የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱ ልማት እና የሕብረተሰቡ ፍላጎት እየጠየቀ ያለውን ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪከ ኃይል በተለያዩ አማራጮች እያመረተ ወደ ሥራ ሲያስገባ ቆይቷል፤ በአሁኑ ወቅትም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። የኤሌክትሪክ ኃይሉን በዋናነት ከውሃ ለማመንጨት እየተሰራ ሲሆን፣ ከንፋስ፣ ከጸሀይ እንዲሁም ከእንፋሎት የኃይል አማራጮች እየተመረተ ነው።
ኃይል የማመንጨት አቅምም በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ወደ 17 ጊጋ ዋት ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቅርቡ አስታውቋል። በቀጣዮቹ ስድስት ዓመታትም የኢኮኖሚውን ፍላጎት ማሟላት የሚችል ኃይል ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከፀሐይ እና ከከርሰምድር እንፋሎት ለማመንጨት ታቅዷል።
በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ከአምስት ጊጋ ዋት በላይ መድረሱን ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፣ ይህንን አሀዝ የዓባይ ግድብ ሙሉ በሙሉ በሚጠናቀቅበት ጊዜ እጥፍ እንደሚያደርገውም አመልክቷል። በእዚህ ላይ የኮይሻና ሌሎች የኃይል ምንጮች ሲጨመሩበት በቀጣይ ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ኃይል የማመንጨት አቅም 17 ጊጋ ዋት ይደርሳል።
በቅርቡ አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የተደረገለት የአባይ ግድብ ግንባታ በአብዛኛው ተጠናቋል፤ ሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጩ ሲሆን፣ ዘንድሮም አምስት ተርባይኖች ሥራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
ሌላው በግንባታ ላይ ያለውና በኦሞ ወንዝ ላይ ግንባታው እየተካሄደ የሚገኘው የኮይሻ ግድብ ነው። ይህ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንታ ዞን እየተገነባ ያለው የኮይሻ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ለቀጠናው የኤሌከትሪከ ኃይል አቅርቦትም ተጨማሪ አቅም ያበረክታል ተብሎ ታምኖበታል። ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነቱ በተጓዳኝ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጠናው አረንጋዴ ልማት የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለውም እየተገለጸ ነው።
የኮይሻ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አባይነህ ጌትነት በቅርቡ በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት በአካባቢው ጉብኝት ላደረገው የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች እንደገለጹት፤ የኮይሻ ኃይድሮኤሌከትሪክ ፕሮጀክት በኦሞ ወንዝ ላይ ከተከናወኑት ፕሮጀከቶች አራተኛው ነው፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በአንድ ጊዜ አንድ ሺህ 800 ሜጋ ዋት ኃይል፤ እንዲሁም ዓመታዊ ስድስት ሺህ 400 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢንርጂ ያመነጫል።
ፕሮጀክቱ በሁለት ነጥብ 42 ቢሊየን ዩሮ እየተገነባ ሲሆን፣ የግንባታ ሥራው የተጀመረው የወንዙን የፍሰት አቅጣጫ እንዲቀይር ከተደረገ በኋላ ነው፤ ግንባታውም ያለማቋረጥ ለ24 ሰዓታት እየተከናወነ ሲሆን፣ አሁን ላይ የግድቡ ሥራ 38 በመቶ ደርሷል። በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ 52 በመቶ፣ የግድቡ አርማታ ሙሌት 30 በመቶ፣ የማስተንፈሻው ግንባታም 13 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራው በጥናት ላይ ይገኛል።
የኮይሻ ግድብ ቁመቱ አንድ ኪሎ ሜትር ይጠጋል፤ ከግድቡ ወደ ኋላ 130 ኪሎ ሜትር የሚተኛ ሀይቅም ይፈጠራል። የሚፈጠረው የውሃ አካል እስከ ጊቤ ሶስት ግድብ ይደርሳል።
የ200 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፣ በRCC (Roller Compacted Concret) ቴክኖሎጂ እየተገነባ እንደሚገኝ የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጠቅሰው፣ ለዚህም ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ሜትር ኪዩብ አርሲሲ ያስፈልጋል ብለዋል። ግድቡ አሁን ላይ ከጠቅላላ 200 ሜትር ከፍታ ግንባታው 70 ሜትር ከፍታ ላይ መድረሱን አመላከተዋል።
