ማለዳውን የአስፓልት መንገዱን ይዘው የሚከንፉ መኪኖች ረፋዱ ላይ ቁጥራቸው ይጨምራል። ለነገሩ የመኪኖቹ ጉዞ ጠዋት ላይ ብቻ አይደለም። ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዙ ማደር ልማዳቸው ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ታዲያ ስለፍጥነታቸው ገደብ ደንታ ላይኖራቸው ይችላል። የሌሊቱ ጭርታ ከግርግር የጸዳ ስለሚመስላቸው ባሻቸው አካሄድ ይጓዛሉ።
መቼም በዚህ ሰዓት መንገድ የሚጀመሩ ሾፌሮች ልክ እንደ ቀኑ ውሎ መንገደኛ ይኖራል ብለው አያስቡም። ያስባሉ ቢባል እንኳን ዜብራ ላይ ቆመው ቅድሚያውን ለእግረኛ እንስጥ ላይሉ ይችላሉ። የሆነ ሆነና ቀንም ይሁን ሌሊት ጥንቃቄን መላበሱ አይከፋም። ተረቱም እኮ ‹‹አይመጣምን ትተሸ ይመጣልን ያዢ›› ይላል።
‹የመንገድን ነገር መንገድ ያነሳዋል›› እንዲሉ ከሰሞኑ በመንገዴ ላይ የታዘብኩትን አንድ እውነት ‹‹እነሆ!›› ለማለት ወደድኩ። ቦታው ከጀሞ አንድ ወደ ሜክሲኮ በሚወስደው አቅጣጫ ላይ ይገኛል። ይህ መንገድ በቅርቡ ተጨማሪ ሆኖ የተገነባ ሶስተኛ መንገድ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በወጉ ተጠናቆ ሥራ አልጀመረም እንጂ እንደታሰበው ከዓላማው ቢገናኝ በርከት ያሉ ችግሮችን ያቃልል ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል ጀምሮ መተው ለመደብንና የዚህንም ታላቅ መንገድ ጠቀሜታ ሳናጣጥመው ቀረን።
ወዳጆቼ! አሁንም በዚሁ መንገድ ላይ ነኝ። ሳምንቱን ሙሉ ጠዋት ማታ ሳልረግጠው አላልፍም። ጉዞዬ በመኪና ቢሆንም ዓይኖቼን ጣል አድርጌ ማማተር ለምዶብኛል። ታዲያ ይህ ልምዴ ከብዙ አጋጣሚዎች ሲያገናኘኝ ቆይቷል። በአንዳንዱ አስቃለሁ፣ አዝናለሁ እገረማለሁ።
ከሰሞኑ ያጋጠመኝ ግን ለእኔ ከሁሉም ይለያል። በዚሁ አዲስ መንገድ ላይ ያየሁት እውነት ብዙ ሲያሳዝነኝ፣ ሲያስገርመኝ ቀናት ተቆጥረዋል። አሁንም በየቀኑ እያየሁት ነውና ከነግርምታዬ ቀጥያለሁ። ወደ ዋናው ጉዳይ ልውሰዳችሁ ። በዚሁ የጀሞ መንገድ የግራ አቅጣጫ የአዲሱ መንገድ አካፋይ ላይ።
መንገዱ አሁንም እንዳማረበት ተዘርግቷል። ይህ ጅምር መንገድ ባሳለፍነው የክረምት ጊዜ ብዙ ጫናዎች አሳልፏል። ከባድ መኪኖች፣ ትንሽ ትልቅ ተሽከርካሪዎች፣ ፈረስ ጋሪዎች ባጃጆች፣ እግረኞች እንዳሻቸው ረግጠውታል። አፍ የለውም እንጂ አፍ ቢኖረው ኖሮ ግማሽ አካሉ ፈርሶ ሲቦረቦር የጎርፍ ውሃ ሲሞላውና ሲሰነጣጠቅ ‹‹በሕግ አምላክ» ባለን ነበር። ግን ማለት አልቻለም። ዛሬም ከነሸክሙ ሊቀጥል ተገዷል።
የክረምት ወራት አልፎ መስከረም በባተ ማግስት ደግሞ የዚህ መንገድ ዓላማ በሌላ ገጽታ ተገልጧል። የመንገዱ ያልተደፈነ አካፋይ እንደ ምቹ አልጋ እንደ ሰፊ እልፍኝ ሰዎችን አስተኝቶ ማሳደሩን እያሳየን ነው። ‹‹ማሳደር›› ሲባል ደግሞ ለጊዚያዊ ዕንቅልፍ ብቻ እንዳይመስላችሁ። ስፍራውን የመረጡ ጥቂት የጎዳና ተዳዳሪዎች ከበላዩ ጣራ ቢጤ ሰርተው ፣ ዙሪያውን በካርቶን መሰል ግርዶሽ ከልለው ውለው ያነጉበታል።
