በቆሎውን የሚሰባብርበት ሁኔታ ስላለ የተሰባበር የበቆሎ ፍሬ ደግሞ ለዘር ስለማይሆን ያ ቀርቶ በዚኛው ማሽን እንዲተካ ሆኗል::

‹‹አርሶ አደሩ ከምርቱ ላይ ለሚቀጥለው ጊዜ የሚሆነው ዘር ማስቀረት ስለሚፈልግ ይህንን ማሽን በጣም ወዶት ይጠቀምበታል›› የሚሉት አሰልጣኙ፤ በአዲሱ ማሽን የሚመርተው ምርት ለዘርም ሆነ ለገበያ፣ ለምግብ ፍጆታ ለሚፈልገው አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችለው እንደሆነ ይናገራሉ::

ይህ የፈጠራ ሥራ በቅርብ ጊዜ የተሰራ እንደመሆኑ መጠን በድሬዳዋ አካባቢዎች ላሉ አርሶ አደሮች እና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ተደራሽ ተደርጎ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው:: ማሽኑ ቀደም ሲል ባለው የዋጋ ተመን ከ30ሺ እስከ 40 ሺ ብር ይሸጥ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የብረት ዋጋ ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ማሽኑን ለመሥራት የሚወጣው ወጪን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአሁኑ ጊዜ በ55ሺ ብር እንደሚሸጥ ይናገራሉ:: ‹‹ማሽኑ የሚሰራው ከጠንካራ ብረቶች ስለሆነ ቶሎ ሊበላሽ የሚችል አይደለም::

ረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው:: ስለሆነም አርሶ አደሮች ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በአንድነት ሲገዙት ብዙ ድካም፣ ልፋትና ጊዜ የሚቆጥብ በመሆኑ በእጅጉ ጠቃሚ ነው:: አሁን ላይ ገዝተው እየተጠቀሙበት ያሉት አርሶ አደሮች እንደሚሰጡት አስተያየት ከሆነ ከዚህ ቀደም ከሰጠናቸው በቆሎ መፈልፈያ ማሽን አንጻር ይሄኛውም ማሽን እንደወደዱት የሚያሳይ ነው:: ከዚህ ባለፈ የሌሎች አዝርዕቶችን ምርት መሰብሰብ የሚያስችል የፈጠራ ሥራ ሰርተን እንድናቀርብላቸው ይጠይቃሉ›› ብለዋል::

የድሬዳዋ ሻሎም ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሟሉ ማሽነሪዎች ያሉት ሲሆን፣ የሰውን ኃይል ጨምሮ ይህን ማሽን በሀገሪቱ ለሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አቶ ሙሉቀን ይናገራሉ:: ከድሬዳዋ አካባቢ ውጭ ያሉ አርሶ አደሮች ማሽኑን ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው እየገለጹላቸው መሆናቸውን ተናግረው፣ እሳቸውም ማሽኑን እያመረቱ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ለማዳረስ እየሰሩ እንደሚገኙም ይናገራሉ:: በቀጣይ በርከት ያሉ ማሽኖችን በማምረት ለሁሉም አካባቢዎች እንዲዳረስ ለማድረግ እቅዱ እንዳላቸው አመላክተዋል::

ከዚህ በተጨማሪም ኮሌጁ ሌሎች የግብርና ሥራን ሊያቀሉ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ነው የሚናገሩት:: ለአብነትም ሲጠቅሱ የወተት መያዣ፣ ቅቤ መናጫ እና የመሳሰሉ የፈጠራ ሥራዎችን የአርሶ አደሩን ልፋትና ድካም ሊቀንሱ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመፍጠር ለአርሶ አደሩ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ::

ይህ ማሽን ለአርሶ አደሩ ተላልፎ ዝም ብሎ የሚተው ሳይሆን፣ አርሶ አደሩ እንዴት መጠቀም እንዳለበት፤ በምን መልኩ መያዝ እንዳለበትና መሰል ማድረግ ያለበት ጉዳዮች አስመልክቶ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉም ይናገራሉ:: የፈጠራ ሥራዎቹም ከተሰሩ በኋላ ጥራታቸውና ደረጃቸው በመቆጣጣሪያ መሳሪያ ተፈትሾና ተረጋግጦ እንዲሁም በባለሙያ ተጠንቶ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰጥ ይናገራሉ:: ከአርሶ አደሩ በሚሰበሰበው ግብረ መልስ መሠረትም መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ታይተው እንዲሻሻሉ እንደሚደረግ አስረድተዋል::

አቶ ሙሉቀን እንደሚሉት፤ ማሽኑ ነዳጅ ስለማይጠቀም ምንም ዓይነት አካባቢ ሊበክል የሚችል ነገር የለውም:: የሚጣል ተረፈ ምርት የለውም ከፍሬው ጀምሮ እስከ ቆረቆንዳው ጥቅም ላይ ይውላል:: የሚያስከትለውም የጎንዮሽ ጉዳት የለም:: ለአጠቃቀም በጣም ቀላል ነው:: እስካሁን ተደራሽ ከሆነባቸው አካባቢዎች የቀረበ ቅሬታ የለም::

እንዲህ ዓይነት የፈጠራ ሥራዎች የሚሰሩት ከህብረተሰብ ችግር በመነሳት ችግሮችን ለመቅረፍ ታሰቦ ነው የሚሉት አቶ ሙሉቀን፤ ይህም ሆኖ ግን የተሰሩ የፈጠራ ሥራዎችን ህብረተሰቡ አይቶና ተረድቶ አምኖባቸው እንዲጠቀምባቸው ለማድረግ ብዙ ጊዜ እንደሚፈጅ ይናገራሉ:: እስካሁን ድረስ በኮሌጁ ብዙ ዓይነት የህብረተሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ሥራዎች ቢሰሩም ህብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽ ሆነው እንዲጠቀምባቸው ለማድረግ ብዙ ሥራዎች እንደሚጠይቁ ጠቅሰው፤ ብዙ ዓይነት የህብረተሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ሥራዎችን ሰርቶ ተቀባይነት ሲጠፋና በፋይናንስ የሚደግፍ አካል ሳይኖር ሲቀር ደግሞ የፈጠራውን ሥራ የሚሰራው አካል ለሌሎች ተጨማሪ የፈጠራ ሥራዎች እንዳይነሳሳ በማድረግ ወደኋላ እንዲመለስ እንደሚመለሰውም አመላክተዋል::

ህብረተሰቡ ለፈጠራ ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እንዲጠቀምባቸው በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል የሚሉት አቶ ሙሉቀን፤ ችግሩን ሊቀርፉ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን ጥቅም በሚገባ ተገንዘቦ ተጠቃሚ ቢሆን ጊዜና ጉልበት በመቀነስ የሚፈለገው ሥራ ላይ ማዋል ይቻላል ብለዋል:: በተለይ ይህ የፈጠራ ውጤትም ሆነ ቴክኖሎጂ በሁሉም አካባቢዎች በማስፋፋት ለህብረተሰቡ በስፋት እንዲደርስ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2016

Recommended For You