ከሞት አፋፍ የተመለሰች ነፍስ

ከተለያዩ የካንሰር በሽታዎች አንዱ የጡት ካንሰር ነው። የጡት ካንሰር ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ዕድገት እና በጡት ኅብረ ሕዋስ ላይ በሚከሰቱ ለውጦች ምክንያት የሚመጣ በሽታ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ጊዜም በዓለም አቀፍ እያጠቃ ያለው የጡት ካንሰር ሁለተኛ ደረጃ የሚባለው እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይ ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት እየተስፋፋ መምጣቱና አሳሳቢ የጤና ችግር ስለመሆኑም ይነገራል። እ.ኤ.አ በ 2018 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ወደ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች የጡት ካንሰር በሽታ ተገኝቶባቸዋል። ከ 8 ሴቶች መካከል አንዷ (13 በመቶ) በሕይወት ዘመኗ በጡት ካንሰር በሽታ የመያዝ ዕድል ሲኖራት፤ ከ 39 ሴቶች መካከል አንዷ (3 በመቶ) ደግሞ በዚህ በሽታ ምክንያት ለሞት ትዳረጋለች።

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.ኤ.አ በ 2018 ባወጣው መረጃ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የጡት ካንሰር በፈጣን ሁኔታ እያደገ ነው። ከሁሉም የካንሰር ዓይነቶች 22 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነውን የሚያካትት ቀዳሚ የካንሰር መንሥኤ ሲሆን፣ ከ100 ሺ ሰዎች ውስጥ 22 ነጥብ 9 የሚሆኑትን በዚህ በሽታ ምክንያት ታጣለች።

የጡት ካንሰር በአብዛኛው በሴቶች ላይ የሚከሰት በሽታ ቢሆንም፤ በወንዶችም ላይ የመከሰት ዕድል አለው።

እኤአ 2020 በመላው ዓለም 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ሴቶች ላይ የጡት ካንሰር መገኘቱን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። በዚሁ ዓመትም 685 ሺ ሰዎች በዚሁ የጤና ችግር ሕይወታቸው አልፏል። የችግሩ አሳሳቢነት እየከፋ በመምጣቱ በየዓመቱ ጥቅምት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የጡት ካንሰር ወር ተብሎ እንዲታሰብ ተደርጓል። በዚህ ጊዜም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችና ተያያዥ መልእክቶች ይተላለፋሉ።

በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰዎች ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ በሚተላለፈው መልእክት የጡት ካንሰር አስቀድሞ ከተደረሰበት ሊድን እንደሚችልም ትምህርት ይሰጣል። ነገር ግን አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ በርካቶች በጡት ካንሰር ምክንያት እየተጎዱ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

የዚህ የጡት ካንሰር ተጠቂዎች ወደ ሕክምና የሚሄዱት በጣም ተባብሶ ካንሰሩ ስር ከሰደደ እና ወደ ሌላ አካባቢ ከተሰራጨ በኋላ መሆኑም ሌላው ችግር፡ ብዙ ጊዜም የመዳን ዕድላቸው የጠበበ ሆኖ ነው የሚታየው። ይህም የሚያሳየው አሁንም ግንዛቤ መፍጠር ላይ ሰፊ ሥራ መሰራት እንዳለበት ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጡት ካንሰር ምልክቶች በሁሉም ሰው ላይ ተመሳሳይ አይደሉም። አንዳንድ ሰዎች የከፋ ደረጃ እስከሚደርስ ምንም ምልክቶች ላያሳዩ ይችላሉ። ስለዚህም መደበኛ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ በተገቢው መንገድ ማድረግ ጥቅሙ የላቀ ይሆናል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በጡት ካንሰር ከሚጠቁት 13 ሺህ ሰዎች ውስጥ 53 በመቶዎቹ ለሞት ይዳረጋሉ። ሕብረተሰቡ ለጡት ካንሰር ያለው የግንዛቤ ማነስና ሕክምናውን የሚሰጡ የጤና ተቋማት በቂ አለመሆን በሽታውን በቀላሉ መከላከል እንዳይቻልም አድርጎታል።

የጡት ካንሰር በቅድሚያ በጡት ላይ በመከሰት ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በመዛመት ለሞት የሚያጋልጥ በሽታ ሲሆን፤ በሽታው በዋናነት ሴቶች ላይ ይታይ እንጂ አልፎ አልፎ ወንዶችንም ያጠቃል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 13 ሺህ ሰዎች ለጡት ካንሰር የሚጋለጡ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ 7 ሺህ ያህሉ እንደሚሞቱ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል። የጥቅምት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የጡት ካንሰርን በተመለከተ ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ሆኖ ይቆያል።

የጡት ካንሰር መንስኤዎች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከልም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ። ጡት አለማጥባት፣ ሲጋራ ማጨ፣አልኮል መጠጣት፣ ከሆርሞን ጋር የተያያዙ መድሀኒቶችን መውሰድ፣ ቶሎ አለመውለድ እና ሌሎቹ ተጠቃሾች ናቸው።

የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስም በየቀኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ߹ ከ 1 ዓመት እስከ 2 ዓመት ጡት ማጥባት߹ ከ20 እስከ 30 መካከል ባለው እድሜ ልጅ በመውለድ ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚያስችል ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት። የጡት ካንሰር ምርመራውም ሆነ ሕክምናው በጣም ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅና ሕይወትን ሊያሳጣ ስለሚችል ሕብረተሰቡ ቅድመ ምርመራ በማድረግ መከላከል እንዳለበትም ይመከራል።

አሁን ላይ 12 የመንግስት ሆስፒታሎች ሕክምናውን እየሰጡ ቢሆንም የሕክምና ማዕከላት እጥረትን ለመቀነስ ተጨማሪ የሕክምና ማዕከላት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ እየተገነቡ ስለመሆኑ መረጃዎች ይናገራሉ።

ካንሰር ሲባል ብዙዎች በቶሎ የሚያስቡት የማይድን ሕመም ነው የሚለውን ነው። ሆኖም ግን በቂ የሕክምና አማራጮች ባሉባቸው ሃገራት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የጡት ካንሰር ሕመም አጋጥሟቸው ታክመው የዳኑ ሰዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም። የጡት ካንሰር በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት በሰዎች ላይ የሚገኝ የካንሰር አይነት እየሆነ የመጣ ሲሆን ታማሚዎቹ ለሕክምና እርዳታ ወደ ሀኪም ቤት የሚሄዱት ግን በአብዛኛው ሕመሙ ስር ከሰደደ በኋላ መሆኑ ለመዳን የሚኖራቸውን እድል የጠበበ ያደርገዋል።

የጡት ካንሰርን ለመከላከል በዘርፉ ባለሙያዎች ምክረሃሳቦች ይሰጣሉ።በአካል ላይ ለውጥን መከታተል በተለይ የጡት ካንሰር በሚያሳያቸው አንዳንድ ምልክቶች ፈጥኖ ሊደረስበት እና ታክሞም ሊድን እንደሚችል በማወቅ ምልክቶችን መከታተልና በዛ መሰረትም ሕክምና ማግኘት ይገባል። ነገር ግን አብዛኛው የማሕበረሰብ ክፍል በቂ መረጃ ባለማግኘት ምልክቶችን እያዩ እንኳን ወደኋላ የሚሉበት ሁኔታ የበዛ ነው።

ለሕብረተሰቡ ስለጡት ካንሰር ግንዛቤ ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጥቅምት ወርን ተከትለው ይሁን በተለያዩ ስራዎቻቸው ውስጥ እያካተቱ እንዲሁም መደበኛ ስራቸው አድርገው አስቀድሞ መመርመር እና ችግሩን ማወቅ ሕይወት ለማትረፍ ያለውን ከፍተኛ ጥቅም እያስረዱም ነው።

እኛም በተለይም ጥቅምት ወር የጡት ካንሰር ወርን ምክንያት በማድረግ በሕመሙ ተይዛ ግን ደግሞ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ትጋትና ራስን በማሳመን በሽታውን ድል የነሳችዋን ፋጡማ አደም አሊን ለዛሬ የሕይወት ገጽታ አምዳችን እንግዳ አድርገናታል።

ፋጡማ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ ተራ ከአዲሱ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ ነው። እድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰም ከእህት ከወንድሞቿ ጋር በመሆንም በአቅራቢያዋ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራ በነበረ አካባቢ በሚገኘው አወሊያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ ከዊንጌት በላይ በሚገኘውና ስሙን በማስታውሰው ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቷን ተከታትላለች።

ፋጡማ ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ በትምህርቷ አልገፋችም። ሶስት ጉልቻ መመስረቱን ነው የመረጠችው። ትዳር መሠረተች። ትዳሩም ቢሆን እንዳሰበችው አልሰመረም። ከትዳር አጋሯ ጋር በነበራት አጭር ጊዜ ቆይታ አንድ ወንድ ልጅ ወልዳ ተለያየች።

ትዳሯን ማጣቷም አዝናለች። ቀጣይ የኑሮ አቅጣጫዋን ለማመቻቸት ልጇን ለቤተሰቦቿ መስጠት ነበረባት። ራሷንና ልጇን ለመደገፍ የሚያስቸል ገቢን ለማግኘትም ስራን መስራት እንዳለባት ማሰብ ጀመረች፤ ግን ምን ልስራ ? የሚለውን ነገር ለመወሰን ጊዜ ቢወስድባትም የግድ መወሰን ስለነበረባት ወሰነች።

እራስዋን ለመለወጥና ልጇን ለማሳደግ ምርጫዋ ያደረገችው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት መሄድ ነበር። የመን አገር ነበር ለሥራ የሄደችው። በየመንም ለአምስት አመታት ቆየች። ገንዘብ እየላከች ልጇን አሳደገች።

ፋጡማ ረዘም ላለ ጊዜ በየመን ቆይታ ልጇን እየረዳች ለእርሷም ጥሪት የሚሆናት ገንዘብ ለማጠራቀም ፍላጎቱ ቢኖራትም ያልታሰበ ነገር ገጠማት። እናቷ አረፉ። ወደሀገሯ መመለስ ግድ ነበር ተመለሰች። ልጇ ብቻ ሳይሆን፣ እኗቷ ጥለዋቸው ያለፉት ራሳቸውን ያልቻሉ ድጋፍ የሚፈልጉ ልጆች በቤት ውስጥ ስለነበሩና እንደ እናት ሆኖ የሚንከባከብ ሴትም ስላልነበር የእርስዋ ታስፈልግ ነበር። የእሷን ልጅ ደግሞ የግድ ወደ አባቱ ቤተሰቦች ቤት እንዲሄድ ማድረግ ነበረባትና ልጇን ሰጠች።

ፋጡማ ተመልሳ ለሥራ ወደ ውጭ ሄደች። ስለሁለተኛው ጉዞዋም እንዳጫወተችኝ፤ ሳውዲ ነበር የሄደችው። ለስድስት ዓመታት ሰርታለች። ከየመን ቆይታዋ እንደውም የሳውዲው ጥሩ ሆኖ ነው ያገኘችው። ነገር ግን ከስድስት ዓመት ቆይታ በኋላ የመኖሪያ ፍቃድ ስላልነበራት በመንገድ ላይ ተይዛ አገሯ እንድትገባ ሆነ። አገሯ ገብታም የምትችለውን እየሰራች ከወንድሞቿ ጋር መኖርን ቀጠለች። ልጇም የአባቱ ቤተሰቦች እያሳደጉትና እያስተማሩት ስለነበር የተቸገረችው ነገር እንዳልነበር ትናገራለች።

ፋጡማ ኑሮን ለማሸነፍ እንጂ በጤና ችግር ውስጥ እወድቃለሁ ብላ አስባ አታውቅም። በተለይም ከሕመም ሁሉ የከፋው ካንሰር ወደእኔ ይመጣል ብላ አልገመተችም። ‹‹ኸረ እኔ ስሙንም ሰምቼ አላውቅ›› ትላለች እንደውም ፋጡማ።

ፋጡማ እዛው ሳውዲ እያለች የስኳር ሕመም ተገኝቶባት መድሃኒት ትወስዳለች። ከዛ ውጪ ግን በአካሏም በሌላ የሰውነቷ ክፍሏም ሆነ ውስጧ ሕመም ተሰምቶት አያውቅም። በዚህም እንደ አብዛኞቻችን ጤነኛ ነኝ ብላ የለት ኑሯዋን ከቤተሰቧ ከጎረቤቶቿ ጋር ትኖራለች። ግን ደግሞ ነገሩ ሌላ ነበር።

ፋጡማ ድምጽ አልባው የጡት ካንሰር ከጎበኛት ስድስት ያህል ዓመታት ተቆጥረዋል። “እኔ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ከስኳር ሕመሜ ውጪ አሞኝ የሚያውቅ ነገር አልነበረም። ነገር ግን ጡቴ ላይ የመክበድ በተለይም ግራ ጡቴ በየቀኑ የመጠን ጭማሪ ማሳየት ነበረው። ምንድነው ብዬ ግን ቦታ

 አልሰጠሁትም ነበር። እየቆየ ሲሄድ ግን የቀለም ለውጥ አመጣ የጡቴ ጫፍም ወደ ውስጥ መግባት ጀመረ” በማለት በሕመሙ ምክንያት የታያትን አካላዊ ለውጥ ትገልጻለች። ይህም ቢሆን ግን ፋጡማ አሁንም ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠችውም ነበር።ትኩረት ላለመስጠቷ ዋናው ምክንያት ደግሞ ስለ ጡት ካንሰርም ሆነ በጠቅላላው ስለ ካንሰር ሰምታ የምታውቀው መረጃ ስላልነበራት ነው።

ፋጡማ እርሷ እንደምትለው አላህ ሊያድናት ፈልጎ ነበርና አንድ ቀን ከጎረቤቶቿ ጋር ቁጭ ብላ ቡና ስትጠጣ ለአንደኛዋ ሴት በጡቷ ላይ እያየች ያለውን ለውጥ ገልጣ አሳየቻት። ሴትየዋ በጣም በመደናገጥ በቶሎ ወደ ሕክምና እንድትሄድ መከረቻት።

‹‹በጡቶቼ ላይ እያየሁት የነበረው ለውጥ ዓመት ያህል ይሆነዋል። ነገር ግን ሕመም ስለሌለው ምንም ነገሬ አላልኩትም ነበር፤ የአላህ ስራ ሆኖ አንድ ቀን ከጎረቤቶቼ ጋር ተሰብስበን ቡና እየጠጣን ለአንደኛዋ በሰውነቴ ላይ እየተከሰተ ያለውን ለውጥ አሳየኋት እሷም በጣም በመደንገጥ ምን እየሆንሽ ነው ብላ ጮኸችብኝ፤ እንደዛ እየጮኸችብኝና እየተቆጣችኝ በቶሎ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ አለበሽ እያለችኝ እንኳን ምንም አልመሰለኝም ነበር። ምክንያቱም ስለ ካንሰር የማውቀውም የሰማሁትም ነገር ስላልነበር ” በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።

እዛው ቡና ላይ ያሉት ሌሎች ሰዎችም አዩዋትና አይ ይህማ “ቡጉንጅ ” ነው ስለዚህ “እንደሆላ” በሚባል ቅጠል መጠበስ አለበት ይሟሽሻል በማለት ሃሳብ አቀረቡ። ፋጡማም የጎረቤቶቿን ሃሳብ በመቀበል በተለይም ብጉንጅ የሚለውን ነገር በማመን ተቀመጠች። ቅጠሉም አለ ከተባለበት ቦታ ተፈልጎ መጥቶ ተሰጣት። አለማወቅ መቼም ክፉ ነገር ነውና ፋጡማ የጎረቤቶቿን ምክር አንድም ሳታስቀር በመቀበል ያበጠውን የጡቷን ክፍል ቅጠሉን በከሰል እሳት እያሞቀች ስትጠብሰው አመሸች። ከዛ በኋላ የነበረውን ነገር ስታስታውሰው እንባዋ ይቀድማታል።

” ጎረቤቶቼ ብጉንጅ ነው በእንዳሁላ ቅጠል ይጠበስ ብለው ቅጠሉን ፈልገው ሲያመጡልኝ እኔም በተመከርኩት መሰረት ቅጠሉን እሳት እያሞኩ ያበጠውን ቦታ በደንብ ጠበስኩት ከዛ በኋላ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ የሆነ ሌሊቱን አሳለፍኩ። ወላሂ የምሞት ብሆን ኖሮ ያን ቀን ሌሊት ነበር ሞቼ የማድረው። ነገር ግን ያልተቆረጠች ነፍስ ሆና እኔም ለዛሬ ደረስኩ። ሁኔታው ግን ከመግለጽ በላይ የሆነ አሰቃቂ አሰቃይ ብቻ ምኑ ቅጡ አሳብዶኝ አደረ ” በማለት ትናገራለች።

ይሄ ጎረቤቶቿም ሆኑ እሷ ስለጡት ካንሰር የነበራቸው አረዳድ ያሳያል።በቀላሉ ተሽሏት ትገላገላለች በሚል ቀናነት የመከሯት ምክር ወይም ያዘዙላት መድሃኒት ትክክለኛ ቦታውን አላገኘምና ታማሚዋን አሰቃያት። አይነጋ የለም ሲነጋ ፋጡማ ጉዞዋን ያደረገችው ወደጤና ጣቢያ ነበር።

ጤና ጣቢያ ደርሳ ለምታክማት የጤና ባለሙያ ጡቷን ስታሳያት በጣም ስለመደናገጧ ታስታውሳለች። “ወጣቷ የሕከምና ባለሙያ ጡቴን ሳሳያት በጣም ደነገጠች በእኔም በጣም ተናደደች እንዴት የከተማ ሰው ሆነሽ ስለዚህ ጉዳይ መረጃ አይኖርሽም? መገናኛ ብዙሀንንስ እንዴት አትከታተይም? በማለት በጣም ተቆጣች። ምንም ስላላመመኝና የተለየም ስሜት ስላልተሰማኝ ትኩረት አልሰጠሁትም አልኳት። ባለሙያዋ ያለበት ሁኔታ በጣም ስላስፈራት ምንም የማደርግልሽ ነገር የለም ነገር ግን ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ሪፈር ጽፍልሻለሁ” በማለት እንዳሰናበተቻት ትናገራለች።

ዘውዲቱ ሆስፒታል ስትሄድም ያጋጠማት ይኸው መደናገጥ ነበር። ለምን ዘገየሽበት? የሚል ጥያቄ ነበር፤ ፋጡማ ለሁሉም ጥያቄዎችና ቁጣዎች ተግሳጾች መልሷ አንድና አንድ ነበር እሱም “አለማወቄ” የሚል። ያም ሆነ ይህ ፋጡማ ብትዘገይም አልቀረችምና የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሰራተኞች ተሯሩጠውላት ሕክምና እንድታገኝ ችግሩ ያለበት ጡቷም ተቀጠርጦ እንዲወጣ ሆነ።

‹‹እኔ ጉዳዩን እንደ ቀልድ ነው ያየሁት ሌላው ቀርቶ ቀዶ ሕክምና ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል እንኳን ግምት አልነበረኝም። ዘውዲቱዎች አቀባበላቸው ልክ ጤና ጣቢያ እንዳገኘኋት የሕክምና ባለሙያ ነበር፤ በጣም ተደናግጠው በቃ ሙሉ ምርመራ አድርጊ ብለውኝ አደረኩ ችግር ካለበት ቦታ ላይም ናሙና ተወስዶ ቅዱስ ዻውሎስ ሆስፒታል ተሰራ። ከዛ በኋላ በቀጥታ ወደ ሕክምና ነው የገባሁት “በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።

መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም የመጀመሪያውን ቀዶ ሕክምና በግራ ጡቷ ላይ ያደረገችው ፋጡማ፤ ምንም እንኳን በዚህን ያህል ሁኔታ ሕክምናው ከፍ ያለ ባይመስላትም መሆን ያለበት ነገር ግን ሆነ። ፋጡማ በወቅቱ ፈርማ ቀዶ ሕክምና ክፍል ስትገባ ዳግም በሕይወት አልመጣ ይሆን የሚል ከፍ ያለ ስጋት ውስጧን እየናጠው ነበር። በወንድሟና በዘመድ አዝማዶቿ ተበረታታ ገባች። የአምላክ ፈቃድ ሆኖም ቀዶ ሕክምናዋ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ከሆስፒታል ወጣች።

ፋጡማ ግን ሕክምናዋ በዚህ የሚያበቃ አልሆነም ዘውዲቱ ያሉት ባለሙያዎች ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታ ላኳት። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስትሄድ ግን መሰሎቿን አገኘች በተለያዩ የካንሰር ሕመሞች ተይዘው በኬሞቴራፒ የመጡ ብዙ ወዳጆችንም አፈራች፤ ፋጡማ በዚህን ጊዜ ሞራሏ ተነሳሳ ብዙ ታማሚ መኖሩን ስታውቅ እሷ ላይ ብቻ የመጣ አለመሆኑን ተረዳች። ይህም እድናለሁ የሚል መንፈስ በውስጧ እንዲያቆጠቁጥ አደረገ።

የኬሞ ቆይታ

ፋጡማ ቁስሏ ጠገግ ካለ በኋላ የሕክምናው አንድ አካል የሆነውን ኬሞ ቴራፒ መውሰድ ነበረባት፤ ሕክምናውንም ለመውሰድ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገባች፤ ምንም እንኳን ሰዎች ስለ ኬሞው የሚያወሩት ነገር የሚያስፈራና ከባድ ቢሆንም የመዳን ተስፋ ግን እንድታደርግ ገፋፍቷት ወደ ሕክምናው ገባች።

‹‹ከቀዶ ሕክምናው በበለጠ የጎዳኝ ኬሞ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ሕክምናውን ወስደን እንደጨረስን ምግብ መመገብ አይደለም ሽታው ያስጠላል፤ ወደ ላይ የሚለው ስሜትም ከባድ ነው፤ እግርን ለመራመድ እንዳይችል ያደርጋል፤ እንቅልፍ አይወስድም ብቻ ምን ልበልሽ በጣም ስሜቱ ከባድ ነው። የእውነት ለጠላት አይስጠው ከባድ ነው” በማለት ከእንባ ጋር የነበረውን ሁኔታ ታስረዳለች።

ኬሞ ሌላው የጎንዩሽ ጉዳቱ ጸጉር መነቃቀሉ የእጆችን መዳፍና ጥፍር ማጥቆሩ ፊትን መቀየሩ ነው፤ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደግሞ ፋጡማ ላይ ተከስተዋል፤ ምንም እንኳን ዛሬ ላይ ሁሉም ነገር አልፎና ጨርሳ ወደቀደመ ሁኔታዋ መመለስ ብትችል ፋጡማ ስምንት ዙር ነው ኬሞን የወሰደቸው። በዚህ መልኩ መውሰዷ ደግሞ ለሕክምናው ውጤታማነት ከፍ ያለ አስተዋጽዖን አበርክቷል።

ሰው ሲታመም የሚጨንቀው አስታማሚው ነው። እንደውም አንዳንድ ሰዎች ሕመምን በተለይም እንደ ፋጡማ አይነት ሕመምን በመፍራት ” አትመመኝ አስታማሚ የለኝም ” ብለው እስከመጸለይ ይደርሳሉ። አዎ ጎንበስ ቀና አድርጎ ምን ላርግልሽ ? ምን ልስጥሽ? ብሎ አጥቦና አጉርሶ የሚያስታምም ሰው የግድ ነው። ፋጡማም ይህ አይነቱ ሀሳብ ገብቷት ነበር፤ ነገር ግን አላህ የባረካት የምትላት የወንድሟ ባለቤት ቤቷን ጥላ ለአንድ ወር ከእርሷ ሳትለይ የሚያስፈልጋትን አድርጋ ገላዋን ልብሷን አጥባ አብልታ አጠጥታ ተንከባክባ ፋጡማን እዚህ አድርሳታለች። ፋጡማም ምስጋናዋን በእንባ እየታጀበች ነው የምትገልጸው።

የጡት ካንሰርና ሕክምናው

ፋጡማ ፈጣሪ ፈቅዶላት በጡቷ ላይ የታየው ካንሰር ወደየትኛውም የሰውነቷ ክፍል አልተዛመተም፤ እሷም ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ያለውን የኬሞ ሕክምና ሀኪሟ በቃሽ እስከሚላት ጊዜ ድረስ በአግባቡ ተከታትላለች ይህም ለውጤት አብቅቷታል።

“ካንሰር የያዘው ሰው ሁሉ ይሞታል ብሎ ማለት ሀሰት ነው። እኔም እሞታለሁ ብዬ አላስበም ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ካንሰር እንደ ማንኛውም ሕመም ታክሞ የሚድን በመሆኑ ምንም ችግር የለውም። ዋናው ነገር በሕክምናው ወቅት ያሉ ፈታኝ ነገሮችን በጽናት ከፍ ያለ ተስፋን በማድረግ መከታተል ተከታትሎም በማጠናቀቅ በሽታውን ድል መንሳት ይቻላል። አሁን ላይ ከበሽታው የዳንኩ ቢሆንም በየሶስት ወሩ ሀኪም ጋር እየሄድኩ ክትትል አደርጋሁ። ሰንፌ ቀርቼ አላውቅም። እዛ ሄጄ የማገኛቸውን አዳዲስ ታማሚዎችም እኔ ያለፍኩበትን መንገድ በመናገር ሕመሙ ሕክምናውን በአግባቡ ከተወሰደ የሚድን መሆኑን በተቻለኝ መጠን ለመናገር እሞክራለሁ ” ትላለች።

አሁን ላይ ፋጡማ ብርድ ሲሆን ከሚሰሟት አንዳንድ ሕመሞች ውጪ በጤናዋ ምንም ችግር አልገጠማትም፤ ሙሉ ጤነኛ የሚባል ደረጃ ላይ ናት፤ እንደውም ትላለች ፋጡማ ላለፉት ስድስት ዓመታት የወሰደችው መድሃኒት ከሀኪሟ በቃ ጨርሰሻል አቁሚው ብትባል ተመልሳ አረብ አገር በመሄድ የመስራት ፍላጎት አላት ።

ማህበራዊ ሕይወት

ፋጡማ ከሰፈር ጎረቤቶቿ ከዘመዶቿ እንዲሁም ከጓደኞቿ ጋር ጠበቅ ያለ ግንኙነት የነበራት በሀዘን በደስታው አብራ የምታሳልፍ ነች። ዛሬ ላይ ሕመሟ አንዳንድ ጥንቃቄዎችን የሚፈልግ ቢሆንም እንኳን ከሕመሟ በፊት የነበራትን ማሕበራዊ ግንኙነት አላቋረጠችም እንደውም አጠናክራ ቀጥላለች። በዚህ መካከል ደግሞ የሰዎች እንክብካቤና ፍቅር በጣም ያስደስታታል።

ምስጋና

ፋጡማ በሕይወቷ ያገዟትን ሁሉ ታመሰግናለች። በተለይም በሕመሟ ወቅት ያልተለዯትን ቤተሰቦቿን የወንድሟን ባለቤት ወንድሞቿን ጎረቤት ጓደኞቿን ሁሉ አመስግና አትጠግብም። በተለይ ብላም የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መድሃኒት ሲጠፋ እያፈላለጉ በሌላቸው አቅምም ቢሆን ሕሙማን አንዳይቸገሩ የሚያደርጉትን ጥረት በጣም በማድነቅ ታመሰግናለች። እንዲህ ዓይነት ተቋማትም ትኩረት ቢያገኙ በርካቶችን ያግዛሉም በማለት ትገልጻለች።

 በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2016

Recommended For You