የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ጋሹ ሃብቴ ይባላሉ፡፡ ተውልደው ያደጉት በቀድሞው አርሲ ክፍለ ሀገር፣ በጎቤሳ ወረዳ ሽርካ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ሽርካ በሚባል ትምህርት ቤት ሲሆን፣ ከዘጠነኛ እስከ 10ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ደግሞ በአሰላ ከተማ በቀድሞው አጠራሩ ራስ ዳርጌ በአሁኑ ስያሜው ደግሞ ጭላሎ ትምህርት ቤት ነው፡፡ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርት የተማሩት በዚያው በአሰላ ከተማ አሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በ1965 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጀመሩ፤ በዚህ ጊዜ በ1964 ዓ.ም አጼ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲውን ዘግተው ተማሪዎችን አባርረው ስለነበር ዩኒቨርሲቲው በወቅቱ በነበረው ግርግር ተረብሾ ነበር፡፡ ከተባረሩ ልጆች መካከል የእርሳቸው ጓደኞችም ስለነበሩ የእነርሱ እድል እንዳይገጥማቸው ይሰጉ ነበርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደጅማ እርሻ ኮሌጅ እድሉን አግኝተው በዲፕሎማ ለመማር አቀኑ፡፡
የኮሌጅ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ከጂማ እርሻ ኮሌጅ በዲፕሎማ የተመረቁት የዛሬው እንግዳችን፤ ትምርታቸውን እዛው ላይ ሊገቱ አልፈለጉምና ተመልሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ገቡ፡፡ ሁለት ዓመት እንደተማሩ በሱማሊያ በኩል ጦርነት ስለነበር ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ መረበሹን ተከትሎ ዩኒቨርስቲው እርሳቸው ያሉበት አዲስ አበባ ሲመጣ፣ ከአራት ኪሎ ወጥተው ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ በእርሻ ምጣኔ ሃብት (Agricultural economics) ከዓለማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ አገኙ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በዚሁ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ የትምህርት አይነት ሠሩ፡፡ በኋላም ከኦክለሆማ እስቴት ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዶግሪ በተመሳሳይ ሙያ አግኝተዋል፡፡
ከትምህርት ዝግጅታቸው ባሻገር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ተቋማት አገልግለዋል፡፡ ለአብነትም፣ በግብርና ሚኒስቴር በእርሻ ወኪልነት፤ በጂማ እርሻ ኮሌጅ በአስተማሪነት፣ በክፍል ኃላፊነት፣ በተማሪዎች ዲንነት እና በኮሌጅ ዲንነት አገልግለዋል። በአሜሪካን ሀገር ደግሞ በአርከንሳስ እስቴት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሠርተዋል፡፡
ዶክተር ጋሹ፣ በሀገረ አሜሪካ ኦክላማ ከተማ ከዩኒቨርሲቲ እንደወጡ መሬት ገዝተው የራሳቸውን እርሻ ጀመሩ፡፡ በማወቅ ሳይሆን ባለማወቅ ሰው ሁሉ የማይዘራውን ኦክራ የተባለውን የአትክልት አይነት 40 ሔክታር መሬት ላይ አመረቱ፡፡ ይሄ አትክልት በጣም በሰፊ ማሳ ላይ ስለመዘራቱም የተመለከቱ ጋዜጠኞች ጉዳዩን አራገቡት። በጋዜጣም ወጣ፡፡ የዚያ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪም በሁኔታው ደስ ብሏቸው በስፋት ኦክራን የዘራ በሚል የ15 ሺ ዶላር ሽልማት ሰጧቸው፡፡
በዚህና ሌሎችም ተግባራት ስማቸው የሚነሳው የዛሬው እንግዳችን፣ በአሁን ወቅት በግል ሥራ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ሲሆን፤ ለ33 ዓመት በውጭ አገር ከመቆየታቸው ባሻገር ዛሬም በኢትዮጵያ ሙያቸው የሚፈቅድላቸውን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ አዲስ ዘመንም ለዛሬው የዘመን እንግዳ ዓምድ እትሙ በተለይ በእርሻ ምጣኔው ዘርፍ ያላቸውን የካበተ ልምድ ያጋሩት ዘንድ እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብርና ከትናንት እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ ያለው አበርክቶ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ጋሹ፡- ግብርና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያለው፤ ማንም እንደሚረዳውም የአገራችንን 120 ሚሊዮን ሕዝብ የሚመግብ ሴክተር ነው:: የግብርና አስደናቂ ሌላው አቅሙ በቁጥር 96 ሚሊዮን ሕዝብ ወይም 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ኑሮውን ቀን በቀን በግብርና የሚያሳልፍ መሆኑ ነው:: ስለዚህ ግብርና በምግብ ብቻ ሳይሆን 96 ሚሊዮን ሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮውን ያደረገው ግብርና ላይ መሆኑ የሴክተሩን አበርክቶ ከፍ ያደርገዋል::
ሌላው ቀደም ሲልም ሆነ አሁን የግብርናውን ሚናና ጠቃሚነት የሚያጎላው ነገር የውጭ ምንዛሪ ምንጫችን መሆኑ ነው:: በአግባቡ ሳንጠቀምበት ቀርተን ነው እንጂ የዚህች አገር የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ግብርና ነው:: በእርግጥ ወርቅና ሌላም ሌላም ነገር የውጭ ምንዛሪ ማግኛችን ነው ሊባል ይችላል:: ከግብርና ጋር ሲነጻጸር ግን ተከታታይነቱና ያስገኘው ጥቅም የሚስተካከለው አይሆንም:: እንደሚታወቀው እስካሁን የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛው ቡና ነው:: በእርግጥ ቀደም ሲል የሻይ ቅጠል ምርትን እኛው ራሳችን እናመርት ነበር:: ከዚህ የተነሳም የውጭ ምንዛሪ አያስወጣንም::
ከውጭ ምንዛሪ አኳያ ውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) እንዲሁም የውጭ ሀገራት የሚሰጡት ብድርም ሆነ እርዳታ ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን እነዚህ እንደግብርና ቀጣይነት ያላቸው አይደሉም:: ግብርና ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ልክ እንደማይደርቅ ወንዝ ሁልጊዜ የሚኖር ነው:: ስለዚህ ቀድሞም ሆነ አሁንም ድረስ ትልቁ የውጭ ምንዛሪ ምንጫችን ያው ግብርና ነው::
ሌላው የግብርናን ሚና ለማየት ጎዳና ላይ ሽር ጉድ የሚሉ ተሽከርካሪዎችን ብቻ ማየቱ በቂ ነው። እያንዳንዱ ተሸከርካሪ ነዳጅ ሊያገኝ የቻለው የግብርና ውጤት ባስገኘው የውጭ ምንዛሪ ነው:: ነዳጅ ብቻ አይደለም። ለመድኃኒትም ሆነ ለኬሚካልና ለሌላው ገቢ ምርታችን የውጭ ምንዛሪ የሚገኘው ከግብርና ነው:: ስለዚህ ግብርና ስንል እህል የሚመረትበት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፤ ግብርና ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ነው:: ለምሳሌ፣ ለትምህርት ዘርፉም ሆነ ለጤናው ዘርፍ አስፈላጊ ግብዓቶችን የምናገኝበት ቁልፉ ነገር ከግብርና ምርት በተገኘው የውጭ ምንዛሪ ቢባል ግነት አይሆንም:: ስለዚህ ለረጅም ዓመታት ግብርና ለኢትዮጵያ ምኗ ነው ሲባል፤ “ሁሉ ነገሯ ነው” የሚለው ገለጻ ያጠቃልለዋል::
አዲስ ዘመን፡- ከእስካሁኑ የግብርናው ዘርፍ ጉዞ አንጻር ባለፉት አምስት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎችንስ እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ጋሹ፡- ግብርና ባለፉት 50 ዓመታት በጣም እንግልት ከደረሰበት ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ አንዱ ነው:: የመጀመሪያው የእንግልት ምንጭ የሚወጡት ፖሊሲዎች እንደግለሰብ እንጂ እንደቡድን ባለመሆናቸው ነው::
እንዲያውም ግብርና አናት አናቱን ቢባል የማይሞተት አውሬ ሆኖ ነው የዘለቀው። በአግባቡ አልተያዘም:: ግብርና የሚሰጠውን አገልግሎት ያህል እንክብካቤ ያልተደረገለት ሴክተር ነው:: ለምሳሌ አንደኛ በየጊዜው የሚመጡ መንግሥታት እንዳሻቸው የሚያደርጉት ካልሆነ በስተቀር የግብርና ፖሊሲ እንደ ግብርና ተለዋዋጭነት የሚለዋወጥ አይደለም::
ሁለተኛው የመሬት ፖሊሲው ሲሆን፣ ይህም በጣም የተበላሸ ፖሊሲ ነው:: ምናልባት በፌዴራል ደረጃ ያለው ፖሊሲው ጥሩ ነው ቢባልም፤ ወደ የክልሉ ሲወርድ ግን ፖሊሲው ወጥ አይደለም። የተለያየ ነው:: መሬት መኮናተር የሚቻለው አንዱ ክልል ላይ በጣም ለጥቂት ዓመታት ሲሆን ሌላው ዘንድ ደግሞ ትንሽ ከፍ ያለ ሆኖ ይታያል::
በመሆኑም፣ በዘርፉ በብዙ እድለኛ የሆንባቸው ነገሮች ቢኖሩም፤ የፖሊሲ ማነቆ ስለነበረበት ባለፉት 50 ዓመታት ግብርናችን ማስገኘት የሚችለውን ውጤት አላስገኝም:: ለምሳሌ የ1975ቱ ፖሊሲ ለአርሶ አደሩ መሬት ይሰጣል የሚል ነው:: የ1995ቱ ፖሊሲ ደግሞ መሬትን የመንግሥት አደረገው:: እኤአ 2005 ደግሞ ፖሊሲውን እንደገና አዋቀሩት::
የኢትዮጵያ ሕዝብ መማር ያለበትና ሚዲያም በአግባቡ መሥራት ያለበት መንግሥት በግብርናው ሴክተር ሠርቶ ሕዝቡንና ሀገሩን ያሳደገ ሀገር አለመኖሩን ነው:: ለምሳሌ ራሺያውያን ከ70 ዓመት በኋላ ነው መነሳት የቻሉት:: የራሽያ መንግሥት እያረሰ፣ ሕዝቡን እየመገበ፣ መሬቱንም እያስተዳደረ ለመኖር ጣረ። ግን አልቻለም:: ምናልባት መንግሥት እያረሰ የሚመግባቸው ሀገራት ይኖራሉ:: ለምሳሌ፣ ኩባንና ሰሜን ኮሪያን ልንጠቅስ እንችላለን:: ነገር ግን እነሱ እንደኛ ብዙ ሕዝብ የላቸውም::
በተመሳሳይ ቻይናዎች ግብርናን በመንግሥት ማስኬዱን አልቻሉም:: እኤአ 1989 ማኦ ሴቱንግ ካረፉ በኋላ ዴንግ መጡ። ዴንግ ደግሞ የመንግሥት ሥራ አቁመው ግለሰቦች ሴክተሩን እንዲቀላቀሉ አደረጉ። እስከ 1992 ድረስም ቻይናውያን በኢኮኖሚው ማደግ ጀመሩ:: በመሐል ዘግየት ብሎ 2012 ላይ አሁን አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ያሉ ዢ ጂንፒንግ ሲመጡ ሀገሪቱ በዓለም ካሉ ሀገራት መካከል ታላቅ መሆን ቻለች::
እና የእኛም አቅጣጫ ጥሩ ቢመስልም ግለሰቦችን በዘርፉ እንዲሠሩ አሁንም አልጋበዘም:: እጅግ በጣም ግዙፍ ሕንጻ ያላቸው ሰዎች ወደ ግብርናው ገቡ ወይ? ቢባል አልገቡም:: እኔ የተወለድኩበት ጎቤሳ ወረዳ ከዛሬ 60 ዓመት በፊት ትራክተሮች ነበሩ። አምና ሔጄ ስጠይቅ የሉም:: ስለዚህ ይህ ግለሰቦችን ያለማበረታታትና መንግሥት ደግሞ እኔ እሠራዋለሁ የሚል አካሄድ ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ ይህ አይነት አካሄድ ደግሞ የትም አያደርስም::
ባለፉት ጥቂት ዓመታትም ቢሆን መሻሻል ካልሆነ በስተቀር ይህ ነው የሚባል ለውጥ የለም። ኢትዮጵያ በጣም ለምና ሰፊ ሀብት ያላት ሀገር ናት። ነገር ግን የፖሊሲ ችግር ምርታማ እንዳትሆን አድርጓታል:: ኢትዮጵያ ለግብርና ሥራ ለም መሬትና ሰፊ ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም በዘርፉ ያለው የፖሊሲ ማነቆ ምርታማ እንዳትሆን አድርጓል:: ከዚህ የተነሳ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሙከራዎች ቢኖሩም ጥሩ ተሠርቷል ብዬ መናገር ይከብደኛል::
ነገር ግን አንድ የሚሰማኝ መልካም ነገር አለ:: ይህም የሀገሪቱ ሀብት እንደቀድሞው በሰፊውና በትልቅ ቁጥር ወደውጭ ሀገር አይሸሽም የሚል ግምት አለኝ:: እዛ ላይ ጥሩ ነገር አለ:: አልፎ አልፎ በመስኖ የተሠራው ሥራም ጥሩ ነው:: ይሁንና እሱ ደግሞ በቂ አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- በግብርናው ዘርፍ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረግ ጥረት አለ። ምርትን ለውጭ ገበያ የማቅረቡ ሁኔታ አለ። ስንዴም በስፋት እየተመረተ ነው:: በአጠቃላይ ጅማሬውን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ጋሹ፡- ይሄ በጣም ጥሩ ነው:: ጥሩነቱ ግን ከሚገኘው ምርት ሳይሆን የይቻላልነቱ አርአያነት ላይ ነው:: ይሁን እንጂ መንግሥት ትራክተር እየገዛ በመስኖ አርሶ ሕዝቡን የሚመግብበት ሀገር የለም:: ኢትዮጵያም የተለየች ልትሆን አትችልም:: እነዚህ ነገሮች ከሚያበረክቱት ድርሻ ይልቅ ሞዴል መሆናቸው በጣም የሚበረታታና የሚደገፍ ነው:: ስለዚህ መንግሥት ቆም ብሎ በሴክተሩ የግሉ ዘርፍ እንዲገባ የሚችልበት ጉዳይ ላይ መሥራት አለበት:: ፖሊሲውንም መቃኘት ይገባል:: ይህ ካልተደረገ በስተቀር በመንግሥት ብቻ የሚሠራው ሥራ ማሳያ ከመሆን የዘለለ ብቻውን ሰርቶ የትም የሚያደርስ አይሆንም::
እኛ ደግሞ ትልቅ ሀገር ነን:: በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕዝብ ብዛት 12ኛ፣ በቆዳ ስፋት ደግሞ 27ኛ ነን:: እስካሁንም አመራረታችን በጣም ወደ ኋላ የቀረ ነው:: ስለሆነም በመንግሥት የተጀመረውን ሞዴል ተከትሎ ግለሰቦች ሴክተሩን ተቀላቅለው የየበኩላቸውን የሚያደርጉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሩዝ፣ ሻይ ቅጠልና ሌሎችም የግብርና ምርቶች እየተመረቱ ነው። ይሄ ደግሞ ቡናን በመሳሰሉ የተወሰኑ ምርቶች ላይ የተንጠለጠለውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት የሚለውጥ ነው:: ይሄን ከማላቅ አኳያ ምን ሊሠራ ይገባል?
ዶክተር ጋሹ፡- በእርግጥ ወደውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ ይችላሉ ከምንላቸው የግብርና ምርቶች ውስጥ ቡና ቀዳሚ ነው:: በእውነት ለመናገር የቡና ምርትን ሀገራችን የምትሰጠንን ያህል አልሠራንበትም::
በ1917 ዓ.ም የዛሬ 99 ዓመት ገደማ ማለት ነው የዩጋንዳ ቡናን ከተለያየ ርቀት ካለው ቦታ ሀብታሞች እየመጡ ምን እንደሚመስል ያዩ ነበር:: እኛ ግን ቡና ማምረት የጀመርነው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው የሚባል አይደለም፤ ረዥም ጊዜ ነው:: ያ ሁሉ ታሪክ እያለንና ወሳኝ የሆነ የአየር ንብረት እያለን ከቡና የተገባንን ጥቅም አላገኘንም:: ለቡና በቅጡ ትኩረት ከተሰጠው የዚህችን ሀገር የውጭ ምንዛሬ ችግርን በመፍታት ረገድ ሊደጉም የሚችል ሴክተር ነው::
ምክንያቱም ቡና አንዴ ከተተከለና በአግባቡ መያዝ ከተቻለ ለ70 ዓመት ያህል ምርት የሚሰጥ ነው:: ባለቤቱ ከፈለገ በ40 ወይም በ50 ዓመቱ ሊጎነድለው ይችላል:: ሲጎነደል ደግሞ እንደ አዲስ ተክል መሆን የሚችል ነው:: ስለዚህ ሰው ቡና ተከለ ማለት እድሜውን በሙሉ አመረተ ማለት ነው::
ስለዚህ በቡና ላይ መደረግ ያለበት ሒደት በስፋት መሠራት የሚገባው ነው:: ቡና አምራች የሆኑ አካባቢዎችን ጨምሮ በሌሎችም ቡና በስፋት እንዲመረት ቢደረግ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል:: አሁንም ቢሆን መጥፎ የሚባል አይደለም::
የቀሩትም ምርቶች እየተመረቱና ወደፊት እየመጡ መሆናቸው የሚበረታታ ነው:: ጅማሬው በጣም ጥሩ የሚባል ነው::፡ ነገር ግን መንግሥት መቼ ነው እርሻውን ትቶ ወደ ሌላ ሥራው የሚገባው? እስከመቼስ ነው የሚያርሰው? የሚለው ነገር መታሰብ አለበት:: ግለሰቦችን አበረታትቶ ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ማድረግ አለበት:: ድጎማውንም ብድሩንም ሰጥቶ እንዲሠሩ ቢያደርግ መልካም ነው:: ኩባና ሰሜን ኮሪያ ግትር ያሉ ሶሻሊስት ሀገሮች በመሆናቸው መንግሥት እስካሁን እያረሰ ነው:: እኛ ግን ከዚህ መውጣት አለብን::
አዲስ ዘመን፡- የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ የሌማት ትሩፋት፣ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችና ሌሎችም ተግባራት ለግብርናው ዘርፍ ውጤታማነት አጋዥ አቅም እንደሆኑ ይነገራልና እርስዎ ይህን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ጋሹ፡- እነዚህም መልካም ጅምሮች ናቸው:: ሆኖም ቀደም ብዬ እንዳልኩሽ ሞዴል ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው እንጂ አጋዥ ሊሆኑ አይችሉም:: ምክንያቱም ግብርና ማለት በጣም ግዙፍ ሴክተር ነው:: ከዚህ የተነሳ የጠቃቀስሻቸው እንደ አንድ ጉዳይ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ እንጂ አጋዥ ሊሆኑ አይችሉም ባይ ነኝ:: ይህ ግብርና ትልቅ ሴክተር ስለሆነ የተጠቀሱት ጥሩ ሞዴልና ሌሎችን ለማነሳሳት፣ ብሎም የይቻላልን መንፈስ ለመፍጠር የሚችሉ ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደሆነች ይታወቃል፤ በእንስሳት ሀብት ልማቱ ዘርፍ በእስካሁኑ ሒደት በአግባቡ ያልተሠራባቸው ናቸው የሚሉት ነገርና ከእጽዋት ምርቱ ጋር ተያይዞ መሠራት አለበት የሚሉት ነገር ካለ ቢጠቅሷቸው?
ዶክተር ጋሹ፡- በጥቅሉ የግብርና ፖለሲ ለግብርና ሙያተኞች ተሰጥቶ እንደገና መከለስ አለበት:: ድሮ የወጣው ፖሊሲ ለሶሻሊስት እንዲያመች ተብሎ ባለሙያዎችን አባርረው የተጻፈ እንጂ ሙያተኛው የጻፈው ፖሊሲ አይደለም:: የኢሕአዴግ መንግሥትም ሲመጣ የቀረጸው ፖሊሲ ከእዛ የተሻለ አይደለም::
የእንስሳት ሀብቱን በአግባቡ ለመጠቀም የመጀመሪያው ነገር የፖሊሲ ለውጥ መደረግ አለበት:: የሚቀረጸው ፖሊሲ ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚስማማ፣ ከሕዝቧ እድገት ጋር መሄድ የሚችል መሆን አለበት:: ይህ በጥቅሉ ሲታይ ነው::
ጠበብ አድርገነው ወደ ዕጽዋት ሳይንሱ (Plant Science) ማለትም በዕጽዋት ምርት የመጣን እንደሆነ የተለያዩ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል:: ኢትዮጵያ ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነው ምርት ከማሳ እስከ መጋዘን (ጎተራ) መግቢያው ድረስ የሚበላሸው በተባይ እንደሆነ ይነገራል:: ስለዚህ ይህን ማስተካከል ተገቢ ነው:: ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ መሬትን መታደግ ላይ ጥሩ የሆነ ሥራ ቢሠራ፤ እንዲሁም ሜካናይዜሽን ላይ የተሻለ ሥራ ቢሠራ ጥሩ ነው::
ከዚህ ሌላ ደግሞ አርሶ አደሩ ያምርት ስንል መሸጥ ያለበትንም ቦታ በማመቻቸት መሆን አለበት:: ግብርና ለሌሎች ሴክተሮች ማስፈንጠሪያ ብቻ ሳይሆን ራሱ ሯጭ መሆን አለበት:: ሲያስፈልገውም ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል::
እኛ በመልካዓምድራዊ አቀማመጣችን በጣም ሞቃታማ ከሆኑ ሀገሮች ጎን ነን:: በሌላ መልኩ ደግሞ ከአውሮፓም ሩቅ የምንባል አይደለንም:: ስለዚህ በአካባቢያችን ያሉ ሞቃታማ ሀገሮች የማያመርቱትን ብናመርት ኢትዮጵያን በጣም የሚያዋጣት ነው:: በዕጽዋት ሳይንስ በደንብ የተጠና እና ሁሉም ነገር የተሟላ ሆኖ እነ ሳዑዲ አረቢያ፣ የመንና ሱዳንም የማያመርቱትን የግብርና ምርት ብናመርት ከፍተኛ ደረጃ መድረስ እንችላለን::
በጥቅሉ ሊሠሩ የሚገባቸው ዋና ነገሮች የመሬት ፖሊሲ፣ ሜካናይዜሽንና አግሪካልቸራል ብድርና ፋይናንስ፣ ብሎም ገበያው ላይ ነው:: እነዚህ በጣም የተጠናከሩ መሆን አለባቸው::
የእንስሳት ሳይንሱን የተመለከትን እንደሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደሚባለውም በእንስሳት ከአፍሪካ አንደኛ በዓለም ደግሞ አስረኛ ናት:: ይህ በጣም ትልቅ ሀብት ነው:: በዚህ ሀብት ልንኮራም ደስተኛ ልንሆንም ይገባል:: ይህን ያህል ሀብት እያለን ስለምንድን ነው ይህ ነው የሚባል ጥቅም ማግኘት ያልቻልነው? እነ ኒውዝላንድ የሚታወቁት በወተት ምርት በተለይም በቺዝ ምርት ነው:: ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ የትኛውም የሠለጠነ ሀገር ብትሔጂ የምታገኘው የኒውዝላንድን የቺዝ ምርት ነው::
ስለዚህ እንስሳቱ ውጤት ያስገኙልን ዘንድ የመኖ አቅርቦት ሊኖረን ይገባል:: ይህ ግን በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ቢኬድ ታስቦበት የሚዘጋጅ አጥጋቢ መኖ የለም:: በዚህ ላይ ሊሠራ ይገባል::
ሌላው የእንስሳቱ የጤና አጠባበቅ ዘርፉ የተጠናከረ ነው ማለት አይቻልም:: በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ከብት ታመመ ሲባል ተፈልገው ከመምጣት ሌላ ከብት ከመታመሙ በፊት የሚደረግ ነገር እምብዛም የለም:: እንደ ሀገራችን በሽታው ከመከሰቱ በፊት በአግባቡ ህክምና የሚያገኘው የደስታ በሽታ ብቻ ነው:: ሌላ የከብትን ጤና የሚጠብቅ እንቅስቃሴ የለም የሚያስብል ነው:: የከብት ጤና አጠባበቅ ላይ ያለው ሒደት ደካማ ነው::
ሌላው የገበያ ሁኔታ ነው:: እንደሚታወቀው ደግሞ የግብርና ምርት ሰፊ እንዲሁም ደግሞ ቶሎ ካልተሸጠ በቀላሉ የሚበላሽ ምርት ነው:: ስለዚህ ምርቱን ከአንዱ ወደ አንዱ ለማዘዋወር የትራንስፖርቱም ሁኔታ ምቹ መሆን አለበት::
አሁን አሁን በመንግሥት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ሰምቻለሁ:: ሌላው ቀርቶ በዶሮ ምርት ለውጥ ለማምጣት ከሳዑዲ አረቢያ ድረስ ጫጩት እየመጣ እንደሆነም አውቃለሁ:: እነዚህ መልካም ተግባራት ሊሰፉ እና ባለሀብቱን በስፋት እንዲያቅፉ ማድረግ ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- ግብርናው በቀጣይ የምግብ ዋስትናም፣ የገቢ ምንጭንም የኢንዱስትሪ ዘርፉ መጋቢም ከማድረግ አኳያ ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
ዶክተር ጋሹ፡- መጀመሪያ ወዳነሳሁት ጉዳይ ልመልስሽና የመጀመሪያው ጉዳይ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልጋል:: ፖሊሲው በዘርፉ ባለሙያዎች የሚቀረጽ ሲሆን፣ ካለፈ ድክመትም ጥንካሬም ተቀምሮ የሚሠራ ቢሆን መልካም ይሆናል:: የተቀረጸም ካለ መከለስ አለበት:: ውጤታማ የሆንባቸው ዘርፎች ካሉ ደግሞ እነሱንም ማጠናከር መቻል አለብን:: የዚህ አይነት ልምድ ያለን ስለመሆኑ ግን እጠራጠራለሁ::
ለዚህም ሁለት ምክንያት ልጠቅስልሽ እችላለሁ:: የኢትዮጵያ ግብርና በትልቅ ደረጃ ውጤታማ ሥራ የተሠሩባቸው ሁለት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ነበሩ:: እኔ የማውቃቸው ናቸው እንጂ ከዛም በላይ ሊሆኑ ይችላሉ:: አንደኛው ካዱ ነው፤ የካዱ ውጤታማነት ለኢትዮጵያ ትምህርት መሆን ነበረበት:: ኢትዮጵያ እንዴት አድርጋ የግብርና ኤክስቴንሽን (Agricultural extension) ማስፋፋት ይቻላል የሚለው ቲዮሪ ተጠይቆ የካዱ ልምድ ኢትዮጵያ ውስጥ መስፋፋት ነበረበት::
በወቅቱ ሥራውን ሲሠሩ የነበሩት የእኛው ጓደኞች ከዘጠነኛ እና ከአስረኛ ክፍል ተቀጥረው ነበር:: ነገር ግን በዚያን ጊዜ የበሰለ ማንነት ባይኖረኝም አሁን አሁን ወቅቱ ላይ ይሠራ የነበረውን ሥራ ሳስብ የካዱ ሥራ በዚያን ጊዜ የነበረው ልክ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሚሠራው አይነት ሥራ ነው:: ትምህርት ሥርዓት ውስጥ ለመምህሩ የሚሰጠው ሰዓት ወይም ክፍለ ጊዜ ተቆጥሮ ነው፤ ያንን ማስተማር ያልሆነለትን መምህር መቀበል አይቻልም:: የግብርና ሥራ ላይ ግን ቁጥጥር ማድረጊያ ሥርዓቱ ራሱ ምንድን ነው? የሚያስብል ነው:: አንድ የእርሻ ወኪል ምን ሠራ? ለወኪሉ ዓመቱን ሙሉ ደመወዝ ከተከፈለው በዓመቱ መጨረሻ ምን ሠራህ? የሚል ነገር መምጣት መቻል አለበት::
ሌላው ኤክስቴንሽን ኤንድ ፕሮጀክት ዲፓርትመንት ኦፍ ዘ ሚኒስቴር ኦፍ አግሪካልቸር (Extension and project department of the minister of agriculture) (ኤፕድ) የተባለው ሲሆን፣ በአጼ ኃይለሥላሴ ከዚያም በደርግ ጊዜ የነበረ ነው:: ኤፒድ ኢትዮጵያን በግዛት ሳይሆን በራሱ የከለላት ነበር:: ቀደም ሲል የግብርና ምርምር ቢሮው የተለያዩ ቦታዎችን የሚያካልል ነበር፤ አሁን ያንን ነገር አላይም::
የኢትዮጵያ የግብርና የአስተዳደር ሥርዓት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ (ፌዴራል)፣ ክልል፣ ዞን ከዚያ ወረዳ እያለ ነው፤ ትልቁ ሥራ አሁን የሚሠራው በዞንና በወረዳ መካከል ነው:: ድሮ ዞንና ወረዳን የሚያገናኝ አውራጃ የሚባል ነበር:: በአሁኑ ወቅት በዞን ስር አስራ አምስትና ሃያ ወረዳ ሊኖር ይችላል:: ከወረዳው ብዛት የተነሳ ለባለሙያዎቹ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ይሆናልና ግብርና የራሱን መዋቅር አበጅቶ ቢንቀሳቀስ ጥሩ ነው::
ሌላው ምርምር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር በእውነቱ በጣም በሚያሳዝን ደረጃ ላይ ነው ያለው:: በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ውስጥ ሶስተኛ ዲግሪ ያላቸው ዘጠኝ በመቶ ብቻ ናቸው:: 41 በመቶ ሁለተኛ ዲግሪ፣ 50 በመቶ ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው:: የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው በቴክኒክ ጉዳይ ላይ ረዳት ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ በምንም አይነት መንገድ ተመራማሪ ሊሆኑ አይችሉም::
የኬንያን ተሞክሮ ብንወስድ፣ ተመራማሪዎቹ ከፍተኛ ተከፋይ ናቸው:: በምርምር ዘርፉ መሥራትን የሚጋብዝ ነው:: በርካታ ታላላቅ ምሁራን ጡረታ ከወጡም በኋላ በምርምሩ ይሳተፋሉ::
ስለዚህ የሀገሪቷን የግብርና ሥራ በተፋጠነ ሁኔታ ለማሳደግ የምርምር ማዕከሉ በጣም ማደግ አለበት:: የአርሶ አደሩን አኗኗር ማዕከል አድርገው አብረው የሚሠሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚል አተያይ አለኝ::
ዩኒቨርሲቲዎች ከማስተማር ጎን ለጎን በተለይ የግብርና ትምህርት የሚሰጥባቸው ተቋማት ለግብርናው ያበረከተው ነገር ምንድን ነው ተብሎ ሊጠየቁ ይገባል:: ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በወሬ ሳይሆን በተግባር መተሳሰር አለባቸው:: ለምሳሌ ሰላሌ፣ ጅማና አሰላ ዩኒቨርሲቲ ሄደሽ የግብርና ድጋፍ የሚያደርግላችሁ ማን ነው? ብለሽ አርሶ አደሮችን ብተትጠይቂያቸው የግብርና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡሽ እንጂ ያሉበት አካባቢ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ አይሉሽም ብዬ አስባለሁ:: በወሬ ደረጃ ሥራው አለ ሊባል ይችላል፤ መሬት ላይ ግን ያለ አይመስለኝም:: እናም ዩኒቨርሲቲዎች ከማስተማር ጎን ለጎን የሚጠበቅባቸው ምርምር ማድረግ ነው:: የሚሠራው ምርምር ደግሞ ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል::
እኔ በአርከንሰስ ዩኒቨርሲቲ በማስተምርበት ጊዜ ጊቢው ውስጥ የሀገሪቱ የግብርና ሚኒስቴር ቢሮዎች በመኖራቸው ምቹ በሆነ ሁኔታ ሥራችንን እንሠራለን:: ቀደም ሲል ደግሞ እኔ ኢትዮጵያ ጅማ እርሻ ኮሌጅ ሆኜ ለመሥራት ስነሳሳ መካከለኛ የሆኑ የዘርፉ ባለሥልጣናት እንኳ ምቹ ሁኔታ እንዳይኖር ይከለክሉን ነበር::
በእኛ ሀገር አሁንም አንድም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የግብርና ጽህፈት ቤት የለም:: ቢኖር ኖሮ በዘርፉ የሚሠራ ሰው በጊቢያቸው ውስጥ አለ ማለት ነው:: ሁለተኛ ደግሞ ወደ ወረዳ አካባቢ ለመሄድ የተያያዘ ነገር ይኖራልና ለመሥራት አይከብድም::
ሌላው ልጠቅስ የምፈልገው፣ ኢትዮጵያ በእርሻ ወኪል (የግብርና አገልግሎት በሚሰጡ ሰዎች ቁጥር) ከዓለም ሀገራት ከቻይና ቀጥላ ሁለተኛ ናት፤ ከሕንድም ሆነ ከኢንዶኔዥያ በላይ ናት:: አንድ መቶ ሁለት ሺ የግብርና ሰዎች አሉን:: ህንድ ያላት ወደ 60 ሺ ገደማ ነው:: ቻይና ደግሞ ወደ መቶ ምናምን ያህል ሺ ነው:: ይሁንና እኛ ይህንን አልተጠቀምንበትም:: ችግሩ ምንድን ነው? በሚለው ላይ ግን መነጋገር ያስፈልጋል::
የኤክስቴንሽን ሙያተኞች ተመካክረው ኤክስቴንሽኑን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል:: በተለይ ውሃ በማቆር ክረምት ከበጋ አርሶ አደሩ ማምረት እንዲችሉ እገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል:: ቢያንስ እያንዳንዱ አርሶ አደር ቤተሰቡን መመገብ የሚያስችለውን ውሃ በክረምት ይዞ በጋውን ሁሉ ማምረት የሚችልበት መንገድ መፈጠር አለበት። ይህ በጣም ቀላል ነው:: ግብርና ሚኒስቴር በዚህ ዙሪያ በአግባቡ መሥራት አለበት:: ትልቁ ሀብታችን ውሃ ነው፤ ይሄን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስፈልገው ብልሃት ብቻ ነው:: ክረምቱን የሚባክነውን ውሃ መያዝ ከቻልን አሳውንም በጓሯችን ማግኘት እንችላለንና::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::
ዶክተር ጋሹ፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም