በሀገሪቱ በግለሰቦችም ሆነ በተቋማት ደረጃ የተለያዩ የቁንጅና ውድድሮች እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አንዳንድ ተቋማት በየዓመቱ በመደበኛነት የቁንጅና ውድድርን ሲያዘጋጁ እየተመለከትን ነው፡፡
ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ አንዱ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የቁንጅና ውድድሮችን ማካሄዱን የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኢፈባስ አብዱልወሃብ ይናገራሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ኮሚሽኑ የዘንድሮውን ጨምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት በየዓመቱ ‹‹ቪዚት ኦሮሚያ›› በሚል ርዕስ የቁንጅና ውድድር አካሂዷል፡፡ የውድድሩ ዓላማ የኦሮሚያ ክልልን የቱሪዝም መስህቦችና መዳረሻዎች ለዓለም ማስተዋወቅ ነው፡፡ በየዓመቱ የኦሮሚያ ክልል ቆንጃጅቶች ይወዳደራሉ፤ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡትም የገንዘብና የተለያዩ ማበረታቻ ሽልማቶች ይሰጧቸዋል፡፡ ከተወዳዳሪዎቹ አንደኛ የወጣችው አሸናፊ ቆንጆ ደግሞ የኦሮሚያ ቱሪዝም አምባሳደር ሆኗ የክልሉን የቱሪዝም እምቅ ሀብት፣ መስህቦችና መዳረሻዎችን ለዓለም እንድታስተዋውቅ ይደረጋል፡፡
የቁንጅና ውድድሩ በየዓመቱ የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን የውድድሩ አሸናፊ የኦሮሚያ የቱሪዝም አምባሳደር ሆና የምታገለግለው ለአንድ ዓመት ያህል ነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም የኦሮሚያ ክልልን የቱሪዝም ሀብቶችና መዳረሻዎች የተለያዩ መድረኮችን (ፕላትፎርሞችን) በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያ፣ በሜኒስትሪም ሚዲያ፣ የምታስተዋወቅበትን እድል ትፈጥራለች።
ይህ ደግሞ ወጣቶች ስለ ቱሪዝም ያላቸው ግንዛቤ እንዲዳብር፣ ውበታቸውን እንዲጠብቁ መነሳሳት እንዲፈጠር እና ሌሎች እነሱን አርአያ አድርገው እንዲበረታቱ እድል የሚፈጥር እንደሆነም አቶ ኢፈባስ ይገልጻሉ፡፡ በመላው ኦሮሚያ ያሉ ሴቶች ተነቃቅተው ሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያ ለመሆን ለመወዳደር የሚችሉበት ሰፊ
እድል ይፈጥርላቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ውድድሩ ከባለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በመስከረም ወር የዓለም ቱሪዝም ቀን ከሚከበርበት መስከረም 17 ጀምሮ ባሉት አንድ ወይም ሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ለውድድሩ የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ ተወዳዳሪዎችም ምዝገባውን ያደረጉት በኦንላይን እንደሆነ ነው የተናገሩት። ተወዳዳሪዎቹ ባሉበት ሆነው ማመልከት እንደቻሉ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ በውድድሩ መሳተፍ ለሚፈልጉ ለወጣት እንስቶች ሰፊ እድል መፍጠሩን ነው ያስረዱት፡፡
በዘንድሮው ውድድር ላይ በርካታ ተወዳዳሪዎች መሳተፋቸውን አስታውሰው፤ በቁንጅና ውድድር ላይ የካበተ ልምድ ባላቸው ከተለያዩ ተቋማት በተጋበዙ አራት ዳኞች አማካይነት በመስፈርቱ መሠረት ውድድሩ መካሄዱን ገልጸዋል። ከተመረጡት ከ25 እስከ 30 የሚሆኑት ከየአካባቢያቸው ወደ አዲስ አባባ እንዲመጡ መደረጉን ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባም በውበት አጠባበቅና በሞዴሊንግ ዙሪያ የተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን፤ ፈተናውን ያለፉ 15 ተወዳዳሪዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል። ለውድድሩ ከቀረቡት 15 ተወዳዳሪዎች መካከልም የመጨረሻዎቹ አምስት ተወዳዳሪዎች ተለይተው ከአምስቱ ተወዳዳሪዎችም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ያገኙ ተወዳዳሪዎች መመረጣቸውን አብራርተዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በውድድሩ ከኦሮሚያ ክልል ካሉት ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ አሸናፊዎች የኦሮሚያን የቱሪዝም መስህቦችና አካባቢዎች የማስተዋወቅ ኃላፊነት የሰጣቸው ሲሆን፣ ትልቁ ኃላፊነት የሚጣለው ግን አንደኛ በወጣችው አሸናፊ ነው፡፡
አንደኛ የወጣችው ተወዳዳሪ በኮሚሽኑ የሚያዘጋጁ ማስታወቂያዎችን በመሥራትና የጉዞ ፕሮግራሞች በማስተዋወቅ የክልሉን የቱሪዝም ሀብቶች የምታስተዋውቅ ይሆናል፡፡ ኮሚሽኑ የተለያዩ ፕሮግራሞች ይኖሩታል፤ ቤተሰባዊ ጉዞ (ፋሚላይዜሽን ትሪፕ) በተሰኘው ፕሮግራም አሸናፊዋ የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችን ለኤምባሲዎች፣ ለዲፕሎማቶች፣ ለሚዲያ ባለሙያዎች፣ ለቲክ ቶከሮች፣ ለዩቲዩበሮችና ለመሳሰሉት ታስተዋውቃለች፡፡ በሚዘጋጁ የጉብኝት ፕሮግራሞች የቱሪዝም ሀብትነታቸውን በደንብ ተረድታ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ይጠበቅባታል። በዚህ በኩል አሸናፊዋ የበለጠ ኃላፊነት ቢኖርባትም ሦስቱም አብረው የሚሠሩ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡
በሦስቱ ተከታታይ ዓመታት በተካሄደው የቁንጅና ውድድር የመጀመሪያው ዓመት አሸናፊ የነበረችው ሀሊማ አብዱልሸኩር ከባሌ ዞን አዳባ አካባቢ የመጣች መሆኗን አስታውሰው፤ የሁለተኛው ዓመት አሸናፊ ደግሞ ሀዊ ማቲዩስ ከወለጋ ደምቢዶሎ አካባቢ የመጣች እንደሆነ ገልጸዋል። የዘንድሮዋ አሸናፊም ማህደር ፍቃዱ ከአርሲ ዞን በቆጂ አካባቢ እንደሆነች አመላክተዋል፡፡
የእስካሁኑ አሸናፊዎች ዓመቱን በሙሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ የዘንድሮዋ አሸናፊ የሆነችው ማህደርም ባለፈው ሳምንት ከተከበረው ከኢሬቻ በዓል አንስቶ የቱሪዝም መስህቦችንና መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ሥራዋን ጀምራለች ነው ያሉት፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በየዓመቱ ‹ሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያ› ተብላ የምትመረጠው እንስት የኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም አምባሳደር በመሆን የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስተወዋወቅ፣ ሆቴልና ሆስፒታሊቲ አገልግሎትን የማዘመን፣ የጉዞና አስጎብኚ ድርጅቶች ያላቸው ፓኬጅ ኦሮሚያ ላይ የመሸጥ እና ጉብኚዎችን እንዲያመጡ ማድረግ እና የመሳሰሉ ሥራዎች መሥራት ይጠበቅባታል። ከዚህም ባሻገር ከቱሪዝም ጋር ተያያዥነት ባላቸው ለቱሪዝም ሥራዎች አጋዥ በሆኑ የአካባቢ ጽዳትና ውበት ሥራዎች ላይ የህብረተሰብ ንቅናቄ ሥራዎችን ትሠራለች፤ ታስተምራለች፤ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፈጠር ሥራዎችንም ታከናውናለች፡፡
የቁንጅና ውድድር አሸናፊዎቹ ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ከኮሚሽኑ ጋር አብረው የሚሰሩ ሲሆን፤ የተለያዩ እድሎች የሚፈጠርላቸው እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች ማስታወቂያዎች ለአብነትም (ለባንኮች፣ ለከተሞች እና ለመሳሳሉ ተቋማት) የመሥራት እድል እንደሚያገኙም ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ የማስታወቂያ ሥራዎች ለራሳቸው የሚሆን የገቢ ከማግኘት ባሻገር ለወደፊት የሥራ እድል የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸውም ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም