እኤአ በ2016 በተደረገ ጥናት ጎረቤት ሀገር ኬንያ በአሁኑ ወቅት ከቻይናና ከህንድ ቀጥሎ ሶስተኛዋ ዓለም አቀፍ የሻይ አምራች ናት፡፡ ሀገሪቱ የሻይ ቅጠል ምርትን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በስፋት የምትልክ ስለመሆኗም ጥናቱ አመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ስላለው የሻይ ቅጠል ምርት ስናነሳ ደግሞ ታሪክ የኋሊት ይወስደናል፡፡ የሻይ ተክል በካቶሊክ ሚሲዮናውያን አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ይታመናል፡፡ የሻይ ተክል ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከ40 ዓመታት ቆይታ በኋላ ጉመሮና ውሽውሽ የሻይ ልማቶች መወለድ እንደቻሉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የልማት ድርጅቶቹ በ1958 እና በ1966 ዓ.ም በአነስተኛ እርሻዎች በቅደም ተከተል እንደተቋቋሙ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡
በኢሉአባቦራ ዞን ጎሬ አካባቢ በነበሩ የካቶሊክ ሚሲዮናውያን አማካኝነት በወቅቱ ከህንድ ሀገር የተወሰኑ የሻይ ተክል ዝርያዎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን፤ የሻይ ልማቱ በተወሰነ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ባህላዊ በሆነ መንገድ ተዘጋጅቶ ለአካባቢው ገበያ ይቀርብ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ የሚገኙት ሁለት ግዙፍ የሻይ ቅጠል ልማት እርሻዎች ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚገኘው ጉመሮ ሻይ ልማት አንደኛው ሲሆን፤ ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ከተማ በ630 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በኢሉአባቦራ ዞን በአሌ ወረዳ ይገኛል፡፡ ሁለተኛው ግዙፉ የሻይ ቅጠል እርሻ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በከፋ ዞን በጊንቦ ወረዳ ከአዲስ አበባ 460 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
በዕለቱ የግብርና አምዳችንም ትኩረት ያደረገው በኦሮሚያ ክልል ስላለው የሻይ ቅጠል ልማት ይሆናል፡፡ በአንድ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሲናገሩ፤ የሻይ ቅጠል ልማት ለአርሶ አደሩም ሆነ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከሚያበረክቱ የኤክስፖርት ምርቶች አንዱ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ይህን በመረዳትም የሻይ ቅጠል ልማት ኢኒሼቲቭ በ2014 ዓ.ም “የአሌ የሻይ ቅጠል ልማት ዲክላሬሽን” መታወጁን አስታውሰዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሻይ ቅጠል ልማት በኢሉአባቦራ ዞን አሌ ወረዳ ብቻ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁመው፤ ልማቱን ወደ ጅማ፣ ቡኖ በደሌ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ማስፋፋት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ሁለትና ሶስት ዓመታትም የሻይ ተክሉ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ እንደሆነና ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሊያሳድግ የሚችል እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ በክልሉ ያለውን አጠቃላይ የሻይ ቅጠል ምርት ሥራን አስመልክቶ በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የቡናና ሻይ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አቦሴ እንደሚሉት፤ ክልሉ ለሻይም ሆነ ለቡና ልማት እምቅ አቅም አለው፤ ኢኮሎጂው ለቡናና ሻይ ልማት እጅግ በጣም ምቹና ተስማሚ ነው፡፡
የሻይ ምርት ቀደም ባሉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦራ ውስጥ ብቻ ይለማ እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን የሻይ ልማቱን ማስፋት እንደተቻለ ነው ያስረዱት፡፡
እሳቸው እንዳሉት ፤ በክልሉ የሻይ ተክል ልማትን ማካሄድ የጀመረው የሚድሮክ እህት ኩባንያ ሲሆን፤ ጊዜውም ከሰባና ሰማንያ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ከዛሬ አምስት ዓመት ወደዚህ ግን በመንግሥት ተነሳሽነት የሻይ ተክል ልማቱን ወደ አርሶ አደሩ በማውረድ በአካባቢው ያለው አርሶ አደር የሻይ ተክልን በስፋት ማልማት እንዲችል እየተሠራ ነው፡፡ በተለይም ብቸኛ የሆነው የሚድሮክ ኩባንያ ባላበት አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች የሻይ ቅጠልን እያለሙ ለፋብሪካው እንዲያቀርቡ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የሻይ ቅጠል ምርት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሻ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ቅጠሉ ከማሳ ላይ ተለቅሞ በሶስት ሰዓት ውስጥ ወደ ፋብሪካ መግባት አለበት ይላሉ። ያለበለዚያ ግን ጥቅም የሚሰጥ አይደለም ይበላሻል ብለዋል፡፡ ለዚህም ነው ፋብሪካው ባለበት አካባቢ ላይ ትኩረት ተደርጎ ልማቱ እንዲካሄድ እየተደረገ ያለው። ፋብሪካው ከ800 እስከ 900 ሄክታር በሚደርስ ማሳ ላይ የሻይ ቅጠል ተክሉን አልምቶ፣ በእሴት ጭመራ አቀነባብሮ ለገበያ የሚያቀርብ መሆኑን ያስረዱት አቶ ተስፋዬ፤ በአሁኑ ወቅት ግን አርሶ አደሩ የሻይ ቅጠል ምርትን በስፋት ማልማት የሚችልበት መንገድ እየተፈጠረ ነው ይላሉ፡፡
አቶ ተስፋዬ እንዳብራሩት፤ ኩባንያው ከዛሬ 15 ዓመት በፊት በአካባቢው የሚገኙ የተወሰኑ አርሶ አደሮችን አሰባስቦ የሻይ ተከል ማልማት የሚችሉበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡ አርሶ አደሮቹም በ159 ሄክታር መሬት ላይ ሻይ ቅጠል አምርተው ለኩባንያው ያቀርቡ ነበር ፡፡
ከተወሰነ ጊዜ አቅርቦት በኋላ አርሶ አደሮቹ ሻይ ቀጠል የማምረቱን ሥራ አቁመውም እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ ሌሎች አርሶ አደሮች ግን በሻይ ቅጠል ልማቱ ለመሰማራት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ልማቱ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ በኩል መንግሥትም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የሻይ ቅጠል ምርትን በክልሉ በስፋት ለማልማት በየዓመቱ ችግኞችን በማፍላት በአካባቢው በሚገኙ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ችግኙ ሲተከል ቆይቷል፡፡ ልማቱን ከአካባቢው ወጣ በማለትም ማስፋት የተቻለ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመትም እንዲሁ ወደ ጅማ ቡኖ በደሌ አካባቢ ማስፋት ተችሏል። የሻይ ቅጠል ምርት ወዲያው ምርት የሚሰጥ አለመሆኑን አቶ ተስፋዬ ጠቅሰው፣ ከአራት እስከ አምስት ዓመታት የሚያህል ጊዜ እንደሚፈልግ አስረድተዋል፡፡
በክልሉ የዛሬ አምስት ዓመት የተጀመረው የሻይ ልማት በቀጣይ ዓመታት ምርት መስጠት እንደሚጀምር የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ በ42 ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ቅጠል እያለሙ ያሉ አርሶ አደሮችም በአሁኑ ወቅት በመጠኑም ቢሆን ምርት መሰብሰብ እንደጀመሩና ለኩባንያው እያቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ሌሎችም ከስር ከስር ምርት እንዲያቀርቡ እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ ዘንድሮም የሻይ ቅጠል ልማቱን በሰፊው ለማካሄድ በመንግሥት በኩል ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሰፋፊ ማሳዎች በሻይ ቅጠል ተክሎች እየተሸፈኑ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የሻይ ቅጠል ልማት በርካታ ግብዓቶችንና ሙያዊ ድጋፍ እንደሚጠይቅ አቶ ተስፋዬ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅትም የመንግሥትን አቅጣጫ በመከተል ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ግብዓቶችን እያሟላ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ከፕላስቲክ ማሸጊያ ጀምሮ ኬሚካሎችና የተለያዩ ቁሳቁስን በማሟላት በተያዘው በጀት ዓመት ችግኞቹን በስፋት ለማልማት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የሻይ ችግኝ እንደ ቡናና ሌሎች ችግኞች አይደለም ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ችግኙ ተቆርጦ የሚተከል በመሆኑ ቁርጥራጩን ማግኘት ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም ከሚድሮክ ኩባንያ ጋር በመነጋገር ባለፉት ዓመታት ቁርጥራጮቹን ከኩባንያው ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል። ችግኞቹንም ወደ አርሶ አደር ችግኝ ጣቢያ በመውሰድ በባለሙያዎች ባገኙት ሥልጠና መሠረት በስፋት እየተተከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም በርካታ የሻይ ቅጠል ችግኞች እንደሚዘጋጁ እንደሆነ አመላክተዋል።
የሻይ ቅጠል ችግኝ ለማዘጋጀት ጊዜ የሚፈልግ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ በትንሹ ከ10 እስከ 18 ወራት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ችግኝ ተተክሎ ነርሰሪ ላይ እስከ 18 ወራት ቆይቶ ወደ አርሶ አደር ማሳ እንደሚወሰድና ሰፋፊ ማሳዎችን ለመሸፈን ጊዜ እንደሚፈልግ ተናግረዋል። በመሆኑም በርካታ አካባቢዎችን በሻይ ቅጠል ችግኝ ለመሸፈን በርትቶ መሥራት የግድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በርካታ ችግኞችን መትከል ይቻላል፡፡ በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ እስከ 13ሺ800 የሻይ ቅጠል ችግኝ መትከል ይቻላል፡፡ ከዚህም ከፍተኛ መጠን ያለውን ምርት ማግኘት የሚቻል ሲሆን፣ በተለይም አንድ ጊዜ ምርት መስጠት ከጀመረ በየዓመቱ እየጨመረ ይመጣል። ከአንድ ሄክታር ከ130 እስከ 140 ኩንታል ግሪን ሊፍ ይገኛል፡፡
ሚድሮክ ኩባንያ እያለማ ካለው በተጨማሪ በአካባቢው አርሶ አደር እየለማ ያለው የሻይ ልማት ከአምስት ዓመት ወዲህ በስፋት ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፣ በቅርቡ ብቻ ከ200 ሄክታር በላይ ማሳ በሻይ ተክል መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ችግኝ ምርት መስጠት ሲጀምር በሄክታር እስከ 140 ኩንታል ግሪን ሊፍ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የሻይ ቅጠል ተክሉ በስፋት እየለማ ያለው ኢሉአባቦራ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ጅማ ማስፋት ተችሏል። ያለፈውን ክረምት ጨምሮ ጅማ ላይ በ52 ሄክታር ማሳ ላይ የሻይ ቅጠል ችግኝ ተተክሏል። በሚቀጥለው ክረምት የሚተከሉ በርካታ የሻይ ቅጠል ችግኝ እየለማ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፤ በቀጣይ በየዓመቱ የሻይ ቅጠል ተከል ችግኞች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድና ተከላውም በስፋት እንደሚካሄድ አመላክተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በባለሀብቶች ብቻ ሲለማ የነበረው የሻይ ቅጠል ምርት በአሁኑ ወቅት መንግሥት በሰጠው ትልቅ ትኩረት ወደ አርሶ አደር እየሰፋ መሆኑን ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩም ሻይ ቅጠልን የማልማት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። የሻይ ቅጠል ተክል አሁን ላይ እየለማ ካለባቸው አካባቢዎች በተጨማሪ በምዕራብ በኩል እስከ ቄለም ወለጋ ድረስ ሻይ ቅጠል ለማልማት ምቹ የአየር ሁኔታ መኖሩን ማረጋገጥ መቻሉንም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች አርሶ አደሩ የሻይ ቅጠልን በክላስተር እያመረተ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ አገሪቱ ለሻይ ልማት ምቹ ሁኔታና ከፍተኛ አቅም እንዳላትም ተናግረዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ የሻይ ቅጠሉን ከአርሶ አደሩ ተረክቦ ማቀነባበር የሚችሉ ፋብሪካዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቅመዋል፡፡ የሻይ ቅጠል ከማሳ ላይ ተለቅሞ በፍጥነት ወደ ፋብሪካ መድረስ ካልቻለ የመበላሸት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም ፋብሪካው ባለበት አካባቢ ምርቱን ማስፋት ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
የሻይ ቅጠል ምርት ለማምረት ኢትዮጵያ ምቹ ሁኔታ ያላት መሆኑንም አመልክተው፣ አሁን እየለማ ካለበት አካባቢ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ምርቱን ለማስፋት የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ክልሉ ከተለያዩ የመንግሥት አካላትና ባለሀብቶች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡ ለጊዜው እየተሰበሰበ ያለው ግሪን ሊፍ ለሚድሮክ ኩባንያ እየቀረበ መሆኑንም ተናግረው፣ ከምርቱ ጎን ለጎን የፋብሪካ ግንባታው ሊታሰብበት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
ኢትዮጵያ በሻይ ልማት ዘርፍ ገና ምንም ያልሠራች መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ ወደፊት ብዙ ሊሠራበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ አያይዘውም የሻይ ቅጠል ተክል እድሜው ረጅም እንደሆነ ጠቅሰው፤ ችግኙ አንድ ጊዜ ተተክሎ መስመር ከያዘና የመጀመሪያዎቹን አምስት ዓመታት አልፎ ምርት መስጠት ከጀመረ በተከታታይ ምርት እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ አስፈላጊውን እንክብካቤ አግኝቶ ምርት መስጠት ከጀመረ ከ70 እስከ 80 ዓመታት ድረስ ያለማቋረጥ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት አስራ ሁለት ወራት አንድ ሺ 879 ነጥብ 38 ቶን የሻይ ምርት ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ሶስት ነጥብ 19 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 899 ነጥብ 60 ቶን (ከዕቅዱ 48%) በመላክ ሁለት ነጥብ 03 ሚሊዮን የአሜርካ ዶላር (ከዕቅዱ 64%) ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ያመላክታል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም