የኮንትሮባንድ ንግድ እንደ ሀገር መሻገር ያልቻልነው ችግር ሆኖ ዘመናትን ከማስቆጠሩም በላይ፤ ችግሩ አሁን ላይ የብዙ ሀገራዊ ፈተናዎቻችን ምንጭ እየሆነም ይገኛል። ችግሩ በወጪም ሆነ በገቢ ምርቶች ላይ የሚስተዋል እንደመሆኑ እንደ ሀገር ሊያሳድር የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።
አሁን አሁን ችግሩ ከተለመዱ ሸቀጣ ሸቀጦች፤ ከኤሌክትሮኒክስ፣ ልባሽ ጨርቆች …ወዘተ አልፎ ወሳኝ የሚባሉ መድኃኒቶች እና የጦር መሣሪያዎችን ሳይቀር እያካተተ መጥቷል፤ በዚህም ከኢኮኖሚ ችግርነት ባለፈ፣ በጤና እና በሀገር ደኅንነት ላይ አደጋ መፍጠር የሚያስችል ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ሰሞኑን እንዳስታወቀው፤ ከመስከረም 26 ቀን እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ባደረገው ክትትል ፤ ከ155 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች ሲይዝ፤ በአጠቃላይም ባለፈው ዓመት ብቻ 80 ቢሊዮን ብር የተገመቱ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ሸቀጦችን ይዟል። አኃዙ ችግሩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ በተጨባጭ የሚጠቁም ነው ።
በዚህ መልኩ በሚደረግ የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ሥራ በተደጋጋሚ ከተያዙ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሣሪያዎች፣ አደንዛዥ እፆች፣ የምግብ ዘይትና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች እንደሚገኙበትም ነው የኮሚሽኑ መረጃ ያመላከተው።
በእነዚህና ሌሎችም ባልተገለጹ የኮንትሮባንድ ዝውውሮች ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ጠረፎች ወደ ውጭ የሚወጡ ምርቶችና በርካሽ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኮንትሮባንድ ምርቶችና ሸቀጦች ምክንያት የሚታጣው የታክስ ገቢ እጅጉን ከፍ ያለ ነው። ይሄም ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ ስለመሆኑ የሚያስገነዝብ ነው።
ችግሩም ሀገርን ከሚያስከፍለው ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ባሻገር፤ ለሀገር ሰላም እና ማኅበራዊ ችግሮች የቱን ያህል ፈተና እየሆነ እንደመጣ አመላካች ነው። በተለይም በጦር መሣሪያና በአደንዛዥ እፅ ዝውውር ዙሪያ የሚስተዋለው እውነታ ሀገርን እንደ ሀገር ምን ያህል ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል ለማሰብ የሚከብድ አይሆንም።
ኮንትሮባንድ የአገር ኢኮኖሚ ነቀርሳ ስለመሆኑ፤ በተለይም በሕጋዊ ግብር ከፋይ ነጋዴ ላይ ሊያሳድር የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ፤ ከሸቀጣሸቀጥ ንግድ ባለፈ፤ በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚኖረው የገዳይነት ባሕሪ ለአፍታም ሊዘነጋ የሚገባ አይደለም ።
ይህ አሳሳቢ ችግር በጊዜ ፈር ካልያዘ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ የሚያመርተው የሀገር ውስጥ አምራች በኮንትሮባንድ በሚገባውና በዝቅተኛ ዋጋ መሐል ከተማ ላይ እየተሸጠ በሚገኘው ምርት ሕልውናውን ማጣቱ የማይቀር ነው ።
የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪው በዚህ መልኩ ፈተና ውስጥ እንዲገባ መሆኑም በራሱ ከሚፈጥረው ሀገራዊ ፈተና ባለፈ፤ በውጪ ኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ይዞት ሊመጣ የሚችለው ተግዳሮት እንደሀገር የጀመርነውን ልማት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ሊከተው የሚችል ነው ።
በርግጥ ለዓመታት ስር ሰዶ የቆየውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከቁጥጥር እንዳይወጣ በማድረግ ሀገርን ለመታደግ በየወቅቱ ፤ ወቅቱን የሚመጥኑ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እየተሠሩም ነው። እየተገኘ ያለው ውጤትም አበረታች ነው።
የኮንትሮባንድ ንግድ የሚያደርሰውን የምጣኔ ሀብት ጫና፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመቅረፍ በመንግሥት በኩል ወቅቱን የሚመጥኑ ሕጎችና መመሪያዎችን ከማውጣት ጀምሮ አዳዲስ የቁጥጥር ኬላዎችን ከፍቶ በመሥራቱ አበረታች ውጤት ተገኝቷል።
ያም ሆኖ ከችግሩ ውስብስብነትና ስፋት አንፃር በቂ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ችግሩ በባሕሪው ተለዋዋጭ ከመሆኑ አንጻር ያሉ አሠራሮችን በየጊዜው መገምገምና ክፍተቶችን አውቆ ፈጥኖ መድፈን፤ አዳዲስ አሠራሮችንና የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን መጠቀም ፤ በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ንቁና ብቁ ማድረግ ያስፈልጋል።
የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገር ላይ እያሳደረ ያለውንም ሆነ ወደ ፊት ሊያሳድር የሚችለውን ፈርጀ ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል በመንግሥት/በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉ ሆኖ፤ የባለድርሻ አካላትና የኅብረተሰቡ ኃላፊነት የተሞላበት የተነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም