ለተሻሻለው የትምህርት ፖሊሲ ተግባራዊነት እንሥራ

በፍጥነት ተቀያያሪ በሆነው ሉላዊ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን የማያቋርጥ የእድገት ሰንሰለት መኖሩ የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ በቴክኖሎጂ፣ በምርምር እና በፈጠራ ውጤቶች መደገፍ አስፈላጊ ነው። ለእነዚህ እውን መሆን ደግሞ ትምህርት አይተኬ ሚና ይኖረዋል። ትምህርት የሰው ልጅ ለእድገትና ለለውጥ በሚያደርገው ትግል ውስጥ ትልቁ አቅም/መሣሪያ ተደርጎ ይቆጠራል። አዳዲስ ግኝቶቹን እና በዓመታት ውስጥ የተከማቸ እሴቶቹን የሚያስተላልፍበት ሂደትም ነው።

በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ትምህርት ግለሰቦች እና ማኅበረሰቡ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል። ለሕልውና፣ ለልማት፣ ለእውቀት፣ ችሎታን ለማዳበር፣ ችግር ለመፍታት፣ የማድረግ አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም የተዛቡ አመለካከቶችን በማሻሻል የማያቋርጥ የእድገት ሂደት ለማምጣት ወሳኝ ነው።

ከላይ ለማንሳት የሞከርኩት ርዕሰ ነገር ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያንም የሚሠራ ነው። ለዚህም ነው ለበርካታ ምዕተ ዓመታት በራሳችን ባሕል፣ እሴት፣ እውቀትንና ክህሎትን የማስተላለፊያ መንገድ ትውልዱን በትምህርት ስናንፅ የነበረው። በጥንታዊው ኢትዮጵያ የታሪክ መዛግብትም እውቀት፣ ጥበብ፣ የፈጠራና ምርምር አቅም የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሁንም ድረስ ሕያው ሆነው ያሉት ።

ከጥንታዊው የትምህርት ሥርዓት ወጣ ስንል በዘመናዊው ዓለም፤ ከለውጥ ሂደቱ ጋር የሚያስተሳስራት ስትራቴጂ በመዘርጋት ውጤት ለማምጣት ሙከራ ስታደርግ ቆይታለች። እነዚህ ሙከራዎች በሥርዓት ለውጥ፣ በርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና ቶሎ ቶሎ መቀያየር የተነሳ ከጥራት ጋር የሚያያዙ ጉድለቶች እንዲታዩ አበርክቶው ከፍያለ ሆኗል ።

ከመንግሥት ለውጥ ጋር አብረው የሚለወጡ የትምህርት ፖሊሲና ፍልስፍናዎች በፈጠሯቸው ጫናዎች ወጥ የሆነ፣ በክህሎት፣ በእውቀት፣ በፈጠራ፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ፣ በተግባር ትምህርቶች የላቀ ትውልድ ማፍራት ላይ የሚያተኩር ሥርዓት እስካሁን ለመዘርጋት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል።

በወረቀት ላይ ምሉዕ የሚመስሉ ድንጋጌዎችና የትኩረት አቅጣጫዎች በፖሊሲውና እርሱን የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ቢቀመጡም በተቀናጀና ስልታዊ በሆነ አግባብ ተግባራዊ ሲደረጉ ሳይቻል አስርተ ዓመታቶች አልፈዋል። የዚህ ውጤትም በትምህርት ሥርዓት ውስጥ አልፈው የሚመረቁ ባለሙያዎች ከፅንሰ ሀሳብ በዘለለ ችግሮችን የሚፈቱ፣ ተግባር ላይ የጠነከሩ፣ የፈጠራና የአዳዲስ የምርምር ውጤቶችን የሚያፈልቁ እንዳይሆኑ ምክንያት ሆኗል። ይህም በጥቅል ሀገራዊ ልማትና እድገት ላይ እንቅፋት ፈጥሯል።

ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በተወሰደው ጠንካራ ክትትልና የተቀናጀ የፈተና አሰጣጥ ማሻሻያ ምክንያት የተገኘው ውጤትም ይህንኑ የሚያሳይ ነው። የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል፣ በትምህርት ገበታቸው ላይ ዝቅተኛ አፈፃፀም ማሳየትና መመዘኛ መስፈርቱን አለማሟላት ከላይ ያነሳናቸው ቁልፍ ችግሮች የፈጠሩት እንደሆነ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል። በጥራት ያልተማረ ምሩቅ መምህር ይሆናል፤ መምህሩ ደግሞ ተመሳሳይ ተማሪዎችን አስተምሮ ያስመርቃል (ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ)።

ለዓመታት በኢትዮጵያ ብቁና ሀገርን ተረከበው ወደ እድገትና የሚወስዱ ወጣቶች እንዳይፈጠሩ የተከተልነው የትምህርት ሥርዓት ጋሬጣ ሆኖ ቆይቷል። የመፍጠር አቅማቸው ጠንካራ፣ ፅንሰ ሀሳብን መሬት ላይ አውርዶ የማኅበረሰቡን ቁልፍ ችግሮች የሚፈታ እንዳይሆን የምንከተለው የመማር ማስተማር ዘዴ ወንዝ የማያሻግር እንደነበር የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያምናል። ከዚህ መነሻ “ለመሆኑ የትምህርት ፖሊሲ፣ የመማር ማስተማር ዘዴያችን ምን ይዘት ነበረው? አሁንስ በምን መልኩ መሻሻል ይገባዋል?” የሚሉትን ጉዳዮች እንደሚከተለው ለመመልከት እንሞክር።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 20 ቀን 2015 ዓም አንድ ውይይት አድርጎ ነበር። የዚህ ምክክር ማጠንጠኛ የነበረው በ1986 ዓም ተረቅቆና ፀድቆ ወደ ሥራ የገባው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ማሻሻያ ላይ ነበር። በዚህ ውይይት ላይ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲውን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት ተገልፆ ነበር። በተሻሻለው በዚህ ፖሊሲ ላይም በክፍል ሁለት “መነሻ ምክንያቱን” በመግለፅ እንዲህ የሚል ሀሳብ ሰፍሮ እናገኛለን።

“….የትምህርት ጥራትም እያሽቆለቆለ የመጣ ሲሆን እንደ ማስረጃ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችለው በየደረጃው ያሉ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የትምህርት ውጤት በፖሊሲው ላይ የተቀመጠውን 50 በመቶና በላይ ውጤት ማምጣት አልቻሉም። ሥርዓተ- ትምህርቱም በንድፈ ሃሳብ የታጨቀ ለነባራዊ የሀገሪቱ ሁኔታዎች ምላሽ የማይሰጥ የሀገር በቀል እውቀትን ያላካተተ፣ በየጊዜው የማይፈተሽ፣ ዜጐችን በግብረገብና በመልካም ሥነ ምግባር በበቂ ሁኔታ ያላነፀ ከመሆኑም በላይ ለሥራ ፈጣሪነትና ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያዘጋጅ አልነበረም።

”መምህራንም ብቃትን ተላብሰው ተማሪዎችን በመረዳትና በመርዳት እንዲሁም ከሚፈለገው የብቃት ደረጃ ላይ በማድረስ ረገድ ውስንነት ያለባቸው ሲሆን ትምህርት ቤቶችም ቢሆኑ ለመማር ምቹ ያልሆኑ አስፈላጊው ግብዓት ያልተሟላላቸውና ትምህርቱንም በዘመናዊ ቴከኖሎጂ አስደግፈው የሚሰጡ አይደሉም….” ይላል።

የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲውን ለማሻሻል እንደ መነሻ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ከላይ ያነሳነው አመክንዮ ዋንኛው ነው። መንግሥት ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ የትምህርት ሥርዓቱን ለማሻሻል በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ትውልዱ በተሻለ የትምህርት ጥራት ተምሮ እንዲያልፍና የሀገርን የልማት አጀንዳዎች እንዲያስፈፅም፤ ኢትዮጵያንም ወደከፍታው እንድትወጣ አጋዥ ኃይል እንዲሆን እየሠራ መሆኑ ነው። በዋናነት ግን የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ቁልፍ ችግሮች ውስጥ የዛሬው ማጠንጠኛችን የሆነው የተሻለና ጥራት ያለው ትምህርት ማቅረብ ያልተቻለበት ምክንያት ነው።

ከላይ እንደተመለከተው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲውን እንዲሻሻል ገፊ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ አንዱ “የትምህርት ጥራትም እያሽቆለቆለ” መምጣት ነው። ለዚህ ደግሞ ተማሪዎች ከተግባር ይልቅ ንድፈ ሀሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ ትምህርት እንዲወስዱ መደረጉን ይሄው ማስረጃ ይነግረናል። እዚህ ላይ ተመርኩዘን ያለፉትን አንድና ሁለት ዓመት የተመዘገቡ የሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን ውጤት እንመልከት።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተዘረጋው ጥብቅ ቁጥጥር እና የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ምክንያት ብዙኃኑ ተማሪዎች ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ሆነዋል። ከሰሞኑ ብቻ የትምህርት ሚኒስቴር ያስፈተናቸው ከ800 ሺህ በላይ የሆኑ ተማሪዎች ውስጥ 3 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ጥብቅ ክትትልና የተከተለውን የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ማለፍ ችለዋል። ከእነዚህ ውጪ ያሉት ብዙኃኑ ተማሪዎች ከ50 በመቶ በታች ያመጡ አብዛኞቹ ደግሞ እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው።

ከዚህ መረዳት የምንችለው ላለፉት በርካታ አስርተ ዓመታት ስንከተለው የነበረው የትምህርት ሥርዓት ከስር መሠረቱ ችግር እንደነበረበት፤ ስር ነቀል ለውጥ ሊደረግበት እንደሚገባ ነው። ትውልዱ በትምህርቱ የተሻለ ውጤት እንዳያመጣ ከእራሱ፣ ከቤተሰብ፣ ከትምህርት ቤትና መምህር ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት ኃላፊነት ቢኖርባቸውም በዋናነት ግን የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ባላገናዘበ ሁኔታ የተቀረፀው “የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ” እንዲሁም አስፈፃሚ አካል የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ እንዳለበት መገንዘብ አያዳግትም።

ለትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው መሻሻል ገፊ ምክንያት ካልናቸው መካከል “በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ከኢንዱስትሪው ጋር የተሳሰረና የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ትምህርትና ሥልጠና አለመሰጠቱ፤ በቂና ተገቢ የሰው ኃይል አለመቅረቡ፤ ሠልጥነው ተመርቀው የወጡ ዜጎችም ሥራ ፈጣሪ አለመሆናቸው” ይጠቀሳል።

ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ከንድፈ ሀሳብ የዘለለ ትምህርት የማያገኘው ተማሪ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥም ተመሳሳይ ችግር ይገጥመዋል። በተግባር የተደገፈ እውቀትና ክህሎት ባለማግኘቱም ወደማኅበረሰቡ ሲቀላቀል ችግር የሚፈታ አቅምን ይዞና አዳብሮ አይደለም። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ባሳለፍነው ዓመት ተግባራዊ የሆነው የመውጫ ፈተና ነው።

ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ተፈትነዋል ካላቸው 150 ሺህ ለመመረቅ ዝግጁ የሆኑ ተማሪዎች ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ፈተናው የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልተው ለመመረቅ ብቁ መሆናቸው ነው። በተለይ ካለፉት ውስጥ 63 በመቶ የሚሆኑት ከመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች ቀሪውን 37 በመቶ ብቻ ማስመዝገባቸው ትኩረታችን የቱ ጋር ሊሆን እንደሚገባ ቁልጭ አድርጎ ያስመለከተን ይመስላል።

የሆነው ሆነ “16 እና ከዚያ በላይ ዓመት እውቀትን ለመገብየት ትምህርት ቤት ሲመላለስ የነበረ በርካታ ሚሊዮን ትውልድ ጥራት ያለው ትምህርት እያገኘ አይደለም” ስንል የሚያስነሳው ጥያቄ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል። ሂደቱ ሀገራዊ ፍላጎትን በትክክል ያላገናዘበ እንደነበር፣ የሙያ ደረጃ በማውጣትና የትብብር ሥልጠናን መተግበር የሚያስችልና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ሥርዓት አለመዘርጋቱን እንድናስተውል ያስገድደናል። ሀገር ጠንካራ ኢኮኖሚ እንድትገነባ በእውቀት፣ ክህሎትና የማድረግ አቅሙ የዳበረ ትውልድ ልትመራ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የትምህርት ፖሊሲ እና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ሊኖሩን ይገባል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥት የትምህርት ሥርዓቱን ለማሻሻልና ጥራትን ለማስጠበቅ ቁርጠኝነትን እያሳየ ነው። ለዚህም ፖሊሲን ጨምሮ ልዩ ልዩ የአሠራር ሥርዓቶችን እያሻሻለ ይገኛል። በቀዳሚነት ግን ባሳለፍነው ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ “የትምህርት አሰጣጣችንና ትውልዱ” ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ሽፍንፍኑን ገላልጠን ማየት ችለናል።

በቀደመው የትምህርት ሥርዓታችን ያፈራነው ትውልድ የቀረፅነው ተማሪ ውጤት ሲመዘን ከጭድ ቀልሎ ታይቷል። ይህንን ካወቅን ዘንዳ ቀጣይ መሆን የሚገባውን መዘየድ ተገቢ ነው። የኢትዮጵያን የማደግ ፍላጎት፣ ነባራዊ የልማትና እድገት ደረጃ የሚመጥን ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ቀርጸናል። ይህ ፖለሲና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ግን መሬት ላይ እንዲወርድ ርብርበ ማድረግ ይጠበቅብናል።

ከዚያ ባለፈ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት እና እየመጣ ባለው ውጤት ማዘንና “ሙሾ” ማውረድ ብቻ ለውጥ ስለማያመጣ በቀጥታ ወደ ተግባራዊ ሥራው መሸጋገር ይኖርብናል። በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው መሻሻል ገፊ ምክንያት ከሆኑት መርሆች በመነሳት የሚከተለውን ምክረ ሀሳብ ይሰጣል።

የመጀመሪያው ጥራት ያለው ትምህርትና ሥልጠና ለሁሉም በማዳረስ የግለሰብን አዕምሯዊ አካላዊ፤ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ እንዲሁም መልካም እሴቶችን ማጎልበት እንደሚገባ ነው። የፖሊሲው ዋና ርዕሰ ነገር ለሆነው ለዚህ ቀዳሚ ዓላማ ተፈፃሚነት ደግሞ ሙሉ አቅምን መጠቀም ያስፈልጋል።

በሁለተኛና በመጨረሻ መነሳት ያለበት ቁልፍ ዓላማ “የኢትዮጵያን ባሕል፣ እሴቶች የተገነዘበ ለሀገር አንድነት እድገት የሚሠራ፣ በራሱ የሚተማመንና ሙሉ የሆነ” የተማረ ኃይል እንዲፈጠር በወረቀት ላይ ያስቀመጥነውን ራዕይና እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው።

ይህንን ማድረግ ስንችል ለሁለትና ሦስት ዓመታት “ጉድ” ያስባለንና ብዙ ጉድለቶች የነበሩበትን የመማር ማስተማር ሥርዓት ከስር መሠረቱ መቀየር ያስችለናል። በመሆኑም ከቁጭት ወጥተን “ለተሻሻለው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ተግባራዊነት እንሥራ” የሚለው የዛሬ ርዕሰ ነገር መቋጫችን ይሆናል። ሰላም!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2016

Recommended For You