ሌላኛው የፕሮጀክቱ አካል የሆነው እና 60 ሜትር ቁመት ያለው እና ከጂ + 18 ህንጻ ግንባታ ጋር አኩል የሆነው የተርባይን ማስቀመጫው ግንባታ ነው። የዚህም ግንባታ 52 በመቶ መድረሱን ምክትል ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል። የዚህ የፓወር ሀውስ ግንባታ ሲቪል ስራም ተጠናቋል ብለዋል። ኃይል ማመንጫው እያንዳንዳቸው 300 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ስድስት ተርባይኖች እንደሚኖሩት ጠቁመው፣ አሁን ላይ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው በዲዛይን ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከፍተኛ የውሃ ክምችት በሚኖርበት ወቅት የሚያስፈልገው የማስተንፈሻ ግንባታ ሥራም የፕሮጀክቱን መዋቀር በማይጎዳ መልኩ ለማስተንፈስ የሚያስችሉ እያንዳንዳቸው 70 ሜትር ከፍታ እና 40 ሜትር ስፋት ያላቸው ስድስት የውሃ ማስተንፈሻዎች /መውጫዎች/ እየተገነቡ ናቸው። ሌሎች ከግድቡ ጋር ተያያዥ የሆኑ የመንገድ፣ ካምፖች፣ ወርክሾፖች ግንባታዎች ተከናውነዋል። በጠቅላላውም ፕሮጀከቱ 61 በመቶ ያህል የደረሰ ሲሆን ፐሮጀከቱን ለማጠናቀቅም ከሶስት እስከ አራት ዓመታት ያስፈልጋሉ።
የፕሮጀክቱ ግንባታ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ መገንባት ብቻ ሳይሆን ለዘርፉ ልማት ወሳኝ የሆነው የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበትም ነው። ምክትል ሥራ አስኪያጁ ፕሮጀክቱ ለአምስት ሺህ የአገር ውስጥ ሰራተኞች እንዲሁም 140 ኤክስፐርቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ገልፀዋል። ከሀገር ወስጥ የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚዎቹ 30 በመቶ ያህል የሚሆኑት የግድቡ አቅራቢያ በሆኑ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ነዋሪዎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። በሜጋ ፕሮጀከቱ ክፍ ያሉ ቴከኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውንም ተናግረው፣ በዚህም የሀገር ውስጥ ሰራተኞች በርካታ ልምዶችን እያገኙ እና እየቀሰሙበት መሆኑንም አመላክተዋል።
የኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያውያን የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የላቀ ድርሻ እንዳለው በፕሮጀከቱ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ሰራተኞች አመላከተዋል። ሰራተኞቹ እንደገለጹት፤ ከሆነ በእንደነዚህ አይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶች መሳተፋቸው አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ትልቅ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
የ33 ዓመቱ ሙሉቀን ተከስተብርሃን፣ በፕሮጀክቱ የሴፍቲ ሱፐርቫይዘር ነው። ወጣቱ ላለፉት 15 ዓመታት በበለስ፤ በአባይና ግድብ ግንባታዎች ሰርቷል። አሁን ደግሞ በኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ እየተሳተፈ ይገኛል። በመሰል ፕሮጀክቶች መሳተፉ የተለያየ እውቀት እንዲቀስም እንዳስቻለው ጠቅሶ፣ በዚህ ስራ ላይ መሰማራቱ በሙያም ራሱን ለማሳደግም ሃገሩን ቤተሰቡን ለመለወጥ እንዳስቻለው ይናገራል።
“አሁን እኔ የሴፍቲ ባለሙያ ነኝ። በሃገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ አገር ሄጄ መስራት የሚያስችል እውቀት አግኝቻለሁ። የሚያሰራኝ ድርጅት ለረጅም ጊዜ አብረውት የሰሩትን ውጪ አገር ድረስ ልኮ ያሰራል። እኔም ወደፊት ባካበትኩት እውቀትና ልምድ የዚህ እድል ተጠቃሚ መሆኔ አይቀርም።” ብሏል።
መሀመድ ደልዋናም እንዲሁ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት በፕሮጀክቱ አናጺና የክሬን ረዳት ሁኖ ሰርቷል። ፕሮጀክቱ ላይ በመሳተፉ እድለኛ መሆኑን ይገልጻል። መሃመድ በእስከ አሁኖቹ ፕሮጀክቶች ባለመሳተፉም እየተቆጨ ነው። ቀደም ሲል ስራ አጥና ጊዜዬን ባልባሌ ቦታዎች የማሳልፍ ነበርኩ የሚለው መሀመድ፣ አሁን ግን የሙያ ባለቤት ሁኜ፤ በራሴ ሰርቼ፤ የወር ደመወዝ ቆጥሬ መቀበል መቻሌ በራሱ ትልቅ ለውጥ ነው ሲል ይገልጻል።
የ28 ዓመቱ ወጣት ነዚፍ አባመጫ የግልገል ግቤ ሦስት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ በሚከናወንበት ወቅት ነው በኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ መስራት የጀመረው። ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በኃይል ማመንጫ ግንባታ ስራ ላይ መሰማራቱ የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን ኑሮ ማሻሻል እንዳስቻለው ይናገራል። “በፕሮጀክቱ ያገኘሁትን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም ወደፊት የራሴን ስራ ፈጥሬ ከጓደኞቼ ጋር አብሬ በመስራት ለመለወጥ ሃሳብ አለኝ ሲልም ነው የተናገረው።
ቤዛዊት ኃይሉ በፕሮጀክቱ የጂኦሎጂ ኢንስፔክተር ነች። በፕሮጀክቱ መስራት መቻሏ በሙያው የካበተ ልምድ ካላቸው የሃገር ውስጥና የውጪ ባለሙያዎች በርካታ እውቀትና ልምዶችን እንድትቀስም እድል እንደፈጠረላት ተናግራለች። “ይህን መሰል እውቀትና ክህሎት ማግኘት መቻላችን በንድፈ ሃሳብ ያገኘነውን እውቀት በተግባር አንድንፈትሽው ያግዛል›› ስትል ገልጸ፤ በሃገሪቱ የሚታቀዱ ተመሳሳይ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በውስጥ አቅም ለመስራት እንደሚያስችልም ነው ያመለከተችው።
የፕሮጀክት ኮንትራክተሩ ድርጅት ኃላፊ ኢንጂነር ዞፒስ ኢውጊኒዮ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ 5000 ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ፈጥሯል። እነዚህ ሰራተኞች እውቀትና ልምዳቸውን እንዲያሳድጉ ብቻ ሳይሆን የስራና የደመወዝ እድገት እንዲያገኙም እየተደረገ ነው። “ይህ አይነቱ የአቅም ግንባታ ስራ ሀገሪቱ ወደፊት በራስዋ አቅም ለምትገነባቸው መሰል ፕሮጀክቶች ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ‹‹እኛም በዚህ እንኮራለን›› ሲሉ ነው ኃላፊው የተናገሩት። ብዙዎች ከዝቅተኛ የስራ ደረጃ ተነስተው የትልቅ ሙያ ባለቤቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ከአረንጔዴ ልማት ጋር የተጣመረ ነው። በፕሮጀከቱ ዙሪያ የሚገኘው የአረንጓዴ ልማት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት እየተካሄደ ያለው የጨበራ ጩርጬራ ፓርክ አካልና በመላ አገሪቱ ከሚገነቡት ሦስቱ ዋና ዋና የቱሪዝም መስህብ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። ይህ ፕሮጀክት ለአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ሌላ መስህብ ስፍራ ይጨምራል።
በዚህ ግድብ የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ አስደናቂ እይታ ይፈጥራል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ይህ ፕሮጀክት በቱሪዝም ልማትና እንቅስቃሴ በተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ረገድ የሚኖረው አበርክቶው ሰፊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የመጣው መንግስት ካደረገው ማሻሻያ በፊት ሜጋ ፕሮጀክቶች ትልቅ ችግር ውስጥ ነበሩ ሲሉ አስታውሰው፣ ያን ሁኔታ ለመቀየር መሰራቱን ገልጸዋል። የመንግስት አንዱ ትኩረት የዚህን ግዙፍ ፕሮጀክቶች አስተዳደር ማሻሻል እንደነበርም ጠቅሰዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ብዙ ማሻሻያዎችን ሲደረጉ ቆይተዋል። ለዚህ በአባይ ግድብና ሌሎች ፕሮጀክቶች የተሰሩት ስራዎች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ። ሀገራዊ ሪፎርሙ የእነዚህን ፕሮጀክቶች አስተዳደር አቅም በማሳደግ ላይ ያተኮረ መሆኑን አመልክተው፣ በዚህም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ጥሩ አፈፃፀም እያሳየ መምጣቱን ተናግረዋል።
ግድቡ አንድ ሺህ 800 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ይጨምራል ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፣ የሕብረተሰቡን የኃይል ፍላጎት ከማሟላት በዘለለ የሀገሪቱን ኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ያሳድጋል ብለዋል።
መንግስት በአገራችን ብቻ ሳይሆን በጎረቤቶቻችን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ፕሮጀክትም ከተፈጥሮ ሃብት ልማትና ክብካቤ ጋር ያለውን ተዛምዶ በግልፅ ያሳያል ብለዋል። ይህ አካባቢ ግድቡ ከጀርባው በሚፈጥረው ኃይቅ ምክንያት ወደ ተፈጥሯዊ መስህብነት ሲሸጋገር ለቱሪዝም ልማት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል። አካባቢው ብዙ የዱር እንስሳት ማለትም ዝሆኖች፣ አንበሶች፣ ብርቅዬ ወፎች እንዲሁም ዕፅዋት እና ሌሎች የዱር አራዊት በብዛት ያሉበት መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ፕሮጀክቱ በማህበረሰቡ ውስጥ የተፈጥሮ ጥበቃ ጽንሰ-ሀሳብን ይጨምራል ብለዋል።
በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በፕሮጀክቱ ውስጥ በመቀጠር የዚህ ፕሮጀክት መገኘት ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ተገንብቶ በኦሞ ወንዝ ምከንያት ተለያይቶ ለነበረው ሕብረተሰብ በኢኮኖሚና ማሕበራዊ ትስስሩ እንዲጠናከር ሆኗል ብለዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2016