ከትምህርት የሚጠበቀውን ፍሬ ለማግኘት

የአንድ አገር ስልጣኔ ከሚገለጽባቸው እውነታዎች መሀል ጠንካራ የትምህርት ስርዓት አንዱ ነው። ይህንንም በእውን ለማድረግ ሀገራት በርካታ ጥረቶችን ያደርጋሉ። በሀገራችንም ይህንኑ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ሀገር አሻጋሪ የተማረ ትውልድ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ጥረት ስታደርግ ቆይቷል።

ጥረቱ በየወቅቱ በተለያዩ ተግዳሮቶች ቢፈተንም፤ አሁን ድረስ በተጠናከረ መንገድ እንደቀጠለ ነው። በቅርቡም ለትምህርት ጥራት በተሰጠው ልዩ ትኩረት የነበሩ ችግሮችን አስወግዶ የተሻለ የትምህርት ስርዓት ለመገንባት የተጀመረው ሀገራዊ ጥረት የዚሁ እውነታ አንድ አካል ነው።

የትምህርት ዘርፍ ሰፊና ውስብስብ ነው፤ ከዚህ የተነሳ በጥናት ላይ የተመሰረተ ግልጽ ፖሊሲ እና ፍኖተ- ካርታ ሊቀረጽለት የሚገባ ነው፣ በዚህ ሂደት የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ማየቱ ለውጤታማነት የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።

ብዙዎች እንደሚስማሙበት የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው በሚዘጋጁ ፈተናዎች ጥንካሬ ብቻ አይደለም። ጥራቱን በወጉ መለየት የሚቻለው አጠቃላይ የሆነውን የትምህርት ስርዓቱንና አተገባበሩን ተሳቢ በማድረግ ነው።

በዚህ ውስጥ ስርዓተ ትምህርቱ፣ የመምህራን ብቃት፣ የማስተማር ሥነ ዘዴዎች፣ የትምህርት ቤቶች ደረጃ፤ የተማሪ ክፍል ምጠና፤ የመጽሀፍት ዝግጅት ወዘተ የሚካተቱ ናቸው። በማህበሩ ውስጥ ስለ ትምህርት ያለው አመለካከትም የዚሁ እውነታ አካል ነው።

ማሕበረሰቡ ስለ ትምህርት ያለው አመለካከት በታሰበው ልክ ለትምህርት ስርዓቱ አቅም ይሆናል ወይ ? ትምህርትን የነገ ተስፋ አቅም አድርጎ የመውሰድ፣ ተምሮ ከመቀየር ይልቅ ለመለወጥ ሌሎች አማራጮችን ማየት.. ወዘተ በትምህርት አጠቃላይ እሳቤና ጥራት ላይ የሚኖራቸው አሉታዊ ተጽእኖ የጎላ ነው።

‹‹ትምህርት ሕይወትን ይለውጣል›› እንደሚሉ ወገኖች እምነት ትምህርት ማሕበራዊ መሰረት እያጣ በመጣ ቁጥር ለዘርፉ የሚሰጠው ዋጋ እየወረደ ይሄዳል። ሰዎች በልፋት ድካም፣ ከዕውቀት ሳይጋመዱ የሚያገኙት ዕድል ለትምህርት የሚሰጠው ግምት ይበልጥ ያሽቆለቁለዋል። በየጊዜው እንዲህ አይነቱ ልማድ መበራከቱም የትምህርቱን ዘርፉን እያቀጨጨው እንዲሄድ ያደርገዋል።

ይህ አይነቱን የተበላሸ አመለካከት ለማረም ኃላፊነቱ የሚወድቀው በመንግስት ትከሻ ላይ ብቻ አይደለም ። ስለ ትምህርት ያለው አመለካከት ይለወጥ ዘንድ ትግሉ ከቤት፣ ከቤተሰብ ሊጀምር ይገባል። ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ከመላክ ባለፈ ስለትምህርት ጠቀሜታ አውቀው ማሳወቅ ከነሱ የሚጠበቅ ግዴታ ነው።

የትምህርት ዘርፉ እውነታ ትውልድን ይዞ መቀጠል እንደመሆኑ ልዩ ጥንቃቄን ያሻል። ዕውቀት ጨብጦ ከማሻገር ይልቅ በአቋራጭ መቅደም በበዛ ቁጥር ትምህርት ይሉት ውድ ጉዳይ ዋጋው ይራከሳል። አንዳንዶች ለወረቀቱ ሲሉ ብቻ በገንዘብ የሚገዙት የትምህርት ማስረጃ ውሎ አድሮ ውጤቱ የሚመነዘር ነው።

በተለይ ይህ አይነቱ እውነት በመምህራን የሚተገበር ሲሆን ጉዳቱ ውስን አይሆንም። የዕውቀት ደጃፍን ሳይረግጡ በእጃቸው ያስገቡት ሰነድ ከተማሪዎች ሕልውና ሲገናኝ መጨረሻውን የከፋ ያደርገዋል።

የመምህራን ዕውቀት ማነስና ራስን ለማብቃት አለመዘጋጀት የትምህርት ስርዓቱ እንዲታመም ከሚያደርጉ አንኳር ምክንያቶች መሀል ዋንኛው ነው። አንድ መምህር ከራሱ የሚተርፍ ዕውቀት ይዞ ለተማሪው ማካፈል ካልቻለ የመማር ማስተማሩን ሂደት በግልጽ ያስታጓጉላል።

ይህ አይነቱ መምህር ተብዬ ከተማሪው ያነሰ ዕውቀት ይዞ ለማስተማር መቆሙ ትውልድን በግልጽ ከመግደል የሚተናነስ አይሆንም። እንዲህ አይነቱ ችግር እየታወቀ ከሚመለከተው አካል ዝምታ መስተዋሉ ደግሞ ለትምህርት ሂደቱ ስብራት ዋንኛ ተባባሪ እንደመሆን ይቆጠራል።

ጊዜና ወቅትን የዋጀ ስልጠና ለመምህራን ተደራሽ በሆነ ቁጥር ችግሮችን ለይቶ ለማውጣት ያግዛል። አንድ መምህር የዕውቀት ደረጃውን በሚመጥን አግባብ ሲሰማራ ጊዜ እና ዕውቀት ሳይባክን ተገቢው አካል ተገቢውን እውቀት እንዲያገኝ ያስችላል። በስልጠና ተሞክሮን ያማከለ ዕውቀት ተጋርቶ በማጋራት የተሻለ የትምህርት ሥርዓት እውን ማድረግ ይቻላል።

ለዘርፉ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ አቅርቦቶች አለመሟላት የትምህርት ስርዓቱ ተጨማሪ ፈተዎናዎች ናቸው። በወጉ ያልተሰነዱ፣ ለተማሪዎች ዕውቀት የማይመጥኑ መጽሀፍት ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል። ይህ እውነታ በተለይ ትምህርትን ሀ ብለው በሚጀምሩ ህጻናት አዕምሮ ላይ የሚኖረው ጫና ከፍ ያለ ነው። በዚህ ጅማሬ የሚጓዝ ተማሪ ቀጣይ የትምህርት ጉዞው ምን ያህል ክፍተት ሊኖረው እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም።

በተገቢ መልኩ ያልተዘጋጁ የትምህርት ቁሳቁሶች በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ ክፍተት ማስከተላቸው አይቀሬ ነው። አንድ ተማሪ ዓመቱን የሚያስጨርሰው ደብተር፣ የመጻፊያ መሳሪያዎችና መሰል አቅርቦቶች ከሌሉት በትምህርቱ ብቁ ነው ለማለት ያስቸግራል።

በመንግስት በኩል ሊሟሉ የሚገባቸው የመማሪያ መጻህፍት በአሁኑ ጊዜ የበርካታ ትምህርት ቤቶች ችግር ስለመሆኑ ይነገራል። አጋዥ የመማሪያ አቅርቦት በሌለበት ጠባብ እድል ደግሞ የሚፈለገውን የውጤት ደረጃ መጠበቅ የሚቻል አይሆንም።

አብዛኞቹ ተማሪዎች ዘንድ የተለመደው የትምህርት አቀባበል ትምህርትን ለዕውቀት ሳይሆን ለፈተና ብቻ በማሰብ ላይ የተመሰረተ ነው። በትምህርት ዘመኑ ከዕውቀት ሳይገናኝ የቆየ ተማሪ ፈተና በደረሰ ጊዜ በሽምደዳ ራሱን ሲያስጨንቅ ይስተዋላል።

ይህ አይነቱን ዘዴ የማይሹ አንዳንዶችም ‹‹የዓይን ጥራት›› ይሉትን ልማድ ተጠቅመው በኩረጃ ፈተናን ለማለፍ ሲጥሩ ማየት ብርቅ ሆኖ አልኖረም። አሁን ላይ እንዲህ አይነቶቹ ልማደኛ ተማሪዎች ቀን መሽቶባቸዋል።

የዚህ አይነቱ ልምድ የነበራቸው ተማሪዎች ከነተሞክሯቸው የመቀጠላቸው እውነታ ሀገርን ጭምር መጉዳቱ የማይቀር ነው። ለዚህም ሰሞኑን የትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ተማሪዎቻቸውን ካስፈተኑ 3106 የመደበኛ ትምህርት ቤቶች መካከል 50 ፐርሰንትና ከዛ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች 57 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ናቸው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከ50 ፐርሰንትና ከዛ በላይ ያስመዘገበ አንድም ተማሪ የሌላቸው ትምህርት ቤቶች በቁጥር 1328 ሆነው ተለይተዋል። ይህም የፐርሰንት ስሌቱን 42 ነጥብ 8 ብቻ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጎታል።

እንደ ትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ባለፈው ዓመት በተደረገው ጥረት የፈተና ሌብነትንና ኩረጃን ለመከላከል ከፍተኛ የሚባል ጥንቃቄ ተደርጓል። እንዲያም ሆኖ የተቀመጠውን ሕግ ተላልፈው መመሪያና ደንቡን ለመጣስ ሙከራ ያደረጉ ተፈታኞች አልጠፉም ።

ትምህርት የሀገርና ትውልድ መሰረት ከመሆኑ አንጻር፤ ዕውቀትን በተገቢው መንገድ አሻግሮ ፍሬያማ የሚባል ውጤት ለማግኘት የሁሉም ወገን ድርሻና ኃላፊነት ሊሆን ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የሚጠበቅበትን በኃላፊነት መንፈስ ሊወጣ ይገባል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2016

Recommended For You