«የእጅም የልብም ንጽሕና ያለው አመራርና ማኅበረሰብ መፍጠር አለብን ብለን እየሠራን ነው»አራርሶ ገረመው (ዶ/ር)፣ የሲዳማ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ

የሲዳማ ክልል ከተመሠረተ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በርካታ ለውጦችም እየተመዘገቡ መሆኑ ይነገራል፡፡ የክልሉ የፋይናንስ አጠቃቀምና አንዳንድ አሠራሮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉና ከሀገራዊ እቅድ ጋር የተናበቡ መሆናቸውም ይገለፃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚነሱባቸው ጉዳዮችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡

በዛሬው የተጠየቅ ዓምድ ዕትማችንም የክልሉ የፋይናንስ አሠራርና አጠቃቀም፣ ክልሉን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች፣ መሠረተ ልማቶችን ለማሳለጥና የኅብረተሰቡን ጥያቄ በወቅቱ ለመመለስ እየተከናወኑ ስለሚገኙ ተግባራት እና ከዚሁ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከሲዳማ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አራርሶ ገረመው (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከባለፈው በጀት ዓመት በመልካም ተሞክሮ ተወስዶ ወደ 2016 በጀት ዓመት የሚሻገር ምን አሠራር አላችሁ?

አራርሶ (ዶ/ር)፡– ባለፈው በጀት ዓመት የተመደበው ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ልዩ ትኩረት ሰጥተን ስንሠራ ነበር፡፡ በተለይም በ2015 በጀት ዓመት የክልላችን ፋይናንስ ሥርዓት ዲጂታላይዝ ለማድረግና ከቴክኖሎጂ ጋር ለመሄድ በርካታ ውጥኖችን አስበን ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ በዚህ ረገድ አጠቃላይ በወረዳ እና በክልል የፋይናንስ ሥርዓት የተዘረጋው የኦን ላይን ሥራ ለመጀመርና ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ነው ታቅዶ የነበረው፡፡

በዚህ ረገድ እንደ ክልል በአጠቃላይ በክልል ማዕከል እና የወረዳዎችን ጨምሮ ካሉን ከ80 በላይ ተቋማት ውስጥ፤ 48 የሚሆኑትን በኦን ላይን ሥርዓት አስገብተናል፡፡ በዚህም የፋይናንስ ሥርዓቱን በአንድ ተቋማት የመመልከትና የማየት ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፤ ይህን 38 ከመቶ አሳክተናል፡፡ ቀሪውን በ2016 በጀት ዓመት ለማሳካት እቅድ ይዘናል፡፡

ሌላው በ2015 ለውጥ ለማምጣት ስንተጋ የነበረው፣ ቀደም ብሎ የነበረው ዝርክርክ አሠራር ማዘመንና ባለሙያዎችን ማሠልጠን ነበር፡፡ ይህን መቶ በመቶ አሳክተናል፡፡ ሌላኛው እንደ ሀገርም ለመንግሥት ትልቅ አቅም የሚሆነውና አብዛኛው ሃብት የሚውለው ግዥ ላይ ነው፡፡ 60 ከመቶ ሃብት የሚውለው እዚህ ላይ ነው፡፡

በዚህ ረገድ በፌደራል የተጀመረው የኤሌክት ሮኒክስ ግዥ ሥርዓት መሠረት 70 ተቋማት ጥቅም ላይ አውለዋል፡፡ እንደ ክልላችንም በፌደራል የተጀመረ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት በመጀመር የመጀመሪያው ነን፡፡ በ2015 የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ አትኩረን ሠርተናል፡፡ በ2016 ሙሉ ትግበራውን እንጀምራለን፡፡

በአጠቃላይ በ2016 በጀት ዓመት ሐዋሳ ከተማ ጨምሮ 12 ቢሮዎች ይህን ሙሉ ትግበራ እንዲጀምሩ ሥልጠና ሰጥተን አጠናቀናል፡፡ አሁን ድህነት ቀናሽ የሚባሉ ሰባት ተቋማትና ከፍተኛ ሃብት የሚንቀሳቀስባቸው ከፍተኛ በጀት ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ወደዚህ ሂደት በቅርቡ ይገባሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኤሌክትሮኒክስ ግዥ እና የኦንላይን ሥርዓት ትግበራ በመጀመራችሁ እንደ ክልል ምን አተረፋችሁ?

