የ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤት ማሽቆልቆል መንስኤውና መፍትሄው በአግባቡ ሊጠና ይገባል

አዲስ አበባ፡- የ12 ክፍል ሀገር ፈተና ውጤት ማሽቆልቆል መንስኤውና መፍትሄውን በአግባቡ በማጥናት የትምህርት ሥርዓቱን ማስተካከል እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፈቀደ ቱሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ተከትሎ ችግሩን ለመረዳት በቅድሚያ ጥናት ሊደረግ ይገባል።

ተማሪዎች ላይ ያጋጠሙ ችገሮችን ሳይረዱ በየዓመቱ ፈተና ደጋግሞ በመስጠት ብቻ የትምህርት ጥራትን ማምጣት አይቻልም ያሉት ዶክተር ፈቀደ ፤ ያለው ችግር ከተማሪው፣ ከመምህሩ፣ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ወይም ከሌላ ጉዳዮች ጋር አያይዞ የሚከናወን ጥናት ያስፈልጋል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ሶስት ነጥብ ሶስት በመቶ ብቻ ተማሪዎች ማለፉቸውን በማስታወስ ፤ ውጤቱን ተከትሎ ጥናት ሳይደረግና ችግሮች ታውቀው አቅጣጫ ሳይቀመጥ ድጋሚ ተማሪዎች መፈተናቸው ተመሳሳይ ውድቀት እንዲከሰት ማድረጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም የተሻለ ውጤት ለማምጣትና የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል ሰፊ ጥናት ማድረግና ስብራቱን መጠገን ይገባል ሲሉ አስረድተዋል። ዶክተር ፈቀደ እንደተናገሩት፤ ምንም ተማሪ ያላለፈባቸው አንድ ሺህ 328 ትምህርት ቤቶች ችግራቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት ጥልቅ ጥናት ማድረግና ችግሩን ከስር መሰረቱ መመርመር ያስፈልጋል።

በሀገሪቱ 50 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹን በማስታወስ፤ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ባለበት የተሻለ ውጤት መጠበቅ አዳጋች ነው ብለዋል።

ትምህርት ቤት ትውልድ የሚቀረጽበት ተቋም እንደመሆኑ በትምህርት ላይ የሚሠሩ ሥራዎች እንደ አዋጭ ኢንቨስትመንት ሊታዩ ገባል ያሉት ዶክተር ፈቀደ፤ በትምህርት ዘርፉ የተጓደሉ ነገሮችን በማሟላት ትምህርት ቤቶች ዝቅተኛ ደረጃ እንዲወጡ ማድረግ ይገባል ሲሉ ሃሳብ ሰጥተዋል።

የመምህራን አቅም ማጣትና በዘርፉ ለመቆየት ፍላጎት ማነስ፤ የተማሪ ለትምህርት ያለው ዝቅተኛ አመለካከት ፤ የአመራር ክፍተት እና የሀገሪቱን የሰላም ሁኔታን ለውጤት ማሽቆልቆሉ እንደችግር በመሆናቸው ለመፍትሄው በጋራ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ዘርፍ ተመራማሪ የሆኑት አማረ አስግዶም (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ችግሩን ለመፍታት ከታች እስከ ላይ ያለውን የትምህርት አሠራር መፈተሽ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

መንግሥት ትኩረት አድርጎ ሲሠራ የቆየው ትምህርትን ማስፋፋትና ተማሪን ማብዛት ላይ ነው ያሉት ተመራማሪው ፤ ለትምህርት ጥራት ይበልጥ ትኩረት በመስጠትና ጥናትን መሠረት ያደረገ ሥራ በማከናወን መፍትሄ ማበጀት ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።

በተጨማሪ ከትምህርት ጋር ልቡ የተዋሃደና ሙያውን ወዶና ፈቅዶ የሚያስተምር ብቁ መምህር በብዛት ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ችግሩ እንደ ሀገር እየጎዳን በመሆኑ ምርምርና ሳይንሳዊ መፍትሄዎች ላይ በማተኮር ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አጠቃላይ የመማር ማስተማር አሠራሩ መፈተሽና ከ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ጋር ተያይዞ በተማሪውም ሆነ በመምህራን ላይ በቂ ጥናት በማካሄድ የትምህርት ጥራት ችግሩን ቁልፍ መነሾ መለየትና ማስተካከል ይገባል ብለዋል።

 አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2016

Recommended For You