የኢትዮጵያን መልክ በአንድ ቦታ ከማሳየት ባሻገር

አገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ያላትን ዕምቅ ሃብት በማስተዋወቁ በኩል ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በተለይም አምራችና ሸማችን የሚያገናኙ የተለያዩ የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛሮችን ጨምሮ በርካታ አገርን፣ ምርቶቿን፣ እምቅ አቅሞቿን፣ ማስተዋወቅና የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችሉ እውቀትና ቴክኖሎጂን የማስተላለፍ አቅም ያላቸው አውደ ርዕዮችን ማዘጋጀት እየተለመደ መጥቷል። ከሰሞኑም በዓይነቱ ለየት ያለና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ተብሎ የሚጠበቀው ሀገር አቀፍ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንቨስትመንት አውደ ርዕይ በይፋ ተከፍቶ እየተጎበኘ ነው፡፡

ይህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት አውደ ርዕይ፤ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም በተከፈተበት ወቅት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አሁን ጊዜው ድህነትን የምንታገልበት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በማውጣት በጋራ የምናለማበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ ውበቶችና ግኝቶች መዳረሻ መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህን በማስተዋወቅ እንዲሁም ያለንን አቅም በማውጣት እያንዳንዳችን አገሪቱ ያላትን ሀብት ማየት፣ ማውጣት፣ ማስተዋወቅና ማገልገል ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በአገር አቀፉ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንቨስትመንት አውደ ርዕይ ላይ ከ100 በላይ በዘርፉ የተሰማሩ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የክልል ቱሪዝም ቢሮዎች፣ የሚዲያና የቴክኖሎጂ ተቋማት ፣ በባህል አልባሳት ምርት፣ በሽመና እንዲሁም በሸክላ ሥራ የተሰማሩ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ናቸው። አምራቾቹ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ዕድል ለመፍጠርና አንዱ ከሌላው የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የተሻለ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ይናገራሉ።

አቶ ሰለሞን ወረደ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ በሆነው በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት የስጋጃ ባለሙያ ናቸው፡፡ በአውደ ርዕዩ ድርጅቱ መሳተፉ ምርቶቹን ለጎብኚዎች ለማስተዋወቅና ለገበያ ትስስር ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ይናገራሉ። በተለይም የድርጅቱ ምርቶች በሙሉ ባህላዊና ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከቱሪዝሙ ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ በ1957 ዓ.ም በስድስት ሠራተኞች የተቋቋመ ነው፡፡ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የእጅ ሥራ ምርቶችን በመሥራት ለገበያ ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የበርካታ ሙያ ባለቤት በሆኑ ሠራተኞቹ አማካኝነት የተለያዩ ምርቶችን እያመረተ ይገኛል፡፡ ከምርቶቹ መካከልም የቀርከሃ፣ የስጋጃ፣ የሸክላ፣ የስዕልና የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህን ምርቶች በስፋት ለቱሪስቶች እንደሚያስተዋውቁ ያመላከቱት አቶ ሰለሞን፤ ቱሪስቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች በሙሉ ምርቶቻቸውን ይዘው በመቅረብ በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩ ይናገራሉ፡፡ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የድርጅቱ ደንበኞች በተጨማሪ አብዛኛውን ጊዜ የገበያ መዳረሻዎቹ ቱሪስቶች እንደሆኑ ተናግረዋል። ድርጅቱ በትዕዛዝ ተቀብሎ ከሚያመርታቸው ማንኛቸውም ምርቶች በተጨማሪም በራሱ ዲዛይንና ቀለም የተለያዩ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል ይላሉ፡፡

ይሁንና ድርጅቱ ምርቶቹን በስፋት ለማህበረሰቡ ማድረስ አለመቻሉን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ እንዲህ ያሉ አውደ ርዕዮች ድርጅቱን ከአብዛኛው ማህበረሰቡ ጋር እንደሚያስተዋውቁና የገበያ ዕድል እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ አሁን ካሉት ደንበኞች በተጨማሪ ምርቶቹን በስፋት አምርቶ ለሸማቹ ለማቅረብ እየሠራ እንደሆነ ነው ያስታወቁት።

ድርጅቱ ሥራውን እያሰፋ እንደሚገኝም ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት አያት አደባባይ አካባቢ ከ1000 ካሬ ሜትር በሚበልጥ ቦታ ላይ የማስፋፊያ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ የማምረቻ ቦታ ላይ የተለያዩ ባህላዊና አገር በቀል ምርቶችን ከማምረት ባሻገር በዘርፉ ስልጠና እንደሚሰጥም አስታውቀዋል። ምርቶችን በስፋት በማምረትና በማሰልጠን እስካሁን በስፋት ያልገባባቸውን ገበያዎች እንደሚለቀላቀልም ጠቁመዋል፡፡ ምርቶቹን በአገር ውስጥ ለሚገኙ ሸማቾች ከማድረስ ባለፈ የማምረት አቅሙን በማሳደግ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ድርጅቱ ምርቶቹን በስፋት እያቀረበ ያለው ለተለያዩ ዘመናዊና የባህል ሆቴሎች እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ ባህላዊ ከሆኑ ሆቴሎች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥሮ ምርቶቹን እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡ ዮድ አቢሲኒያ፣ ቃተኛና የመሳሰሉት ባህላዊ ይዘት ያላቸው ሆቴሎች ደንበኞቹ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ሆቴሎቹ ከቤት አሰራራቸው ጀምሮ ባህላዊ ይዘት ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቤት ውስጥ ያሉ ቁሳቁስ ወንበርና ጠረጴዛን ጨምሮ የሸክላ ሥራ፣ የስጋጃ ሥራ፣ የቀርከሃ ሥራ፣ በተለያዩ ስዕሎችና መጋረጃዎቹ ጭምር በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ምርት የተንቆጠቆጡ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

