መንገዶችንና ድልድዮችን ከአደጋና ብልሽት የመታደጊያው ጣቢያ

ኢትዮጵያ ለመንገድ ልማት በሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት የተለያዩ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ገንብታለች፤ እየገነባችም ትገኛለች። ሀገሪቱ 22 ሺ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የአስፋልት መንገድ እየገነባች እንደምትገኝም ባለፈው ዓመት የወጣ መረጃ ያመለክታል።

መንገዶችን ከመገንባት በተጓዳኝም መንገዶች ለታሰበላቸው ዓላማ በአግባቡ እንዲውሉ ማድረግ ላይ ይሠራል። መንገዶች እና ድልድዮች በተለይ ከመጠን በላይ በጫኑ ተሽከርካሪዎች ሳቢያ ለጉዳት እንዳይደረጉ፣ የአገልግሎት ዘመናቸው እንዳያጥር በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በኩል ቁጥጥር ይደረጋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመላ ሀገሪቱ 14 የሚደርሱ የሚዛን ጣቢያዎችን አቋቁሞ የተሽከርካሪዎችን የጭነት ክብደት የመቆጣጠር ሥራ ይሠራል። ጣቢያዎቹም በሞጆ፣ ሆለታ፣ ሱሉልታ፣ ሠንዳፋ፣ ዲማ(ሰበታ)፣ ጅማ፣ ሻሸመኔ፣ አዋሽ፣ ሠመራ፣ ደንገጎ፣ ኮምቦልቻ፣ ጢቅ (ደጀን )፣ ወረታ፣ የሓ (መቀሌ) የሚገኙ ናቸው።

የጣቢያዎቹ መቋቋም ዋና ዓላማ የተሽከርካሪዎችን ክብደት መቆጣጠር ሲሆን፣ በመንገዶች ላይ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው የአክስል ክብደት መጠን በላይ ጭነት ይዘው ሲንቀሳቀሱ በከፍተኛ ወጪ በተገነቡ የመንገድ አውታሮች ላይ ጉዳቶች እንዳይደርሱ መከላከል እንዲሁም መንገዶች እና ድልድዮች ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማድረግ ነው። ከተፈቀደው ክብደት በላይ ጭነው መንገዶችንና ድልድዮችን እንዳይጎዱ ለማድረግ ይሠራል፤ የህዝብ ሀብት የሆኑትን የጭነት ተሽከርካሪዎችንም ከጉዳት መጠበቅ ነው።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር(ኢመአ) እያንዳንዱ የተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ በባለቤትነት ስሜት በሕግ በተደነገገው የክብደት መጠን መሠረት እንዲጭኑ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪ ሹፌሮችና ባለቤቶች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያለመ ጉብኝት እያካሄደ ይገኛል። ጉብኝቱም መንገዶችና ድልድዮችን ከብልሽት ለመታደግ እንዲሁም ተሽከርካሪዎችን ብሎም የሕይወትና ንብረት ውደመትን መከላከልን ያለመ ነው። በቅርቡም በሞጆ የከባድ ጭነት ሚዛን ጣቢያ ጉብኝት ተደርጓል። የጋዜጣው ሪፖርተርም የጉብኝቱ ታዳሚ ሆኗል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ ከአዲስ አበባ በ76 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሞጆ ከተማ የአዲስ አበባ ጀቡቲ መውጫ ኮሪደርና የሀገሪቱ የገቢና ወጪ ጭነቶች መተላለፊያ ነች። ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚደረጉ የከባድ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴዎች በስፋት ይታይባታል፤ በሀገሪቱ ከተገነቡት ደረቅ ወደቦች ትልቁ ደረቅ ወደብ የሚገኘውም በዚህችው ከተማ ነው፤ ደረቅ ወደቡ 188 ሄከታር መሬት ላይ ያረፈ ነው። በዚህች ከተማ መግቢያና መውጫ በር ላይ ነው /በነባሩ አዲስ አበባ ሞጆ ናዝሬት መንገድ/ የጭነት መቆጣጠሪያ ሚዛን ጣቢያው የሚገኘው።

በከተማዋ በሚገኘው የተሽከርካሪ ሚዛን ጣቢያ አካባቢ ሰሞኑን በሞንታርቦ የታገዘ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል። በወቅቱም በርካታ ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደው ክብደት በላይ አሸዋ፣ ሲሚንቶ የተለያዩ የማእድንና የግንባታ እቃዎችን ጭነው በመገኘታቸው ሲቀጡ፣ የእርምት ርምጃ ሲወሰድባቸውና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሲሰጣቸው ተመልክተናል፤ የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች መኪናቸውን ሲያስመዝኑና የግንዛቤ መስጫ ፖስተር ሲለጠፍላቸው፣ ከተፈቀደው በላይ የጫኑ አሽከርካሪዎችም ጥግ ይዘው እንዲቆሙ ተደርገው ጭነታቸውን በተፈቀደው መጠን ሲያስተካክሉና ቅጣት ሲጣልባቸውም ለማየት ችለናል።

የሲኖትራክ አሽከረካሪው አቶ ሄኖከ ደጉ ጭነት በግምት እንዲሁም በማሽን እንደሚጫን ጠቅሰው፣ ግምቱን ሳያውቁ ከተፈቀደው ክብደት በላይ የሆነ ድንጋይ ጭነው መያዛቸውን ገልጧል። አሁን ከተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መቅሰሙን ይናገራል። በቀን አበል ተቀጥሮ እንደሚሠራና በተሽከርካሪው ባለቤት ትዕዛዝ መጫኑን በመግለፅ በቀጣይ በተፈቀደው ልክ እንደሚጭን አስታውቋል።

አቶ ክብሩ ኪዳኔንም ተሽከርካሪውን ሲመዝን አግኝተነው፤ ከተፈለገው ክብደት በላይ ሲጫን መንገድ ሊጎዳ እንደሚችል ጠቅሶ፣ ድርጊቱ ተሽከርካሪውን እንደሚጎዳ ተናግሯል። ለእዚህም የቁጥጥር ሥራው እና የሚዛን አገልግሎቱ ተጠናከሮ እንዲቀጥል፣ የተበላሹ መንገዶች እንዲጠገኑ አመልክቷል። ከመጠን በላይ መጫኑ የተሽከርካሪውንም ጎማ እንደሚበላና መንገድ ላይ ብልሽት እንደሚያስከትል የተናገረው አቶ ክብሩ፣ ከመነሻው ሲጫን የጭነቱ ክብደት የሚታወቅበት አሠራር ሊዘረጋ እንደሚገባም ነው ያሳሰበው።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሞጆ ሚዛን ጣቢያ ኃላፊ አቶ ያሬድ ዓለማየሁ በግንዛቤ ማስጨበጫ ጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፤ አሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በሕግ በተፈቀደላቸው ክብደት መጠን መሠረት በመጫን መንገዶችን እና ድልድዮችን እንዲሁም ተሽከርካሪዎችን ከብልሽትና ከጉዳት መታደግ ይገባቸዋል።

አቶ ያሬድ የሞጆ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት 14 የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የመጀመሪያውና በምስራቅ እና በደቡብ አዋሳኝ ኮሪደሮች ላይ ትልቁን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ መሆኑንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ 14 አካባቢዎች ከተገጠሙት ሚዛኖች አገልግሎት እየሰጡ ያሉት አምስቱ ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የተቀሩት በብልሽት ምክንያት አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ አቶ ያሬድ ገልጸዋል።

የሞጆ የተሽከርካሪ ሚዛን ጣቢያ በቀን ከ300 እስከ 400 ተሽከርካሪዎችን የመመዘን አቅም እንዳለው ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ከ80 እስከ 120 ለሚደርሱ ተሽከርካሪዎች ብቻ የ24 ሰአት አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ለእዚህም አንዱ ምክንያት የአማራጭ መንገዶች በመብዛትን ተከትሎ ተሽከርካሪዎች በተለያዩ መንገዶች መሄዳቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከሻሸመኔ የሚመጡ መኪናዎች ቆቃ ላይ ገብተው በአዱላላ አድርገው ሚዛን ጣቢያውን ሳያገኙ በቢሾፍቱ እንደሚወጡ ጠቅሰው፣ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ የሚሄዱት ቢሾፍቱ ላይ ገብተው በአዱላላ አድርገው እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በሌላም በኩል በጃፓን መንግሥት ድጋፍ የተገጠመው ዘመናዊ አዲስ ሚዛን በኤሌክትሪክ ሃይል መዋዠቅ ምክንያት ለብልሽት መዳረጉም ሌላው በሚፈለገው ልክ አገልግሎት መስጠት አለማስቻሉንም ጠቁመዋል። ይህ ለብልሽት የተዳረገ ሚዛን በመጪው ጥር አካባቢ በጃፓን መንግሥት ሙሉ ጥገና ተደርጎ ወደ አገልግሎት እንደሚመለስም ጠቁመዋል።

የሚዛን አገልግሎት እየተሰጣቸው ከሚገኙት መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ከመጠን በላይ የሚጭኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የእነዚህን ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎች በመክሰስ፣ በማስተማር እና ጭነቱንም በማራገፍ አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ ያሬድ በሙሉ አቅም ለመንቀሳቀስ እና ተሽከርካሪዎቹን ተደራሽ ለማድረግ አማራጭ መንገዶቹ ላይ ተንቀሳቃሽ የክብደት መለኪያ ድልድዮች ሊኖሩ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በጣቢያዎች የሚደረገው ቁጥጥር እና ቅጣት ብቻውን ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣ የሚናገሩት አቶ ያሬድ፣ የተሽከርካሪ ባለቤቶች እና አሽከርካሪዎች በባለቤትነት ስሜት በሕግ በተፈቀደው ክብደት ልክ ብቻ እንዲጭኑ አሳስበዋል።

እያንዳንዱ የተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ “መንገዱ የእኔው ነው” በሚል የባለቤትነት ስሜት በሕግ በተደነገገው የክብደት መጠን መሠረት በመጫን እና መንገዶቹን በመጠቀም የዜግነት ግዴታውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በጣቢያው አብዛኛውን ጊዜ የሚያልፉት ተሽከርካሪዎች ከክብደት በላይ የጫኑም፣ የማይጨኑም መሆናቸውን አቶ ያሬድ ጠቅሰው፣ ከትራፊክ ፍሰቱ 80 በመቶ የሚሆነው ከጅቡቲ ኮሪደር እንደሚመጣ ገልጸዋል። የተቀሩት በአካባቢው የሚታዩት እንደ አሸዋና የመሳሰሉትን የኮንስትራክሸን ግብአቶች የጫኑና በአጭር ርቀት የሚንቀሳቀሱ መኪናዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የመንገዶች አስተዳደር በመንገዶች ጥገና ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያወጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለሀብቶችም ለተሽከርካሪ እንዲሁም ጎማ፣ ዘይትና መለዋወጫ የሚያወጡት ሀብት አንደ ሀገር የሚያሳደረው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም ይህን በሀገርና በህዝብ ሀብት ላይ የሚደርስ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። ለእዚህም አዲስ ሕግ አዋጅ 491/ 2022 የሚባል ሕግና ደንብ ወጥቶ መመሪያ እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ እና የመሳሰሉትን ችግሮች ለመፍታትም ለ14ቱም ጣቢያዎች የየራሳቸውን የሶላር ባትሪ እና ጀነሬተር አገልግሎት ያካተተ የፓወር ሀውስ ግንባታ 90 በመቶ መጠናቀቁን አመላክተዋል። ማሽኑም እስከ ጥር ወር ድረስ እንደሚገጠም ጠቅሰው፣ ይህም ሚዛን ጣቢያዎች 24 ሰዓት ያለምንም መቆራረጥና ችግር መስራት የሚያስችል አቅም ላይ እንደሚያደርሳቸው ተናግረዋል።

የተቋሙ መረጃ እንዳመለከተው፤ ከተፈቀደው በላይ በመጫን በመንገድና ድልድይ ደህንነት ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ተሽከርካሪዎችን የተመለከተ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል በ8561 ነፃ የስልክ መስመር በማሳወቅ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሕዝብ አስተያየት መስጫ ሥርዓት በመዘርጋት እየሠራ ይገኛል።

የወንጀል መከላከል ድልድል ኢንስፔክተር ምስጋና ያደታ በበኩላቸው ሚዛን ጥሰው የሚሄዱ መኪናዎች ሲያጋጥሙ፣ ሕግ የተላለፈ አሽከርካሪ ሲያመልጥ ይዞ ለሕግ ለማቅረብ ድጋፍ በመስጠት በኩል በሞጆ የሚዛን ጣቢያ ከሚሠሩ ባለድርሻ አካላት በጋራ የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ክፍያ የሚሸሹ አሉ፤ ሚዛን መኖሩን ካለማወቅና ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ሳያስመዝኑ የሚያልፉ ያጋጥማሉ፤ እነዚህም አብዛኛውን ጊዜ በቅጣት ብቻ ሳይሆን የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት የሚታለፉበት ሁኔታ አለ።

ሞጆ ከተማ ውስጥ ከተመደቡ ፖሊሶችና የመንገድ ትራንስፖርት ሠራተኞች ጋር በየጊዜው ስብሰባ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ኢንስፔክተሩ ጠቅሰው፣ አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪዎችን በአግባቡ በማስመዘን ከገደብ በላይ ጭነትን በማስቀረት የህዝብ ንብረት የሆኑት የመንገድና ድልድይ መሠረተ ልማቶችን በመጠበቅ የሕግ የበላይነትን እንዲያከብሩ አሳስበዋል።

የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችም መጫን ከሚገባቸው ክብደት በላይ የሚጭኑ ከሆነ ራሱ ንብረቱ ለጉዳት እንደሚዳረግ አስታውቀው፣ ንብረቱም የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እንዲሰሩም መክረዋል። የተሽከርካሪው ባለንብረትም ንብረቱን ለመጠበቅ እና ለማሻደግ የሚችለው የሕግ የበላይነትን ሲያከብር መሆኑን ጠቅሰው፣ ንብረቱን መከታተል እና በአሽከርካሪውም በንብረቱም ላይ አደጋ እንዳይደርስ ለማድረግ እንዲሠሩም መክረዋል።

የመንገድ ትራንስፖርት ኤጀንሲው አቶ ካሳሁን ደበበ እንደገለጹት፣ ከሞጆ ከተማ ክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ጋር በመሆን በተሠሩ የቅንጅት ሥራዎች ተሽከርካሪዎች መመዘናቸውን የማረያረጋግጡ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉትም ከክብደት በላይ መጫን ለትራፊክ አደጋ ለመጋለጥ እንዲሁም ለመንገድ ጉዳት አስተዋፅኦ ያደርጋል። አሽከርካሪዎች ከመጠን በላይ መጫናቸው መንገዶች እንዲበላሹና እድሜያቸው እንዲያጥር ምክንያት ይሆናል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኤጀንሲው ከሞጆ ክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ጋር ከልክ በላይ ክብደትን የማስተካከል ሥራዎች ይሠራል፤ ተሽከርካሪው ላይ ቅጣት ይጥላል፤ በቀጣይ ሌላ መንገድ ችግር እንዳያስከትል የቁጥጥር ባለሙያ በመደብ ጭነት የማራገፍ ሥራ ይሠራል።

በሚዛን አገልግሎት ላይ ያለው ችግር እንደሚታይ ጠቅሰው፣ ለሚዛን ሽሽት በሚል በከተማዋ አማራጭ መንገዶች መጠቀም እንደሚታይ ተናግረዋል። የሚዛን ሽሽቱ የከተማውን መሠረተ ልማት እያጠፋ መሆኑን ጠቁመዋል። ለታክሲና ለእግረኛ የሚያገለግሉ መንገዶች እንዲበላሹ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ሹፌሮች ግንዛቤ እንዲወስዱና በትርፍ ጭነት የሚያገኙትን ትርፍ ብቻ ከማየት መቆጠብ እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት።

ሹፌሮችን የሚያስገድዷቸው ባለንብረቶችና የግንባታ ድርጅቶች የራሳቸውን ጥቅም በማየት ጫና እያሳደሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመፍታትም ግንዛቤ ማስያዝ ላይ በቅንጅት መሠራት አለበት ብለዋል። ሚዛን በመመዘን እና ሹፌር በመቅጣት ብቻ ለውጥ እንደማይመጣ አስታውቀው፣ ጭነቶች የሚራገፉበት ቦታ ድረስ በመሄድ ጭምር ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You