ኢትዮጵያ የበርካታ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች መዳረሻ ነች። የታሪክ፣ የባህል፣ የተፈጥሮ ሀብቶቿን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በብዛት ካስመዘገቡ አገራት በቀዳሚነትም ትጠቀሳለች። ምድረ ቀደምትና የሰው ዘር መገኛነቷን ያስመሰከረች ጥንታዊት አገር እንደመሆኗ፣ እነዚህን የመስህብ ፀጋዎቿን በዓለም መድረክ ላይ በማስተዋወቅ ረገድ ግን ገና ብዙ መስራት ይጠበቅባታል። በተለይ ዘላቂነት ያለው የማስተዋወቅ፣ የመዳረሻ ልማት ተግባራት እና የገበያ ልማት ስራዎች በማከናወን በኩል ከመንግሥት ገና ብዙ ይጠበቃል።
በዋናነት ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚ አቅም ለመቀየር እና የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር የማስተዋወቅ ስራ ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል። ከዚህ አንፃር የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ ቢሆንም፣ ይህ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ። በተለይ ዓለም አቀፉን የቱሪዝም ገበያ ሰብሮ በመግባት የጎብኚዎችን ቀልብ ለመሳብ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ በርከት ያሉ አማራጮችን መመልከት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። ከእነዚህ እድሎችና አማራጮች ውስጥ አንዱ በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ፎረምና ኤግዚቢሽኖች ላይ መሳተፍ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት በአውሮፓ፣ አፍሪካ፣ ኤዥያና በመካከለኛው ምስራቅ በሚካሄዱ አውደ ርዕዮች ላይ ስትሳተፍ ቆይታለች። ይሁን እንጂ የአገሪቱን የቱሪዝም ሀብቶች በሚፈለገው ልክ ሁሉንም አስተዋውቆ ጎብኚዎች “የመዳረሻ ምርጫ” እንዲያደርጓት ለማድረግ በቂ አይደሉም። በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እና እጅግ ትላልቅ መድረኮች ላይ የአገሪቱን የባህል፣ የተፈጥሮና የታሪክ ሀብቶች ለማስተዋወቅ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪና መዋለ ንዋይ ሊጠይቅ ይችላል። ይህም የማስተዋወቅ ስራው ተከታታይና ቀጣይነት ያለው እንዳይሆን እንቅፋት ይሆናል። ይህን ችግር ለመፍታት በአገር ውስጥ በሚፈጠሩ ትላልቅ መድረኮችና ውስን ሀብትን በሚጠየቁ ውጤታማ ስልቶች ሀብቶቹን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ከማስተዋወቂያ ስልቶቹ መካከል ዩኔስኮን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለመስህቦቹ እውቅና እንዲሰጡ ማድረግ ሲሆን፣ ይህ መንገድ በቀላል አማራጭ የቱሪዝም ዘርፉን ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ይናገራሉ። ሌላውና ቀላል አማራጭ ተደርጎ የሚወሰደው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ የቱሪዝም አውደ ርዕዮች /ኤግዚቢሽኖች/ እና መሰል ሁነቶችን በዲጂታል አማራጭ ለቀሪው ዓለም የሚደርሱበትን መንገድ ማመቻቸት ነው።
የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች፣ አዳዲስ መዳረሻዎች እና የዘርፉን ጅምር ስራዎች በኤግዚቢሽን እና ፎረሞች የማስተዋወቅ ስራ ከቅርብ ጊዜ ውስጥ እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይ ትላልቅ ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት በዲጂታል አማራጭ ተደራሽ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል። ለምሳሌ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እና ሌሎች በግል የሚሰሩ‹‹ማይስ ኢትዮጵያን›› የመሰሉ መድረኮች የአገሪቱን የቱሪስት መስህብ ሀብቶች ከመጠበቅና ከማልማት ባሻገር አስተዋውቆ ጎብኚዎችን ለመሳብ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ናቸው። ከዚህ አኳያ ጅምር እምርታዎች እየታዩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት እስኪረጋገጥና ኢትዮጵያም ከዓለም ተመራጭ መዳረሻዎች መካከል እስክትሆን ድረስ መቀጠል ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት፣ አዳዲስ መስህቦችን በማስተዋወቅ እንዲሁም ከመሰረተ ልማት ግንባታ አንፃር ባለፉት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት በተከናወኑ ተግባሮች አስደናቂ ለውጦች እየታዩ ይገኛሉ። መንግሥት ከማልማት ባሻገር ማስተዋወቅ ላይ መሰራት ተገቢ እንደሆነ በማመኑም በዚህ ረገድ የሚሰሩ በርካታ ተግባራት እያስተዋልን ነው።
ባሳለፍነው መስከረም 29 በሳይንስ ሙዚየም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ በይፋ የተከፈተው አገር አቀፍ የቱሪዝም ፎረምና ሆስፒታሊቲ ኤግዚቢሽን የዚሁ እቅድ አካል ነው። የቱሪዝም ሚኒስቴር በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት አንድ ላይ እንዲመጡ በትብብር አገራቸውን “በትንሿ ኢትዮጵያ መድረክ” ላይ እንዲያስተዋውቁ እድሉን አመቻችቷል።
መድረኩን በይፋ የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ኢትዮጵያ ብዙ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ የተፈጥሮ ስጦታዎች፣ አዕዋፍ፣ የዱር አራዊት እና ሊጎበኙ የሚችሉ ድንቅ ሁነቶች እንዳላት ግምት ውስጥ በማስገባት ከኢኮኖሚው ዘርፍ ዋና ምሰሶዎች አንዱ የቱሪዝም ሴክተሩ እንዲሆን መደረጉን አስታውቀዋል።
አውደ ርዕይው ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ምቹ መዳረሻ የሚያደርጋትን ሀብት በናሙና እንዲያዩ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያን ድንቅ የቱሪዝም አቅሞች ከማልማት ባሻገር ማስተዋወቅ ላይ በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም ለማውጣት፣ ኢትዮጵያን የብዙ ውበቶች እና ግኝቶች መዳረሻ አድርጎ ለማስተዋወቅ እና ለማገልገል ኢትዮጵያውያን አገራችሁ ያላትን ሀብት ማየት፣ ማውጣት፣ ማስተዋወቅ እና ማገልገል ይጠበቅባችኋል በማለትም መዳረሻዎችን ከማልማት ባሻገር በሚገባ ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት በማሻሻል ረገድ አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ መንግሥት በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አማካኝነት ለቱሪዝም ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይ ያሉትን ድንቅ የቱሪዝም አቅሞች ከማልማት ባሻገር ማስተዋወቅ ላይ በትብብር መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው አውደ ርዕይ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች እንደሚያሳይ ጠቅሰው፣ ሁሉም የአገሩን ሀብት በስፍራው ተገኝቶ በመጎብኘትና በዲጂታል አማራጭ ለቀሪው ዓለም በማስተዋወቅ የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎችም መድረኩ በየክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም እምቅ ሀብቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው በማመን ተሳታፊ ሆነዋል። በተለይ በየአካባቢው ስላሉት መስህቦች በቂ እውቀት ሊኖር እንደሚገባና ኤግዚቢሽኑ ይህንን በመፍጠር በኩል ጉልህ አስተዋፆኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። መድረኩ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር የሚያገናኝ እንዲሁም ልምድ መለዋወጥም የሚያስችል መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። እስካሁን ያልታወቁ በርካታ የቱሪስት መስሕቦችን በኤግዚቢሽኑ ለመመልከት እንደሚያስችል መረዳት ይቻላል። በመድረኩ ከፌዴራልና ክልል ቱሪዝም ባለድርሻዎች ባሻገር አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ቱር ኦፕሬተሮች እና ሌሎች የዘርፉ አንቀሳቃሾች ተሳታፊ ናቸው።
አቶ እንደገናው አሰፋ 250 የሚደርሱ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ነው። በሳይንስ ሙዚየም እስከ ጥቅምት 28 ድረስ በሚቆየው የቱሪዝም፣ ሆስፒታሊቲ ፎረምና ኤግዚቢሽን ላይ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል እየተሳተፈ ይገኛል። ኤግዚቢሽኑ በአይነቱ ለየት ያለና ቀደም ሲል ከተዘጋጁት መድረኮች በትልቅነቱና በይዘቱ ለየት ያለ ስለመሆኑም አቶ እንደገናው ይገልፃል።
“ቱሪዝምን እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምሰሶ ለመውሰድ በተወሰነው መሰረትና እርሱን ለማሳካት በሚደረገው ትግበራ ላይ መሰል ኤግዚቢሽኖችና የማስተዋወቂያ ስልቶች ትልቅ ፋይዳ አላቸው” የሚለው የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የቱሪስት ፍሰቱ ቢቀንስም፣ የዘርፉ አንቀሳቃሾች በአንድ ላይ ተሰባስበው መገናኘታቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራል። እርስ በእርስ ለመተዋወቅና በሕብረት የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማሳደግ ቅንጅት ለመፈጠር ሁነኛ መድረክ እንደሆነ ነው የሚያነሳው። በተለይ በአንድ ወር ቆይታው ውስጥ በሚካሄዱ የፓናል ውይይቶችና የፎረም መድረኮች ችግሮችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለማምጣትና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚረዳ ይገልፃል።
ቱሪዝም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻ የሚሰራ አይደለም የሚለው ማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ኢሚግሬሽንና ሌሎች አስፈፃሚ አካላት እንደሚሳተፉበት ይገልፃል። በኤግዚቢሽኑ በተዘጋጁ ፓናል ውይይቶች ላይ እነዚህ የመንግስት አካላት ተሳታፊ በመሆናቸው የቱሪዝም ባለድርሻዎች በስራ ወቅት የሚገጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መፍታት እንደሚችሉ በጋራ ለመወያየት እድል እንደሚፈጥር ያስረዳል።
“ኤግዚቢሽኑ ስለ ቱሪዝም በስፋት ከማውራት ባሻገር ወደ መሬት አውርዶ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በር የሚከፍት ነው” የሚለው ፕሬዚዳንቱ፤ በቱሪዝም ዘርፍ በፀጥታ፣ በመዳረሻ ልማት፣ በገበያና በማስተዋወቅ ረገድ መሰራት ያለባቸው ተግባራትን ለመለየት ፋይዳ እንደሚኖረው ይናገራል። ኢትዮጵያ በተለያዩ የፀጥታ ጉዳዮች ፈተና ላይ መሆኗን አንስቶ፣ እነዚህን እንቅፋቶች በማለፍ በዘርፉ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ይናገራል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ በፀጥታ ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው አገራት ከችግራቸው ባይወጡም ቱሪዝማቸውን በማስተዋወቅና በዚያም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማግኘት ትርፋማ መሆን መቻላቸውንም በመጥቀስ፣ የሰላሙ ሁኔታ እልባት እስኪያገኝ መሰል ሞዴል መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመልክቷል። በተለይ ለዚህ አንደ ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑት ውስጥ አገረ እስራኤልን በመጥቀስ፣ አገሪቱ በተለያየ ጊዜ ጦርነት ውስጥ ብትቆይም የቱሪዝም እድገቱና የቱሪስት ፍሰቱ እንዳልቆመ ይገልፃል።
የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር በኤግዚቢሽኑ ላይ በመሳተፍ ከ250 በላይ የሚሆኑ አስጎብኚ (ቱር ጋይዶች) ስለሚሰጡት ሙያዊ ግልጋሎት እያስተዋወቀ መሆኑን የሚናገረው የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ አባላቱ ኢትዮጵያ ያላትን የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና አርኪዮሎጂ ሀብቶች በልዩ ልዩ የውጭ ሀገር ቋንቋዎች (በእንግሊዘኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በስፓኒሽ፣ በሩሲያኛ እና በመሳሰሉት) በማስጎብኘት ቱሪስቱ ባገኘው አገልግሎት ተደስቶ እንዲሄድ እንደሚሰሩ ይገልፃል። ይህንን ስራ በኤግዚቢሽኑ ላይ ተገኝተው በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኙ ይናገራል። በዝግጅቱ ላይም ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር መገናኘቱን ገልፆ፤ ይህም ሙያዊ ግንኙነታቸውን ለማስፋት እየተጠቀመበት እንደሆነ ያስረዳል።
“በኤግዚቢሽኑ ስለማህበራችንንና ስለምንሰራው ስራ በሚገባ እያስተዋወቅን እንገኛለን” የሚለው ፕሬዚዳንቱ፤ ጎብኚዎች በቦታው ሲገኙ ስለሚሰጡት የማስጎብኘት አገልግሎት ማህበሩ እንደሚያስረዳ ይገልፃል። በሌላ መልኩ ማህበሩና አባላቱ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በስፍራው ለተገኙ የሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት በማስረዳት መፍትሄ ለማግኘት እየተጠቀሙበት እንደሆነም ገልፆልናል። በተለይ የማስጎብኘት ስራ ሙያዊ እንደሆነ፣ የስነ ምግባር መርህና መመሪያ ያለው እንዲሁም በትምህርትና በእውቀት የታገዘ መሆኑን ለማስረዳት ይህ መድረክ ትልቅ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግሯል።
እንደ መውጫ
ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሶስተኛ ዓመት የስራ ዘመን መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ የቱሪዝም ዘርፍ በብዝኃ የዕድገት አማራጭ አንዱ ቁልፍ ዘርፍ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህ በኩል በዓመቱ የቱሪስት ፍሰቱን በማሳደግ በኩል ፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መታለፉን ጠቅሰው፣ እንዲያም ሆኖ አበረታችና አወንታዊ ዕድገት ለማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።
ከዚህ መረዳት የምንችለው ኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር በሰራችው የማስተዋወቅ እና የገበያ ልማት ስራ ውጤታማ እየሆነች መምጣቷን ነው። ይህንን አቅም ለማሳደግና ከዚህ በተሻለ አገሪቱን በማስተዋወቅ በውጪ ምንዛሪ፣ በቱሪዝም ኢንቨስትመንትና በመሰል ተመሳሳይ ዘርፍ ላቅ ያለ ውጤት ለማስመዝገብ በቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና ባለድርሻ አካላት የሚዘጋጁ መሰል ዝግጅቶች መበረታታት ይገባቸዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2016