መነሻውን ዘጠና ዘጠኝ ብር ከዘጠና ሳንቲም ያደረገው የባለራዕዩ ስኬት

ሰዎች ሥራን ሳይንቁ አቅማቸውን አሟጠው መጠቀም ከቻሉ ውጤታማ እንደሚሆኑ ይታመናል። ‹‹ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው›› እንደሚባለው ብዙዎች የሥራን ትርጉም ተረድተው፣ አውቀውና ተገንዝበው መሥራት በመቻላቸው ሙሉ ሰው መሆን ችለዋል። በተለይም ከዝቅታው ዝቅ ብለው ከትንሽ የተነሱቱ ሙሉ ጊዜያቸውንና አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም ትናንት የነበሩበትን ወደ ኋላ ትተው ሽቅብ ወጥተዋል። ከመጨረሻው የድህነት ወለል ተነስተው ከስኬት ማማ ላይ ከወጡ በርካቶች መካከል የዕለቱ እንግዳችን አንዱ ነው።

እንግዳችን ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የወላጆቹ ኑሮ እየደቆሰው አድጓል። በአንድ ወቅት የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ወታደር እንዲሆንም ሕይወት አስገድዳዋለች። ይሁንና በውትድርና ሕይወት ብዙ አልገፋም፤ ገና በጥዋቱ የመቁሰል አደጋ ገጥሞት በቦርድ ጡረታ ወጥቷል። ከውትድርና የተረፈች ሕይወቱን ለማቆየት ያለችው የዘጠና ዘጠኝ ብር ከ90 ሳንቲም ጡረታ ብቻ ነበረች። በዚሁ ገንዘብ ሕይወቱን ለማቆየት ጥረት ቢያደርግም አንድ ቀን ሲሞላ ሌላ ቀን እየጎደለ በብዙ ተፈትኗል።

በሕይወት መንገድ ውስጥ ይልሰው ይቀምሰው አጥቶ ያውቃል። ማደሪያም ቅንጦት ሆኖ በረንዳ ላይ ተጠልሏል። ታዲያ በዚህ ጊዜ በቂ ገንዘብ ባይኖረውም ሕይወቱን ከማቆየት አልፎ “የተሻለ ኑሮ ይኖረኛል፤ ከራሴ አልፌ ለሌሎችም እተርፋለሁ” የሚል ተስፋን ሰንቆ ራዕዩን ለመኖር ታግሏል። ተስፋውን ዕውን ለማድረግም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሥራ ሳይንቅ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ይሠራ ነበር። ከጥበቃ ጀምሮ ቤት ለቤት እየተዘዋወረ በጋሪ ደረቅ ቆሻሻን ሲሰበስብ ኖሯል። ዛሬ ግን ራዕዩን ማሳካት ችሎ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም ተርፏል።

በሕይወት ውጣ ውረድ ጠመዝማዛ መንገድ ዛሬ ከስኬት ማማ ላይ የደረሰው እንግዳችን አቶ ሄኖክ ዶንጋቶ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ቱላ ክፍለ ከተማ ተወልዶ አድርጓል። የስምነተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነትን ወቅት ወታደር ሆኗል። የሕይወት መስዋዕትነትን በሚጠይቀው የውትድርና ሥራ ላይ እያለም በጥይት ተመትቶ ቆስሏል። ባድሜ ሽራሮ ግንባር ላይ በመመታቱ ገና በጥዋቱ በቦርድ ጡረታ የወጣው አቶ ሄኖክ፤ እዛው ወታደር ቤት ቀለል ያለ ሥራ ተመድቦ ስንቅና ንብረት ክፍል ጥበቃ ሆኖ አገልግሏል።

በተጨማሪም ስልጠና ወስዶ የተለያዩ መሳሪያዎችን አቀናጅቶ ወደ ግንባር በመላክ ሂደት ውስጥ ሲያገለግል እንደነበርም ያስታውሳል። የተመቱ ወታደሮች በሙሉ ጡረታ ይውጡ በሚለው የመንግሥት አቅጣጫ መሰረት በ1997 ዓ.ም ዘጠና ዘጠኝ ብር ከ90 ሳንቲም የጡረታ ደምወዙን ይዞ ማህበረሰቡን ተቀላቅሏል። የሕይወት ውጣ ውረዱ ከዚህ ጊዜ እንደጀመረ ነው አቶ ሄኖክ ያጫወተን። ዘጠና ዘጠኝ ብር ከዘጠና ሳንቲም የጡረታ ደምወዙን 100 ብር አድርጎ ለመቀበል ወደ ጡረታ ሚኒስቴር አስር ሳንቲም ይዞ መሄድ ይጠበቅበት እንደነበር ያስታውሳል። በወቅቱ በ100 ብር የእግዜር ውሃ ጠጥቶ እንደነገሩ በልቶ ቢውልም ማረፊያ ጎጆ መከራየት ግን ፈተናው ነበርና በረንዳ ያድራል።

ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንዳለበት አብዝቶ ያስብና ያሰላስል የነበረው አቶ ሄኖክ፤ የሸክም ሥራ ጀምሮ እንደነበር አጫውቶናል። ነገር ግን ቁስለኛ በመሆኑ እንደልቡ መሸከም አልቻለም። ያም ቢሆን ግን ሌሎች የሥራ አማራጮችን ለማግኘት ባደረገው ጥረት በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ የጥበቃ ሥራ የመሥራት ዕድል አግኝቷል። በዚህ ጊዜ ታዲያ በረንዳ ከማደር ወጥቶ ቤት መከራየት ቢችልም ኑሮ ያው ከእጅ ወደ አፍ ነውና አሁንም ተጓዳኝ ስራ ማግኘት እንዳለበት በማመን ትጋቱን ጨመረ። ይሄን ጊዜ ነው ውሃ፣ አፈርና ሌሎች ነገሮች የመጫን ሥራን ለመስራት በማሰብ ዕቁብ ሰብስቦ አንድ አህያና ጋሪ መግዛት የቻለው።

ከጥበቃ ከሚያገኘውን 2010 ብር ቆጥቦ አንድ አህያና ጋሪ መግዛት የቻለው አቶ ሄኖክ፤ በወቅቱ በአካባቢው የተለያዩ ግንባታዎች እንደነበሩ ያስታውሳል። በመሆኑም ጭድ፣ ድንጋይ፣ አፈርና ሌሎች ሌሎችንም የማመላለስ ሥራ መሥራት ቀጠለ። ሥራው አዋጭ ሆኖለታል። ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ኑሮም እያሻሻለለት ነው። ያም ቢሆን ግን አቶ ሄኖክ ሥራውን ለማስፋት ሩቅ ሲያስብ አንድ ደንበኛው ከሀሳቡ አነቁት። ተጨማሪ ሥራ እንዲሰራ በር ከፈቱለት። ደረቅ ቆሻሻ ከግቢያቸው ሰብስቦ እንዲያስወግድላቸው ጠየቁት፤ አቶ ሄኖክ አላመነታም ምክንያቱም እሱ ሥራ አይንቅምና ለመሥራት ጓጓ።

አህያና ጋሪውን አቀናጅቶ ከግቢያቸው ያለውን ቆሻሻ ጠራርጎ አስወገደላቸው። በሌላኛውም ቀን እንዲሁ አደረገ። በቋሚነት የግቢያቸውን ቆሻሻ ማስወገድ የዕለት ተዕለት ሥራው ሆነ። በዚህ ጊዜ ታድያ በወር ከጥበቃ ከሚያገኘው ገንዘብ የበለጠ ደንበኛው ይከፍሉት እንደነበር አቶ ሄኖክ ያስታውሳል። ደረቅ ቆሻሻ የማስወገድ ሥራው ወደ ሌሎችም ተጋባና ደንበኞቹ ተበራከቱ። ከተለያዩ ሰዎች ጋር ደንበኝነቱን በማጠናከር የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ሥራውን አስፋፋ። እየሰፋ የመጣው ሥራ ከአቅሙ በላይ ሆነና አንድ ሁለት እያለ አብረውት ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎችን መቅጠር ቻለ።

ገቢው እየጨመረና ደንበኞቹ እየተበራከቱ ሲመጡ ታድያ ተጨማሪ ዕቁብ በመግባት የአህዮቹን ቁጥር አንድ ሁለት እያለ ሶስት ማድረስ ቻለ። በዚህ ጊዜም ለሶስት ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ማታ ማታ ከሚሰራው የጥበቃ ሥራ ጎን ለጎን የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ሥራውን ሳያቋርጥ ቀጥሏል። ይሁንና ሰዎቹን ወደ ሥራ ከማሰማራት ጀምሮ አህዮቹን የመቀለብ ሥራ የእሱ ነበርና ከጥበቃ ሥራው ጋር ጫና የፈጠረበት በመሆኑ የጥበቃ ሥራውን በገዛ ፈቃዱ በማቆም ሙሉ ጊዜውን በደረቅ ቆሻሻ የማስወገድ ሥራ ላይ አደረገ።

ሕይወት ፈተናዋ ብዙ ነውና የአህዮቹ ቁጥር ጨምሮ ለሶስት ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ጥሩ እየሠራ ባለበት ወቅት ያላሰበው ችግር እንደገጠመው አቶ ሄኖክ አጫውቶናል። አጋጣሚው እንዲህ ነው። በሀዋሳ ከተማ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ቤት ሰርቶ ለማስመረቅ እንዲሁም ልጁን ሊድር ትልቅ ድግስ ደግሷል። በዛ ድግስ ላይ የሚታደሙ በርካታ ሰዎችንም ጠርቷል። ድግሱ እነዚህን በርካታ ሰዎች ታሳቢ ያደረገ ሰፊ ድግስ ነው። ይሁንና ባለታሪካችን በማያውቀው ምክንያት በድግሱ የተገኘ ሰው ባለመኖሩ የበሰለው ምግብ ለአፍ ሳይደርስ ቀረ። በዚህ ጊዜ ታድያ ምግብና መጠጡ ሁሉ ይበላሻል። እናም የተበላሸውን ምግብ ለማስወገድ ሲባል አቶ ሄኖክ ይፈለጋል። ተፈልጎ የተገኘው አቶ ሄኖክ፤ የተበላሸውን ምግብ እንዲያስወግድ በታዘዘው መሰረት ምግቡን ከግቢው ማስወገድ ጀመረ።

ለአፍ ያላለውን ምግብ አንድ ሁለት ጊዜ እንደጣለ ‹‹ለምን እጥላለሁ አህዮቼን ለምን አላበላም›› የሚል ሀሳብ ብልጭ ይልለታል። ድፎ ዳቦን ጨምሮ የተለያዩ የበሰሉና የተበላሹ ምግቦችን አቶ ሄኖክ ለአህዮቹ አስቀርቶ ማታ ላይ ከተለመደው ጊዜ የተለየውን ምግብ ለአህዮቹ ይመግባል። አህዮቹም ተለየብን ሳይሉ እምሽክ አድርገው ይመገባሉ ግና ነገሩ ሌላ ሆነ። ምግቡ አልተስማማቸውምና ሶስቱም አህዮች በዛው ለሊት ሞተው አደሩ። ይሄን ጊዜ ሁሉም ነገር እንዳሰበው ሳይሆን ቀረና ለብዙ ችግር ዳረገው። በወቅቱ የበላው ዕቁብ በመኖሩ ችግሩን ይበልጥ አጠናበት። ገንዘቤን አምጣ የሚሉ ሰዎችም ተበራከቱ ያም ቢሆን ግን አቶ ሄኖክ ተስፋ አልቆረጠም።

ከአህዮቹ ሞት በኋላ ሕይወትን ከዜሮ ለመጀመር ሲነሳ የሚያውቁት ሰዎች እንደተባበሩት አቶ ሄኖክ አጫውቶናል። እሱ እንዳለው ጓደኞቹ አንድና ሁለት ብር ከፍ ሲልም አስር ብር አሰባስበው አንድ አህያ ገዝተው ሰጥተውታል። እንደ ዕድል ሆነና አህያው ታማሚ በመሆኑ በእርዳታ የተገዛው አህያ በ15ኛው ቀን ሞተ። በዚህ ጊዜ ችግሩ ጸንቶ ለአንድ ዓመት ጎዳና ላይ ወጥቷል። ያም ቢሆን ታድያ የሕይወት መንገዷ ብዙ ነውና ሳይታክት ሌላኛውን መውጫ ቀዳዳ ያፈላልግ ጀመረ።

በዚህ ጊዜ ታድያ ችግሩን የተረዱ አንድ ደንበኛው ጋሪ ገዝተው የሰጡት መሆኑን ያስታወሰው አቶ ሄኖክ፤ ተመልሶ በአንድ አህያና ጋሪ የቀድሞ ሥራውን ደረቅ ቆሻሻን ማስወገድ ቀጠለ። ጠንክሮ መሥራት በመቻሉም አሁንም ከቀደመው ጊዜ በበለጠ የአህዮቹን ቁጥር ወደ አስር በማድረስ ለአስር ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ሲሰራ ሌላ ችግር ይገጥመዋል። ችግሩም አህዮቹ ማታ ማታ ስለሚጮሁ ጅብ ይጠራሉ በሚል ቤት የሚያከራየው አጥቶ ተቸግሯል። ይሄን ጊዜ አህዮቹን በመኪና መተካት እንዳለበት በማሰብ ከጅብ ጋር እየታገለ ሥራውን ቀጥሏል።

በከተማው የሚሰራውን ሥራ ከግምት ውስጥ በማስገባትም የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት አህዮቹን ማሳደር የሚችልበት ቦታ እንደተሰጠው ያነሳው አቶ ሄኖክ፤ እግዚአብሔርም ረድቶት መኪና መግዛት እንደቻለም ነው ያጫወተን። በዚህ ጊዜ ከደረቅ ቆሻሻ ውስጥ ፕላስቲኮችን ለብቻ በመሰብሰብ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ሥራ ለተሰማራ አንድ ኩባንያ ማቅረብ ጀመረ። ከደረቅ ቆሻሻው ይበልጥ ፕላስቲኩ ከፍተኛ ገቢ ያስገባለት ጀመር። በዚሁ ጊዜም መኪኖችን መግዛት ችሏል።

አቶ ሄኖክ እንዳጫወተን ሥራ ሳይንቅ ጠንክሮ በመሥራቱ ውጤት ማምጣት ቢችልም ለስኬት ያበቃኝ ኮባ ኢንፓክት የተባለ የጣልያን ካምፓኒ ነው ይላል። ካምፓኒው የወዳደቁ ፕላስቲኮችን እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል ወደ ውጭ ኤክስፖርት ያደርጋል። በሥራ አጋጣሚ ያገኘው ይህ ካምፓኒ ሁለተኛውን መኪና መግዛት እንዲችል ትልቅ እገዛ ያደረገለት መሆኑን ያስረዳው አቶ ሄኖክ፤ ጥቅም ላይ የዋሉ ፕላስቲኮችን በከፍተኛ መጠን ማቅረብ ከቻለ መኪና እንደሚገዛለት ካምፓኒው ቃል ገብቶለት እንደነበር አስታውሶ፤ በገባው ቃል መሰረትም አዲስ አይሱዙ መኪና ገዝቶ ሰጥቶታል። የመኪናውን ዋጋ ከሚያቀርበው ፕላስቲክ በአንድ ኪሎ ግራም ሃምሳ ሳንቲም እየቆጠበ በሁለት ዓመት ውስጥ የመኪናውን ሙሉ ዋጋ ስምንት መቶ ሺ ብር መክፈል ችሏል። ይህ በሕይወቱ ትልቅ ስኬት ሆነለት።

በአሁን ወቅትም ከዚሁ ካምፓኒ ጋር ለሶስት ካምፓኒዎች ፕላስቲኮችን በጥሬው ሳይሆን በመጨፍለቂያ ማሽን ታግዞ እየጨፈለቀ ያቀርባል። ሁለቱ የቻይና ካምፓኒዎች ዱከም ላይ የሚገኙ ሲሆን ሶስተኛው የጣልያን ካምፓኒ አዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ላይ የሚገኙ መሆኑን የጠቀሰው አቶ ሄኖክ፤ የቻይና ካምፓኒዎች ፕላስቲኮቹን በመጠቀም የውስጥ ሱሪ፣ ካልሲ፣ ታይት፣ አርተፊሻል ጸጉር፣ ሚጎ ገመድና ቦንድድ ፍራሽ ጭምር የሚያመርቱ እንደሆነም አጫውቶናል።

አምስት መጨፍለቂያ ማሽኖችን ተጠቅሞ ጨፍልቆ ያዘጋጃቸውን ፕላስቲኮች በአራት መኪኖቹ ወደ ደንበኞቹ የሚያደርሰው አቶ ሄኖክ፤ እነዚህን የወዳደቁ ፕላስቲኮች የሚሰበስበው ከሀዋሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ ከሚገኙ 11 ከተሞች እንደሆነም ነው ያስረዳን። በ11 ከተሞች የሚገኙ በርካታ ዜጎች ፕላስቲኮችን ሰብስበው ለአቶ ሄኖክ በማስረከባቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ከእነዚህ በተጨማሪ በቋሚነት የሥራ ዕድል የፈጠረላቸው 86 ሠራተኞችም አሉት።

ሠራተኞቹ ፕላስቲክ ጠርሙሶቹን ከመለየት ጀምሮ በማጠብ፣ ክዳኑን በመለየት፣ በመጨፍለቅ፣ በጫኝና አውራጅ እንዲሁም በጆንያ ጠቅጥቆ በማሸግና በሾፌርና ረዳትነት ሥራ የተሰማሩ ናቸው። መልሶ ጥቅም ላይ ከሚያውለው የፕላስቲክ ሥራ በተጨማሪ የከተማዋን ደረቅ ቆሻሻ የማስወገድ ሥራም ጎን ለጎን እያስኬደው እንደሆነ አቶ ሄኖክ ተናግሯል።

አቶ ሄኖክ ለ86 የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች እንደሆኑ ነው የገለጸው። ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የገቢ ምንጭ ያልነበራቸው እናቶችን ወደ ሥራ በማስጋባት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ከተፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ አቶ ሄኖክ ማህራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም በርካታ ተሳትፎዎችን የሚያደርግ ሲሆን፤ በርካታ ቁጥር ላላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት ድጋፍ እያደረገ ያስተምራቸዋል።

በመጨረሻም በዘጠና ዘጠኝ ብር ከ90 ሳንቲም ሕይወቱን ለማቆየት ሲጥር የነበረው አቶ ሄኖክ በአሁን ወቅት ያሉትን ንብረቶች ጨምሮ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ካፒታል ማፍራት የቻለ ሲሆን፤ በቀጣይም ሥራውን አጠናክሮ የመሥራት ዕቅድ ያለውና ከወዳደቁ ፕላስቲኮች መጥረጊያ ለማምረት ፋብሪካ የመገንባት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ የሚገኝ መሆኑን አጫውቶናል።

 ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2016

Recommended For You