እርቅ ሀገር የሚያንጽ የትውልድ ድልድይ

 በሀገራችን እርቅ የሚያሻቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ከትናንት የመጡ፣ ዛሬ የተፈጠሩ ፤ ታሪክ አጣመው፣ እውነት አዛንፈው ትርክት በፈጠሩ ራስ ወዳድ ግለሰቦችና ቡድኖች የተፈበረኩ የልዩነት ቁርሾዎችም ጥቂት አይደሉም። እኚህንና መሰል የትውልዱን መረማመጃ የዘጉ የጥፋት ሃሳቦች እንዲወገዱና በምትኩ አዲስ የፍቅርና የእርቅ መረማመጃ እንዲሠራ ሀገር የሚያንጽ እርቅ ያስፈልጋል ።

ሀገር ብዙ እጆች ከብዙ ሃሳብ፣ በብዙ ጥበብ አላቁጠው የሠሯት ነች ። ይቺ በብዙ ሃሳብ ከብዙ ጥበብ ተላቁጣ የተሰራች ሀገር ሰፊና ጥልቅ፣ ብዙሃነትን የለበሰች ነች ። በዚህ እሳቤ እንደ ሀገር ከተሠራንበት አብሮነት የመለያየት ሃሳብ እንዴት ገባብን? የዚህ ርዕስ ጥያቄ ነው።

ከሥነምግባርና ከግብረገብነት እንዲሁም ደግሞ ከአብሮነት አንጻር ኢትዮጵያን ድሮና ዘንድሮ ብለን ብንመለከታት ሁለት አይነት ማንነቶችን እናገኛለን። የበፊቱ ትውልድ ኢትዮጵያዊነትን ሲገልጸው የታሪክና የአብሮነት ውህድ ብሎ ነው። የአሁኑ ትውልድ ይሄን ስም ሲፈታው.. እኔና የእኔ ብሎ ነው። በእኚህ ሁለት ፊትና ኋላ አረዳዶች ውስጥ ጸጋውም ሆነ መርገምቱ የሚያርፈው በሀገርና ህዝብ ላይ ነው።

‹እኔ እና እኛ› ትናንትም ሆነ ዛሬ ዓለምን ለሁለት የገመሱ እዛና እዚህ የሚረግጡ አመለካከቶች ናቸው። እኛ ስንል ብዙሃነትን ከማስታወስ ጎን ለጎን ለጋራ ታሪክና ለጋራ እሴቶች እውቅና እየሰጠን ነው። ሰላምና አንድነትን መቻቻልንም እየሰበክን ነው። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያሉ በወርቅ ምንጣፍ ላይ ያራመዱንን የወንድማማችነት ፈለጎችን እየገለጥን ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የሕግ ሁሉ በኩር፣ የሥርዓት ሁሉ መነሻ የሆነውን ፍቅር ለትውልዱ እያስቀመጥን ነው።

እኔ ስንል ግን ከሰፋና ከገዘፈ ህብረብሄራዊ ማንነት ውስጥ አንድ ነጠላ እውነት መምዘዝ ነው። በፍቅርና በአብሮነት የተገነባውን ኢትዮጵያዊነት ሌላ ባዕድ መልክ መስጠት ነው። የጽናትና የአይበገሬነት ምሳሌ የሆነውን ብዙሃነት ማደብዘዝ ነው። ፍቅርን ምንድነህ ፣ አብሮነትን ወዲያ ሂድ እንደማለት ነው። ከፍ ሲል ደግሞ ትውልዱን ጥላቻና ራስ ወዳድነትን ማስተማር ነው። ትውልድ ፍቅር ያልወረሰባት ሀገር ደግሞ ከመደማማት በስተቀር ምንም መዳኛ የለውም ። ከዚህ አንጻር እንደመጣንበት እና እንደወረስነው ታሪክ እኛ ብለን ጀምረን እኛ ብለን የምንጨርሰው አሁናዊ የጋራ ተግባቦት ያስፈልገናል።

ሀገር ትናንትና ዛሬ በትውልዶቿ በኩል የተለያየች ናት። ጀግና ትውልድ ሁልጊዜም መነሻው ፍቅር ነው። ፍቅር የገባበት፣ እርቅና ተግባቦት ያለበት ፖለቲካና ማህበራዊ መስተጋብር ለትውልዱ ትልቅ እድል ይዞ የሚመጣ ነው። የዚህ ትውልድ ሰፋፊ አዳራሾች አነጋግረው የሚያግባቡ፣ አደማምጠው አንድ የሚያደርጉ መሆን አለባቸው።

የእኛ ድምጽ ወደ ነገ የሚሄድ ነው። የእኛ ፖለቲካ፣ የእኛ ንግግር ሩቅ የሚሰማ ነው። ማንም አይሰማንም ብለን በሹክሹክታና በለሆሳስ ያወራነው እንኳን ለሌላው ጆሮ የሚሰማ ነው። ማንም አየኝ አላየኝ ሳንል ከእኛ የሚጠበቀውን በጎ ነገር ማድረግ ብንችል ብዙ የምንቀርፋቸው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ነበሩ።

ትውልድ ሂደት ነው። በአንድ ጊዜ የሚሆን አይደለም። ግን ዛሬ ላይ በምንሆነው በየትኛውም ነገር እየተፈጠረ እና እያደገ የሚሄድ ነው። አሁን ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የምናደርገው የትኛውም ነገር በትውልዱ አእምሮ ውስጥ ወደነገ የሚሄድ ነው። ዝግ ያልን ቢመስለንም ከፖለቲካና ከብሄር ሽኩቻችን ጋር ወደነገ እየሄድን ነው። ዝግ ያልን ቢመስለንም ከጥላቻና ከእኔነታችን ጋር ወደ ፊት እየገሰገስን ነው።

አሁን ላይ ቆመን ስለፍቅር አንድ ወንበር ላይ ካልተቀመጥን፣ ባማሩ ባዶ አዳራሾቻችን ውስጥ ስለአብሮነት ካልተሰበሰብን ትውልዱን እየበከልነው ነው። በርግጥ ከየትኛውም ሀገርና ህዝብ በላይ የአብሮነት ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን። ዓለምን ለአፍታ ብንቃኛት የእኛን ያክል የተደባለቀና የተሰናሰለ ታሪክና ትውፊት፣ እምነትና እውነት ያለው ህዝብ የለም። ከዚህ ውስጥ መውጣት አይቻልም። የሚበጀን እንዳነሳሳችን አብሮ መቀጠል ነው። የሚጠቅመን ኢትዮጵያን ከፊት አድርጎ መከተል ነው። አብሮ ከመውደቅና ታሪክ አልባ ከመሆን ባለፈ ግፊያ ማንንም ፊተኛ፣ ማንንም በኩር አያደርግም።

እንደ ሀገር ሀገር ስንሆን፣ እንደ ህዝብ ህዝብ ስንሆን ያማረብን ምን ነበር? በተጋመዱና በተጠላለፉ እጅና ክንድ የተጠላለፈ ታሪክ ስናበጅ ያማረብን ምን ነበር? ለክብርና ለነጻነት ስንታገል፣ ከነጭ አገዛዝ ስንወጣ፣ ለሰብዓዊነት ስንተጋ ያማርነው እንዴት ነበር? በአንድነት ልቀን በዓደዋ ጀብድ ስንጽፍ፣ በአብሮነት ደምቀን ኢትዮጵያዊነትን ስናስጠራ መነሻችን ምን ነበር? የሚሉትን መጠየቅ ተገቢ ነው ።

ከጋሞ ዮ መስቀላ፣ ከወላይታ ጊፋታ፣ ከሲዳማ ጨምበላላ መዐድ ስንቀርብ፣ በሴራ እና በያኦዴ፣ በኤሬቻና አሸንዳ ሶለን ፊት በወንድማማች ስንቆም ያበረታን ምን ነበር? በመስቀል ፋሲካው፣ በኢድና አረፋ ተያይዘን ስንመጣ፣ ተቀራርበን ስናወጋ ጥበባችን ምን ነበር? ከራቀ ትናንት ወደዛሬ ስንመጣ፣ ከቀረበ አሁን ወደ ራቀ ነገ ስንሄድ በምን ተሳፍረን፣ ምንን ተስፋ አድርገን ነው? መልሱ ፍቅር ነው.. መልሱ አንድነት ነው።

ኢትዮጵያዊነትን በዚህ ልክ ያገነነው ፍቅር ነበር። በዚህ ልክ እንድንበረታና እንድንጠነክር ያደረገን አብሮነት ነበር። አሁንም ፍቅር ነው የሚያስፈልገን። ተቀራርቦ እንደመወያየት፣ ተወያይቶ እንደመስማማት ታላቅ ጥበብ የለም። ብዙዎች ጥበብን ያልሆነ ቦታ ይፈልጉታል። ታላቁ ጥበብ ያለው ከሰው ልጆች ጋር በጋራ መኖር ውስጥ ነው። ይሄ እውነት በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ላይም ሳይቀር ሰፍሮ ይገኛል።

ፍቅርን የሕግ መጀመሪያ፣ የሥርዓት ፊተኛ ያላደረገ ሀገርና ህዝብ፣ ፖለቲካና ፖለቲከኛ በምንም ቢበረታ መዛሉ አይቀርም። አጀንዳችንን ፍቅር አድርገን ለእርቅ ስንቀመጥ ብቻ ነው ፍሬ የምናፈራው። ጉዳያችንን ሀገርና ህዝብ አድርገን ስንሰበሰብ ብቻ ነው በልዩነቶቻችን ውስጥ የጋራ አቋም የሚኖረን። ፍቅር ማሸነፍ አይደለም። ፍቅር ልክ የሚሆነው በመሸነፍ ውስጥ ነው። የኛ ፖለቲካ ደግሞ የለመደው ማሸነፍን ነው። የእኛ ጭንቅላት የተለማመደው ጥሎ ማለፍን ነው። ማሸነፍን ሽተን የምንቀመጥ ከሆነ እርቅና ስምምነት አይመጣም።

ትውልዱ ሳይገፋፋ፣ ፖለቲከኞቻችን ሳይጠላሉ የሚሄዱበት የፍቅር ድልድይ መገንባት አለበት። በእርቅ ደማችንን ካላደረቅን ወደፍቅር መቅረቢያ ሌላ መንገድ አናገኝም። አባቶቻችን ሲያስታርቁም ሆነ ሲምሩ ‹ይቅር ለእግዜር› ብለው ነው። አማኝ ለሆነ ማህበረሰብ ፍቅርና ይቅርታ ማህበራዊ እሴቶች እንጂ በል ተብለው የሚባሉ ሃይልና ግዴታ የሚያሻቸው ነገሮች አይደሉም። በአንድነት መዐድ ፊት በአንድ የበላንባቸው ፎሌዎቻችን፣ በአንድ የጠጣንባቸው ሽክናዎቻችን ታሪክ አውሪ ከመሆን በላይ ለዛሬ መቧደናችን መልስ የሚሰጡን ናቸው።

ብዙ ታሪክ፣ የተለያየ ህዝቦችና እሴቶች ባላት ሀገር ውስጥ ነን። ልዩነታችን ከአንድነታችን አይበልጥም፣ በልጦም አያውቅም። ኢትዮጵያ ሰፊ ግዛት ናት። ባህሏ፣ ተፈጥሮዋ፣ መልካምድሯ፣ ሥርዓቷ፣ ወግ ልማዷ በፍቅር ለሚኖሩ የበቃ ነው። በፍቅር ካልሆነ ግን ሀገር ጠባብ ናት። ሁላችንንም የሚያግባባ አንድ እውነት ቢኖር ጥላቻ መልካሙን የሚያከፋ፣ ሰፊውን የሚያጠብ መሆኑ ነው። የሚያምርብን ፍቅር ነው። በአንዳንድ አለመግባባት የወየበው አብሮነታችን እንዲመለስ ልባችንን ከጥላቻ አጽድተን ለዳግም ትንሳኤ መቀመጥ ከእንዳንዳችን የሚጠበቅ አሁናዊ ግዴታ ነው።

አበው ሲተርቱ ‹እርቅ ደም ያድርቅ› ይላሉ። እውነት ነው እርቅ ደም የሚደርቅበት፣ ፍቅር የሚመለስበት መድረክ ነው። የትኛውም መቆሳሰል፣ የትኛውም መደማማት በእርቅ ካልሆነ አይሽርም። ትናንትና በህዝቦቿ ፍቅርና አንድነት ወንዝ የተሻገረችው ሀገር ዛሬ ጥላቻን ባነገቡ አመለካከቶች ከክብሯ እየተንሸራተተች ያለችበት ሁኔታ ስለመኖሩ ሁላችንም ምስክሮች ነን። ችግርን ከስሩ ከመቅረፍ ይልቅ የማሽሞንሞን ልማድ አለን። ያሽሞነሞናቸው ችግሮች ዛሬ ላይ ፈርጥመው ጥርሳቸውን አግጠውብናል። ችግርን ከስሩ የሚል አዲስ ልምምድ ያስፈልገናል።

ውሎ የሚያድር ችግር ውሎ የሚያድር መጨረሻ አልባ ተግዳሮት ነው ይዞ የሚመጣው። በምንም ይሁን ትናንት ላይ የተፈጠሩ የፖለቲካም ሆነ የሃሳብ ልዩነቶች ወደዛሬ መጥተው ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ። ወደነገ እንዳይሄዱና ሌላ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ምንጫቸውን ማድረቅ ከእርቀ ሃሳብ ጎን ለጎን ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው። ፍቅርና አንድነትን ሊያዳብሩ የሚችሉ እንደ ውይይትና ምክክር ያሉ ትናንት ላይ ያልነበሩ አዳዲስ ህዝባዊ መድረኮች ያስፈልጉናል።

መድረኮቻችን እንደዚህ ቀደሙ አውርተንና ተሳስቀን ወይም ደግሞ አድማጭና ተናጋሪ በሆነ ሁናቴ ገብተን የምንወጣባቸው ሳይሆኑ ለችግሮቻችን የመፍትሄ ሃሳቦች የሚመነጩበት፣ መሰል ችግሮች እንዳይደገሙ መንገድ የምንዘጋበት ነው። አዲስ ልምምድ ይሄ ነው። ከዚህ ቀደም ያለአንዳች ተግባቦት ገብተን የወጣንባቸው፣ ተሰብስበን የተለያየንባቸው ብዙ መድረኮች አሉ። በጋራ ጉዳይ ላይ አድማጭና ተናጋሪ የለም። ሀገር በአንድ ሰው ሃሳብ ብቻ አትጸናም። ላሉብን ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅሎች ዘርፈ ብዙ ህዝባዊ ተሳትፎ ያስፈልጋል። በሀገራችን ላይ ያየነው የሰማነው እንዲህ ቢሆን እንዲህ ይሆን ነበር ብለን የምናምነው የመፍትሄ ሃሳብ አለ። ያን ሃሳብ በመወርወር ከዛ ሃሳብ ጋር የተቧደኑ ሌሎች ሃሳቦችን በመፍጠር ነው ሀገር የምናረጋጋው።

‹ነገርን ከስሩ ውሃን ከምንጩ› እንዲሉ የዛሬዎቹ ወደ ነገ እንዳይሄዱ፣ የትናንቶቹም ዛሬ ላይ እንዲያበቁ ሁሉንም አይነት የተግባቦት አማራጭ ማየቱ ተገቢ ይሆናል። ባለን የፖለቲካ አረዳድም ሆነ ሁለንተናዊ ቅኝት ትናንትና ዛሬ የተለያየን ለመሆናችን ማስረጃ አያስፈልገውም። ብዙሃነትን ታቅፋ ላለች ዥንጉርጉር ሀገር ዋናው እና ወሳኙ ነገር ከልዩነት በፊት ፍቅር ከልዩነት በኋላ ምክክር የሚለው ነው። ከልዩነት በፊት ፍቅር ልዩነት እንዳይፈጠር የሚያደርግ ሲሆን ከልዩነት በኋላ ምክክር ደግሞ ተፈጥሮ የነበረን ልዩነት የምንመልስበት ጥበብ ነው።

ኢትዮጵያ ቡራቡሬ ናት..ዥንጉርጉር። ይሄ ውበቷ..ይሄ ማማሯ ደግሞ እኔና እናተ ነን። የእኔና የእናተ የተለያየ መሆን ነው የተለየች ያደረጋት። ልዩነትን ለበጎ ነገር መጠቀም ጸጋና በረከት የሚያስገኝ የእድሎች ሁሉ እድል ነው። ባለን ብዝሃነትና የባህል ስብጥር መለያየትን ትተን በአንድ ብንቆም ብዙ የምናተርፈው ይኖር ነበር። ብዝሃነት የእድል መገኛ ነው። እድሉ የሚወጣው ደግሞ ፍቅርን አስቀድመን ስንከተል ነው።

ድሮና አሁንን ለአፍታ ጨረፍ ብናደርገው ብዙ ልዩነቶችን እናገኛለን። ፍቅር ያልገባበትን ዘመናዊነት ዓለም አታውቀውም። አራዳነታችንና ሥልጣኔአችን ፍቅርን ሳንይዝ በብቻ ጉዞ ያደረግን ብዙ ነን። እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሀገር፣ ባህል፣ ታሪክ ይነጥቃል እንጂ ማንነት አያቆይም። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ብዙ እጆች በብዙ ሃሳብና በብዙ ጥበብ አላቁጠው ያጸኗት የእኔ የአንተ ያንቺና የሁላችን መልክ ናት። እናም ፍቅርና እርቅ የአዲሱ ትውልድ አዲስ አስተሳሰቦች ይሁኑ የመጨረሻ መልዕክቴ ነው።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You