ወላጆቿ ካወጡላት በዛወርቅ አስፋው ከሚለው መጠሪያዋ እኩል “የትዝታዋ ንግሥት” የሚለው ሕዝብ የሰጣት መጠሪያዋ ሆኗል። በቅርቦቿ ዘንድ መጠሪያዋ በዝዬ ነው። እሷም ታዲያ “በሙሉ ስሜ በዛወርቅ ሲሉኝ ሌላ ሠው የጠሩ ይመስለኛል” ትላለች። ትውልዷ በአዲስ አበባ ሲሆን፣ ቅድስት ማርያም ሰፈር አፈር ፈጭታ ለቁም ነገር የበቃችበት ነው። ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ደግሞ እውቀት የቀሰመችበት የእውቀት ቤቷ። ያኔ ለሰፈሯ ቅርብ ከነበረው ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን የማትጠፋ መንፈሳዊት ልጅ ነበረች።
በቤተክርስትያን መንፈሳዊ ዝማሬዎችን የምታቀርብ ድምጸ መረዋ ናት። ለመንፈሳዊ ነገር የምትሳብ ታዳጊ ብትሆንም በሬድዮም ሆነ በካሴት የሰማችውን አለማዊ ዘፈን ወዲያው በመያዝና በማንጎራጎርም ጎበዝ ነበረች። የክብር ዘበኛ አባል የነበሩት እነ ጥላሁን፣ እነ ብዙነሽ በሚለማመዱበት አጋጣሚ ከሰፈር ልጆች ጋር በመሆን በአጥር ተንጠላጥለው ትመለከት ነበር። ከዛ የዘለለ ለሙዚቃ የተለየ መሻት አልነበራትም። የድምጿን ችሎታ የምታውቅበት ሁኔታም አልነበረም። የማርያም ቤተክርስትያን ዘማሪ ናት፤ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ከቤተክርስትያ የማትጠፋ ናት።
በዘመነ ደርግ ወጣቶች “ንቃት″ የተሰኘ የፖለቲካ ትምህርት መከታተል፤ ወይም፣ በኪነት ታቅፎ ሀገርን ማገልገል የውዴታ ግዴታ ነበር። እሷም ከቤተክርስትያን ዝማሬ በተጓዳኝ በአካባቢዋ በሚገኝ ኪነት ታቅፋ አብዮታዊ መዝሙሮችን መለማመድ ጀምራ ነበር። በወቅቱ ሁሉም ለሀገሩ በሚችለው ማገልገል ግዴታው ነበር። “ለእናት ሀገር ጥሪ″ የተሰኘ ትልቅ የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ዝግጅት በጃን ሜዳ ለማካሄድ በመንግሥት አካላት ሽርጉዱ ጦፏል። በመድረኩ አንጋፋ ሙዚቀኞችና በመሃል የቀበሌ ኪነትንም ለማሳተፍ ተወስኖ የእነ በዛወርቅም ኪነት መዝሙር ልምምዱ ላይ በርትተዋል።
እነ በዛወርቅ በመድረኩ ተቀባይ ሊሆኑ ሲታሰብ፤ በጃን ሜዳው መድረክ ከኪነታቸው ዋና ዘማሪ እንዲሆን የተመረጠው ወንድ ነበር። እነ በዛወርቅ እሱን በማጀብ ልምምድ አድርገዋል። እሱም ዋና ድምጻዊ ሆኖ ልምምዱን አጠናቋል። በዘመኑ ያለ ግምገማ ሥራዎች ለመድረክ አይቀርቡም ነበርና የሚያቀርቡት መዝሙር ለመድረኩ የሚሆን መሆኑን የሚያረጋግጡ ገምጋሚዎች በአዳራሹ ተሰየሙ። ሆኖም ዋና ዘፋኙ መዝሙሩ ለገምጋሚዎች ቀርቦ በሚገመገምበት መድረክ ላይ ሳይገኝ ይቀራል። እሷም እሱን ተክታ የተለማመዱትን የክብር ዘበኛ የአብዮት ዘፈን አቀረበች፤ ከገምጋሚዎችም በመድረኩ እንዲቀርብ ይሁንታን አገኘ።
የተዘጋጁበት ቀን ደረሰ፤ በጃንሜዳው ዝግጅት የክብር ዘበኛም ዝግጅቱን የሚያቀርብበት ነበር። እነ ጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለና ሌሎችም አንጋፋ ድምጻውያን በመድረኩ ታዳሚን ያዝናናሉ። በመሃል ዋና ድምጻውያኑን ለማሳረፍ የቀበሌ ኪነት ዝግጅቱን እንዲያቀርብና ለሀገር የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ታሳቢ ያደረገ ነው። ሆኖም ተራቸው ቢደርስም የቡድኑ ዋና ድምጻዊ ተብሎ የተሾመው ልጅ ሳይመጣ ቀረ። በዛወርቅ እንደ ግምገማው ቀን ሁሉ ዋናው መድረክ ላይም ለታዳሚዎች በብቃት መዝሙሩን አቀረበች።
ወዛደር ጓዴ ተነሳ
በሬው ገበሬው እረስ
ጠላትህን ለመደምሰስ
የእናት ሀገር ጥሪ ላይ የተሳተፉ ለሀገር ለዋሉት ውለታ ምስጋና ይሆን ዘንድ በብሔራዊ ትያትር የተዘጋጀ ዝግጅት የሚታደሙበት ነጻ መግቢያ ተሰጣቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ትያትርን የምታይበት አጋጣሚ ተፈጠረ። የመድረኩ ትልቀነት፣ መጋረጃው፣ መብራቱ ሁሉ ነገር ደስ ብሏታል። ከምንም በላይ የማይረሳት ግን በወቅቱ እውቅ ድምጻዊ የነበረችው ጸሀይ እንዳለ የወታደር መለያ ለብሳ መድረክ ላይ በሚያምር ድምጿ “በጠረፍ ላይ ይሁን እኔስ መቃብሬ″ እያለች ስታዜም ተማርካ እዚህ መድረክ ላይ እኔም አንድ ቀን በዘፈንኩ የሚል ምኞት አደረባት። ምኞቷ ተሳክቶ ብሔራዊ ትያትር ለረዥም ዘመን ያገለገለችበትና አሁንም ድረስ በደግ የምታነሳው መስሪያ ቤቷ ሆኗል።
ብሔራዊ ትያትር ማስታወቂያ ማውጣቱንና ሄደው እንዲሞክሩ እነ በዛወርቅ ለሚገኙበት የኪነት አባላት መረጃው ይደርሳቸዋል። ይሄ የብሔራዊ ትያትር ማስታወቂያ በየቀበሌው በየናይት ክለቡ ተሰምቶ ነበርና በርካታ ተመዝጋቢዎች ይመዘገባሉ። ከበርካታ ተመዝጋቢዎች መሃል ለማጣሪያ 75 ሰዎች አለፉ። በዛወርቅ አብረዋት የተመዘገቡ ጓደኞቿ ማጣሪያውን ሳያልፉ ብቻዋን ብታልፍም የማጣሪያ ፈተናው ቀን የብዙነሽ በቀለን፦
ምንም ሳላስበው ውጥን ሳይኖረኝ
የሚያስለቅስ ፍቅር በድንገት ያዘኝን
በግሩም ሁኔታ ተጫወተች። ፈተናው በዚህ ብቻ አልበቃም፤ ዶሬሚፋ በፒያኖ እንድትል ተነገራት፤ ከሙዚቃ ትምህርት ጋር ዝምድናም ባይኖራት ያሉትን ደገመችላቸው። ሲቀጥል ውዝዋዜ እንድታሳይ ተጠየቀች፤ ውዝዋዜ እስከዚህም ብትሆንም የአቅሟን፣ የምትችለውን ሞከረች። በዚህ ሁሉ ፈተና ተጣርተው ካለፉ፤ ብሔራዊ ትያትርን ለመቀላቀል ከተመረጡ ተወዳዳሪዎች መሃል ስሟ ተካተተ።
አዲስ ዓመት በብሔራዊ ትያትር በተለየ ድባብ የሚጠበቅ ተናፋቂ በዓል ነው። ታዲያ የትያትር ቤቱ ዝግጅት የሚጀምረው አስቀድሞ ነው። በዛወርቅ ትያትር ቤቱን ስትቀላቀል ለአዲስ ዓመት ሦስት ወር ይቀረው ነበር። ታዲያ ሦስት ወሩን ሙሉ ሌት ተቀን የውዝዋዜ ሥልጠና ተከታትላለች። ተናፋቂው አዲስ ዓመት ሲደርስ በውዝዋዜም ሆነ በድምጻዊነት መድረኩን ተቆጣጠረች። በወቅቱ ትያትር ቤቶች ሁለገብነት መርሃቸው ነበርና እሷም በድምጻዊነቱም ሆነ በውዝዋዜ ገፋችበት። ሆኖም የባህል ክፍሉ ውስጥ ከሌሎች ዜመኞች ጋር በጋራ እንድታዜም መደረጉ ጎልታ እንድትወጣ አላደረጋትም ነበር።
በ1970 ትያትር ቤቱን ስትቀላቀል ምንም እንኳን የተለየ ድምጽ ቢኖራትም ቅጥሯ የባህል ክፍል፤ ምድቧም ውዝዋዜ ነውና ዋና ሥራዋ የባህል ተወዛዋዥነት ሆነ። እሷ በወቅቱ ትያትር ቤቱን ለመቀላቀል የነበራትን ጉጉት መለስ ብላ ስታስታውስ “ጭቃ ረጋጭም ቢያደርጉኝ እሰራ ነበር” ትላለች። በትያትር ቤቱ ወደ መደበኛ ዘፋኝነት ለመሸጋገር አራት ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሏታል።
ወደ ሙዚቃ ሕይወት ስትቀላቀል ለረዥም ጊዜ ከአባቷ ተደብቆ ነበር። በኋላ ላይም ከሰሙ በኋላ ደስተኛ አልነበሩም። በዚህ የተነሳም ከእናቷ ጋር ተመካክረው እሷን ሲያይዋት እንዳይናደዱ ለረዥም ጊዜ አንድ ቤት ቢኖሩም እሳቸውን ፊት ለፊት ሳትጋፈጥ ቆይታለች። የመጨረሻ ልጃቸው ስለሆነች ከሚሳሱላትና “እናቴነሽ” እያሉ በፍቅር ከሚጠሯት አባቷ ጋር ሙዚቃ አኮራርፏት ነበር። ሆኖም በመጀመሪያ ወር ደሞዟ ለአባቷ ነጠላና ጭራ ገዝታ ክሳቸዋለች።
በትያትር ቤቱ የልቧን መሻት በድምጽ የምታወጣበት በቂ እድል እያገኘች አልነበረም። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች አንድ ቀን ከብሔራዊ ትያትር ሥራዋን ጨርሳ ወደ ቤት ለመሄድ በዝግጅት ላይ ሳለች አንድ ባልደረባዋ “ነይ እስቲ ወደ ካሳንቺስ እንሂድ” አለቻት። ካዛንቺስ ምን እንዳለ ሳይገባት ባልደረባዋን ተከትላ ካሳንችስ የሚገኝ የባህል ቤት ደረሰች። ሁኔታውን ካየች በኋላ እንደ ነገሩ በማሲንቆ ታጅባ ትዝታን አዜመች። በሽልማት በርካታ ብሮች ጎረፉላት።
ችግሩ ታዲያ ያንን ብር ምን ብላ እቤት ትስጥ። በአንድ ምሽት በሽልማት ያገኘችውን 700 ብር ለእናቷ መስጠት ፈልጋለች፤ ግን ብሰጣት ሌላ ነገር የጀመርኩ መስሏት ትሰጋለች ስትል ስለፈራች ግራ ተጋባች። በማግስቱ መስሪያ ቤት ወስዳ አስቀምጭልኝ ስትል ለአንድ ባልደረባዋ ሰጠቻት። በማግስቱ «ነይ» ብትባልም ያገኘችውን ብር የምታደርግበት ቸግሯታልና እምቢ አለች። በሂደት ብሩም ጥሟታልና ቀጠለችበት።
በቀጣይ ድምጻዊ ከተማ መኮንንም እዛው ቤት ሥራ በመጀመሩ የሙዚቃ ጥምረታቸውም ሰመረ። ችግሩ ታዲያ ያኔ በዛወርቅ የምሽት ሥራ ትሰራለች የሚል ወሬ ተዛመተ። የምሽት ሥራ መስራት በወቅቱ በትያትር ቤቱ አይፈቀድም ነበርና የትያትር ቤት ሰዎች እሷ የምትሰራበት ቤት መጡ ከተባለ እሷ ጓዳ ትደበቅ ነበር። በትያትር ቤቱ በውዝዋዜም ስታጅብ አብራ ታቀነቅን ነበርና ይህን ችሎታዋን የሚያውቁ “በዛወርቅ እኮ ድምጽ አላት፤ ለምን አትዘፍንም?” ሲሉ ለአለቆች አደረሱ። «እስቲ ትሞክር»በማለት በወቅቱ አለቃ የነበረ ሰው የጻፈውን ግጥም እስቲ በይው ብሎ ወረቀቱን አቀበላት። አይ ወረቀት እንኳን ይዤ አልወጣም፤ ሌላ የማውቃቸው ግጥሞች አሉ ብላ ዘፈነች።
በትያትር ቤቱ ቅጥሯ በኮንትራት ነበር። ለዛም ይሁን በወቅቱ እጥረት ያለው በተወዛዋዥነት ይሁን ግልጽ ባይሆንም በቋሚነት የምትሰራው ከድምጽ ይልቅ ውዝዋዜ ላይ ነው። ይህ እውነት ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ኮንትራቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ቀጠለ። ከዛ በአዲስ ተወዳድራ በድምጻዊነት ትያትር ቤቱን ተቀላቀለች። በትያትር ቤቱ በድምጽ የምታገለግልበት ቋሚ መድረክ ባይመቻችም ችሎታዋን ባዩ ሰዎች አማካኝነት ለዘማች ቤተሰቦች በኢትዮጵያ ሬድዮ በተዘጋጀ ዝግጅት ላይ ሥራዋን እንድታቀርብ እድል ተፈጠረ።
በመድረኩ ላይ ከበዛወርቅ በተጨማሪ ድምጻዊ መሀሙድ አሕመድ፣ ድምጻዊ ከተማ መኮንንና ድምጻዊ ኤልያስ ተባበል ተመርጠው ተዘጋጁ። በዝግጅቱ ላይ በዛወርቅ “አንተየ ሎሚ ነህ ወይ”ን ለብቻዋ እሷ “የትዝታ ንግሥት” ስትባል “የትዝታ ንጉሥ” ከተባለው መሀሙድ አሕመድ ጋር ተጣምራ “አማሌሌ”ን በጋራ አቀነቀኑ። ምንም እንኳን መድረኩ የተዋጣ ቢሆንም በመድረኩ የተጫወቱት ዘፈን ከነሱ እውቅና ውጪ ተቀድቶ በሙዚቃ ቤት በኩል ለገበያ ቢቀርብም ምንም ጥቅም ባለማግኘታቸውና ፈቃደኝነታቸው ባለመጠየቁ ቅሬታ ፈጥሮባታል።
153 ብር በብሔራዊ ትያትር ቤት ለረዥም ጊዜ የተከፈላት ደሞዝ ነው። ሆኖም ልምምድ ሲኖር አራት ብር የንጽህና መጠበቂያና የላብ መተኪያ ስለሚታሰብልን ለዛን ጊዜ ኑሮ በቂ ነበር ትላለች። በተለይ ምሽት ቤት ስትሰራ ድምጿ የተለየ ውበትና ጉልበት ስላለው በሸላሚዎች “ከበቂ በላይ″ የሚባል ሽልማት ይበረከትላት ስለነበር ኑሮዬ ጥሩ ነበር ትላለች። በተጨማሪም ሰርግ፣ እንዲሁም የተለያዩ ዝግጅቶች ትሰራ ስለነበር በሀገሯ ጥሩ ኑሮ ነበራት። ምንም እንኳን የሚከፈላት ክፍያ አነስተኛ የነበረ ቢሆንም ትያትር ቤቱ ብዙ ነገር ያስተማራትና ባለውለታዋ መሆኑን ትናገራለች። የ153 ብር ደሞዟ ከሀገር ልትወጣ አካባቢ ወደ 230 ብር ከማደጉ ውጭ ለረዥም ጊዜ በተቀጠረችበት ደሞዝ ሠርታለች።
ድምጻዊቷ “በሀገሬ እያለሁ ከብሔራዊ ትያትር ውጭ ክለብ፣ ሠርግ፤ እንዲሁም፣ የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ እሰራ ስለነበረ ኑሮዬ ጥሩ ነበር” ትላለች። ለዚህም ከሀገር ወጥቶ የመቅረት ሀሳብ እንዳልነበራት ትናገራለች። ከሀገር አወጣጧ በሀገረ ካናዳ ሥራዋን አቅርባ ለመመለስ ነበር። በወቅቱ የሁለት ዓመት ልጇን ጥላ ከሀገር የወጣችው ትንሽ ሰርታ ጥሪት ቋጥራ ለመመለስ ነበር። ካናዳ ሥራዋን ስትጨርስ በሀገረ አሜሪካ፣ ቦስተን በተካሄደው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እግር ኳስ ግጥሚያ ላይ ከጥላሁን ገሠሠ፣ ከመሀሙድ አሕመድ፣ ከጸሀዬ ዮሀንስ ጋር በመሆን ሰራች። ከአሜሪካ ተመልሳ ወደ ካናዳ በወሰዳት በኪዊን ኦፍ ሼባ ሬስቶራንት ሰባት ወር ሰርታለች። በካናዳ የነበራት የሥራ ስምምነት ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ወቅቱ ሰላም ስላልነበረ፤ በአሜሪካ ሊያሰሯት የፈለጉ ሰዎችም ስለነበሩ የአሜሪካ ቪዛ ብትጠይቅም አልተሳካላትም። በሂደት የፈለጓት ሰዎች የሥራ ፈቃድ ልከውላት አሜሪካ ሄደች።
ዛሬ ነገ እመለሳለሁ ብትልም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ 10 ዓመት መጠበቅ ግድ ሆኖባታል። በዛወርቅ በሥራ ሕይወቷ ከ“ሦስት ዓመት″ ጋር የተለየ ቁርኝት ያላት ይመስላል። ካሳንችስ የምሽት ሥራ በጀመረችበትና “ጥሩ እናቴ″ ስትል በምትገልጻቸው የወይዘሮ እልፍነሽ የባሕል ቤት ሦስት ዓመት ሰርታለች። በመቀጠል የገባችበት ዳዲሞስ ቤትም በተመሳሳይ ሦስት ዓመት ሰርታለች። ኢትዮ ስታርም ሦስት ዓመት ሰርታለች። አሜሪካ እንደመጣች ሥራ በጀመረችበት በነጋሪት ሬስቶራንትም ሦስት ዓመት ሠርታለች። በቋሚነት በአሜሪካ መኖሪያዋን ካደረገች 30 ዓመት አለፋት። ለሥራና ቤተሰብ ጥየቃ በተለያየ ጊዜ ወደ ሀገር ቤት ከመግባቷ ውጭ ኑሮዋን በሀገሯ ለማድረግ ብታስብም አሁንም ቋሚ መኖሪያዋ አሜሪካ ነው። የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናት።
በዛወርቅ የከተማ መኮንን ክራርና የሱ አጨዋወት በትዝታ ዘፈን እንድወጣ አግዞኛል ትላለች። ለዛም ይመስላል ድምጻዊውን “የሙዚቃ አባቴና ባለውለታዬ” በማለት የምታነሳው። ከጥላሁን ገሠሠ፣ መሀሙድ አሕመድ፣ አስቴር አወቀ ጀምሮ ከሀገር ውስጥ መድረኮች አንስቶ በተለያዩ ሀገራት አብራ ያልሰራችው እውቅ ድምጻዊ የለም። በ2003 ዓ.ም በወጣው «ለመኖር» የተሰኘው አልበሟ ላይ የተካተቱት«ለመኖ» እና “የማነሽ ይሉኛል። የተሰኙ ሙዚቃዎቿ ይለያሉ። ለመኖር በተሰኘው ሙዚቃዋ የሕይወትን ውጣ ውረድና ለመኖር የሷ ምኞት የነበረውን ታዜማለች።
ለመኖር እየተፍጨረጨርኩኝ በምድር
ሕይወቴን በደስታ ለማለፍ ብሞክር
ስንቱን ስንቱን ስንቱን አየሁ
ስንት አሳየኝ የእድሜዬ ሚስጥር
ይሁና ከማለት በስተቀር
አይወጣኝም ክፉም አልናገር
በማሕበረሰባችን የተለመደውን ሴት ልጅን ግድ ከአንድ ወንድ ጋር እንድትሆን የመጠበቅና ከማን ጋር ነሽ እያሉ በጥያቄ ማስጨነቅን የምትቋወምበትና የማንም አይደለሁም የምትልበት ዘፈኗ መለያዋ ነው።
የማነሽ ይሉኛል የማን ልበላቸው
ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ልቤን አቆሰለው
አይቻልም ወይ መኖር የማንም ሳይሆኑ
ልብ የፈቀደውን እስኪለግስ ቀኑ
የማነሽ ይሉኛል የማን ልበላቸው
ብቻዬን ብቆይስ ምን አስጨነቃቸው….
ልብ የፈቀደውን እስኪለግስ ቀኑ
መኖርም ይቻላል የማንም ሳይሆኑ
በዛወርቅ የመድረክ ብቋቷ የተለየ ነው። በዚህ የተነሳም በዘፈነች ቁጥር በሽልማት ትጥለቀለቃለች። መኖሪያዋን ካደረገችበት አሜሪካ ለሥራ ወደ ሀገሯ ተመልሳ ስታዜም በድምጿ የተደነቀ ታዳሚዋ የሸለማት የ500ሺህ ብር ቼክ የሽልማት ጣሪያዋ ነው።
የሁለት ወንድ ልጆች እናት የሆነችው በዛወርቅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሙዚቃን «በቃኝ» ብላ ፊቷን ወደ ኦርቶዶክስ መዝሙር አዙራለች። ሆኖም በ1978 ዓ.ም በወጣው አልበሟ ውስጥ የተካተተው “ትዝታ» የተሰኘው ሙዚቃዋ ሙዚቃ እስክታቆም ድረስ በየረገጠችው መድረክ እንድትጫወት የሚጠየቅ ተወዳጅ ሥራዋ ነው።
ከከተማ መኮንን ጋር የነበራቸው ጥምረት ደግሞ የተለየና ምን ጊዜም የሚታወስ ነው። የበዛወርቅ የትዝታ ዘፈኖች ለምን የትዝታ ንግሥት እንደተባለች ምላሽ የሚሰጡና እውነትም “የትዝታ ንግሥት» የሚያሰኙ ናቸው። እንደተመኘችው ኑሮዋን በሀገሯ የንግሥትነት ማዕረግ ከሰጣት ሕዝብ ጋር እንዲያደርግላት በመመኘት አበቃን!
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2016