የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማዕድን ሀብት የታደለ ነው። ክልሉ በስፋት ከሚታወቅባቸው ማዕድናት መካከል ወርቅ አንዱ ነው። የወርቅ ማዕድኑ በባህላዊ መንገድ በማህበራት እየለማ ሲሆን፣ ምርቱም ለብሔራዊ ባንክ ገቢ እየተደረገ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ነው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወርቅን በኩባንያ ለማምረት የሚያስችሉ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የማዕድን ልማቶቹ፣ በተለይ የወርቅ ማምረት ሥራው፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እየቻሉ ነው። የወርቅን ያህል ባይሆንም የሌሎች ማዕድናት ልማት ተግባርም ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል።
የክልሉ ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀመድ እንደሚገልጹት፤ በክልሉ እንደ ወርቅ ካሉት የከበሩ ማዕድናት በተጨማሪ ለኢንዱስትሪና ለግንባታ ግብዓትነት የሚውሉ ሌሎች በርካታ ማዕድናት በስፋት ይገኛሉ። ኮንስትራክሽን ግብዓት ማዕድናት መካከል ለግንባታ ማጠናቀቂያነት የሚውለው እምነበረድ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ እንደ ሲሚንቶ ፋብሪካ ላሉ ኢንዱስትሪዎች የኃይል ምንጭ በመሆን እያገለገለ ያለው የድንጋይ ከሰል ነው።
ከእነዚህ በተጨማሪ በምርት ደረጃ የማይታወቁም ሌሎች በርካታ ማዕድናት በክልሉ አሉ የሚሉት ኃላፊው፤ ሌሎች በክልሉ አሉ የተባሉት ማዕድናት ላይ ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል። በግኝት ያልተረጋገጡ የማዕድናት ዓይነቶች በርካታ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል የእምነበረድ ማዕድን ልማት በስፋት ሲካሄድ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በሚፈለገው ልክ እየተመረተ እንዳልሆነ አስታውቀዋል። ዘንድሮ እምነ በረድ በማምረቱ ሂደት ከሌላው ጊዜ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በድንጋይ ከሰል ምርትም ካለፈው ዓመት የተሻለ ምርት እየተገኘ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ክልሉ በማዕድን ልማት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ተመራጭ እንዲሆን የሚያደርጉ የኢንቪስትመንት አማራጮች እንዳሉት እንደሚጠቁም ተመልክቷል።
ዘንድሮ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች በግብዓትነት የሚያገለግለውን እምነበረድ ማዕድን የማምረት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ኃላፊው ጠቅሰው፣ ባለፉት ጊዜያት በክልሉ በታየው የጸጥታ ችግርና አለመረጋጋት ምክንያት እምነበረድ ለማምረት የሚያስችል ሁኔታ እንዳልነበር ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት እምነበረድ የማምረት ሥራ አፈጻጸም በጣም ዝቅተኛ እንደነበርም አስታውሰዋል።
በበጀት ዓመቱ 20ሺ ሜትር ኪዩቢክ ለማምረት ታቅዶ 1ሺ327ሜትር ኪዩቢክ እምነበረድ ብቻ መምረቱን ነው ኃላፊው ያመለከቱት። ከዓመት በፊት በክልሉ ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ እምነ በረድ ለማምረት ፈቃድ ወስደው በዘርፉ የኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማሩት ትልልቅ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ለማድረግ የማይችሉበት ሁኔታ እንደነበርም አስታውሰዋል። ችግሩ በዘርፉ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይካሄድ ማድረጉን ነው ኃላፊው የተናገሩት።
ዘንድሮ በእምነበረድ ልማቱ የተሻሻለ አፈጻጸም ሊታይ እንደሚችል ኃላፊው ጠቅሰው፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም እየታየ ካለው አፈጻጸም መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ መሆኑን ገልጸዋል። በ2016 በጀት ዓመት በሩብ ዓመት ውስጥ 2ሺ ሜትር ኪዩብ ለማምረት ታቅዶ፤ 209 ሜትር ኪዩብ እምነ በረድ ማምረት መቻሉን አስታውቀዋል። የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አብዛኛው ወቅት ክረምት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሁኔታም ለማዕድን ልማት ምቹ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ሩብ ዓመቱ ብዙ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማድረግ የማይቻልበት ወቅት መሆኑን ገልጸው፣ የምርቱ መጠን ያነሰውም በዚህ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ከሁለተኛው ሩብ ዓመት ጀምሮ እምነበረድ በእጥፍ መመረት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉም አመላክተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ለማዕድን አምራቾች ፈቃድ የሚሰጠው በሁለት ዓይነት መንገድ ነው፤ በክልሉ እምነ በረድ በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን፣ አምራቾቹም ከፍተኛ ባለፈቃድ አምራቾችና አነስተኛ አምራቾች ተብለው ፈቃድ የወሰዱ ናቸው። ከፍተኛ ባለፈቃድ አምራቾች ፈቃድ የሚሰጣቸው በማዕድን ሚኒስቴር ነው። አነስተኛ አምራቾች የሚባሉት ደግሞ ከክልሉ ፈቃድ ወስደው በማምረት ሥራ ላይ ይሰማራሉ።
በክልሉ የእምነ በረድ ማዕድንን ለማምረት ከ200 በላይ ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ። እነዚህ ባለሀብቶች ካምፖቻቸውን አድሰው ወደሥራ መግባት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመለየት እየተሰራ ነው። አብዛኛዎቹ የመሥሪያ ቦታዎች በአምራቾች እጅ ሲሆኑ፣ ወደ ማምረት ሥራ መግባት ሲፈልጉ ካምፓቸውን አድሰው ሥራ መጀመር የሚችሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል።
የእምነበረድ ማዕድን በክልሉ በሦስት ዞኖች ይገኛል የሚሉት ኃላፊው፤ ማዕድኑ በአብዛኛው በመተከል ዞን አካባቢ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። በዞኑ ማዕድኑን የማልማት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሶሳ እና በከማሼ ዞንም እምነበረድ እንደሚመረት ይገልጻሉ።
ኃላፊው እንዳሉት፤ በክልሉ ስላለው የእምነበረድ ድንጋይ ክምችት ጥናት እየተደረገ ነው። በጥናት የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም በሄክታር በርካታ መጠን ያለው ክምችት እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ። እስካሁን ባለው መረጃ ለማንኛውም በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልግ ባለሀብት የሚበቃ ክምችት በክልሉ አለ።
ቀደም ሲል የክልሉ የእምነበረድ ምርት በብሎክ ብቻ እየተመረተ ወደተለያዩ ቀለሞችና ቅርጻ ቅርጾች የሚቀይሩ ፋብሪካዎች እንደሚወሰድ የጠቆሙት ኃላፊው፤ አሁን ላይ በክልሉ የተቋቋመው ፋብሪካ ብሎክ የማምረት ሥራ ከጀመረ ወዲህ የተሻለ ምርት ማምረት እየተቻለ መሆኑንም ይናገራሉ። ፋብሪካው በሚፈለገው መጠንና ቅርጽ ብሎክ በመቅረጽ እምነበረድ እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተለያዩ ነገሮች ለማምረት የሚያገለግለውን ተረፈ ምርት መልሶ መጠቀም ላይ ግን ክፍተቶች እንዳሉበት አመላክተዋል።
የእምነበረድ ተረፈ ምርት የተለያዩ ነገሮች ሊመረትበት እንደሚችል ኃላፊው ጠቅሰው፣ ለአብነት በጥቃቅንና አነስተኛ የሚደረጁ ወጣቶች ከተረፈ ምርቱ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችን፣ የቀለም ዓይነቶችን እና የመሳሰሉትን ሥራዎች መሥራት የሚችሉበት ፋብሪካ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
አሁን ላይ ያለው ፋብሪካ የብሎክ ሥራውን ብቻ እንደሚሰራ አመልክተው፣ በቀጣይ ከዚህ ጎን ለጎን የቀለም ፋብሪካ ቢቋቋም ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም ውጤታማ ሥራ መሥራት ይቻላል ይላሉ። ከተረፈ ምርቱ ብዙ ነገሮች ማምረት እየተቻለ ብዙ ተረፈ ምርት እየባከነ መሆኑን ተናግረው፣ ይህ ለብዙ ሥራ ሊውል የሚችል ተረፈ ምርት እንደማንኛውም ዓይነት ቆሻሻ እየተጣለ እንደሆነ ይናገራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ እስካሁን ባለው መረጃ ከተረፈ ምርቱ ቀለም ማምረት ይቻላል፤ መድኃኒቶችንም እንዲሁ ማምረት ይቻላል፤ በቀጣይ በተረፈ ምርቱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራበታል።
በክልሉ በተመሳሳይ እምነበረድን ለማምረት የሚችል ሌላ ሁለተኛ ፋብሪካ በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አቶ ካሚል ጠቅሰው፣ ‹‹ግንባታው ሲጠናቀቅ እምነበረድ የማምረቱ ሥራ በይበልጥ ይጠናከራል፤ የተሻለ ምርት ማግኘትም ይቻላል›› ብለዋል።
ለእምነበረድ ምርት ቀደም ሲል የገበያ ትስስሮች መፈጠራቸውን አስታውሰው፣ ለምርቱ ምንም ዓይነት የገበያ ችግር እንደሌለም አስታውቀዋል። በሥራ ላይ ያለው የእምነበረድ ፋብሪካን የገበያ ሁኔታ ለአብነት ጠቅሰው ኃላፊው ሲያብራሩም፣ እስካሁን ምንም ዓይነት የገበያ እጦት አጋጥሞት እንደማያውቅ አመልክተዋል። እንዲያው ፋብሪካው ቅድመ ክፍያ ተከፍሎት እንደሚያመርት ነው የተናገሩት።
ፋብሪካው እምነበረድ በራሱ ቦታ ላይ እንደሚያመርት ጠቅሰው፣ ገበያ ለማፈላለግ ሲል የሚያጠፋው ጊዜ እንደሌለና የማምረት ኃላፊነቱን ብቻ እንደሚወጣ አስታውቀዋል። ፋብሪካው እምነበረድ በማምረት ሥራ ዋንኛው ትኩረት መሆን ያለበት ማምረት መቻል ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ የገበያ ችግር የለበትም ሲሉ ተናግረዋል።
ሌሎች አምራቾችም አዲስ አበባ አካባቢ ካሉ ፋብሪካዎች ጋር ውል ገብተው እንደሚሰሩ ጠቅሰው፣ አንዳንድ አምራቾች ደግሞ ሌላ ቦታ ላይ ፋብሪካ እንዳላቸውና ምርታቸውን ወስደው ቀጣዩን ሥራ እንደሚሰሩ ኃላፊው ጠቁመዋል።
አሁን በዘርፉ የተሰማሩ አብዛኛዎቹ አምራቾች የካምፕ እድሳት በማድረግ ወደ ማምረት ሥራ ለመግባት የሚያስፈልጓቸውን ቅድመ ዝግጅቶች እያደረጉ መሆናቸውን የሚናገሩት ኃላፊው፤ ይህ ደግሞ ዘንድሮ ምርቱ በተሻለ ሁኔታ እንደሚመረት እንደሚያመለክት ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ባለው የክልሉ ጸጥታ ሁኔታ ካምፓቸውን ሳያድሱ የቆዩ ሌሎች አምራቾችም እንዲሁ ዘንድሮ ካምፓቸውን አድሰው ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ማዕድኑ በተሻለ ሁኔታ ይመረታል፤ የተያዘው እቅድም ከግብ ይደርሳል ብለዋል።
በክልሉ አሁን ያለው ሁኔታ የእምነበረድ ምርት መሻሻሎች የታየበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁሉም አምራቾች ወደ ማምረት ሥራው ሲገቡ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ይህን ለማስቀጠል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በክልሉ የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ የታየውን አፈጻጸም በተመለከተ ሲያብራሩም በ2016 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፍ ለአንድ ሺ453 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልጸዋል። በሩብ ዓመቱም 1ሺ 159 ያህል ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል። ይህም ከአፈጻጸም አንጻር ሲታይ የተሻለ የሥራ እድል የተፈጠረበት መሆኑን አመልክተው፣ የሥራ እድሉ በአብዛኛው በወርቅ ማዕድን ዘርፍ የተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። በእምነበረድ ፣ በድንጋይ ከሰል እና በሌሎች ማዕድናት ላይ ያለው የሥራ እድል ፈጠራ ብዙ የሚባል እንዳልሆነም ገልጸዋል።
የሀገሪቱ የግንባታ ዘርፍ እንደ እምነበረድ ያሉ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶች በስፋት እንደሚያስፈልጋት ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የግንባታ ማጠናቀቂያ ከውጭ እንደሚገባም መረጃዎች ያመለክታሉ። ለእዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ እየወጣ ነው። በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ የግንባታ ማጠናቀቂያዎች ጭምር ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ ነው። የዚህ አንዱ ምክንያት ደግሞ በሀገሪቱ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶች ላይ ያለው የአመለካከት ችግር መሆኑ ይጠቆማል።
በሀገር ውስጥ ከሚመረቱ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶች አንዳንዶቹ የጥራት ችግር እንደሚስተዋልባቸው ቢታወቅም፣ በጥራታቸው ጥርጣሬ ውስጥ የማይገቡም እንዳሉም አቶ ካሚል የክልሉ የእምነበረድ ምርት ምንም ዓይነት የገበያ ችግር የለበትም ሲሉ ከሰጡት መረጃ መረዳት ይቻላል። ይህን ምርት በስፋት እንዲመረት በማድረግ በግንባታ ማጠናቀቂያ ግብዓቶች በኩል ያለውን ክፍተት በተወሰነ መልኩ ለመሙላት ይቻላል። ይህ መሆኑ ሀገሪቱ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በስፋት በማምረትና በመጠቀም ከውጭ የሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶችን ለመቀነስ እያከናወነች ላለችው ተግባር ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
የእምነበረድ ማዕድን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በስፋት ይገኛል። ይህም ማዕድን በስፋት ለማልማት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የግንባታውን ዘርፍ የግንባታ ማጠናቀቂያ ችግር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባል። ለእዚህም ሰላምን በማረጋገጥ በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችን አጠናክሮ ከመቀጠል በተጨማሪ ለዘርፉ ኢንቨስትመንት ትኩረት ሰጥቶ መሰራትም ያስፈልጋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2016