የሁሉንም አትኩሮት የሚያሻው የትምህርት ሥርዓታችን

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየሰማነው ያለው የትምህርት ሥርዓታችን ገበና በብዙዎቻችን ዘንድ ድንጋጤም፤ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡ በሀገራችን ጉዳይ ዳሩን እንጂ መሃሉን የማናውቅ ብዙ ነን፡፡ አሁን ላይ ወደመሃሉ ገብተን የትምህርት ሥርዓታችንን አየን እንጂ በጉዳዩ ዙሪያ የነበረን ምልከታ በብዙ መልኩ የተዛባ እንደነበር ለመናገር አያዳግትም፡፡ በለውጥና በአዲስ ሥርዓት እምርታ እያሳየ የመጣው ትምህርት ሚኒስትር ገበናችንን ገልጦ መጪውን ጊዜ በአንክሮ እንድንመለከት እድል ሰጥቶናል፡፡

ትምህርት የሀገር ዋልታ እየተባልን አድገን በትምህርቱ ዘርፍ ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅም ይሄነው የሚባል በጎ ሥራ አለመሥራታችን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ እስከዛሬ ስናሽሞነሙነው የነበረው የመማር ማስተማር ሥርዓት ብዙ ነውሮችን፣ እልፍ የጓዳ ሚስጢሮችን ይዞ እንደነበር በተማሪዎች ውጤት ላይ የተስተዋለውን የውጤት ማሽቆልቆል ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡

ያለፈውን አንድ ዓመት በትምህርቱ ረገድ ያልገባንን የገለጠ፣ የገባንን የሻረ ለአዲስ አመለካከት ያሰናዳን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ራሳችንን ብሎም ሥርዓቱን ከፍ ሲልም መጪውን ጊዜ እንድንመለከት ያደረገ ነው፡፡ በኩረጃ እና ትውልድ በማይቀርጽ ሥርዓት ተምረን መመረቃችን ሳያንስ ትውልዱ ላይ የምንጭነው ራስን ያለመቻል ልማድ ሀገር እየጎዳ ተመልክተናል፡፡

ያለፈው ዓመት የተማሪዎች ውጤት በብዙ አስደንግጦ ማለፉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በዛ የተፈጠረብን መደናገጥ ሳናበቃ ፤ በዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ሌላ መገረምን አትርፈናል፡፡ ለአብነት እነዚህን አነሳሁ እንጂ ባለፈው ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር የፍተሻ ወቅት ለማመን የሚከብዱ በርካታ ዜናዎችን አስደምጦናል፡፡ ዘንድሮም ሚኒስቴሩ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ተመሳሳይ ዜና አሰምቶናል፡፡

የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የተማሪዎች ውጤት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ያለፍንባቸውን ሂደቶች ያጋለጠ ከመሆኑም በተጨማሪ በስፋትና በጥልቀት እንድንሠራ ጥቁምታ የሰጠም ነው፡፡ ለፈተና ከተቀመጡ 845 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ 50 ከመቶና ከዛ በላይ ያመጡት 27,267 ተማሪዎች ናቸው። ይህ ማለት 3.2 ከመቶ ብቻ ማለት ነው፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር 422, 500 ሺህ ተማሪ ከ26 በታች ነው ያመጡ መሆናቸው ነው፡፡ 649 በተፈጥሮ ሳይንስ የዘንድሮው ከፍተኛ ውጤት ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 533 ተመዝግቧል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመግለጫቸው ፤ ‹ከዚህ ፈተና አንድ ሊያስደነግጠን የሚገባ ነገር..ሲሉ ከተፈተኑት ጠቅላላ ተማሪዎች ውስጥ 50 ከመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ከ26 ከመቶ በታች ማምጣታቸውን ተናገረዋል፡፡ የሚኒስትሩ ንግግር ስሜት ያዘለ መሆኑ የሚያነጋግር ባይሆንም ከመግለጫው በኋላ ብዙዎቻችን የተጋራነው ሆኗል፡፡

