ዓለም አቀፍ ሥርዓትን መሰረት ያደረገ የሕፃናት ድጋፍና ክብካቤ መመሪያ ክለሳ ተደረገ

አዲስ አበባ፡- ዓለም አቀፍ ሥርዓትን ያቀፈና ሕጻናት አማራጮች እንዲኖራቸው የሚያደርግ ድጋፍና ክብካቤ መመሪያ ላይ ክለሳ መደረጉን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ።

በመርሀ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መንግሥት በተለይ ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር ለተጋለጡ ሕጻናት ጥበቃና ክብካቤ በማድረግ ጤናማ የኅብረተሰብ ክፍል ሆነው እንዲያድጉና ለሀገራቸው መልካም ዜጋ እንዲሆኑ በማሰብ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በ2009 ዓ.ም የተለያዩ የድጋፍና ክብካቤ አማራጮችን የያዘ መመሪያ በመንደፍ ሥራ ላይ እንዲውል አድርጎ ነበር።

ነገር ግን ይህ ሥራ ላይ የዋለው መመሪያ ጥልቀት የሌለውና የበለጠ አማራጮችን እያካተተ የሚሄድ ባለመሆኑ በጥናት በተደገፈ መልኩ ክለሳ እንዲደረግለት ተደርጓል። በዚህም መመሪያው የተሻለ አማራጭ፣ ድጋፍና ክብካቤ እንዲያስተዋውቅ እንዲሁም ሕጻናትን የሚያግዙ ፕሮግራሞችን በተሳካ ሁኔታ እንዲተዋወቁ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የተከለሰው መመሪያ መንግሥት ያመነበት፣ የዓለም አቀፍ ሥርዓት ያቀፈና ሕጻናት የተለያዩ አማራጮች እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።

የነገ ተስፋ የሆኑ ሕጻናት በመልካም ጤንነትና ስብዕና ታግዘው እንዲያድጉ፣ እድገታቸውን ሊያሰናክሉ ከሚችሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመጠበቅ አስፈላጊው ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል፤ በተለይም በተለያዩ ሰው ሰራሽ መንስኤዎች ሳቢያ ለከፋ ችግር የተጋለጡ ሕጻናት የሚገባቸውን ትኩረት አግኝተው እንዲያድጉና የወደፊት ህይወታቸው የተቃና እንዲሆን ሁሉም ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

ዶ/ር ኤርጎጌ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን እንደተጨማሪ ክብካቤ ፕሮግራም በመውሰድ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻቸውና ከአካባቢያቸው የራቁ ሕጻናትን ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል ሲሉ ገልጸው፤ በዚህም በርካታ ሕጻናትን መደገፍና ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ሆኖም ከመንግሥት ጥረት ጎን ለጎን ኅብረተሰቡና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሕጻናቱን ህይወት ለማሻሻልና ወደፊት ተስፋቸውን ለማለምለም እያገዙ በመሆኑ ይህን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

ለመመሪያው ዝግጅት ትብብር ያደረጉ ዩ.ኤስ.ኤይድ፣ ቤታኒ ክርስቲያን እና ሌሎችም አካላትን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም ተመስግነዋል፤ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጥቷል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You