ሠላም ለቱሪዝም

 ኢትዮጵያ እጅግ ብዙ ታሪክ፣ ቅርስ ፣ባህል ፣ የተፈጥሮ ፀጋ የተቸራት ፤ምድሯም በሚያማምሩ አዕዋፋት እና በብርቅዬ የዱር እንስሳት የደመቁ ፤ ሀገር ነች። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ጥምቀት፣ መስቀል፣ ፍቼ ጨምባላ እና ኢሬቻ ያሉ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ኩነቶች ደምቀው የሚከበሩባት የተለያየ ኃይማኖቶችና ባህሎች መገኛ ናት ።

እነዚህ ተፈጥዊ ፣ኃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ውበቶች ሀገሪቱ በብዙ መልኩ ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ የሚያደርጓት ናቸው ። ዘርፉ የአንድን ሀገር በኢኮኖሚ ከመደገፍ አንጻር ካለው አበርክቶም ሀገሪቱ ለጀመረችው ልማት ትልቅ አቅም እና ተስፋ እንደሚሆን ይታመናል።

እንኳን እንደ ኢትዮጵያ በባህል፣ በኃይማኖት፣ በታሪክ፣ በብርቅዬ እንስሳት እና በብዝሃነቷ የታደለችን ሀገር ቀርቶ፤ እዚህ ግባ የሚባል ታሪክ፣ ባህል እና ቅርስ የሌላቸው ሀገራት ሠው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በመሥራት ብሎም ጎብኚዎችን በመሳብ ከፍተኛ የሚባል ገቢ እያገኙ እንደሆነ እሙን ነው።

ዘርፉ ለአስጎብኚዎች የሥራ ዕድልን በመፍጠር፣ የሆቴል ዘርፉን በማሳደግ ፣ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠቃሚ በማድረግ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍያለ ነው።

በተለይም እንደ ሀገር ያሉንን ተፈጥሯዊ ታሪካዊ፣ ኃይማታዊ እና ባህላዊ ቅርሳችንን ማልማትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ማስተዋወቅ ከቻልን አሁን ላይ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው ሀገር አቀፍ ጥረት የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።

በተለይም እንደ ሀገር ያለን የቆየና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘው የእንግዳ ተቀባይነት ባህላችን በራሱ ዘርፉን ስኬታማ ለማድረግ ለምናደርገው ጥረት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ከዚህ አንጻር አሁን ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የጸጥታ ችግር የእንግዳ ተቀባይነታችን ባህል እንዳይበርዘው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።

በሀገራችን በአራቱም አቅጣጫ ያሉ የቱሪስት ዓይን የሚስቡ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ትርጉም ያለው የኢኮኖሚ አቅም የሚሆኑት አሁን አሁን እየታየ ያለውን የጸጥታ ችግር አግባብ ባለው መልኩ ለዘለቄታው መፍታት ሲቻል ነው።

አሁን ላይ ያለው የጸጥታ ችግር በቱሪዝም ዘርፉ ላይ እያሳደረ ያለውን ችግር ሃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ በማጤን ፈጥኖ ማረም ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከተቻለ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ሆኑ የታሰቡ ሥራዎች ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም።

ከቦታ ወደ ቦታ በሰላም መዘዋወር ፈተና እየሆነ የመምጣቱ ጉዳይ የውጭ ቱሪስቶችን ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ በዜጎች የሚደረጉ ፤ ለዘለቄታው መለመድ ያለባቸው ፤ አካባቢዎችን የመጎብኘት ባህል ሊያዳክሙት ይችላሉ።

በእርግጥ አሁን ላይ በዘርፉ በርካታ በጥሩ ጎን ሊጠቀሱ የሚችሉ ሥራዎች እየተመለከትን እንገኛለን። የቱሪዝም ዘርፍ ሚናው የጎላ መሆኑን በመረዳት ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም ‹‹ሀገር አቀፍ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ›› መከፈቱ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አውደ ርዕዩን መርቀው ሲከፍቱ እንደተናገሩት ፤ አውደ ርዕዩ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ምቹ መዳረሻ የሚያደርጋትን በናሙና እንዲያዩ ዕድል ይሰጣል።

“በዘርፉ ያለንን አቅም ለማውጣት፣ ኢትዮጵያን የብዙ ውበቶች እና ግኝቶች መዳረሻ አድርጎ ለማስተዋወቅ እና ለማገልገል ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ያላትን ሀብት ማየት፣ ማውጣት፣ ማስተዋወቅ እና ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ።”

እንዲህ አይነት አውደ ርዕይ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን ፀጋዎች ይበልጥ ለማስተዋወቅና የዘርፉን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዕድል እንደሚፈጥር በመገንዘብ፤ መሰል መሰናዶዎችን ማዘጋጀት እና በችግሮቹ ዙሪያ እንዲሁም ለችግሮቹ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በማጤን ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ለሁለቱ ምክር ቤቶች በቅርቡ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት ፤ “የቱሪዝም ዘርፍ የዕድገት አማራጭ አንዱ ቁልፍ ዘርፍ ነው። በዚህ በኩል በዓመቱ የቱሪስት ፍሰቱን በማሳደግ በኩል ፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አበረታች ዕድገት ለማስመዝገብ ጥረት መደረጉን በጥንካሬ ማንሳት ተገቢ ነው።”

በአዲስ አበባ እየተሠሩ ያሉ እና የከተሜውንም ሆነ የውጭ ሀገሩን ጎብኚ ቀልብ ሊስቡ የሚችሉ ፕሮጀክቶች በስፋት እየተመለከትን እንገኛለን። ይህም በእለት ተእለት እንቅስቃሴው ለሚደክመው የከተሜው ሕዝብ፤ ዓይን ማረፊያ ማግኘት መቻሉ መንግሥትን የሚያስመሰግነው ነው። እንደነዚህ ያሉት ፕሮጀክቶች በስፋት መሠራቱም፤ በብዙ ነገር ለታደልነው ሕዝብ ሌላ እሴት የሚጨመር መሆኑን መገንዝብ ያሻል።

እኛ ኢትየጵያውያን የተሰጠን የተፈጥሮ ፀጋ ብዙ ነው። ነገር ግን ይህንን የታደልነውን ነገር በመጠቀም ሆነ ሌሎች እንዲያውቁት ከማድረግ አንጻር ግን ክፍተታችን ብዙ ነው። በአካባቢያችን ሊጎበኙ የሚችሉትን እንኳን አቅሙ እያለንን እና ሁኔታዎች አመቺ ሆነው ፍላጎታችን ዝቅተኛ ነው።

የውጭ ጎብኚውን ለመሳብ ጥረት እንደሚደረገው ሁሉ፤ በተለያዩ ሁነቶች ላይ ለመታደም ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል የሚንቀሳቀሰውን የሀገር ውስጥ ጎብኚውን በስፋት የማሳተፍ ሥራ መሥራት ከዘርፉ ተዋናዮች አሁን ላይ የሚጠበቅ ትልቁ ሥራ ነው ።

ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን በበጀት፣ የተሟላ መሠረተ ልማት፣ የሠው ኃይል፣ ምቹ አካባቢ እና ከሁሉም ከሁሉም ሠላም የሰፈነበት ከባቢ ካለው፤ ትርፋማ ለመሆን የሚያግደው ነገር የለም ። ከላይ የጠቀስናቸው እንዳሉ ሆነው፤ የቱሪዝም ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን እና ሀገሪቱም ከዘርፉ የምታገኘውን ገንዘብ ለማሳደግ ስለ ሠላም የጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጠው ሊሠራ ይገባል።

በተጨማሪም የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ የማይዳሰሱ እና የሚዳሰሱ ቅርሶችን መንከባከብ እና መጠበቅ ግድ ይላል። በተለይ በግጭቶች ወቅት ለነዚህ ቅርሶች ከፍ ያለ ጥንቃቄ ማድረግ እና ከየትኛውም አይነት ስጋት ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው።

ምስጋና ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You