የታመመ ሕይወት…

የተነጠቀ ልጅነት …

የወታደር ልጅ ነች:: አባቷን በሞት ያጣችው የአስራ አንድ ዓመት ህጻን ሳለች ነበር:: አባወራው ከሞቱ በኋላ በቤቱ ችግር ሆነ:: ግዳጅ የቀሩት ወታደር ጎጆን ድህነት ዳበሰው:: የባላቸውን እጅ ሲጠብቁ የኖሩት እማወራ ቀን ጨለመባቸው:: ልጆችን ያለአጋር ፣ ቤትን ያለ አባወራ መም ራት ይከብዳቸው ያዘ::

ወይዘሮዋ ኑሮን በኀዘን ትካዜ የሚገፉት አልሆነም:: ውሎ አድሮ ከራሳቸው መከሩ:: ስለ እሳቸው ይበጃል ያሉ ወዳጆች የመከሯቸውን ሰምተው መተው አልፈለጉም:: አሁን ብቻቸውን ልጆች ማሳደግ እየከበዳቸው ነው:: ይህን ጫና የሚያቀል አንድ መላ ደግሞ ከፊታቸው ደርሷል:: ከልጆቻቸው መሀል አንዷን ለአሳዳጊ ሊሰጡ ወስነዋል::

ይህ ውሳኔ እናትን ከልጅ የሚነጥል፣ ካገር ቀዬው የሚያርቅ ነው:: ድህነት የገባው ኑሮ አስገዳጅ ቢሆን ልጅን ከእጅ አስነጥሏል:: ስለነገ መኖር ዛሬ እንዲህ ሊሆን ግድ ብሏል::

ትንሽዬዋ ብርኃኔ ቱራ ተወልዳ ካደገችበት፣ ሮጣ ከቦረቀችበት ቀዬ ልትነጠል ጊዜው ሆነ:: ልጅነቷን ያዩ፣ ሴት መሆኗን የወደዱ አሳደጊዎቿ እጇን ይዘው ተረከቧት:: ብርሃኔ የትውልድ ቦታዋን ሜታ ሮቢን ተሰናብታ ደብረብርሃን ከተመች::

አሁን በእሷ ልቦና እናት ወንድም፣እህት ይሉት ጉዳይ ትርጉም የለውም :: ሙሉ ማንነቷ በአሳደጊዎቿ እጅ ተወስኗል:: ‹‹አድርጊ›› የተባለችውን ታደርጋለች:: እሷም ሆነች እነሱ ባዕድነቷን አይረሱም:: እንደ ልጅ እያደገች እንደ ሌሎች ትኖራለች::

ኑሮ በጠባሴ…

ደብረብርሃን ‹‹ጠባሴ›› ላይ የተጀመረው ሕይወት ቀጥሏል:: ብርሃኔን ለማደጎ የወሰዷት ሴት እንደማያስተምሯት ነግረዋታል:: የእሷ መኖር ለልጆች ማሳደግ፣ ቤት መጠበቅ ብቻ ነው:: ይህን አሳምራ ታውቃለችና ለምን ብላ አትጠይቅም:: ሁሌም የታዘዘችውን እየፈጸመች፣ የተሰጣትን ትበላለች:: ብርሃኔ እኩዮቿ ትምህርት ቤት ውለው ሲገቡ ይከፋታል:: እነሱን መሆን እያሰበች ብዙ ትመኛለች:: በዕድሜዋ መማር፣ ፊደል መቁጠር አለባት:: ይህ ዕድል አልተቸራትምና ከልብ ታዝናለች::

የጠባሴ ብርድና ጸሀይ የልጅነት ፊቷን አልማረውም:: ቁመቷ ቢያድግም የእናት እጅ እንዳላያት ያስታውቃል:: አሁንም ልጆች እያሳደጉ ቁራሽ ከመቀበል ሌላ ምርጫ የላትም:: ሁሌም የውስጧ ባይተዋርነት ከእሷ እንዳለ ነው:: ከሰው ጋር ሆና ብቸኛ ትሆናለች:: ያለመማሯ ያናድዳታል፣ ያስተክዛታል::

አሁን ብርሃኔ አፍላ ወጣት ሆናለች:: ዛሬም ግን ስለሕይወቷ ግድ ያለው አልተገኘም:: ያሳደገቻቸው ልጆች ዓይኗ እያየ ክፍል ተሻግረዋል:: ይህን ስታስብ ትበግናለች:: በዓይኗ ውሃ ይሞላል:: አንድ ቀን ግን ለሰዎች ምክር ጆሮ ሰጠች:: ያለመማሯን የሚያውቁ ፣ ጠጋ ብለው ለምን? አሏት:: ከእነሱ ብትርቅ አዲስ አበባ ገብታ መማር እንደምትችል አሳመኗት:: ይህን በሰማች ጊዜ ሁሉ ነገር ገባት:: ለሕይወት፣ ኑሮዋ ራሷ መወሰን እንዳለባት ተረዳች:: ብርሃኔ ይህን ስሜት ይዛ አሳደጊዎቿን እንዲያስተምሯት ጠየቀች:: በጎ ምላሽ አላገኘችም:: አሁንም በለመደችው ሕይወት እንድትቀጥል ፈረዱባት::

ቁርጥ ውሳኔ …

ወጣቷ ብርሃኔ አሁን ክፉ ደጉን ለይታለች:: ከዚህ በኋላ ከእነሱ መሆን እያሻት አይደለም:: እስካሁን ያለመማሯ ቢቆጫት ውስጧ ለምን ማለትን አውቋል:: እናም የመከሯትን ሰዎች ቃል ተቀብላ ለራሷ ቃል ገብታለች:: መማር፣ መለወጥ እንዳለባት ወስናለች:: ውሳኔዋ ውስጧ ብቻ አልቀረም:: የአሳዳጊዎቿን ቤት ትታ ደብረብርሃንን ለቀቀች:: ጠባሴን ተሻግራ አዲስ አበባ ከተመች::

አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ያደረሳት እግሯ እንግድነቷን አላሰነበተውም:: ከደላሎች እጅ ገብታ ከእንጀራዋ ተገናኘች:: ከሁሉ ተግባብታ ቤተኛ ለመሆን አልቆየችም:: ብርሃኔ ራሷን ለማሸነፍ በሰው ቤት ሥራ መኖር ነበረባት:: ስምንት ዓመታት በሠራተኝነት የኖረችበት ቤተሰብ ለእሷ መልካም ነበር:: ውጣ ውረድ የበዛው ኑሮዋ ግን እንደ ዕቅዷ አልሞላም:: በጥቂት ደሞዝ የተቀጠረችበት ቤት ከሥራው የሚመጥን ገንዘብ አላመጣም::

አሰሪዎቿ ውሎ አድሮ ጅምር ትምህርቷን እንዳትቀጥል ከለከሏት:: አለመፍቀዳቸውን ባወቀች ጊዜ ‹‹እምቢ›› ባይዋ ብርቱ አሁንም ለምን ብላ ጠየቀች:: ከአራተኛ ክፍል ያላሻገራት ትምህርት በወጉ ሳይጠና ፈተና በዛበት:: ከድካም ፣ ልፋት የዘለለ ተስፋ አልተገኘም:: እንደዋዛ አስር ዓመታት ተቆጠሩ::

አሁን ብርሃኔ ስልችት ድክም ብሏታል:: ልጅነቷን ያለፈችበት መንገድ ውጣውረድ ያለበት፣ ድካም ልፋት የበዛበት ነው:: ይህን ስሜቷን የተረዱ ወዳጆቿ ሲመክሯት አሁንም ጆሮ ሰጥታ ሰማች:: ‹‹እስከመቼ በሰው ቤት›› ባሏት ጊዜ ሃሳባቸው ከልቧ ገባ:: አሁን የሰው ቤት ኑሮ እንዲበቃ እየተመኘች ነው:: ግን እንዴትና መቼ ለማለት አልቻለችም::

መካሪዎቿ መንገዱን ሊጠቆሟት አልዘገዩም:: ከዚህ ሕይወት ለመውጣት ብቸኛ ምርጫ ትዳር ይዞ ጎጆ መቀለስ መሆኑን አሳወቋት:: ብርሃኔ ሃሳቡን አልናቀችም:: ካመጡላት ሰው ጋር ባገናኝዋት ጊዜ በይሁንታ እጇን ሰጠች::

ሶስት ጉልቻ…

አሁን ብርሃኔ ከትዳር አጋሯ ተጣምራለች:: ባለቤቷ ከእሷ በዕድሜ የሚልቅ አንጋፋ ነው:: አልጠላችውም፣ አልናቀችውም:: የቀድሞ ወታደር በመሆኑ የጦር ጉዳተኛ ነው:: አንገቱ ስር ተደብቃ የኖረች ጥይት ጊዜ ቆጥራ ታሰቃየዋለች:: በዚህ ሰበብ በታመመ ጊዜ የጥበቃ ሥራውን ይፈታል :: ቤት ሲውል የጥንዶቹ ጓዳ በችግር ይፈተናል::

ጎጇዋን ለማቆም በቀን ሥራ የምትባትለው ብርሃኔ ከየሰዉ ቤት አሻሮ እየቆላች ልብስ እያጠበች፣ ቤት እያጸዳች፣ ትውላለች:: በህመም የሚሰቃየው ባለቤቷ አገግሞ ሥራ እስኪጀምር ይህን ማድረግ ግድ ይላታል:: በዚህ ችግር መሃል ብርሃኔ የመጀመሪያ ልጇን ወለደች:: አዲስ ነፍስ መጨመሩ የቤተሰቡን ሕይወት ማክበድ ያዘ:: ለህጻኗ የሚያስፈልግ ምግብና ወተት አቅማቸውን ፈተነ::

ህፃኗ ስድስት ወር በሞላት ጊዜ ብርሃኔ በትከሻዋ አዝላ ልብስ አጠባውን ቀጠለች:: ባለቤቷ ባለው አቅም እያገዛት ጊዜያትን ገፉ:: ሁለት የችግር ዓመታት እንዳለፉ ግን ተከታይዋ ህጻን የቤታቸው አዲስ አንግዳ ሆነች:: ከዚህ በኋላ የከፋው ችግር ዓይኑን አፍጥጦ መጣ:: ለዕለት ወጪ የሚሆን፣ ለቤት ኪራይ የሚከፈል ጠፋ::

ባለቤቷ እየጣለ የሚያነሳው ህመም ሀኪም ቤት ያመላልሰው ያዘ:: በድንገት የደረሰበት የመኪና አደጋ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ለቀዶ ህክምና አደረሰው:: ይህ አጋጣሚ የቤተሰቡን ሕይወት አብዝቶ ፈተነው::

አሁን ብርሃኔ ምርጫ ጠፍቷታል:: የልጆቿን ነፍስ ለማኖር ጎዳና ተቀምጣ መለመን ይዛለች:: ሁኔታዋን ያዩ፣ መጎሳቆሏን ያስተዋሉ የእጃቸውን ይጥሉላታል:: ብርሃኔ ውስጧ ሰላም የላትም:: ሰውነቷ ከስቷል:: አቅሟ ደክሟል ደጋግሞ የሚመላለስባት ሳል ካልጋ ይጥላታል:: ህመሟን ችላ ጥርሷን ነክሳ ውሎዋን ትገፋለች:: ለልጆቿ ዳቦ ጥቂት ሳንቲም ታገኛለች::

ኑሮ ደረጃ ስር …

የቤተሰቡ ቁጥር አራት በሆነ ጊዜ የመኖር ዕድል መጥበብ ያዘ:: ቤት ፍለጋ ቢዋትቱም በእነሱ አቅም የሚመጥን መኖሪያ አልተገኘም:: ከሚላስ የሚቀመሰው አልፎ የጎን ማሳረፊያ ጠፋ:: በአንድ አጋጣሚ ኮተቤ ከጋራው ጥግ ቤት የሚሠራ የአንድ ሰው ጊቢውን እየጠበቁ እንዲያድሩ ዕድል ቀናቸው:: ፈጣሪን አመስግነው ኑሮን ጀመሩ:: ይህ አይነቱ የተስፋ ሕይወት ከአንድ ዓመት አልዘዘለም:: የቤቱ ባለቤት ቦታውን እንደሚፈልገው ነግሮ ካሉበት ሸኛቸው::

ይህኔ ለነፍስ ያሉ የጣፎ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች የቤታቸውን የመወጣጫ ደረጃ ስር ፈቀዱላቸው:: ግድግዳውን ተተግነው ዙሪያውን በሸራ ሸፍነው ኑሮ ቀጠሉ:: አራት ነፍሶች ለጊዜው ሕይወታቸው መለስ አለ:: ጎዳና ከመውጣት፣ በጫካ ከመውደቅ ተረፉ::

አሁንም የነ ብርሃኔ ኑሮ እያነከሰ ቀጥሏል:: ሲያገኙ እየቀመሱ ሲያጡ ጦም ማደሩን ለምደውታል:: አንዳንዴ ኑሯቸውን ያዩ የእጃቸውን ይሰጧቸዋል፡፤ የዕለቱን ቀምሰው ማግስቱን ይርባቸዋል:: ብርሃኔ በሰዎች እገዛ ማኮረኒ ፣ፓስታ ባገኘች ጊዜ ማብሰያ ዘይቱ ይጠፋል:: በውሃ ቀቅላ የልጆቿን ጉሮሮ ትደፍናለች::

በድንገት …

ፈታኙ የቤተሰቡ ኑሮ ዛሬም አልሞላም:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብርሃኔ ጤና እያጣች አልጋ መያዝ ጀምራለች:: ሁለተኛ ልጇን ነፍሰጡር በነበረች ጊዜ የጀመራት ሃይለኛ ሳል በርትቶባታል:: ሆዷን እያስጨነቀ ሰላም የሚነሳት ጉዳይ ምን እንደሆነ አልገባትም:: ብርሃኔ ህመሟ ሲደጋገም ጤና ጣቢያ ተመረመረች:: ውጤቱ መልካም አልሆነም:: ለከፍተኛ ህክምና በሄደችበት ሆስፒታል የጨጓራ ካንሰርና የሳንባ ምች እንዳለባት ታወቀ:: ለመፍትሄው ፈጥና መድሃኒት መውሰድ ጀመረች:: ባልሞላ ጎጆ ፣ በባዶ ሆድ ውሎ፣ በጎደለ ኑሮ ራስን ማስታመም ከበዳት::

የእሷን እጅ የሚያዩ ህጻናት ልጆቿ አላስተኟትም:: መድሃኒቱን እየወሰደች ጎኗን ልትደግፍ ሞከረች:: አልሆነላትም:: የህመሟ መክበድ ችግሯን አባሰው:: እየተኛች ፣ እየተነሳች ለሕይወት ታገለች:: ጎንበስ ቀና ባለች ጊዜ ደረቷን እያፈነ የሚያስጨንቃት ህመም ውስጧን ሰቅዞ አላላውስ አላት:: በድካም ናወዘች:: በየቀኑ ደም ያስተፋት ጀመር::

ሁኔታው ቢከብድ ብርሃኔ ጤና ጣቢያ ተመላለሰች:: ዳግም ሪፈር ተብላ ለቀናት የሆስፒታል አልጋ ያዘች:: ህክምናው ተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራ ያሻዋል:: አራት ሺህ ብር ተጠየቀች:: አራት ብር ከእጇ የሌላት ሴት ይህን ማድረግ አልቻለችም:: በራሷ ፈርዳ ወደ ቤቷ ተመለሰች::

ብርሃኔ የታዘዘላትን መርፌ አላቆመችም:: የተጎዳው አካሏ ባይችለውም ስለመዳን ብዙ ሞከረች:: አሁንም ጤናዋ ለውጥ አላሳየም:: ካይኗ ዕንቅልፍ አጣች፣ በስቃይና ህመም ተመላለሰች:: በድካምና ችግር ተፈተነች::

አሁን ብርሃኔ በህመም ከአንድ ዓመት በላይ ቆይታለች፤ ፋታ የማይስጥ ሕይወቷ እረፍት የለሽ ነው:: በቤቷ ችግርና ርሃብ ከርሞ ይሄዳል:: አንዳንዴ ኑሮዋን ያዩ ቀርበው ያዋይዋታል:: ችግሯን አትደብቅም:: ስለእሷ፣ ስለባሏና ጎጆዋ በግልጽ ትናገራለች:: በርካቶች ውስጣቸው ያዝናል:: አንዳንዶች ሰምተው ዝም ይላሉ:: ጥቂቶች የአቅማቸውን ይሰጧታል::

አልፎ አልፎ ከሰዎች የምታገኘው እገዛ ሙሉ አይሆንም:: እንጀራው ሲገኝ ወጡ ይጠፋል፣ ማኮሮኒ ፓስታው ሲሰጣት ማብሰያ ዘይቱ ፣ ማጣፈጫ ሽንኩርቱ አይታሰብም:: እንዲህ በሆነ ጊዜ ለልጆቿ ነፍስ ማቆያ ከእጇ ያለውን በውሃ ቀቅላ፣ በጨው አጣፍጣ ትሰጣለች:: ባዶ ሆድ የሚከርሙ ልጆቿ ‹‹አረረ ፣ መረረን አያውቁም:: የተሰጣቸውን ቀምሰው ያገኙትን ተናጥቀው ያድራሉ::

በነ ብርሃኔ ቤት ድህነት ፣ ህመም ስቃይ የከፋ ነው:: አንዱ ቢሞላ ሌለው ይጎድላል:: በእነሱ ዓለም ‹‹እፎይታ›› ይሉት የለም:: አንዴ ወይዘሮዋ ፣ ሌላ ጊዜ አባወራው በህመም ይሰቃያሉ:: ይህ እውነት በነሱ ፈቃድ ወደምድር ላመጧቸው ሁለት ህጻናት መከራን አጋብቷል:: ወላጆቻቸው ሲታመሙ፣ በችግር ሲፈተኑ ልጆቹ በእኩል ይጋሩታል::

የነ ብርሃኔ ሕይወት ሁሌም የሌሎችን ዓይን ይስባል:: ታሪካቸው አሳዛኝ ጆሮ ገብ ነው:: ይህን የሚያውቁ አንዳንዶች አንዳንዴ የሚችሉትን ያግዛሉ:: የኪሳቸውን ያጋራሉ:: ይህ ብቻ ግን ለምስኪኑ ቤተሰብ ዘላቂ መፍትሄ አልሆነም:: ዛሬ ሳቅ ቢሆን ነገ ዕንባና ኀዘን ይተካል:: በድህነትና በህመም ስቃይ ልጆች የሚያሳድጉት ጥንዶች አምናን አልፈው ዘንድሮ ደርሰዋል::

መልካም ዓይኖች

እነሆ! አዲስ ዓመት ብቷል:: ይህ ወቅት በርካቶች አዲስ ተስፋ ይሰንቁበታል:: ኑሮን ለመለወጥ፣ ሕይወትን ለማሻሻል የሚተጉ አብዝተው ይሮጡበታል:: እነብርሃኔም የክረምቱን ዶፍ አልፈው፣ ብርድና ውርጩን ተሻግረዋል:: ዓመቱ ልክ እንደዓምናው ለእነሱም ተለውጧል:: ኑሯቸው ፣ ሕይወታቸው ግን ዛሬም አልነጋም:: የእነሱ መስከረም አሁንም ገና ነው:: ዛሬም የሕይወታቸው ክረምት አላለፈም:: የኑሯቸው ብርድ አልሞቀም:: ይህ ስሜት ላለፉት ዓመታት አብሯቸው የዘለቀ ሀቅ ሆኗል::

ከቀናት በአንዱ ግን ክረምታቸውን ከሚያበራ፣ መስከረማቸውን ከሚያደምቅ መልካም አጋጣሚ ተገናኙ:: ማንነታቸውን አውቀው ፣ ችግራቸውን የተረዱ መልካም ዓይኖች አስተዋሏቸው:: ከወደቁበት ወለል፣ ካሉበት ችግር የሚታደግ የመኖሪያ ቤት ሊሰጣቸው መሆኑን ባወቁ ጊዜ አፋቸው በምስጋና ሞላ:: ውስጣቸው በተስፋ ደመቀ::

አሁን ብርሃኔና ቤተሰቦቿ ‹‹የድሃ ፣ድሃ›› በሚለው ልየታ ተመርጠው የቤት ባለቤት ሆነዋል:: በወጉ የሚደረብ ልብስ ባይኖርም ዛሬ ከበረንዳ ወድቆ በብርድ የሚቀጣ የለም:: ‹‹ዝናብ መጣ፣ ጎርፍ ደረሰ ብሎ ስጋትም ተወግዷል::

ዛሬን…

ዕንቅልፍ ተኝተው የሚያድሩት እነ ብርሃኔ ስለሆነው ሁሉ ምስጋናቸው የላቀ ነው:: የዓመታት የቤት ችግራቸው ተወግዶ ‹‹እፎይ›› ብለዋል:: ብርሃኔ ዛሬም ለስራ ያላት ስሜት ከእሷ ጋር ነው:: የጤናዋ ጉዳይ ግን አላላውስ እያላት ተቸግራለች:: እንዲህ መሆኑ የቤተሰቡ ችግር ባለበት እንዲራመድ አስገድዷል::

አባወራው ከትናንት ሕይወት የዘለለ ዕድል አላገኙም:: ዛሬም ባልተሻለ ገቢና የጤና ሁኔታ መንገላታት ይዘዋል:: መሥራት የለመዱ የብርሃኔ እጆች በህመም ተሸማቀው ‹‹የሰው ያለህ›› እያሉ ነው:: የቆሰለ ጀርባዋ ፣የተጎዳ አካሏ ግን ለፍላጎቷ አላበቃትም:: ሥራ ወዳዷ ሴት ዛሬም ሰርቶ ለማደር አትለግምም:: ጤናዋ ተጠብቆ በልቶ ለማደር፣ ልጆችን ለማሳደግ የሌሎችን እገዛ ትሻለች::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You