የምርቶቹ ቋሚ ደንበኛ ከሆኑ ሆቴሎች በተጨማሪ ጎንደርና ባህርዳር በሚገኙ ሱቆቹ ምርቶቹን ለገበያ እያቀረበ መሆኑንም አቶ ሰለሞን ተናግረው፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም በመስቀል አደባባይ፣ ዋቢሸበሌ፣ በሂልተን፣ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ፣ 22 አካባቢና አያት አደባባይ በማምረቻ ሥፍራው በሚገኙ መሸጫ ሱቆች ጭምር ምርቶቹን ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ባህላዊ ቁሳቁሱ አሁን አሁን ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መምጣቱንም አመልክተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት የሸክላ ምርቶቹን ከአራት የአፈር አይነቶች ውህድ ያመርታል ፡፡ ከምርቶቹ መካከልም የክትፎ ማቅረቢያ ጣባ፣ ጀበና፣ የሻማ ማብሪያ፣ ድስቶች፣ የላዛኛ ማቅረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የሸክላ ሥራዎቹ ጥራት ያላቸውና በገበያው እጅግ ተፈላጊ መሆናቸውን አመልክተው፣ ለሸክላ ሥራ ጥራት ዋናው የጭቃው ዝግጅት እንደሆነም አስረድተዋል።

የስጋጃ ምርቶቹ ከበግ ጸጉር ይሰሩ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፤ የበግ ጸጉሩን ጠረን በአሁኑ ወቅት ደንበኞች አይፈልጉትም ብለዋል፡፡ የበግ ጸጉሩ በክር ተቀይሮ እንደሚሰራም ገልጸዋል። ክሩ በተለያዩ ቀለማት ተነክሮ ደንበኞች በሚፈለጉት ዲዛይን እንደሚሰራ፣ ድርጅቶችም በድርጅታቸው ሎጎ እንደሚያሰሩ ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ቀርከሃም እንዲሁ ለተለያዩ ምርቶች ይውላል፡፡ ቀርከሃ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት ቢኖርም በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም፡፡ ድርጅቱ ቀርከሃን ለመብራት ጌጥ፣ ለፍራፍሬ ማቅረቢያ፣ ለወንበር፣ ለጠረጴዛና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ አድርጎ እያመረተ ለገበያ ያቀርባል፡፡ ድርጅቱ ኢትዮጵያን መግለጽ የሚችሉ የተለያዩ ስዕሎችን አምርቶ ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፤ ለዚህ ሥራም የድርጅቱ ሰዓሊዎች ትልቅ አበርክቶ አላቸው፡፡

ድርጅቱ በአጠቃላይ በአገር ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁስን ብቻ በመጠቀም ባህላዊ ምርቶችን እያመረተ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ገበያዎቹ የውጭ አገር ቱሪስት እና ባህላዊ ሆቴሎች ናቸው፡፡ ይሁንና አሁን አሁን የአገር ውስጥ ሸማቾችም ወደ ባህላዊ ምርቶቹ እየመጣ በመሆኑ ምርቶቹን በስፋት አምርቶ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አስፈላጊውን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በእነዚህ ምርቶች አገርን ማስተዋወቅና የገቢ ምንጭን ማሳደግ እንደሚቻል አቶ ሰሎሞን ተናግረዋል። ለዚህም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትም ፍላጎት ያላቸውን በሙሉ በተለያየ ዘርፍ ለማሰልጠን መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በአውደ ርዕዩ ላይ የተለያዩ ጌጣ ጌጦችን ይዘው ከቀረቡት መካከል የእንጦጦ ዕደ ጥበብ ድርጅት አንዱ ነው፡፡ እንጦጦ ዕደ ጥበብ 200 የሚደርሱና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የነበሩና ከማህበረሰቡ ተገልለው የቆዩ ሴቶችን አሰባስቦ ወደ ሥራ ማሰማራት የቻለ ሲሆን፤ ጌጣ ጌጦችን፣ ሰፌዶችን፣ መሶቦችንና የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርት ነው ፡፡

የድርጅቱ የማርኬቲንግ ባለሙያዋ ወይዘሪት ይዲዲያ ሰለሞን እንዳለችው ፤ ለተለያዩ ፕሮግራሞች መዋቢያነት የሚያገለግሉ የአንገት፣ የጆሮ፣ የእጅና እግር ላይ የሚውሉ የተለያዩ ጌጣ ያመርታል፡፡ ጌጣ ጌጦቹ የሚሰሩትም ከጥይት ቀለሃ ሲሆን፣ ጌጣ ጌጦቹን ከቀለሃው ለመሥራት ምንም አይነት ማሽን ጥቅም ላይ አይውልም፤ ሙሉ ለሙሉ በእጅ ነው የሚሰሩት፡፡

ምርቶቹን በአብዛኛው የሚገዙት ቱሪስቶች እንደሆኑ የጠቀሰችው ወይዘሪት ይዲዲያ፤ ወደ አገር ውስጥ ለሚመጡ ቱሪስቶች ምርቶቹን በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሱቆቻቸው እንደሚያቀርቡ ገልጻለች፡፡ በአገር ውስጥ ካለው ገበያ በተጨማሪ አሜሪካ፣ ካናዳና በሌሎች አገራትም እንዲሁ ጌጣ ጌጦቹን በመላክ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግራለች። በአገር ውስጥም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት አብዛኛው ሰው ዘንድ መድረስ እየቻሉ እንደሆነ አስረድታለች፡፡ እንደዚህ አይነት ለህዝብ ክፍት የሆኑ አውደ ርዕዮች የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ሥራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ እጅግ ጠቃሚ መሆናቸውንም ወይዘሪት ይዲዲያ ተናግራለች፡፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው እንዳሉት፤ በአውደ ርዕዩ ከ100 በላይ ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ አውደ ርዕዩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፣ ምርትና አገልግሎታቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የገበያ ትስስር የመፍጠርና የልምድ ልውውጥ የማድረግ አጋጣሚንም ይፈጥራል፡፡

አውደ ርዕዩ በይዘቱ ለየት ያለና ኢትዮጵያን መግለጽ የሚችል እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አለማየሁ፣ አገልግሎት ሰጪ ሆቴሎች በአውደ ርዕዩ ተሳታፊ በመሆን አገልግሎታቸውን እያስተዋወቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በከተማ ውስጥ የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ቁጥራቸው በርካታ እንደመሆናቸው በተራ እየገቡ ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። ሌሎች ሽመናን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ የሆኑ ቁሳቁስን የሚያመርቱ ድርጅቶችም በአውደ ርዕዩ ተሳታፊ በመሆን ምርቶቻቸውን እያስተዋወቁና የገበያ ትስስርም እየፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የቱሪዝም ሚኒስቴር ይህን አውደ ርዕይ ያዘጋጀበት ዋና ዓላማ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማነቃቃት፣ በዘርፉ በአንድም ሆነ በሌላ በእሴት ሰንሰለት ውስጥ የተሳሰሩ አካላት እንዲተዋወቁ ማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችም እንደዚሁ በአንድ ቦታ የኢትዮጵያን መልክ እንዲያዩና ወደ ሥፍራው የመሄድ ፍላጎታቸው እንዲጨምር ለማድረግ ነው። በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን የኢንቨስትመንት እድል በማሳየት ኢንቨስትመንቱ እንዲጨምር ማድረግ፣ ጎብኚዎች ከሚጎኙት ነገር ተነስተው የራሳቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲፈልጉ ማስቻል፣ የፈጠራ ክህሎት እንዲዳብርና እንዲጨምር ዕድል መፍጠር፣ አዳዲስ የአሰራር ስርዓቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ እንዲሁም ጎን ለጎን ያሉትን መልካም ነገሮች አበርክቶ ለመጠቀምና በተመሳሳይ በጋራ የመወያትና የመመካከር ዕድል በመፍጠር ችግሮችን መፍታትም ሌሎች የአውደ ርእዩ አላማዎች ናቸው፡፡

በሽመና ሥራ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ቁሳቁስን የሚያመርቱ ድርጅቶች በአውደ ርእዩ እየተሳተፉ መሆናቸውን አመልክተው፣ እነዚህ ድርጅቶች ለቱሪዝሙ ያላቸውን የላቀ ፋይዳ በአውደ ርዕዩ ማሳየት እየተቻለ መሆኑን አቶ አለማየሁ አስታወቀዋል፡፡ እያንዳንዱ ቱሪስት በቦታው ሲገኝ ወደ አገሩ ይዞት የሚሄደውና ኢትዮጵያን ለማስታወስ የሚያስችለውን ከፎቶና ከቪዲዮ ባሻገር የተለያዩ ቁሳቁስን ይፈልጋል ያሉት ስራ አስፈጻሚው፣ ለዚህም በባህላዊ ቁሳቁስ ማምረት ስራ የተሰማሩ ድርጅቶች ኢትዮጵያን የሚገልጹ በርካታ ምርቶችን ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ነገር በአንድ ቦታ ላይ ተከማችቶ የቀረበበትን ይህን አውደ ርዕይ ሁሉም ሰው እንዲጎበኝ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

አውደ ርዕዩ እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

 ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2016

Recommended For You