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በዚህ የመንገድ አካፋይ እስከዛሬ ጥቂት የማይባሉ መኪኖች አቅጣጫ በመሳት፣ አደጋ ሲያደርሱ ተስተውሏል። ይህ በሆነበት አጋጣሚ ሁሉ ጎማቸውን ይዞ ሚዛናቸውን የሚያስተው ደግሞ ይኸው የመንገድ ላይ አካፋይ ነው።
አሁን ደግሞ ዓይናችን በዚሁ ጥግ ጎጆን የቀለሱ ነፍሶች የሞት ቀናቸውን ሲጠባበቁ እያሳየን ነው። ይህ ምሽግ መሰል አካፋይ ከእይታ የተከለለ፣ ሚስጥር የለውም። ማንም ጠጋ ብሎ እውነቱን ላረጋግጥ ቢል ገሀዱ ወለል ብሎ ይታየዋል። ጉዳዩን ያዩ ግን ሁሌም እንደዋዘ ዝም እያሉ ነው። እንደእኔ ይህ ዓይነቱ መዘናጋት ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም።
ርግጥ ነው እነዚህ የጎዳና ላይ ነፍሶች ጎናቸውን ማሳረፊያ ጥግ ያጣሉ። በየስፍራው ኩርምት ብለው ሌሊቱን ማንጋታቸውም ብርቅ ሆኖ አያውቅም። ጎዳና የወጡ ልጆች ጎናቸውን ሲያሳርፉ እንደሌሎቻችን የሚቀድማቸው ጣፋጭ ዕንቅልፍ አይደለም። ካሉበት ቦታ ጋር ተያይዞ ብዙ መከራዎችን ይገፋሉ። ለብርዱ ሲሉ የሚወስዷቸው አንዳንድ ነገሮች የዕድሜ ልክ የጤና እክሎቻቸው ናቸው። መደፈር፣ ለሌሎች ወንጀሎችና አሳሳቢ ለሚባሉ ስጋቶች መጋለጥ ከሕይወታቸው የማይነጠሉ ሀቆች ሆነዋል።
አሁን ላይ ደግሞ ችግሩ ይህ ብቻ አልሆነም። የእነሱ ማረፊያ ለአደጋ መጋለጡ ከተለመደው የኑሮ ልምዳቸው ለየት እያደረገው ነው። ጎማ ስር ተነጥፎ፣ አስፓልት ላይ ተዘርግቶ ራስን ከትራፊክ አደጋ መጠበቅ የሚቻል አይደለም። አይበለውና ሌሊት ላይ በሚከንፉ መኪኖች አደጋ ቢያጋጥም እንኳን ስለእነሱ ሕይወት ማንም ግድ የሚለው ያለ አይመስልም።
በጣም የሚገርመው ጉዳይ በእነዚሁ ልጆች የማረፊያ አካባቢ የሚያዘወትሩ የትራፊክ ፖሊሶች ነገር ነው። ትራፊኮቹ ሁሌም ቢሆን ከአጠገባቸው ቆመው አላፊ አግዳሚ መኪኖችን ያስተናግዳሉ። ሕግ የጣሰ፣ ደንብ የተላለፈ አሽከርካሪ ቢኖር ይቀጣሉ፣ ይገስጻሉ። ልብ በሉ ይህ ሁሉ የሚሆነው የጎዳና ልጆቹ ተደራርበው በሚተኙበት የመንገድ አካፋይ ላይ ነው።
ይህ ሁሉ ሲደረግ ትራፊኮቹ ለአፍታ መለስ ብለው የልጆቹን ስጋት አይጋሩም። ሁኔታቸውን በየቀኑ ቢያስተውሉትም ግዴለሽነት ይሁን ወይም ሌላ ስለነሱ ደንታ ሰጥቷቸው አያውቅም። ምን አልባት ይህን ጉዳይ ደፈር ብዬ መናገሬ ያለ ምክንያት አይደለም። እነሱ ስለነዚህ ወገኖች ግድ የሚላቸው ቢሆን ኖሮ ሞት እንደተጋረጠባቸው እያዩ ዝም አይሉም ነበር። በላያቸው ላይ ከከባድ እስከ ቀላል መኪኖች ሲያንዣብቡባቸው እያስተዋሉም ባላየ አያልፉም ነበር።
አንዳንዴ ስለሰዎች ደህንነት ሲባል ተገቢውን ኃይል መጠቀም የሚያስወቅስ አይሆንም። እናት አባትም ቢሆኑ እኮ ልጆች ሲያጠፉ ቢቆነጥጡ ቢገርፉ ለክፋት አይደለም። ስለነገው መልካምነት እንጂ። የትራፊኮቹም ጉዳይ እንዲሁ ቢሆን ተገቢ ነበር።
እነሱ በዋናነት ከቆሙለት የትራፊክ ሙያ ባሻገር ፖሊስ መሆናቸው ብቻ በብዙ ተግባራት ያሰልፋቸዋል። ሙያቸው የታጠረው መኪኖችን በመዳኘት ብቻ ሳይሆን እንደ ማንኛውም ፖሊስ ሕግን በተገቢው መንገድ በማስከበር ጭምር ነው። ይህ እውነታ ደግሞ ስለጎዳና ሕጻናት ደህንነት ጭምር ያገባቸዋል ማለት ነው።
በእኔ ግምት የትራፊክ ፖሊሶቹ ችላ ባይነት ሌሎች ሰዎች ስለልጆቹ ያገባኛል እንዳይል ሰበብ የሆነ ይመስላል። ፖሊስን የመሰለ ሕግ አስከባሪ ባለበት ሀገር መስመር አልፎ ስጋት ላይ ያሉትን ልጆች ለማንሳት ማስገደድ የሚቻል አይመስለኝም። ጉዳዩ በሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪዎች ፊት ግን ቀላል ይሆናል።
‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› ይሉት አባባል ለጤናው ጉዳይ ብቻ የተቸረ ምሳሌ አይደለም። እንደውም በትራፊክ አደጋ ለሚደርሰው የሕይወት መጥፋት የቀረበ ጥቆማ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ዓይነቱ ሀቅ ግን በጎዳና ወድቀው አደጋን ሊቀበሉ ለተዘጋጁት ነፍሶች ይሰራ አይመስልም።
አያድረሰውና አንድ ቀን እነዚህ ምስኪን ልጆች ለዚህ ስጋት ተጋልጠው ቢገኙ ‹‹ወይኔ፣ ተነስተው ቢሆን ኖሮ ›› ከሚል የተለመደ ጸጸት እንደማናልፍ ዕሙን ነው። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ዓይን ብቻ ሳይሆን ልብ ጭምር አስተውሎ መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል።
በየቀኑ ተደራሽ የሚደረገው የትራፊክ አደጋ ሪፖርት የራሱ ምክንያትና መነሻ አለው። ሁሌም በሾፌሮች ቸልተኝነት፣ በእግረኞች ስህተት፣ በመኪኖች ቴክኒክ ችግር የሚለው ቃል ሰልችቶናል። አባባሉ ከትራፊክ አደጋዎች በኋላ የሚሰማ ቃል ነው።
ይህ በጎዳና ላይ የሚስተዋለው ‹‹ጠብ ያለሽ በዳቦ›› የሞት ጥያቄ ግን ማንም ትኩረት ችሮት በየትኛውም መግለጫ ሲካተት ተሰምቶ አይታውቅም። ራስን ከአስፓልት አንጥፎ ሕይወት የሚነጥቅን አደጋ ‹‹ካልመጣህልኝ›› መባሉ ከማስገረም ባለፈ ከልብ ያሳዝናል። ትራፊኮቹም ቢሆኑ አደጋ ከመድረሱ በፊት መጠንቀቅ ያሻል የሚሉንን ጉዳይ በተግባር ሊያሳዩን ይገባል።
በየቀኑ የሞት ስጋት የተጋረጠባቸው ወገኖቻችን ከእነሱ ዓይኖች የራቁ አይደሉም። ዕለት በዕለት ያዩዋቸዋል። ተኝተው መነሳታቸው፣ ተነስተው መራመዳቸው፣ የአስፓልቱን አካፋይ ቤቴ ብለው የሙጥኝ ማለታቸውን አሳምረው ያውቁታል። ነገር ግን ማየት ማስተዋላቸው ብቻውን ፋይዳ የለሽ ነው። ልባቸው ሊወስን ሙያቸውም ሊፈርድ ይገባል። ዓይናቸው ልብ ሆኖ ነፍስ ሊያድን፣ ሕይወት ሊታደግ ግድ ይላል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም