የመኸር ወቅት እርሻ ሥራ አበረታች ውጤት

ኢትዮጵያ በዓለም በግብርና እና በምግብ መስክ ጥሩ የአየር ንብረት እና ጂኦግራፊያዊ ሁኔታ፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬት እና የተትረፈረፈ የውሃ ሀብቶች ካሉባቸው ጥቂት የዓለም ሀገራት አንዷ እንደሆነች ይገለጻል። ሀገሪቱም እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም በ2023 በግብርናው ዘርፍ በዓለም ላይ ካሉ አምስት ታላላቅ አምራች ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ማቀዷን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህን ዕቅድ ለማሳካትም የበጋ መስኖ ሥራን ጨምሮ በዘርፉ በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት አበረታች ውጤት እንደሚጠበቅ ጠቁሟል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሰሞኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን አስታውቋል። በቀጣይም የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከማዳበሪያ ዝግጅትና ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር ተያይዞ እንዲሁም በሰብል እንክብካቤና በሌሎችም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጿል። በ2015/16 የምርት ዘመን የተሻለ ውጤት እንደሚመዘገብም ተመላክቷል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶክተር) የበልግ እርሻ ወቅት አፈፃፀምን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ በ2015 ዓ.ም የበልግ እርሻ በነበረው የዝናብ ሥርጭት በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች (በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ ደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች) ጥሩ ጊዜ ነበር። በዚህም ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ በዋና ዋና ሰብሎች (በስንዴ፣ በበቆሎ፣ በገብስ፣ በማሽላ እና በሌሎች ሰብሎች) ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል፡፡

እስካሁን ባለው ጊዜ በሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ያለ አዝመራ መሰብሰቡን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ከዚህም ከ48 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል ብለዋል። አዝመራው በአሁኑ ወቅት ተሰብስቦ እንዳላለቀና ያልታወቀ ምርት እንዳለም ተናግረው፣ የምርት መጠኑ ሊሻሻልና ሊጨምር እንደሚችል ነው ያመላከቱት። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለው ግምገማ መሠረት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በዘንድሮ በጀት ዓመት የበልግ ወቅት በመሬት ስፋትም ሆነ በምርት ይዘት ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

የ2015/16 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት የግብርና ሥራ የተሻለ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፤ በዚህ የምርት ዘመን የመኸር ወቅት 17 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት አካባቢ ለማረስ ታቅዶ 18 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከዕቅድ በላይ ማረስ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህ አሃዝ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው አመልክተው፣ ለዚህም አንዱ ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ክልል በመኸር ወቅት በዘር ያልተሸፈነው አንድ ሚሊዮን ሄክታር አካባቢ መሬት ዘንድሮ በዘር በመሸፈኑ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሁለተኛው ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ከሚታረሰው መሬት ተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነበት ዓመት በመሆኑ ነው ብለዋል።

በመኸር ወቅት 17 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን መቻሉን ጠቅሰው፣ በዚህም ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል። በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታሩ በክላስተር ወይም በኩታ ገጠም እርሻ መሸፈኑን አመላክተዋል። ኩታ ገጠም ወይም ክላስተር ባለፈው ዓመት ስድስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ እንደነበረ አስታውሰው፤ በእዚህ ዓመት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ጭማሪ ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ ምርታማነትን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ባለፉት ዓመታት የተጠናከረ ሥራ ተሰርቷል። በተለይም የኩታ ገጠም ወይም የክላስተር እርሻ እየሰፋ መጥቷል። ይህም በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፤ አርሶ አደሩ ለፍጆታ ከሚያመርተው ምርት ባለፈ ቴክኖሎጂንና የተለያዩ የግብርና ሜካናይዜሽኖችን በመጠቀም ተሰባስቦ ማምረቱ ለኢንዱስትሪና ለኤክስፖርት ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ማምረት አስችሎታል። ይህም በኢትዮጵያ ግብርና አሰራር ሥርዓት ውስጥ ከተመዘገቡ ለውጦች መካከል አንዱና ወሳኝ ለውጥ ተብሎ ሊወሰዱ ይችላል፡፡

የኩታ ገጠም እርሻ ተጠናክሮ የቀጠለና ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር የደረሰ ቢሆንም ሜካናይዝድ ሆኖ በትራክተር የታረሰው መሬት አራት ሚሊዮን ሄክታር ብቻ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሜካናይዜሽን ላይ ገፍቶ መሄድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ ኩታ ገጠም እርሻ መሬትን ለሜካናይዜሽን የተመቻቸ ያደርጋል። ትራክተርና ኮምባይነር ያላቸው የተበጣጣሰና የተራራቀ ቦታ ላይ ከመሥራት ይልቅ አንድ ቦታ ላይ 100 እና 50 ሄክታር ቦታ ላይ ለመሥራት ያስችላቸዋል። ይህም የማሽነሪ ፍላጎት እንዲጨምር ያደርጋል። ሜካናይዜሽኑ አሁንም ግማሽ ላይ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ለዚህም ተጨማሪ የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎችን ማስገባትና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ሥራዎች በቀጣይነት መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡

ከሜካናይዜሽን አንጻር በየዓመቱ መሻሻል ስለመኖሩ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ባለፈው ዓመት ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት አካባቢ በሜካናይዜሽን መታረሱን አስታውሰዋል። በዘንድሮው በጀት ዓመት የአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ጭማሪ በማሳየት አራት ሚሊዮን ሄክታር አካባቢ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

የተመዘገበው ለውጥ በቂ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከዚህም በላይ ፈጥኖ እንዲሄድና የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል። ለተመዘገበው ውጤትም ከአመራሩ እስከ አርሶና አርብቶ አደሩ ድረስ የጋራ ግንዛቤ ፈጥሮ ወደ ሥራ መግባቱ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ የ2015/16 የመኸር እርሻ ሥራ እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት የታየበት መሆኑን ዶክተር ግርማ አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት የሰብል እንክብካቤና ጥበቃ ሥራ ትኩረት እንደሚፈልግ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። በዘር የተሸፈነው 17 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት አዝመራ እስኪደርስና እስኪሰበሰብ ድረስ አስፈላጊው ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የአረም ቁጥጥርና ክትትል ሥራው እንዲጠናከር እንዲሁም በምርት አሰባሰብ ወቅት የምርት ብክነቶች እንዳይፈጠሩ መሥራት የግድ እንደሆነ አመላክተዋል።

 በተለይም ድንበር ዘለል ሰብል አጥፊ እንደ በረሃ አንበጣ እና ግሪሳ ወፍ የመሳሰሉትን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራው በባህላዊ መንገድ እንዲሁም በአውሮፕላን በታገዘ ርጭት እየተሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት የበረሃ አንበጣን ሙሉ ለሙሉ በመከላከል በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደተቻለ ነው የተናገሩት።

ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ ይህ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ በቀጣይነትም መሠራት ይኖርበታል። የበረሃ አንበጣው ከሀገር ውስጥ ብቻ የሚነሳ ባለመሆኑና ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጭምር የሚነሳ በመሆኑ ከክልሎች ጋር በሚደረግ ጠንካራ የቅንጅት ሥራ ወደ መሀል ሀገር እንዳይመጣ የመቆጣጠርና የመከላከል ሥራ ተሰርቷል። ይህም ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የበረሃ አንበጣ ክስተቱ የተወሰኑ ክልሎችን መነካካቱን ገልጸው፣ እነሱም አፋር፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ድሬዳዋና ሶማሌ አጎራባች የሆኑ ክልሎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ የግብርና ሚኒስቴር ክትትል ከሚያደርጋቸው ሰብል አጥፊዎች መካከል ግሪሳ ወፍ አንዱ ነው። ግሪሳ ወፍ እንደ ወፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝና የብዝሃ ሕይወት አንድ አካል መሆኑ ይታወቃል። ይህ ወፍ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኝ ሲሆን፣ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ በብዛት ይገኛል። እነሱም በቀድሞው ደቡብ ክልል በአሁኑ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞንና ጉራጌ ዞን አካባቢዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞኖች፣ በአርሲ ዝዋይ ዱግዳ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ሸዋሮቢትና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች ግሪሳ ወፍ በብዛት ይገኛል። ወደ ምስራቅ አካባቢም እንዲሁ ባቢሌና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በስፋት ይታያል፡፡

የግሪሳ ወፍ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመከላከል ሥራ እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በእነዚሁ አካባቢዎች ማለትም በአማራ ክልል፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችና ባቢሌ አካባቢ የመጀመሪያው ዙር ርጭት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል። በአማራ ክልል ሁለተኛው ዙር ርጭት እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ የግሪሳ ወፍን የመቆጣጠርና የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ሚኒስትሩ ግሪሳ ወፍ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ ርጭት እንደማይደረግ አስታውቀው፣ በቅድሚያ ባለሙያዎች በሚያደርጉት ጥናት መሠረት የግሪሳ ወፍ ስበስቡ አስጊ መሆን ተረጋግጦ ጥናቱ በሚኖረው ውጤት መሠረት እንደሚረጭ አስረድተዋል። ከአቅም በላይና ከመጠን ያለፈ ካልሆነ በስተቀር በአርሶ አደሩ አቅም በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራው እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

መደበኛው የሰብል እንክብካቤ የማረምና የእጽዋት ጥበቃ ሥራ በክልል ደረጃ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ሚኒስትሩ አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት ያለው የመኸር ሁኔታ አበረታች ውጤት የታየበት እንደሆነም ገልጸው፣ የተሻለ የሰብል ግምገማ እንዳለም ከመስክ ጉብኝት መረዳት መቻሉን ተናግረዋል። ይህን ውጤታማነት ለማስቀጠል ምርቱ ተሰብስቦ እስኪጠቃለል ድረስ ተከታታይ የሆነ ክትትል ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡

በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በሰሜን በተወሰነ መጠን፣ በሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች የዝናብ መቆራረጥ፣ የመጠን መቀነስና እጥረት ስለሚያስከትለው ተጽዕኖ የግብርና ሚኒስቴር የሚደርሱት ሪፖርቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ይህንንም ከግንዛቤ ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል። በዚህ ላይ ከክልሎች ጋር በመወያየትና በመተባበር ችግሩ ምን ያህል ሊሰፋ ይችላል የሚለውን ለማወቅና ለመከላከል ከወዲሁ የዳሰሳ ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት ጥናቱ የተሟላ ባይሆንም በቀጣይነት ችግሩን መከላከል ይጠቅማል ሲሉ ገልጸው፣ በተለይም ከአደጋና ስጋት መከላከል ጋር በመሆን ከዝናብ መቆራረጥና እጥረት አንጻር ሙሉ ለሙሉ ከምርት ውጭ ሊሆኑ የሚችሉ አካባቢዎች ካሉ የመለየትና የመደገፍ ሥራ ይሰራል ብለዋል። ከዚህ አንጻር ከተሠሩ ሥራዎች መካከል አንዱ የመስኖ ሥራ እንደሆነ ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅትም ከመኸር እርሻ ሥራ ጎን ለጎን የመስኖ ሥራን ለመሥራት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ የመስኖ ሥራ ሁለት ዋና ዋና ጠቀሜታዎች አሉት። ስንዴን በበጋ መስኖ የማልማቱ ሥራ እየሰፋና እየተለመደ በመምጣቱ አንደኛውና ዋናው ጥቅሙ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በተለይም ዝናብ በተቆራረጠባቸው አካባቢዎች ያለውን የመስኖ አማራጭ በመጠቀም በፍጥነት ወደ ማምረት ሥራ ለመግባት የሚያስችል መሆኑ ነው። ከሁሉም ክልሎች ጋር በተደረገው የዝግጅት ምዕራፍ ግምገማም የበጋ መስኖ ልማት የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ለአብነትም በዘንድሮው በጀት ዓመት ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚሸፈን ከክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ባለፈው በጀት ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ የተሠራው አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሆኑን ገልጸዋል። በዘንድሮው በጀት ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴን ከእጥፍ በላይ ለማልማት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You