አራርሶ (ዶ/ር)፡- ሩቅ ለሚገኝ ወረዳ ወይም ሴክተር ቢሮ ዋናው የፋይናንስ ተቋማት መረጃ ያለው በፋይናንስ ቢሮ ነው፡፡ ቀደም ሲል ስንጠቀም የነበረው ሥርዓት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ገብቶ የሚስተካከል ወይንም በባለሙያ የሚታረም ነው። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ሪፖርቶች ላይ መጨመርና መቀነስ ይቻል ነበር፡፡ ይህም ለአሠራር አስቸጋሪ ነበር ፡፡

አሁን ያለው ግን ይህን ያስቀረ ነው፡፡ ይህም ከአንድ ማዕከል በመሆን በሌሎች ሴክተሮች በፋይናንሱ ላይ ምን እየተከናወነ ነው የሚለውን ማወቅና መቆጣጠር ተችሏል፡፡ ጠቅለል ሲደረግ ቀደም ሲል የነበረው የሪፖርት አቀራረብ፣ የሃብት አጠቃቀም ላይ ችግሮች ነበሩብን፡፡ ስለዚህ ይህን ማስቀረት ተችሏል፡፡ የሁሉንም ቢሮ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲዘምን አስችሏል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ይህ አሠራር በፕሮጀክቶች ላይ ያለውን ሙስናን ለመከላከል አስችሏል ማለት ነው?

አራርሶ (ዶ/ር)፡- አዎ! ቀደም ሲል አንድ ሰው ሥራውን ሳይሠራ አድቫንስ ይወስዳል፡፡ አሁን ግን በሲስተም የሚመራ ስለሆነ ያልተሠራበት አይከፈልም፡፡ በመሆኑም ሙስና ለማስቀረት ትልቅ አቅም አለው፡፡ በኦንላይን ሥርዓትም የሚመዘገብ ሥርዓት ስለሆነ ማጭበርበር ወይንም ለሙስና የመጋለጥ ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ስለዚህ በጣም ጥቅም አለው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጥቅም እንዳለው ሁሉ «ፍሌክሲብል» ለመሆን ፈተና አይሆንም?

አራርሶ (ዶ/ር)፡– ቴክኖሎጂ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳት ሊኖረው ይችላል፡፡ ከላይ በገለጽኩት መንገድ ጉዳት የለውም፡፡ ችግር የለውም ማለት ግን መቶ በመቶ ነው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አሁን ለምንሠራው ሥራ ጠቅሞናል፡፡ ለምሳሌ ይርጋለም ላይ ለሚሠራ ሥራ የሂሳብ ማጭበርበር እንዳይኖር ከማዕከል ሆኖ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ይህ ፋይናንስ ሥርዓት የዘመነ ለማድረግና አጠቃቀሙም በዚሁ ደረጃ በሥርዓት የሚመራ እንዲሆን ነው የተደረገው። ስለዚህ በሲስተም የሚመራ በመሆኑ ብዙ ችግሮችን የሚያስቀር መሆኑን ግንዛቤ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ የፋይናንስ ሥርዓት ማዘመኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የፋይናንስ አጠቃቀሙና ልማቱ በዋና ከተማ ሐዋሳ ላይ በማተኮሩ ሌሎች ከተሞችና ወረዳዎችን ዘንግቷል የሚል ወቀሳ አለ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አራርሶ (ዶ/ር)፡- ይህ መረጃ በአግባቡ መታየትና መታረም አለበት፡፡ እንዲያውም የምንታማው ሐዋሳን ዘነጋችሁ በሚል ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሲዳማ ክልል የተሠራው ላለፉት 40 ዓመታት ያልተሠራ የመንገድ ሽፋን ተደራሽ ማድረግ ችለናል፡፡ 1ሺ600 ኪሎ ሜትር በላይ ጠጠር መንገድ ገንብተናል፡፡ በዚሁ ሦስት ዓመት ውስጥ 2ነጥብ3 ቢሊዮን ብር በላይ ለገጠር መንገድ ግንባታ ወጪ አድርገናል፡፡ ለከተማ ልማትም 1ነጥብ1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ አድርገናል፡፡ ይህ ከተለያዩ አካላት የሚመጣው ሳጨመር መንግሥት የመደበው ሃብት ነው፡፡

በውሃ ልማትም በሰፊ የተሠራ ሲሆን ሲዳማ በ2012 ዓ.ም ዞን በነበረበት ወቅት የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 38 በመቶ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የግብረ ሠናይ ድርጅቶችን ትተን ሽፋኑ 56ነጥብ3 በመቶ ደርሷል፡፡ ለዚህም 1ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርገናል፡፡ ስለዚህ የምናከውናቸው የልማት ሥራዎች ፍትሐዊነትን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በሲዳማ ክልል የነበረውን የፍትሐዊነት መጓደል ጉዳይ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከገጠር እስከ ከተማ በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር ረገድ በጥሩ አካሄድ ላይ ነው፡፡

ቀደም ሲል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር በነበረንበት ወቅት እስከ 10 ዓመት ተጓተው የነበሩ ከ40 በላይ ድልድዮችን ያጠናቀቅነው በሦስት ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ አሁናዊ እይታችን አጠቃላይ ሲዳማን ማሳደግ ነው። ሐዋሳ በራሱ ገቢ የሚተዳደር ነው፡፡ ከመንግሥት ትሬዠሪ አይሰጠውም፡፡ ስለዚህ ትልቁ ትኩረት ለገጠሩ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡

የእኛ እይታ ሁሉም ወረዳዎች በራሳቸው ገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ሐዋሳ እና ወንዶ ገነት የራሳቸውን ወጪ መቶ በመቶ እንዲችሉ ነው የተደረገው፡፡ አለታ ጩኮ 80 ከመቶ ሸፍኗል፡፡ ወረዳውም 70 ከመቶ በላይ አንዲደርስ አድርገናል። ይሁንና ከፍትሐዊነት አኳያ መንግሥት በጀት ይዞ በእነዚህ ከተሞችም የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች አሉ፡፡

በእርግጥ በአሁኑ ወቅት የፕላን ቢሮ ከሥርጭት አኳያ እያጠናው ያለው ጥናት አለ፡፡ ምን ያክል ሽፋን፣ ርቀት፣ እንዴት ተከናወነ የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዱ አካባቢ መልክዓ ምድሩ ላይ አራት ኪሎ ሜትር መንገድ በሚሠራበት ሃብት ሌላ መልክዓ ምድር ላይ 25 ኪሎ ሜትር ሊሠራ ይችላል፡፡ ይሁንና ይህን በአግባቡ ለመመለስ የሚያስችለው ጥናት በመሆኑ ወደዚህ ተገብቷል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሁሉም መስክ 514 ፕሮጀክቶችን ማከናወን ችለናል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች የት አካባቢ እንደተሠሩ በደንብ ይታወቃሉ፡፡ ይህ ብዙ ፕሮጀክት ነው፡፡ በየዓመቱ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ነው የምንመድበው ። ባለፉት ሦስት ዓመታት ሐዋሳ ከተማን ጨምሮ 13 ቢሊዮን ብር ከመንግሥት ካዝና ወጪ አድርገናል። ይህ ቻናል አንድ፣ ሁለት እና ሦስት የሚባለውን አያጠቃልልም፡፡ ስለዚህ እንደ ክልል ድህነትን በሚቀንሱ ፕሮጀክቶች ላይ አተኩረናል፡፡ ይህ እንደ ሀገርም ተመሳሳይ ነው፡፡ በክልላችን ለድህነት ቅነሳ የሚያግዙ እንደ ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ እና መሰል ሴክተሮች ላይ እስከ 61 በመቶ በጀት እየመደብን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የሕዝብ ጥግግትና የመሬት ጥበት ያለበት ነው። ይህን ከገቢ አሰባሰብ፣ ፋይናንስ አጠቃቀምና የዘመነ አሠራር ከማስኬድ አኳያ ምን እየተሠራ ነው?

አራርሶ (ዶ/ር)፡– ገቢ አሰባሰቡን ማዘመን ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅ ነው፡፡ ዲጂታላይዝ ከማድረግም አልፎ ትውልድ ላይ ስለ ግብር አስፈላጊነት በደንብ መሠራት አለበት፡፡ በዚህ ላይ ገቢዎች ቢሮ የራሱን ሥራ እየሠራ ነው፡፡ እውቅና ከመስጠት ጀምሮ ብዙ እየተሠራበት ነው፡፡ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

እንደ ሲዳማ ክልል የተጠጋጋ ማኅበረሰብ ያለበትና የመሬቱም ስፋት መጠነኛ ነው፡፡ ከጥቂት አርብቶ አደሮች በስተቀር በሄክታር የሚቆጠር መሬት የላቸውም፡፡ ሌላው እንደ ሲዳማ የሚያሳስበው ከተሜነት እየተስፋፋ ነው፡፡ በየሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ከተማ ይገኛል፡፡ ከ72 በላይ ከተሞች በማዘጋጃ የተያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ማዘጋጃ ገቢውም በዚያው ልክ መጨመር አለበት፡፡ ስለዚህ እነዚህን እቅዶች በስትራቴጂ በ10 ዓመቱ እቅድ እና በአምስት ዓመቱ እና በሦስት ዓመቱ የሚከናወኑት ምንድን ናቸው ለሚለው ፍኖተ ካርታ አለን፡፡

ሲዳማን እንዴት እንመራለን በሚለው ላይ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ላይ በተለይም ደግሞ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ጋር በትይዩ የሚሄድ ነው፡፡ አካሄዳችን ቀጣይነት ያለው ዕድገትን መሠረት አድርገን ነው፡፡ በተለይም በፋይናንስ እና ኢኮኖሚክስ ሴክተሩ የመጀመሪያ ትኩረታችን ሰው ተኮር መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ ሰው መማር፣ መብላት፣ መጠጣት አለበት፡፡ ስለዚህ ሥራችን ሰው ተኮር መሆን አለበት፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ ገቢ ያስፈልጋል፡፡ ሊሠራ የሚችለው በገቢ ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክም ቢሆን እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር የተሰባሰበውን ገቢ ድምር ውጤት ነው የሚመድበው፡፡ በመሆኑም የተሰበሰበው ተመልሶ እንደሚሰራጭ ይታወቃል። ስለዚህ ይህን ለማድረግ ሲዳማ ክልል 2012 ዓ.ም ወይም ደግሞ ሲዳማ ክልል ከመሆኑ በፊት ወጭ የመሸፈን አቅሙ 20 በመቶ ነው፡፡ ስለዚህ ግንዛቤን በማሳደግ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሠራተኛው በቁርጠኝነት በሠራው ልክ የሚመዘን ነው፡፡ በ2015 በጀት ዓመት 44 ከመቶ በላይ በውስጥ ገቢ መሸፈን የቻለ ክልል ሆኗል፡፡ ስለዚህ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ አድጓል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ሥራ እየተሠራ ያለው በዚህ ልክ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ከ55 በመቶ የክልሉን ወጭ በውስጥ ገቢ የመሸፈን ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው፡፡ ይህ ለሀገር እንደ ትልቅ ትምህርት የሚወሰድ ነው፡፡

የክልሉ ገቢ ትልቅ አቅም እየሆነ ነው፡፡ ገቢ ሲኖር በክልሉ ልማት እንዲፋጠን የማድረግ አቅም ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ወንዶገነት ላይ የሚጨነቁት ምን ልሥራ እንጂ እንዴት እንሥራ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በቀን ምን ያህል ገቢ እንደሚሰበሰብ ሲታይ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ አሠራሮችን የማዘመን ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በአጠቃላይ አሠራራችንና ዕይታችን ሰው ተኮር ነው፡፡ ሥራው ምን ያህል ውጤት አመጣ፤ እንዴትና በምን መልኩ የሚለው በአሠራሩ መሠረት እየታየና እየተገመገመ የሚሻሻልና የሚጠናከር ነው፡፡

ሦስተኛው ሰላምን ማስጠበቅ ነው፡፡ ማንም ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም ሲገባ ነው መግባት አለበት፡፡ ኢኮኖሚውም የሚፈልገው ሰላም ነው፡፡ ሰላም ከሌለ መብላት፣ መጠጣት አያምርም፡፡ ስለዚህ ሥራችን ሕዝብ ተኮር ነው፡፡ ኢኮ-ሲስተሙ ዕቅድ ተኮር ነው፡፡ አረንረጓዴ አሻራም ይሁን ሌሎች ተግባሮች በመናበብ የሚሠሩ ሲሆን ሰላምን የማስፈን ጉዳይ እንደ ትልቅ መፈክር ሆኖ የሚሠራበት ነው፡፡ ሁሉም ሰው በልኩ መሥራት የሚችልበት፤ አካባቢው ከራሱ አልፎ ለሌሎች ምቹ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡

ለዚህም የወንድማማችነት ስሜት በክልሉ እንዲፈጠር ይሠራል፡፡ ደጋፊ አካላትና ረጂ ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራ ነው፡፡ ብልጽግናን በዘርፈ ብዙ እይታ እንመለከተዋለን፡፡ መሠረተ ልማት ማሟላት አንዱ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በሞተርም ይሁን በሌሎች ተሽከርካሪዎች በሰላም ወደ ቤቱ ገብቶ ምቾት ካልተሰማው ብልጽግና አይረጋገጥም። የመንገድ መሠረተ ልማት፣ የግብርና ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ማሟላት ላይ በስፋት እየተሠራ ነው፡፡ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ማሟላት፤ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ ምርትና ምርታማነት መቀነስ ማለት ቀጥተኛ ያልሆነ የዋጋ ግሽበትን መፍጠር ነው፡፡ እይታው ሁሉን አቀፍ ነው፡፡ ከ40 ዓመት በኋላ ክልሉ የት ይደርሳል የሚለውን ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢንቨስተሮች በክልሉ እንዲሠማሩ አሠራሩ የዘመነ አትራፊነት እንዲጨምር ከማድረግ አንጻር እንደ ፋይናንስ ቢሮ ምን ተሠርቷል?

አራርሳ (ዶ/ር)፡- ይህን በሁለት መልኩ ማየት ተገቢነት አለው፡፡ 80 በመቶ በላይ ክልሉ የሚዋሰነው ከኦሮሚያ ክልል የሚወሰን ሲሆን ቀሪው በቀድሞ አጠራር ከደቡብ ክልል የሚዋሰን ነው፡፡ ልማት ድንበር፣ ወገን፣ ጎሳ የለውም፡፡

ቡራ ጋጣ የምትባል ከተማቸው ናት፡፡ ከእኛ ከድንበር 10 ኪሎ ሜትር ጠጠር መንገድ አሠራን። ቡራ ላይ የኦሮሚያ አመራር ባለቡት መንገዱ ይመረቃል፡፡ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ለማገናኘት ኢኮኖሚ ወሳኝነት አለው፡፡ መንገድ የሆነ ክልል ላይ ይጀምርና ጫፍ ላይ ሄዶ ይቆማል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ መንገድ እንደ ሀገርም የሚፈጥረው ምስል የሚያመጣውም ጠቀሜታ ቀላል አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ኮሪደሩ በጣም አስቻጋሪ ስለሆነ ብዙ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ እናስባለን፡፡

ሲዳማ ውስጥ መጥቶ ማንኛውም ባለሃብት በፈለገው ሁኔታ ባሰበው ከተማ ላይ ሂዶ ማልማት ይችላል፡፡ ስለሆነም በክልሉ ኦሮሚያ እና የመሰሉ በርካታ የሌሎች አካባቢ ባንኮች አሉ፡፡ በዚህ ዓመት የእኛንም ቢሮ ጨምሮ በአጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ ክፍያውን ቼክ ፍሪ ልናደርግ አስበናል። ቼክ ጋር ተያይዞ እንደሀገርም የተጀመረ አቅጣጫ አለ፡፡ እንደ ክልል አሁን ከንግድ ባንክ ጋር ውል ገብተን በቢሮ ልንጀምር አስበናል፡፡ ወደ ቴክኖሎጂ መግባቱ አጠቃላይ ሥርዓቱን ለማዘመንም ዕድል ስለሚሰጥ በልዩ ትኩረት እየሰራን ነው፡፡ በአጠቃላይ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለንን ሠላም የተረጋጋ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሲዳማ ክልል በኬንያ እና በአጎራባች ሃገራት ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች እንደሚካሄድበት ይታወቃል፡፡ በዚህ ላይ እንደ ክልል ምን እየተሠራ ነው?

አራርሶ (ዶ/ር)፡– የኮንትሮባንድ ጉዳይ ሃገራዊም ችግር ነው፡፡ እንደ ሀገርም የምንፈተንበት ነው፡፡ ሰው ወደ ሕሊናው፣ወደ ቀልቡ እስኪመለስ እና ኢትዮጵያን ወደ መውደዱ ተመልሶ አርበኛ እስኪሆን ድረስ ሰፊ ሥራ እንሠራለን፡፡ ይህች ሃገር ማግኘት ያለባትን ጥቅም፤ መድረስ ያለባትን ጎዳና፤ መድረስ ወዳለባት ከፍታ የምንጓጓው የምንመኘው ብልጽግና እንድትደርስ ዝርክርክ እንደ እኛ ለማይመጥኑ ሥራዎች ዕድል አንከፍትም፤ በርም አንሰጥም፡፡ በዚህ ላይም ከፍተኛ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት እና የጥንቃቄ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ከማዳበሪያ ዕዳ አመላለስ ጋር በተያያዘም ወቀሳዎች ይሰነዘሩበታል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አራርሶ (ዶ/ር)፡- ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ የዕዳ ቀንበር ያለበት ነው፡፡ እሱም የማዳበሪያ ዕዳ ነው፡፡ የነበረው አሠራር፤ የነበረው ሥርዓት እጅግ ጥሩ የማይባል ነበር፡፡ እኛ ክልል ሆነን የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊነት 2013 ዓ.ም ላይ ስንመጣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ወደ 588 ሚሊዮን ብር ዕዳ ነው የወሰድነው፡፡ እንደሚታወቀው፤ የማዳበሪያ ዕዳ ወለድ አለው። ወለዱ ደግሞ ኮምፓውንድ ሬት ነው፡፡ በየዓመቱ ይጨምራል፡፡ ከ2007 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ 747 ሚሊዮን ብር ዕዳ ከፍለናል። በአጭሩ በወቅቱ የነበረውን ጨርሰናል፡፡ ይሁን እንጂ በ2012 ዓ.ም አልከፈላችሁም፤ የሚል ቅሬታ እየመጣ ነው፡፡

የጠፋው ሃብት የት ነው ተብሎ ቢጠየቅ ሚስጥሩ በጣም ከባድ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ የሚባል ተቋም አለ፡፡ ኤጄንት የሚባል አለ፡፡ እኛ ከሕዝቡ ዕዳ አውርደናል፡፡ ቀጥሎ ይህን የወሰደው ማን ነው? የሚለውን በኦዲት ፈልገን ወደ ዘመቻ ልንገባ ነው፡፡ ኦዲት ያላደረከውን ግን እከሌ ነው ማለት አይመችም፡፡

ግን ኦሞ ይሰጥ ነበር፡፡ ኦሞ ውስጥ ኤጀንት ነበር። ኮፕሬቲቭ ውስጥ አመራር አሉ፡፡ በዚህ በርካታ ተዋንያን አሉ፡፡ ያንን ሕያው ለማድረግ በአሁኑ ወቅት እየሠራነው ባለው ኦዲት ነው፡፡ ከዛም የሕግ ተጠያቂነት አለ፡፡ ይህ ዕዳ ተመልሶ ሃብት መሆን አለበት፡፡ ብር ሆኖ ወደ ልማት መግባት አለበት የሚል አቋም አለን፡፡ ሌላው በ2013 ዓ.ም መንግሥት ስንሆን ያደረግነው ወሳኝ ነጥብ ከኦሞ እጅ ነጥቅን፡፡ ይህን አወዳድረን ለአንድ ዩኒዮን ሰጠን፡፡ አሁን ካሽ ነው የምንሸጠው፡፡ እጅ በእጅ ሲሆን ደግሞ እንደ ዱሮ አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ 94 ከመቶ ሥራችንን ማሳካት ችለናል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ይህ ጉዳይ አሁንም ቢሆን የማዳበሪያ ገበያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ የሥራ ኃላፊዎች ተጠያቂ ሆነዋል፡፡ በዚህ ዓመት በራሱ ማዳበሪያ ላይ በማጭበርበራቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው አመራርና ባለሙያ ተጠያቂ ሆነዋል፡፡ በእዳውም የሚጠየቁ አካላት አሉ፡፡ አስጠይቆ የማስከፈል ሥራ ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡ እኛ በዚህ ላይ ያለን ቆራጥነትና ላቅ ያለ ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሰዎችን እየመከርን፣ እያስተማርን፣ እየገሰፅንና እያሠለጠንን እያስተካከልን እንሄዳለን፡፡ በአጠቃላይ ግን በርካታ ሰዎች በማዳበሪያ ጉዳይ ተጠያቂ ሆነው በአሁኑ ወቅም በሕግ ከለላ ሥር ያሉ አሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በተያዘው በጀት ዓመት ከሚያገኘው ገቢ ለታለመለት ዓላማ የማዋልና የፋይናንስ ግልጸኝነት ከማስፈን አኳያ ምን እየሠራ ነው?

አራርሶ (ዶ/ር)፡– በዚህ ዓመት አጠቃላይ በጀታችን 22ነጥብ6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ ከትሬዠሪ እና አንዳንድ አሲስታንት ጋር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 13 ቢሊዮን ብር ከውስጥ ገቢ ነው፡፡ ይህ ሃብት በጣም በትልቅ ቅልጥፍና፣ የፖለቲካ አመራርና ቁርጠኝነት ሰብስቦ ልማት ላይ ማዋል ይገባል። ይህ እንዲሳካ ሌት ተቀን እንሠራለን፡፡ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሕዝብ ፍላጎት ማርካት አለብን፡፡

ሕዝብ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ፍላጎት አለው፡፡ ይህን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት እየሠራን ነው፡፡ የክልሉ የገቢ ምጣኔም በየጊዜው እያደገ ነው፡፡ 2013 ዓ.ም አጠቃላይ ገቢው አንድ ቢሊዮን ብር አይሞላም ነበር፡፡ በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ግን እጅግ በብዙ እጥፍ አድጓል፡፡ ዕድገት እንዲመጣ ግን የእጅም የልብም ንጽሕና ያለው አመራርና ማኅበረሰብ መፍጠር አለብን ብለን ጥረት እያደረግንም፤ እየሠራንም ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ላደረጉት ቆይታ እናመሰግናለን፡፡

አራርሶ (ዶ/ር)፡- እኔም በክልሉ አጠቃላይ የፋይናንስ አሠራር እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ እንድሰጥ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2016

Recommended For You