ለትዝብትም ሆነ ለቀጣይ እንቅስቃሴያችን እንዲረዳን በዘንድሮው የተማሪዎች ውጤት ላይ ተወቃሽና ተወዳሽ የሆኑ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሠረት ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች እንዳለ ያሳለፉ በቁጥር አምስት የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው የተጠቆመ ሲሆን እንደዚሁም ሌሎች አምስት ትምህርት ቤቶች 95 ከመቶ የሚሆኑ ተማሪዎቻቸውን እንዳሳለፉ የሚኒስትሩ መግለጫ ያሳያል፡፡ በዛው ልክ አንድም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች በቁጥር አይለው መገኘታቸው ከስጋታችን ጎን ለጎን ቀጣዩን የቤት ሥራችንን እንድንቃኝ መንገድ የጠረገ ሆኗል፡፡

ይሄን ስጋት ወደአሃዝ ስንቀይረው በሀገሪቱ ካሉ የ12ኛ ክፍል ፈተና ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 42.8 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አላሳለፉም፡፡ ከሶስት ሺህ የሚልቁ ትምህርት ቤቶች አንድ ተማሪ ማሳለፍ አለመቻላቸው ምን አይነት ጥያቄን እንደሚያሳነሳ ለጊዜው እርግጠኛ ባልሆንም በነዚህ ትምህርት በቤቶች ላይ ያለው የአስተዳደር፣ የመማር ማስተማር ፣ የተማሪዎችና የወላጆች ህብረት ሥርዓትና ሂደት ምን እንደሚመስል መገመት አይከብድም፡፡

አስር የሚሆኑ በዘንድሮው የተማሪዎች ውጤት ላይ ከፍተኛ አፈጻጸም ያሳዩ ትምህርት ቤቶች ተሞካሽተዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ በአንድ አይነት ሥርዓት፣ በአንድ አይነት የትምህርት ፖሊሲ እየተመሩ ምንም አይነት ተማሪ ካላሳለፉት ትምህርት ቤቶች መለየታቸው ለቀጣዩ መንግሥታዊ ርምጃም ሆነ ግምገማ እንደአንድ መነሻ ሃሳብ በመሆን የሚያገለግል ነው፡፡

የዘንድሮው ፈተና ካለፈው የሚለየው ከኩረጃና ከሌብነት ነጻ መሆኑ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ራሱ የትምህርት ሚኒስቴር በመግለጫው አረጋግጦታል። እርግጥ ነው ጥብቅ ቁጥጥር በኖረ ቁጥር እንዲህ አይነት እውቀትንና በራስ መተማመንን መሠረት ያደረጉ የተጣሩ ውጤቶች መኖራቸው ገሀድ ነው፡፡ ያለፈው ጊዜ ከቁጥጥር ማነስ የተነሳ በጣት የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ጥሎ ጠቅላላ በሚባል ደረጃ የሚያሳልፍ ነበር፡፡

አምናና ዘንድሮ በተለይ በትምህርቱ ረገድ ሁለት አይነት ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ከሚወድቀው ይልቅ የሚያልፈው የበዛ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ከሚያልፈው ይልቅ የሚወድቀው እየበዛ ነው። ለምን? ብለን ስንጠይቅ ‹የሥርዓት ለውጥ› የሚል ቀላልና ቀጥተኛ መልስ ነው የምናገኘው። አዲሱ የትምህርት ሚኒስትር ሥርዓት በሀገርና በትውልዱ ላይ አዲስ አስተሳሰብን ከአዲስ ሥነልቦና ጋር የፈጠረ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

የእኛን ጊዜ የተማሪነት ቆይታ ባስታውስ እንኳን ከተፈተነው ሶስትና አራት ሺ ተማሪ ውስጥ አራት እና አምስት ነበር የሚወድቀው፡፡ ዘንድሮ በተቃራኒው እብቁን ከገለባ በሚለይ ሥርዓት በሚሉት የለውጥ ወንፊት እየተነፋ ባለእውቀቱን ከኮራጁ የሚለይ አዲስ ፖሊሲ ላይ ነን፡፡ ሂደቱ ይቀጥላል በምንም አይነት መመዘኛ ቢታይ እንዲህ አይነቱ የለውጥና የሥርዓት ተሀድሶ ወደ ኋላ የሚቀለበስ አይደለም። እንደእኛ ሀገር ብዙ ትውልድ ባለባትና ከድህነት ለመውጣት በሚታትር ማህበረሰብ ውስጥ ችግር ፈቺነትን መሠረት ያደረገ እውቀትና መርህ ያሻል፡፡

ያለፈውም ሆነ የዘንድሮው ውጤት ነባሩን ትተን በጀመርነው የለውጥ ሥርዓት እንድንቀጥል የሚያበረታ ነው፡፡ ብዙ ሥራዎችም እንደሚቀሩን ጥቁምታ የሰጠም ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ተማሪዎች ከመጠበቅና ከኩረጃ ነጻ የሆነ ራስን የመቻል መሠረት ይዘው እንዲያድጉ ከወዲሁ አዲስ አሠራርን እንድንዘረጋ እድል የሚሰጠን ነው፡፡ ባለፈው ሥርዓት ያለፈ ታሪክ ትተን በአዲሱ ሥርዓት አዲስ ታሪክ የምንጽፈበት የለውጥና የንቃት ንቅናቄ መነሻም ነው፡፡

ከምናየው ተነስተን ተማሪው ራሱን ችሎ ከክፍል ክፍል የሚሸጋገርበትን፣ መምህሩ ደግሞ ለተማሪው በሚመጥን መልኩ ራሱን በእውቀት የሚያጎለብትበትን ሁኔታ እንዲፈጥር የአቅጣጫ ለውጥ የምናደርግበት የሽግግር ርምጃ ነው፡፡ በእንዴትም ዝቅታ ውስጥ እውቀት የቀና ማለት ብርታት ነው፡፡ ዓላማችን ቀና ማለትና ነውሮቻችንን አጽድተን በምክንያታዊነት መጓዝ ከሆነ የእውቀት አፍ ያስፈልገናል፡፡ የእውቀት አፍ ደግሞ ከበጎ ሥርዓት የሚጀምር፣ በራስ ማመንን መሠረት ያደረገ እሳቤ ነው፡፡

ኩረጃ ወይም ሌብነት ማንንም ፊተኛ አድርጎ አያውቅም፡፡ በትምህርት ጥራት ማነስ ብዙ ዋጋዎችን ከፍለናል፡፡ ይሄ ጊዜ በራስ እውቀት ለብዙሃን የምንተርፍበት የብርታት ጊዜ ነው፡፡ ትላልቅ ሀገራዊ ሃላፊነቶች ከተማሪነት የሚጀምሩ ናቸው፡፡ ትላልቅ ማህበራዊ መስተጋብሮች መነሻቸው ተማሪነት ነው። ከወዲሁ በራሳችን ራሳችንን መምራትና ማሻገር ካልቻልን ነገ ላይ ለሀገር ሸክም ከመሆን ባለፈ ሌላ እጣ ፈንታ አይኖረንም ፡፡

ትውልድ የሀገር መልክ ነው፡፡ ትውልዱ ከተበላሸ የምትረባ ሀገር አትኖርም፡፡ ትውልዱ እንዲረባ እውቀትና ግብረገብነት የመጀመሪያዎቹ የጨዋነት ሚዛኖች ናቸው፡፡ በዚህ ሚዛን ተመዝነን ስንከብድና ስንበረታ ነው ለሀገራችን ተስፋ የምንሆነው፡፡ የትኛውም ዜጋ ሀገሩን ከሚጠቅምባቸው መንገዶች ውስጥ እውቀት የመጀመሪያው ነው፡፡ ሰነፍ ሰው ሸክም ከመሆን ባለፈ ሀገሩን መጥቀም አይችልም፡፡

ዘንድሮ በተስተዋለው የተማሪዎች የውጤት ማሽቆልቆል ሳቢያ ተማሪዎችን ለመካስና ሁለተኛ እድል ከመስጠት አኳያ ዘንድሮም እንደአምናው የሬሜዲያል ፕሮግራም መኖሩ የሚኒስቴሩ መግለጫ አስታውቋል፡፡ በቀጣይ ሂደትም እውቀትና የትምህርት ጥራትን ታሳቢ ባደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመመራት በመማር ማስተማር ሥርዓቱ ላይ አዲስ አብዮት እንፈጥራለን ባይ ነኝ፡፡

ባለፈው ጊዜም ሆነ በዘንድሮው መግለጫ በትምህርቱ ዘርፍ ብዙ እንደሚቀረን አይተናል፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር መሪነት በተካሄደው የአጥኚ ቡድን ውጤት ሀገራችን በመማር ማስተማሩ ዙሪያ ምንም እንዳልሰራች እና መንግሥትም ሃላፊነቱን እንዳልተወጣ በግልጽ ያሳየ ሆኗል፡፡

በቀጣይም የምንሰማቸው ጥናቶች ነውሮቻችንን በይበልጥ የገለጡ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ሀገር በእውቀት ካልተገነባች በምንም ብትገነባ ልክ አይመጣም፡፡ የእውቀት አፎች ሰላምን ከመስበክና ፍቅርን ከመዘመር አንጻር ዋጋቸው የት የሌለ ነው፡፡ የጥበብ ልሳኖች ሀገር ከመለወጥ ጎን ለጎን አንድነትንና አብሮነትን በመፍጠር ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡

ያለፍንባቸው እንቅፋቶች መልሰው እንዳያደናቅፉን ሁነኛ መመላለሻ ማሰናዳት አስፈላጊ ነው፡፡ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ጥናትና መረጃ መሠረት ሀገሪቱ ካሏት 47 ሺህ ገደማ ትምህርት ቤቶች 99 በመቶዎቹ ለመማር ማስተማር ሥርዓቱ አመቺ እንዳይደሉ ባለፈው መግለጫ ተጠቁመዋል፡፡ በተሠራው ግምገማ መሠረት አራት ትምህርት ቤቶች ብቻ መስፈርቱን የሚያሟሉ ሆነው መገኘታቸው ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ የባሰው ደግሞ 86 በመቶ የአንደኛና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 71 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፍጹም ከደረጃ በታች መሆናቸው ሌላው አስገራሚው ነገር ነው፡፡ እዚህ ጋ ብዙ ስጋት አለን፡፡ ትምህርት ቤት ለተማሪ ምቹና በቂ ካልሆኑ ዓላማቸው ምንድነው? ተማሪ ተምሮ ያላወቀበትና ውጤት ያላመጣበት ትምህርት ቤትና የትምህርት ካርኩለም ለሀገር ፍሬ ካልሰጠ መኖሩ ትርጉሙ ምኑ ላይ ነው? ይሄ ብቻ አይደለም በተማሪ ውጤት ላይ ከምንምነት እስከከፍተኛ ልዩነት የሚታይባቸው ትምህርት ቤቶች መነሻቸው ምን እንደሆነ ከጥናት ጋር ምላሽ ያሻዋል፡፡

በዚህ አይነቱ መንገድ ትውልዱን በእውቀት ካላሻገርነው እንደሀገር አደጋ ላይ መውደቃችን በየማይቀር ነው፡፡ ድህነትና ኋላቀርነት እንደመዥገር ለተጣበቁባት ሀገር፣ ማጣትና ጉስቁልና አንገት ላስደፉት ህዝብ ከእውቀት መር ሥርዓት ውጪ ዋስትና የለም፡፡ አሁናዊ ተግዳሮቶቻችን ያለፈ የትምህርት ሥርዓታችን ክፍተቶች ማሳያ ነው፡፡ በኩረጃ ተምሮ መምህር የሆነ አስተማሪ፣ በኩረጃ ተምሮ የተመረቀ ተማሪ ለሀገር ሸክም ከመሆን ባለፈ ምን ፋይዳ አለው?

የከፍታዎቻችንን ማማ በእውቀት ካልማገርን ችግሮቻችንን መብለጥ አንችልም፡፡ መነሻና መድረሻውን ጥራት ከእውቀት ጋር ያደረገ የመማር ማስተማር ሥርዓት ያስፈልገናል፡፡ ከራሳችን አልፈን ከመጪው ዘመን ጋር ልንወዳደር የምንችለው እንዲህ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ዘመኑ የዝማኔ ነው፡፡ በየእለቱ እውቀትን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ ፈጠራዎችን፣ ግኝቶችን እየሰማንና እያየን ነው፡፡ የእኚህ ሁሉ ትሩፋቶች መነሻ ደግሞ እውቀት የሚሉት ሃይል ነው፡፡

ወዳለፈው ማየት ትተን መጪውን እንዴት ሸጋ ማድረግ ላይ እንወያይ፡፡ የትምህርት ዘርፍ በሁሉም የሀገር ጉዳይ ላይ ከፊት የሚመጣ ሰፊ ዘርፍ ነው። እንደሀገር ተስፋዎቻችን ወደመሆን እንዲመጡ በጀመርነው ጥራትን መሠረት ባደረገ ሥርዓት መቀጠል አማራጭ የሌለው ግዴታችን ነው፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You